በዕድሜው ሶስት አስርት ዓመታትን የደፈነው ሰይድ ይመር በ1983 ዓ.ም መሀል ኮምቦልቻ ተወለደ። ዕድሜው ከፍ እንዳለ ወላጆቹ ትምህርት ቤት አስገቡት። ቀለም በመቁጠር እምብዛም አልገፋም። ጥቂት ጊዜያትን ዘልቆ ትምህርቱን አቋረጠ። ይህ መሆኑ ያላስጨነቀው ወጣት ያለምንም ስራ አመታትን ከቤተሰቦቹ አሳለፈ።
ውሎ አድሮ ወደአዲስ አበባ የሚያዘልቀው ጉዳይ ተገኘ። አዲስ አበባ ያመጣው ዋና ምክንያት ወደ ፈረንሳይ አገር ለመሄድ ማሰቡ ነው። በየጊዜው ከኤምባሲ ደጃፍ የሚያመላልሰው ጉዳይም በቀጠሮ እየታሰረ ቀናት ያስቆጥረው ይዟል። አንድ ቀን ሰይድ ሲጠብቀው የቆየው የፈረንሳይ ቪዛ እንዳልተሳካለት አወቀ። ይኼኔ አዲስ አበባ የመቆየት ዕቅዱን ሰርዞ ወደ ደሴ ተመለሰ።
ውጭ መሄድ ዕድሉ እንዳልሆነለት ባወቀ ጊዜ ደሴ ሄዶ የመንጃ ፈቃድ አወጣ። ተመልሶ አዲስ አበባ ሲገባ እህቱ ተቀብላ አስተናገደችው። መኖሪያና ውሎ ሳይቸገር ጊዜያትን አሳለፈ። በእጁ ያለውን የመንጃ ፈቃድ ይዞ ስራ ማፈላለግ ጀመረ። በቂ ልምድ ስላልነበረው ያሰበው አልተሳካም።
ከአዲስ አበባ ደሴ ኮምቦልቻ መመላሱን ያየው ወንድሙ በየጊዜው ገንዘብ እየሰጠ ጎዶሎውን ይሞላለት ያዘ። መኪና እንደሚገዘለትም ቃል ገባለት። ሰይድ ወዲያውኑ ቤት ተከራየ። አሁንም ከወንድሙ የሚሰጠው ገንዘብ በቂው ነው። በገንዘቡ ያሻውን አድርጎ የተረፈውን ይቆጥባል።
አሁን ወደ ደሴ – ኮምቦልቻ የሚያመላልሰው ጉዳይ የለም። አዲስ አበባ ላይ የተረጋጋ ህይወት ጀምሯል። ከቀድሞ ጋብቻው ሴት ልጅ ቢያገኝም በትዳሩ አልዘለቀም። ጎጆውን በፍቺ አፍርሶ ከባለቤቱ ተለያይቷል።
ኢንጂነሯ ወጣት…
የሀያ ስድስት ዓመቷ ወጣት ሄለን ገብረመስቀል ከሁለት ዓመት በፊት ከአዲግራት ዩኒቨርሰቲ በሲቪል ኢንጀነሪንግ ዘርፍ በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቃለች። አድናቆት የተቸራት ይህቺ ወጣት ለሀገር ለወገን የሚተርፍ አቅም እንዳላት በርካቶች ይመሰክራሉ።
የሄለን ወላጅ እናት ኑሮና ህይወቷ በውጭ አገር ከሆነ ቆይቷል። ከአመታት በፊት ወላጅ አባቷን በሞት ያጣችው ወጣት ከእናቷ ያሻትን ሁሉ ታገኛለች። የፈለገችውን የማታሳጣት ወይዘሮ ለአንድ ልጇ የማትሆነው የለም። የእሷ በሰው አገር መኖር ትርጉሙ ለልጇ ሆኖ የፍላጎቷን ትሞላለች። ወጣቷ ዩኒቨርስቲ በነበረች ጊዜ የጎደላት አልነበረም። ከአልባሳት እስከ ገንዘብ፣ የጠየቀችውን ሁሉ ታገኛለች።
ሁሌም በታታሪ ልጇ የምትኮራው እናት ካለችበት ሆና የሄለንን ጥያቄ ስትመልስ የልቧን ሀሳብ ስታደርስ ኖራለች። አንድ ልጇ ዩኒቨርስቲ ገብታ በማዕረግ መመረቋ ለእሷ ኩራትና ደስታ ሆኗል። ልጇ የድካሟ ፍሬ ናትና ማንነቷን በእሷ ውስጥ እያየች ፈጣሪዋን ታመሰግናለች።
ሄለን ከዩኒቨርሰቲ ተመርቃ ከወጣች በኋላ በአንድ የግል ድርጅት ተቀጥራ ትሰራለች። የሚከፈላት ደመወዝ በቂና ጥሩ የሚባል ነው። አሁን ቤት ተከራይታ ዕቃ አሟልታ እየኖረች ነው። ዛሬም ‹‹አለሁሽ›› የምትላት እናቷ ስራ ያዘች ብላ አልተወቻትም። በገንዘብ እየደጎመች፣ ከሀሳቧ ትጋራለች፣ የጎደላትን እየጠየቀች የልቧን ታደርሳለች።
ወይዘሮዋ ልጇ ትዳር ይዛ ዓለም ብታሳያት ትወዳለች። የልጅ ልጆች አሳቅፋ አያት ብታደርጋትም ደስታዋ ነው። ይህ ሁሉ ይሆን ዘንድ ዘወትር ፈጣሪዋን ትለምናለች። አንድ ቀን የልቧ ሞልቶ የልፋቷ ዋጋ እንደሚቆጠር እምነቷ ነው።
ሄለን የፍቅር ጓደኛዋ ከነበረው ወጣት ከተለያየች ወራት ተቆጥረዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አንድ ሰው አብሯት መታየት ጀምሯል። ይህን አይተው ለሚጠይቋት ሁሉ በቂ ምላሽ አትሰጥም።
አንዳንዴ ብቅ የሚለው ወጣት ሁሌም ከእጁ ፌስታል ቢጤ አያጣም። የያዘውን ቋጠሮ እንዳጠበቀ በታክሲ አሊያም በመኪና መጥቶ ያገኛታል። ከሄለን ጋር ጊዜ ወስደው ማውጋታቸውን ያዩ አንዳንዶች ስለማንነቱ ይጠይቋታል። ሄለን – አድበስብሳ በዝምታ ታልፋለች።
ድንገቴው ትውውቅ
ሰይድ አንድ ቀን ወደቤቱ ከመገናኛ ወደ ጎሮ ከሚሄድ ታክሲ ውስጥ ገባ። ከእሱ ጥግ አንዲት ወጣት ተቀምጣለች። ከልጅቷ ጋር የጀመሩት ጨዋታ አግባብቷቸዋል። እሱ ሲያወራ እሷ እየመለሰች መንገዱን አጋመሱ። መውረጃቸው ደርሶ ከመለያየታቸው በፊት የስልክ ቁጥር ተለዋወጡ። ሰይድ ስልኳን በስልኩ መዘገበ። እሰኪለያዩ አወጉ፣ ሀሳባቸው ተናበበ፣ ውስጣቸው ተያየ።
ከጥቂት ደቂቃዎቸ በኋላ በስልክ ተገናኝተው አወሩ። ጨዋታቸው ብዙ አመት እንደሚተዋወቁ ባልንጀሮች ነበር። ስልካቸው በስንብት ከመዘጋቱ በፊት በአካል ለመተያየት ተስማሙ። በቀጠሮ ሲለያዩ በሰአቱ ሊገናኙ ወሰኑ።
ሰይድና ሄለን በመጀመሪያው ቀነ ቀጠሮ በሰአቱ ተገናኝተው እንደልብ አወጉ። እሱ ስራ እንዳለውና ብቻውን እንደሚኖር ነገራት። እሷም ጎሮ አካባቢ ተከራይታ እንደምትኖር፣ እናቷ ውጭ አገር እንዳለችና ስራ እንደያዘች አጫወተችው። በስንብት ተለያይተው ቤት ሲደርሱ ዳግም ተደዋወሉ። በርከት ላሉ ደቂቃዎች አውርተው ስልኮቻቸውን ዘጉ።
የሰይድና ሄለን ግንኙነት ዳብሮ አብሮነታቸው ዘለቀ። በየቀኑ እየተገናኙ ምሳ መብላት፣ ሻይ ቡና መባባል ጀመሩ። ወራትን የዘለቀው መገናኘት አሁንም ከሰው ዓይን ገባ። ዳግም ሌላ ሰው ያዩት ባልንጀሮች የተለመደውን ጥያቄ አቀረቡ። ሄለን ለሚቀርቧት ጠያቂዎች ስለወጣቱ ማንነት ተናገረች።
ሶስት ወራትን በግብዣና በስልክ ጨዋታ የዘለቀው ግንኙነት አንድ ቀን መልኩን ቀይሮ ወደ ፍቅር ተለወጠ። የሁለቱ ወጣቶች ልብ በአዲስ ፍቅር ነደደ። ጠዋት ማታ ማውጋት፣ አብሮ መዋል ማደር ልምዳቸው ሆነ። ቀናትን የቆጠረው የፍቅር ግንኙነት በእሷ ቤት እያዋለ፣ በእሱ ቤት ያሳድራቸዋል። ሲነጋ ሁለቱም ወደጉዳያቸው ይሄዳሉ።
አንዳንዴ ከሄለን ጋር የሚታየው ባለፌስታሉ ወጣት ጊዜ ወስዶ በትኩረት ሲያወራት ይታያል። ሄለን እሱን ባገኘች ቁጥር ፊቷ ላይ ጭንቀት የሚነበብ ትካዜ የሚታይ ይመስላል። ስለሰውዬው ምንም መረጃ የሌለው ሰይድ እንደቀድሞው አብሮነቱን ቀጥሏል።
መስከረም 23 ቀን 2011 ዓም…
ሄለን በዚህ ቀን ከሰይድ ጋር ተገናኝታ ጊዜ አሳልፋለች። ከሰአት ላይ ጨዋታቸውን አቋርጦ ድንገት የጠራውን ስልኳን ስታነሳ እየተጣደፈች ነበር። ንግግሯን እንደጨረሰች ወደ ሰይድ ዞር ብላ አብሯት መሄድ እንዳለበት ነገረችው። ሰይድ ስለ ደዋዩ ማንነትና ስለሚሄዱበት ስፍራ አጥብቆ ጠየቀ።
ሄለን ከአዲስ አበባ ውጭ የሚኖረው አጎቷ የላከላትን ዕጣንና ልብስ መቀበል እንዳለባት አስረዳችውና አብረው ወጡ። ወደቀጠሮው ለመሄድ ኮንትራት ታክሲ መያዝ ነበረባቸው። እቃውን ተቀብለው ወደእሷ ቤት አመሩ። ሰይድ በፌስታል ያለውን ጥቅል ለማየት ዓይኖቹን አሻገረ። ከተላኩት ዕቃዎች መካከል አንዱ የወንድ ጫማ ነው። ምንም አልተናገረም።
እስከ ምሽቱ አንድ ሰአት ተኩል በሄለን ቤት ቆይተው ለመውጣት ተዘጋጁ። ሄለን ዕቃውን በሻንጣ እና በፌስታል ከታ እንደጨረሰች ወደ አከራዮቿ ቤት ብቅ አለች። ለቀናት ፊልድ እንደምትሄድ ነግራም ቤቷን እንዲያዳምጡ አሳሰበቻቸው። አከራዮቿ ቸር እንዲመልሳት ተመኝተው አደራውን ተቀበሉ።
ጥንዶቹ ዕቃውን ይዘው ከግቢው ወጡ። የመንገዳቸው አቅጣጫ ወደመገናኛ ነበር። ታክሲው ውስጥ ገብተው መንገድ እንደጀመሩ የሄለን ሞባይል ጥሪ አሰማ፤ አነሳችው ። ወዲያው ወደ ጎሮ መሄድ እንዳለባት ተናገረች። ሰይድ ለምን? ሲል ጠየቀ። ሰው እንደሚጠብቃትና እሱን ማግኘት ግድ እንደሆነ መለሰች። ማንነቱን ጠየቃት። የአክስቷ ልጅ መሆኑን ነገረችው።
ከታክሲው ወርደው የጎሮን ታክሲ ያዙና እንግዳው ወዳለበት አመሩ። ሄለን ከፊት እሱ ከኋላ ሆነው አጠገቡ ሲደርሱ ሰውዬው ቪትስ መኪና ውስጥ ነበር። ሰይድ ፊቱን ለማየት ሞከረ። ኮፍያ ስለደፋ በወጉ አላየውም። ሄለን መኪናውን ከፍታ የያዘቸውን ዕቃ ከኋለኛው መቀመጫ አኖረች። ፈጠን ብላም ከጋቢናው ተቀመጠች። የመኪናው ሞተር ተነሳ። እነሱ የመገናኛ አቅጣጫን ያዙ። ሰይድ ወደቤቱ ተመለሰ።
በማግስቱ ተቀጣጠሩ። ቦታው ሲደርስ ከመኪና ወርዳ ወደእሱ ስትመጣ አያት። እየተቻኮለች 45 ሺህ ብር እንደምትፈልግ ነገረችው። ደነገጥ ብሎ ለምን አላት፤ አልመለሰችለትም። ወዲያውም 25 ሺህ እንዳላትና 20 ሺህ ብር ብቻ እንዲጨምርላት ጠየቀችው። አሰብ አድርጎ ቤት ካስቀመጠው ገንዘብ 10 ሺህ ብር እንደሚሰጣት ነገራት። ሌላ ጨምሮ እንዲሰጣት ለመነችው። ቀሪው ገንዘብ የሞባይል መግዣ ነው አላት። አዲስና ዘመናዊ ሞባይል ከእጁ አኖረችለት። ከእናቷ ገንዘብ እንደተላከላትና ፈጥና እንደምትመልስ ሲረዳ ቀሪውን ብር ከቤት አምጥቶ አስረከባት። ተለያዩ፣ እሱ ወደቤቱ እሷ ወደመኪናው ተመለሰች።
ምሽት 3፡ ከ45
ሰይድ ቤቱ ቁጭ ብሎ አዲሱን ስልክ ይነካካል። ድንገት ሞባይሉ ጠራ። ሄለን ናት። የት ነህ አለችው፤ ነገራት። ከስፍራው ሲደርሰ ከባለቪትዙ ጋር ጭፈራ ቤት ነበረች። ሁለቱን ወንዶች አስተዋወቀቻቸው። ወዲያውም ቢራ አዘው መጠጣት ጀመሩ። ጥቂት ቆይቶ ሰይድ ስለሰውዬው ማንነት ጠየቀ። ቀድሞ የነገረችው የአክስቷ ልጅ ሳይሆን ጓደኛው መሆኑን ነገረችው። ጨዋታው ቀጠለ።
ጥቂት ቆይቶ እንግዳው ወደውጭ ወጣ። ሲመለስ ለየት ያለና ሲጋራ የሚመስል ጥቅል ይዞ ነበር። እጁን ዘርግቶ ለሰይድ ጋበዘው። ፈቃደኛ አልሆነም። ጥቂት ቆይቶ ቤት ቀየሩ። ሙዚቃው ጨዋታው ደራ።
አሁንም ሰውዬው ሲጋራ መሰሉን ጥቅል ለሰይድ ጋበዘ። አሁን አልተግደረደረም። ከእጁ ተቀብሎ ደጋግሞ ሳበለት። ለሄለን ሰጧት። ጥቂት ሳብ ሳብ ከማድረጓ ክፉኛ ቢያስላት፤ ተወችው። ሲዝናኑ አምሽተው ወደ ሰይድ ቤት ሲያመሩ ለሊቱ ተጋምሶ ነበር። እንግዳው መኪናውን አቁሞ ወደቤት እንደገቡ ሙዚቃውን አደመቁት። ሄለን ደጋግማ ስለመስከሯ መናገር ጀመረች። ሰይድም ጥሩ ምሽት እንዳሳለፉ መመስከር ያዘ።
ሰውዬው ይህን ሲሰማ ለስካር ይበጃል ካለው ቀይና አብረቅራቂ ጥቅል ለሁለቱም አካፍሎ ሰጣቸው፤ ደስ እያላቸው ተቀበሉት። ጥቂት ቆይቶ ሶስቱም በድካም ናወዙ። እንግዳው ከአልጋው ስር ከተነጠፈ ፍራሽ ላይ አረፍ አለ። ሄለንና ሰይድ አልጋቸው ላይ እንደተቃቀፉ ዕንቅልፍ ጣላቸው።
ለሊት 11 ፡ከ 30
ሰይድ በድንገት ከዕንቅልፉ ብንን አለና ከጎኑ የተኛችውን ሄለንን መዳሰስ ጀመረ። አጠገቡ የለችም ። ደነገጠ። ዓይኖቹን እያሻሸ ወደመሬት ተመለከተ። ሄለን ለእንግዳው ከተነጠፈ ፍራሽ ላይ ተኝታለች።
ከአልጋው በፍጥነት ወርዶ ወደእሷ አመራ። ሰውዬው ከጎኗ የለም። ወደውጭ ተመለከተ በሩ መለስ ብሏል። እንግዳው ቀድሞ መውጣቱን አወቀ። ንዴት ወረረው። ወዲያው ትከሻዋን እየወዘወዘ፤ ቀሰቀሳት፤ ዝም አለችው። በሁኔታዋ ተናዶ ድርጊቱን ደጋገመው። ለውጥ የለም። ጠጋ ብሎ አዳመጣት። አትተነፍስም። ከአንገቷ ቀና አድርጎ አያት። የኋላ ጭንቅላቷ እየደማ ነው። እያለቀሰ አንገቱን ደፍቶ ተቀመጠ።
ጥቂት ቆይቶ አእምሮው ብዙ አሰበ። በዚህ ሁኔታ ፖሊስ ቢያገኘው ተጠያቂ እንደሚሆን ገባው። ጊዜ አልወሰደም። ወደ ጓዳ ዘልቆ ሁለት ስል ቢላዎች አመጣ። ሄለንን በጀርባዋ አንጋሎ ልብሷን ሰበሰበ። ለስላሳና ቀይ ሰውነቷ ተጋልጦ አየው። አንዱን ቢላዋ ብሽሽቷ ላይ አሳርፎ መገዝገዝ ጀመረ። ጥቂት ቆይቶ ታፋዋ ከአካሏ ተላቀቀ።
በደም የታጠበ እጁን እየጠረገ ሌላኛውን እግሯን ለማላቀቅ ትግሉን ቀጠለ። ተሳካላት። ሁለት ታፋዎቿን ገንጥሎ እንደጣለ፤ ወደሌላው አካሏ አለፈ። ከወገቧ አንስቶ ወደ አገጯ ያለውን አካል በቢላዋው እየከፈለ አንገቷ ጥግ ደረሰ። በአንድ እጁ አንገቷን ይዞ እንዳጠበቀ ጭንቅላቷን ቆርጦ ጣለው። ይኼኔ በአፉ መሙላት የጀመረው ፈሳሽ ሊያስመልሰው ተናነቀው። ራሱን አረጋግቶ ስራውን ቀጠለ።
ሰይድ ዞር ብሎ ያደረገውን አስተዋለ። የሄለን አካል እንዳይሆን ሆኖ ተቆራርጧል። ፈጠን ብሎ ተነሳ፤ ሁለት አግሮቿን በፌስታል ከተተ። ወገቧንና ሌላውን አካሏን በሌላ ኩርቱ ፌስታል ቋጠረ። ቤቱን እንደነገሩ አጽድቶ ሻንጣ ለመግዛት ሲወጣ ሰአቱ ረፍዶ ጸሀይ ደምቃ ነበር።
መገናኛ ደርሶ ሁለት ሻንጣዎችን በሰባት መቶ ብር ገዝቶ ተመለሰ። በየፌስታሉ ለይቶ ያስቀመጠውን ቋጠሮ መልሶ አነሳና በየሻንጣዎቹ ከፋፈላቸው። የሟችን ሁለት እግር ያየዘውን ፌስታል በነጭ ማዳበረያ ጠቅልሎ ቦታ ሰጠው። የሁለት እጇቿንና አንገቷ ያለበትን ፌስታል ቤት ከነበረው የሚታዘል ሻንጣ ውስጥ ከቶ ሲጨርሳ ላዳ ታክሲ ሊጠራ ከግቢው ወጣ።
ቤት ደርሶ ያስቀመጠውን እየተሸከመ ማውጣት ጀመረ። በግቢው የነበረ የአከራዩ የልጅ ልጅ ከሸክሙ ሊያግዘው ግማሹን ተቀበለው። ተረዳድተው የሻንጣውን ከባድ ቋጠሮ እየተረዳዱ ከታክሲው የኋላ ኮፈን አኖሩት።ልጁ ወደቤቱ ሲመለስ ሰይድ ከኋላ ተቀምጦ ጉዞ ተጀመረ።
አንገቷንና ሁለት እጇቿን በትንሹ ሻንጣ ጨምሮ ከጀርባው እንዳዘለው ነው። ታክሲው የቱሊዲምቱ አቅጣጫን ይዞ ከነፈ። ሁለቱ ሰዎች በዝምታ መጓዛቸውን ቀጠሉ። መረጋጋት የተሳነው ሰይድ በመንድ የሚጓዙ ፖሊሶችን እያየ መደንገጥ ጀምሯል።
የጎሮን መንገድ አልፈው ቱሉ ዲምቱ አደባባይ ሲደርሱ ሰይድ ታክሲው እንዲቆም አዘዘ። ሾፌሩ አወረደውና የኋላውን ኮፈን ከፈተለት። እየተረዳዱ ሁለቱን ሻንጣዎች አወረዱና ከአስፓልቱ ዳርቻ አስቀመጡት። ሰይድ የኋላውን ሻንጣ እንዳዘለ ሂሳብ ከፍሎ ታክሲውን አሰናበተ።
በመንገዱ አልፎ…አልፎ መኪኖች ሽው ይላሉ፤ የመስከረም ጸሀይና ንፋስ በእኩል እየተራመዱ ነው። ሰይድ ጥቂት ራሱን አረጋግቶ ግራ ቀኙን ቃኘ፤ አካባቢው ከእግረኞች ግርግር የፀዳና ጭር ያለ ነው። ሻንጣዎቹን በሁለት እጆቹ አንጠልጥሎ ራመድ አለና ወደ መሀል ሜዳው አለፈ። እምብዛም አልራቀም። የያዘውን ቋጠሮ አስቀምጦ እየተገላመጠ በሌላ አቅጣጫ መንገዱን ቀጠለ።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ራሱን ከቃሊቲ ወደ መገናኛ ከሚሄድ ሀይገር ውስጥ አገኘው፤ ከኋላ ያዘለውን ሻንጣ ከግድግዳው የዕቃ ማስቀመጫው ኪስ አስቀምጦ መቁነጥነጥ ጀመረ። አሁንም በመንገድ የሚያልፉ ፖሊሶች እያስደነገጡት ነው። ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ሲደርሰ ‹‹ወራጅ፣ ወራጅ፣ እያለ መጮህ ጀመረ፤ ረዳቱ በሩን ከፈተለት። ተጣድፎ ወረደ። በሀይገሩ የጫነውን ሻንጣ ስለመርሳቱ ያስታወሰው የለም።
ቤቱ ሲገባ ቀሪው የፌስታል ቋጠሮ ጠበቀው። ጊዜ አላባከነም። የሟችን አልባሳትና የውስጥ ሱሪዎች መቀስና ሌሎች ንብረቷቿን አክሎበት የቤቱን ልጅ እንዲያግዘው ጠራው። ይኼኔ አስቀድሞ የመጣው ታክሲ ደጃፉ ደርሶ ነበር።
ልጁ አንዱን ፌስታል ተሸክሞ ከጋቢናው አኖረለት። እሱ ሌላውን ይዞ ከኋላ ወንበር ተቀመጠና ወደ ጎሮ አቅጣጫ አመሩ። አደባባዩ አጠገብ ሲደርሱ አስቆመውና ከታክሲው ወረደ። ፌስታሎቹን ተሸክሞ መንገዱን ተሻገረና ቋጠሮዎቹን አሽቀንጥሮ ወረወራቸው።
የፖሊስ ምርመራ …
መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ.ም ንጋት አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ከሚባለው አካባቢ የታየው እውነት ብዙዎችን የሚያስደነግጥ ሆነ። በማለዳው በኩርቱ ፌስታልና በሻንጣዎች ውስጥ ተቆራርጦ የተገኘው ነገር የአንዲት ወጣት አካል መሆኑን ፖሊስ በስፍራው ተገኝቶ አረጋገጠ። ወዲያው መረጃዎቹን አሰባስቦ ተጠርጣሪውን በእጅ ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት አደረገ፡፤
ከሟች የስራ ባልደረቦች፣ ከመኖሪያ አካባቢዋ፣ ከቤተሰቦቿና በስፍራው ከተገኙ የግል ንብረቶቿ የተወሰዱ ማስረጃዎች ለምርመራው ጠቃሚ ነበሩ። ከአዲስ አበባ እስከ ኮምቦልቻ የተጓዙ መርማሪዎች ሌት ተቀን የለፉበት ትግል ዋጋ አላጣም። ተጠርጣሪውን ይዘው ቃሉን እንዲሰጥ አደረጉ።
ሰይድ ድርጊቱን በትክክል ስለመፈፀሙ አመነ። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ሄለንን ስለመግደሉ እርግጠኛ እንዳልሆነ ተናገረ። በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 436/11 የተመዘገበው ቃል በማስረጃነት ተመዝግቦ ተያዘ። ግለሰቡ ክስ ይመሰረትበት ዘንድም ዶሴው ለዓቃቤ ህግ ተላለፈ።
ውሳኔ…
መጋቢት 7 ቀን 2013 ቀን በችሎቱ የተሰየመው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በከባድ ሰው መግደል ወንጀል ተከሶ የቀረበውን ተጠርጣሪ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮው ተገኝቷል። ፍርድ ቤቱ ግለሰቡ በፈፀመው እጅግ አሰቃቂና ኢሰብአዊ ወንጀል ጥፋተኛ ስለመሆኑ አረጋግጧል። በዕለቱ በሰጠው የፍርድ ውሳኔም እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የዕድሜ ልክ እስራት ይቀጣልኝ ሲል በየነ።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም