የወንጀል ተካፋይ የሆነን ሰው ምስክር አድርጎ ከክስ ነፃ የሚሆንበትን የሕግ ማዕቀፎች ከመመልከታችን በፊት ከክስ ነፃ የማድረግ ምንነትና ዓይነቶችን መመልከት ተገቢ ነው። ስለዚህ ከክስ ነፃ ማድረግ ማለት ከቃሉ መረዳት እንደሚቻለው በሕግ ከሚጣል ግዴታ፣ ከመከሰስ ወይም ከቅጣት ነፃ ለማድረግ የሚወሰን ውሳኔ ነው፡፡ ከክስ ነፃ ማድረግ የተለያየ ዓይነት ያለው ሲሆን፤ ምስክርን ከክስ ነፃ ማድረግ፣ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመንግሥት ኃላፊዎችን ከክስ ነፃ ማድረግ፣ የሉዓላዊነት ነፃነት እና የዲፕሎማሲ ነፃነት ሊሆን ይችላል፡፡
ምስክርን ከክስ ነፃ ማድረግና ዓላማው
በወንጀል ፍትህ አስተዳደር በወንጀል የተሳተፈን ሰው ከክስ ነፃ በማድረግ እንደ ምስክር መጠቀም በተለያዩ አገራት ተግባራዊ የሚደረግ አሰራር ነው፡፡ ይህ አሰራር ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ የሚጠረጠር ሰው በጉዳዩ ዙሪያ ጠቃሚ ማስረጃ የሚሰጥና ለምርመራና ክስ ሥራ ውጤታማነት ድጋፍ የሚያደርግ ከሆነ ከክሱ ነፃ ተደርጎ የምስክርነት ቃል እንዲሰጥ የሚደረግበት ነው፡፡ አንድ ሰው ከክስ ነፃ የሚደረገው ከእሱ ለሚገኘው ማስረጃ/ምስክርነት ለውጥ ተደርጎ ነው ማለት ነው፡፡
በወንጀል ተካፋይ የሆነውን ምስክር በሁለት ዓይነት መንገድ ከክስ ነፃ ማድረግ ይቻላል። በዚህም ግለሰቡ ምስክር ከሚሆንበት ወንጀል ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረግ አንዱ ሲሆን ግለሰቡ የሚሰጠው ማስረጃ/ምስክርነት ቃል በእሱ ላይ እንደማስረጃ እንዳይቀርብ ማድረግ ሁለተኛው ነው፡፡
ከክስ ነፃ የማድረግ ውሳኔ የሚሰጠው በወንጀል ድርጊቱ ያለው ተሳትፎ አነስተኛ የሆነውን ሰው ነፃ በማድረግና ምስክርነቱን በመጠቀም ከባድ ወንጀለኞችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራን ውጤታማና ቀላል ማድረግን ዓላማ በማድረግ ነው፡፡ አሠራሩ ከባድ ወንጀለኞችን ተጠያቂ በማድረግ የሕዝብን ጥቅም የማስከበር እና የምስክሩን ጥቅም ለማጣጣም የተዘረጋ ነው፡፡
ይህ አሰራር ለወንጀል ፍትህ አስተዳደር ውጤታማነት የሚያበረክተው ጠቀሜታ እንደተጠበቀ ሆኖ ያለአግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውል፣ ምስክሩ በተጽዕኖ የተሳሳተ ማስረጃ እንዳይሰጥ በጥንቃቄ እና በልዩ ሁኔታ አስፈላጊው መስፈርት ሲሟላ ብቻ ጥቅም ላይ እንዲውል ይመከራል፡፡ ለአብነት ነፃ የተደረገው ሰው የሚሰጠው ማስረጃ በሌሎች ማስረጃዎች እንዲደገፍ እና የሚሰጠው ምስክርነት ትክክለኛነቱ የመስቀለኛ ጥያቄ በመሳሰሉ ስልቶች እንዲረጋገጥ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ምስክርን ከክስ ነፃ የማድረግ ቅድመ ሁኔታ
በወንጀል የተሳተፈን ሰው ከክስ ነፃ ማድረግ እና እንደ ምስክር መጠቀም በተለያዩ አገራት የተለያየ አሰራር ያለው ሲሆን፤ በአገራት የሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችም ይለያያሉ፡፡ በዚህ መሰረት በአንዳንድ አገራት ከክስ ነፃ የሚደረገው ሰው ምስክር የሚሆንበት ጉዳይ እና ሰውየው ነፃ የሚሆንበት የወንጀል ጉዳይ ግንኙነት ያላቸው መሆን ይገባል፡፡ በተጨማሪም ከክስ ነፃ ለማድረግ የጉዳዮቹ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ነፃ የሚደረገው ሰው የሚሰጠው ማስረጃ/ምስክርነት ክብደትም ከግምት ይገባል፡፡ ይህ ማለት ነፃ የሚደረገው ሰው የሚሰጠው ምስክርነት ለጉዳዩ ውጤታማነት ወሳኝና ጠቃሚ ማስረጃ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል የተወሰኑት አገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ከወንጀል ክስ ነፃ የማድረግ ውሳኔ ከወንጀል ተጠያቂነት ነፃ የተደረገውን ሰው ከፍትሐብሔር ተጠያቂነት አያድነውም ወይም በፍትሐብሔር ክስ ሊቀርብበት ይችላል፡፡
በአጠቃላይ የብዙ አገራት የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያሳየው ምስክርን ከክስ ነፃ የማድረግ ውሳኔ የሚሰጠው ግለሰቡ ምስክር የሚሆንበት ወንጀል ከባድነት፣ የምስክርነቱ ጠቃሚነትና ቅቡልነት እንዲሁም ግለሰቡ በወንጀሉ ያለው ተሳትፎና ምስክር የሚሆንባቸው ሰዎች ያላቸው ተሳትፎ እንደ መመዘኛ ተወስዶ ነው፡፡
ከክስ ነፃ ማድረግ በኢትዮጵያ
በአገራችን በተለይ በሙስና ወንጀል ጉዳዮች የወንጀል ተሳትፎው አነስተኛ የሆነን ሰው ከክስ ነፃ ማድረግና በሌሎች ላይ ማስረጃ እንዲሆን ማድረግ የተለመደ አሰራር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የአገራችን የሕግ ማዕቀፍ ሲታይ በተለያዩ የሕግ ሰነዶች እውቅና የተሰጠው የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አሰራር እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡
በ2003 ዓ.ም የወጣው የአገራችን የወንጀል ፍትህ ፖሊሲ ለወንጀል ተግባር በተቋቋሙ ቡድኖች፣ በረቀቁ ዘዴዎች ወይም በትጥቅ በታገዘ ወይም በርካታ ሰዎች የተሳተፉበት አመፅ ወንጀሎች ውስጥ የተሳተፈ ሰው ሌሎች ተጠርጣሪዎችን የሚመለከት እና ለምርመራና ክስ ሥራው ውጤታማነት ጠቀሜታ ያለው ማስረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ከሆነ በዐቃቤ ሕግ ውሳኔ ተጠያቂነቱ ዝቅ የሚልበት ወይም በሙሉ የሚቀርበት አሰራር በሕግ እንደሚወሰን ያስቀምጣል፡፡ ይህ አሰራር ተግባራዊ የሚደረገው እንደ ሙስና፣ ሽብርተኝነት ወይም ወንጀሉ ውስብስብ ሆኖ የተጠርጣሪውን ትብብር ማግኘት አስፈላጊ በሚሆንበት ሁኔታ ሊሆን እንደሚችል ፖሊሲው ያመላክታል፡፡
በሌላ በኩል የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 በወንጀል ተካፋይ የሆነ ሰው ስለተፈፀመው ድርጊት ጠቃሚ ማስረጃ ከሰጠ ከክስ ነፃ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀፅ 4 (1) ላይ አንድ ሰው መረጃ በተሰጠበት የወንጀል ድርጊት ያለመከሰስ ነፃነት እንዳለው ተደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ክስ ማንሳት እንደሚችል ይደነግጋል፡፡
በአጠቃላይ ከላይ ከተጠቀሱት የአገራችን ሕግ ማዕቀፎች መረዳት የሚቻለው አሰራሩ ተግባራዊ የሚደረገው ከባድና ውስብስብ በሆኑና የተከሳሹን ትብብር በሚፈልጉ ወንጀሎች፣ በግለሰቡ የሚሰጠው ማስረጃ ለምርመራውና ክስ ሥራው ውጤታማነት ጠቃሚ ከሆነ እና ግለሰቡ ማስረጃ/ምስክርነት ከሰጠ እንደሆነ ነው፡፡
ምንጭ:- የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2013