የጮቄ ተራራ ውስጥ ያሉት የዱር እንስሳት፣ የዕፅዋት እና የማዕድን አይነቶችን ለመግለፅ ያዳግታል:: ይህንን ተዘርዝሮ የማያልቅ ሀብት ለመውሰድ የማይቋምጥ የውጭ አካል የለም:: ከጥንት እስከ ዛሬ የጮቄ ተራራ ታሪክ የሚያመላክተው ይህንን ሃቅ ነው:: “ለዝሆን ሞት ምክንያቱ ጥርሱ እንዲሉ” ጮቄም ሃብቱን ለመንጠቅ በመጡ የውጭ ወራሪዎች ሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ ስንት ጊዜ እንደተወጋ ማሰብ ይሰቀጥጣል::
የጮቄ ተራራ የሚተዳደረው በዱር እንስሳት ነው:: የዱር እንስሳቱ በጫካ ውስጥ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ወጎችን ይጠረቁበታል:: የእድር፣ የእቁብ — ወዘተ ወጎች እና ህግጋት ይራቀቁበታል:: በተራራው የሚኖሩ እንስሳት አንዱ በአንዱ ላይ ጥቃት እንዳያደርስ እና እንዳይጎዳዱ የጮቄ ተራራ የራሱ ህግ እና ስርዓት አለው:: ስርዓቱን የሚቆጣጠሩ ሊቀመንበር እና ኮሚቴዎች ያሉት ሲሆን ኮሚቴዎቹ በየጊዜው ይቀያየራሉ:: የኮሚቴው ምርጫ የሚከናወነው ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደነበረው የሮማን ሪፐብሊክ ገዢዎች በየዓመቱ የሚከናወን ነው:: ልዩነቱ የኮሚቴዎች ምርጫ በውድድር መሆኑ ነው ::
ውድድር ስል አንድ ነገር ትዝ አለኝ:: ተወዳዳሪዎቹ ለመመረጥ የሚያደርጉትን መጋጋጥ የዘመኑን ፍቅር አስታወሰኝ:: የዘመኑ የተቃራኒ ጾታ ፍቅር ግርም የሚል እኮ ነው:: ምንተስኖት እና ዓለሚቱ በአንድ ወቅት ሰው ሁሉ የቀናባቸው ፍቅረኛሞች ነበሩ:: ፍቅራቸውን አይቶ ያልቀና አልነበረም :: ፍቅራቸውን የጀመሩ ሰሞን ከፍቅራቸው የተነሳ በዓለሚቱ አይን ውስጥ የሆነ ባዕድ ነገር ቢገባ ባዕድ ነገሩን የሚያወጣው በእጁ ሳይሆን በምላሱ ነበር:: ይህን ያዩ ሰዎች ‹‹ፍቅርማ እንደነዓለሚቱ እና ምንተስኖት ነው›› እያሉ በየጠላ ቤቱ እና በየቡና መጠጫው የወግ መጀመሪያ አድርገውት ነበር :: እየቆየ ግን ፍቅር ሲቀዘቅዝ በምላሱ ቆሻሻን ሲያወጣለት የነበረን አይን በቡጢ ይነርተው ገባ :: ይህን ያየችው እቴ ጦጢት “ፍቅር እና የአፍሪካ ፖለቲካ ግን ከጅምሩ እስከመጨረሻው አንድ አይነት ነው::” አለች ይባላል::
ተመራጭ ኮሚቴዎች እነሱ ቢመረጡ የሚያደርጉትን ሲናገሩ በጮቄ የሚኖሩት እንስሳት በቅስቀሳው በሰሙት ነገር ለመጠቀም መጎምዠታቸው አልቀረም:: ተወዳዳሪዎች ለኮሚቴነት ምርጫ በሚወዳደሩ ሰዓት አንደኛው እጅግ ከሚባለው በላይ ‹‹አለሁላችሁ›› የሚል እና ሲበዛ ቅቤ አንጓች ንግግር ሲያደርግ አንድ በጌሾ ፍሬ የሰከረ ዝንጀሮ ተነሳና ‹‹ይህ ተወዳዳሪ ኮሚቴ አለቃ ገብረሃናን አስታወሰኝ :: ነገረ ስራው ሁሉ እሳቸውን ነው›› ብሎ ምርጫ ቀስቃሹን አፌዘበት:: የምርጫ ተወዳዳሪው በብስጭት ዝንጀሮውን “አንተ አመለካከትህ ሁሉ የቀኝ ዘመም ነው ::” ይለዋል:: ሰካራሙም ‹‹እኔ ቀኝም ግራም አልዘምም ፤ ሰክርሃል እያልከኝ ነው›› ብሎ እሰጣ ገባ ውስጥ ገቡ :: ጫካውን ከተኩላ ተረክቦ እያስተዳደረ ያለው አንበሳ ጠበኞቹን በጥበብ ገላገላቸው:: ሰካራሙም ‹‹ኤጭ ከኔ ከሰካራሙ ያልተሻለ ተመራጭ ተብዬ›› ብሎ በተመራጩ ላይ ጮኸበት ::
የሰሞኑ ምርጫ ቅስቀሳ ያላሳየን አስተዛዛቢ እና አስገራሚ ነገር ያለ አይመስለኝም :: አንዳንድ የምርጫ ቀስቀሳ ላይ የሚገቡ ቃሎች መሬት ላይ ሊተገበሩ የሚችሉ አይመስሉም :: እንዲሁ አደርጋለሁ ብቻ :: ይህን ስል አንድ ሽማግሌ ያሉት ትዝ አለኝ :: ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሽማግሌ ለየካቲት ጊዮርጊስ ንግስ ታቦቱን ለማንገሥ፤ ልጃቸውን ተከተለኝ ብለው በሌሊት ተነስተው መንገድ ይጀምራሉ:: ልጅ ከኋላ ሲመጣ ግን ጥሩ ነገር ይዞላቸው አልመጣም :: የልጃቸውን ፊት የተመለከቱት አባት ልጃቸው ምን እንደሆነ ይጠይቁታል :: ልጁም በቤት የነበራቸውን አንዱን እና ብቸኛውን በሬ ሌባ እንደወሰደው ይነግራቸዋል:: በቆሙበት ብርክ ይዟቸው ይወድቃሉ:: በወደቁበት ሳይነሱ «አዪ! ጊዮርጊስ እንደው የዛሬን ብለህ በሬዬን ያስመለስክልኝ እንደሁ ስለት በሬ አገባልሃለሁ» ብለው ይሳላሉ:: የአባቱን ስለት ያዳመጠው አቡሽ፤ «አባዬ! ያለን በሬ አንድ ፤ እሱኑ ለጊዮርጊስ ለስለት ካገባነው ለምኑ ነው!» ቢላቸው «ዝም በል! ዝም በል! በሬው ይገኝ እንጂ ማን ይሰጠዋል ብለህ ነው።» አሉት ይባላል። አሁንም በጮቄ ተራራ የሚደረገው የምርጫ ቅስቀሳዎች ምረጡን እንጂ ያልነውን ፈጸምን፤ አለመፈፅም የሚባለውን ነገር የናቁት ይመስላል::
በጮቄ ተራራ የማይወራ ነገር የለም :: ነገር ግን ወጎች ሁሉ እንደፈለጉ አይወሩም:: ሁሉም የዱር እንስሳ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ በማሰብ በጮቄ ተራራ በሚገኙ ዛፎች እና እንደታንክ በተገተሩ ድንጋዮች ላይ በአራቱም ማዕዘን ህግ እና ደንቦች ተፅፈዋል :: ከእነዚህ ፅሁፎች መካከል አንዱ “የጥላቻ ንግግር ማድረግ የተከለከለ ነው::” ይላል:: ይህን ህግ የተመለከቱ የጮቄ ተራራ ነዋሪዎች የጥላቻ ንግግር ላለማድረግ ይጠነቀቃሉ::
የጥላቻ ንግግር ማድረግ በህግ የተከለከለ ቢሆንም ይህን መስመር የተላለፉ ሰዎችን የሚያነሳሱና የሚያባሉ ከዚያም ከዚህም ብዙ ናቸው:: በአንበሳው የሚመራው ኮሚቴ እነኝህን ህገወጥ አካላት ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ቀጭን ትዕዛዝ በተደጋጋሚ ያለመታካት አስተላልፋል:: ነገር ግን ቀጭኑን ትዕዛዝ አልፈው ለጥቅማቸው የሚንፏቀቁትን ከዚያም ከዚህም ስመለከት አማኑኤል ሆስፒታል የሆነው ትዝ አለኝ::
አማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ የሚሰራ አንድ የአእምሮ ህሙማን ዶክተር የአዕምሮ ህሙማኖች ወደ ውጭ እየወጡ ያስቸግሩትና በመውጫው በር ወለሉ ላይ በደማቁ መስመር በማስመር «ከዚህ በኋላ ማንም ከዚህ መስመር እንዳያልፍ» ይላቸውና ይወጣል። ዶክተሩ ትንሽ ቆይቶ ሲመለስ የአእምሮ ታማሚዎች ወለሉ ላይ ሲንፋቀቁ ያያቸዋል:: «ምን እየስራችሁ ነው?» ብሎ ሲጠይቃቸው፤ ከበሽተኞች መካከል አንዱ ተነሳና « ከመስመሩ በሥር ልናልፍ ነው» ብሎ ይመልሳል። በጮቄ ተራራ ያሉ የጥላቻ መርዝ ነስናሾች በዚህ ሲከለከሉ በዚያ ሊሾልኩ ይሞክራሉ:: ኧረ ጎበዝ ምን ይሻላል?
ለስርዓት አስከባሪነት የሚወዳደሩት ኮሚቴዎች አንድ ችግር ሲፈጠር ችግሩን ተባብረው መፍታት ሲገባቸው ጣት ይቀሳሰራሉ:: ከተወዳደሪ ኮሚቴዎች መካከል አንዱ የሆነው አያ ጅቦ አንድ ቀን ስርዓት ለማስከበር እንደሚወዳደር ረስቶት የሚያሰክር መጠጥ በገፍ ጠጥቶ ጥንብዝ ብሎ ሰከረ:: ፈጣሪ ይባርካቸውና አንበሳ እና ጦጣ ጅቡን ስካሩ እስኪለቀው ድረስ ጭንቅላቱ ላይ ውሃ አፈሰሱበት :: ስካሩም በረደለት :: ነገር ግን የጠጣው ብዙ ስለነበር አስመለሰው:: የዱር እንስሳት በሙሉ ተሰብስበው ለምርጫ የሚወዳደረውን ጅብ መስከሩን እና ማስመለሱን ተመለከቱ:: በዚህ ጊዜ ‹‹አያ ጅቦ ሰክሮ አስመለሰ›› እንዳይባል ‹‹አንበሳን እና ጦጢትን ሳይ ያስመልሰኛል::›› ብሎ አረፈው :: የሚገርመው ነገር የአያ ጅቦ ደጋፊዎች የሚደግፉት የኮሚቴ ተመራጭ እንደሰከረ እያወቁ ‹‹አያ ጅቦ ያስመለሰው አንበሳን እና ጦጢትን ስላየ ነው::›› አሉ:: አልበቃ ብሏቸው አንባጓሮ ፈጥረው አካባቢውን አመሱት ::
የኮሚቴ ደጋፊዎች ስለምን ራሳቸው ለሚፈጥሩት ችግር ሌላ ሰው ላይ ጣታቸውን ይቀስራሉ :: ካልሆነ ዝሆን በጥርሱ እንዲሉ የጮቄ ተራራ ሃብት ለመቃረም የሚፈልጉ ሃይሎች እንዲያጠፉት በር መክፈት ነው:: ይህን የደጋፊዎች ደመነፍስነት የተመለከተችው ጦጣ ‹‹የሚሞትለት ዓላማ የሌለው ለመኖር ብቁ አይደለም :: ›› አለ ማርቲን ሉተር ኪንግ ብላ ቆዘመች ::
‹‹የዝሆን የሞቱ ምክንያት ጥርሱ ነው::›› እንዲሉ አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው አሁን በስልጣን ላይ ያሉ የኮሚቴ አባላት ኮሚቴው በተግባር ምድር ላይ እየሰራው ያለውን አስደማሚ ሃቅ መደበቅ ባይችሉም ማጠየማቸው ግን አልቀረም :: ይህ ደግሞ ከጮቄ ተራራም በውጭም ሆነ በውስጥ ለሚገኙ ጮቄን ለሚጠሉ ኃይሎች እኩይ ተግባራቸውን እንዲያከውኑ የራስጌ እና የግርጌ ማህተም ረግጦ እና ፈርሞ እንደመፍቀድ ይቆጠራል:: ያገኘውን ስለሚቀረጣጥፍ እና ስለሚደቋቁስ አንበሳ የሚከበረው በጥርሱ እና በክርኑ ነው:: ስለሆነም የኮሚቴውን መልካም ስራ የሚያጠይሙ አካላት ‹‹ዝሆን ጠላቱ ጥርሱ ነው ›› የሚለው ኮሚቴው ላይ እውን እንዳይሆን ኮሚቴው እንደ አንበሳ መሆን ይገባዋል:: በጉያው ያሉትን አሜካላዎች ባይደቁሳቸውም፣ በጥርሱ ባይቀረጣጥፋቸውም ከጉያው ግን ሊያስወጣቸው ግድ ነው ::
አሁን ላይ ጮቄን ከተኩላ ተረክቦ የሚመራው አያ አንበሶ ከጮቄ ተራራ ውጭ የሚመጡ የሃሰት ህብስት ለጮቄ የዱር እንስሳት እንመግባለን በሚል ሰበብ ጮቄን ለማፍረስ የሚያደርጉት ጥረት መቼም እንደማይሳካ ደጋግመው ይናገራሉ :: ነገር ግን ‹‹ጮቄን የሚመራው የአያ አንበሶ ኮሚቴ ሹመት ሺህ ሞት ሆኖበት በቻለው አቅሙ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ እና ሃገርን እንደ ሃገር ለማስቀጠል በሚላላጥበት ሰማይ ለመቧጠጥ ሳይቀር ጥረት እያደረገ ባለበት በዚህ ወቅት ከዚያም ከዚህም ያሉ ተባዮች የዱር እንስሳቱን ደም የሚመጡበትን ሱስ ሊወጡ በማሰብ ቀይ መስመር ሲረግጡ በተደጋጋሚ ይስተዋላሉ:: ይህን ለመከላከል ሁሉም የኮሚቴ ተወካዮች እና እንስሳት በአንድ ላይ መቆም አለባቸው :: አለበለዚያ ግን ዝሆን በጥርሱ መሆኑን አትርሱ !!“ ስትል ጦጢት በብስጭት ተናግራለች ::
ከልጅነቴ ጀምሮ ነፍስ እስካወኩበት ጊዜ ድረስ የእኛ ሰፈር እድር በዳኛነት የመራው አያ ተኩላ ነው:: የእድሩ አባላትም እስከዛሬ ባንተ ስንመራ ማግኘት ያለብንን ሳናገኝ የዛሬያችንን ብቻ ሳይሆን ነጋችንንም ነጥቀኸናል:: ስለዚህ ከአሁን በኋላ በአንተ መመራት አንፈልግም ሲሉ በምሬት ነግረውታል:: ንግግሩም መስመሩን ስቶ ዱላ እስከማማዘዝ አድርሶ ነበር:: በተፈጠረው ዱላም የዱር እንስሳት ህይወትም አልፏል:: አያ ተኩላም ማምለጥ አይበሉት እንጂ ለጥቂት አምልጧል:: የሚገርመው የአያ ተኩላ ፍርፋሪ ለቃሚዎች እድሩን እና ሰፋራችንን በሃሰት ፕሮፖጋንዳ ሲያምሱት ሰነባብተዋል:: የተወሰኑትን የእድር አባላትንም በእነሱ መስመር እንዲፈስ ለማድረግ ሞክረዋል:: አያ ተኩላን በሃሰት የሚደግፉትን የተመለከተው አያ አንበሶ “እንዴት በአያ ተኩላ ሲበደል የኖረ የእድር አባል አሁን ላይ ምንም እንዳልተበደለ ይረሳል?” ሲል በብስጭት ይናገራል:: አያ ተኩላ የሚዋሸው ውሸት ህጻንንም እንኳን ማታለል አይችልም:: እንደዚህ አይነት ውሸት ስመለከት አለቃ ግብረሃናን ያስታውሰናል አለ አያ አንበሶ :: አለቃ ገብረሃና አንድ ቀን መንገድ ላይ መሽቶባቸው አንዲት ሴትየዋን እንድታሳድራቸው ይለምኗታል:: ቤት ለእንግዳ ብላ አስገባቻቸው። ቀኑም መሸ :: እራትም ተበላ :: እራት በልተው ከጨረሱ በኋላ ሴትየዋ መደብ ላይ አለቃ ደግሞ መሬት ላይ ተኙ:: አለቃ ቅንዝራም ቢጤ ኖረው ጨለማን ተገን በማድረግ ሴትየዋ መደብ ላይ ዘፍ ብላው ወደቁና ሴትዮዋን መዳሰስ ይጀምራሉ። ሴትየዋም በድንጋጤ ነቅታ “እንዴ ምን እየሰሩ ነው አለቃ?” ስትላቸው “ከአልጋ ላይ ወድቄ ነው” አሏት። “እንዴት መሬት ተኝተው ከአልጋ ወድቄ ነው ይላሉ?” ስትላቸው “እኔንስ የገረመኝ እሱ አይደል” አሏት ይባላል ። እንደዚህ አይነት ልብ አውልቅ ውሸት እየዋሸን የዱር እንስሳቱን መጠቀሚያ መደረግ የለበትም በማለት የተናገሩት አያ አንበሶ፤ አክለውም አያ ተኩላ እና ተከታዮቹ ያደረጉትን እና እያደረጉት ያለውን ስመለከት ሮማን ፕሮቻዝካ ኢትዮጵያ (ጮቄን ተራራ) የባሩድ በርሜልና የመርዙ ብልቃጥ ከሰራው ጋር ይስተካከላል ይላሉ::
ሮማን ፕሮቻዝካ ጮቄን ጎብኝቶ የዱር እንስሳቱ ለነጭ አይበገሬነታቸውን ከተመለከተ በኋላ አቢሲኒያ፥ ዘ ፓውደር ባሬል ( Abyssinia: the powder barrel) በሚል በብስጭት በደረሰው ድርሳን ላይ ኢትዮጵያን በዘር በመከፋፈል ማፈራረስ እንደሚቻል አትቷል:: እንዳለውም እነ አያ ተኩላን በመሰሉ የሰይጣን ዛር ውላጅ በሰፈረባቸው ሰዎች በመጠቀም ኢትዮጵያን በዘር በመካፈፈል ሃገሪቱን ከሚገባት በላይ ተፈታትነዋታል::
ግርም የሚለው ይህንን የከፋፋዮች ሃሳብ የሚደግፈው አያ ተኩላ በሰራው ስራ ከመጸጸት ይልቅ በስራው ተኩራርቶ የጮቄን ተራራ ለወራሪዎች አሳልፎ ሊሰጥ አሁንም ይቋምጣል:: ደግነቱ እሱና መሰሎቹ ከምድረ ገፅ እየጠፉ ነው:: ይህን ስመለከት ለአሸናፊነት መገዛት በሚለው መጽሃፍ ውስጥ መለወጥ የማይፈልጉ በሚለው አንቀጽ ውስጥ አያ ተኩላውን በግልጽ ተመለከትኩ:: መጽሐፉም መለወጥ ስለማፈልጉ አካላት እንዲህ ያትታል‹‹ሰዎች አሉታዊ ልምዶች እንዳሏቸው ሲገነዘቡ ወይም ሲያውቁ ለምን አይለወጡም ? የማይለወጡበት ምክንያት ሃላፊነትን ለመቀብል ፍቃደኛ ስላልሆኑ ነው:: በልምዳቸው መቀጠላቸው የሚሰጣቸው እርካታ ከስቃዩ ይበልጣል:: ምናልባትም የመለወጥ ፍላጎት ይጉድላቸው፣ ለለውጡ ራሳቸውን የማስገዛት አቅም ይነሳቸው፣ ለመለወጥ ስለመቻላቸው እምነት አይኖራቸው ፣ አልያም የለውጡን አስፈላጊነት በተመለከተ ግንዛቤ ይጎድላቸው ይሆናል:: እነዚህ ሁሉ ልምዶች አሉታዊ ልምዶቻችን እንዳናስወግድ ይከለክሉን ይሆናል:: በዚህ ጊዜ አንድ አማራጭ ይኖራል:: አሉታዊ ባህሪያችንን ችላ በማለት በራሱ ጊዜ እንደሚወገድ ተስፋ ማድረግ ነው። ይህ በግልፅ የሚታየውን እውነት ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆን ነው :: ›› ይላል::
ሮበርት ሙጋቤ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር:: ‹‹ሴቶች በሙሉ የኤድስ መድሃኒት እስኪገኝ ድረስ የግብረ ስጋ ግንኙነት አንፈጽምም ብለው ቢያምጹ ኖሮ፡ ወንዶች በ30 ቀናት ውስጥ መድሃኒቱን ባገኙት ነበር።›› የጮቄ ህዝብም የውሸት እና የዘር ጥላቻ መርዝ የሚያጎርሱህን ፖለቲከኛ እና አክቲቪስት ባዮችን አንሰማችሁም ቢል ተመራጭ ኮሚቴዎች በስርዓት ወደ መስመር ይገቡ ነበር:: ሃገራችንንም ከውጭ ተናካሽ አውሬዎች በቀላሉ መጠበቅ እንችል ነበር፤ ባይ ነኝ ::
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2013