ወገን ቁም ነገር ሰንቀን የተዛነፈን ሀሳብ የምንተችበት፣ የተሳሳተን እሳቤ የምናርምበት ወጋ ወጋ የተሰኘው አምዳችን ላይ ዛሬም አንድ ሊታረም በሚገባው ጉዳይ ላይ በማጠንጠን፤ መፍትሄ ሊሆን የሚችል መድሃኒት ቀምመን ታማሚዎቹን ለመውጋት አስበን ብዕራችንን አነሳን፡፡ እጅጉን አገሬ ብለው ሲጮሁ የነበሩት አገር በብርቱ ስትፈልጋቸው ድምጻቸውን ያጠፉትን ለምን? እንላለን፤ ተከተሉን፡፡
በቀጣይ ምርጫ ላይ በተለያዩ ምክክቶችና የፖሊሲ አማራጮች ኢትዮጵያን እንመራለን ያሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በወቅቱ አገራዊ ጉዳይ ላይ ድምፃቸው መራቁ አስገራሚ ነውና እዚህ ላይ ማጠንጠን አሰብን፡፡
እዚህ አገር ላይ ስለኛ በብዙ የሚናገሩ እዚህች ምድር ላይ እኛን ለመምራት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አንዴ ምረጡኝ ሌላ ጊዜ ደግሞ እኔን ከመረጣችሁ የተሻለ አስተዳደራዊ ለውጥ እናመጣለን የሚሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ኢትዮጵያ በወሳኝ ወቅት ላይ ድምፃቸውን ስትፈልግ ስለምን ዝም አሉ? በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የመጣን የውጪ ጫና በአገራችን ጥቅም ላይ ጋሬጣን ለመፍጠር ከሩቅ የመጣውን አካል እንዴት በአንድነት ቆመው ተቃውሟቸውን ሳያቀርቡበት ቀሩ፡፡
ምንም ያህል የአቋም ልዩነት ላይ አንቁም፣ መቆሚያችን አንዲት አገር ናት ፤ ኢትዮጵያ፡፡ የቱንም ያህል የአመለካከት ልዩነት ይኑረን፤ በልዩነታችን አቅፋ በያዘችን አገር ብሄራዊ ጥቅም ላይ እንዴት አንድ ሆኖ መቆም ተሳናቸው? እንዴት አብረው ስለአገራቸው ሉዓላዊነት መከበር ለዓለም ማስረዳት ተሳናቸው?
ተሻገሩ ወደ ባህር ማዶ፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአገር ጉዳይ ላይ ያለ ልዩነት ቁርሾና ንትርካቸውን ትተው ሲቆሙ ታያላችሁ፡፡ ርቃችሁ በየትኛውም አድማስ ሂዱ፤ በውስጥ ጉዳያቸው ላይ ልዩነት ያለባቸው እንኳን ቢሆኑ ከውጪ በመጣ ጠላት እና አካል ላይ በአንድነት አንድ ድምፅ ሆነው ባዕዱን ሲሟገቱ ታገኛላችሁ፡፡ የውስጥ ልዩነታቸውን ወደ ጎን በማድረግ ለአገራዊ ጥቅማቸው በእኩል ይሰለፋሉ፡፡
አሁን ላይ የራስዋን ጥቅም ለማስከበር ስትል ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ሀብቷን እንዳትጠቀም ጋሬጣ ለመፍጠር የሚሞክሩት ግብፆች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም ተመልከቱ፡፡ አንዳንድ ስለ ፍትህና እውነት ከሚቆሙ ግለሰቦች ውጪ ፍትሃዊ ባልሆነም ጉዳይ ቢሆን በተለየዩ ጉዳዮች ተለያይተው በአባይ ጉዳይ ግን በአንድ ቆመው ኢትዮጵያ ላይ ይፈርዳሉ፡፡ ፍትሀዊ ባልሆነ ፍርጃ እንኳን ያብራሉ፡፡
ታዲያ የኛዎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን አጥበው ስለምን በአገሪቱ ላይ የተቃጣውን ፍርደ ገምድል ውሳኔና ርምጃ የመሪው /የመንግስት/ አካል ጉዳይ አድርገው የወሰዱት፡፡ ችግሩ የጋራችን ማዕቀቡ የተጣለው በአገራቸው አይደለምን? እንደ ህዝብ የሚጎዳው ነገ እንመራሀለን፤ እናስተዳድርሀለን የሚሉት ህዝብን አይደለምን? ምንም እንኳን መንግስትን ቢቃረኑ በተቃርኖ የሚቆሙበት ዋንኛ አገራዊ ጥቅም ህዝባዊ ሉዓላዊነትን የሚዳፈር ተግባርን እንዴት በአንድነት ቆመው መተቸት ተሳናቸው?
በርግጥ በአገራዊ ጉዳይ ላይ በአንድነት ካላበርን፣ በዚህች አገር መፃኢ ዕድል ላይ በጋራ ካልወሰንን የየራሳችን ፍላጎት እንዲተገበር ብቻ ብንተጋ ምንስ ለውጥሊመጣ ይችላል? አንድ አገር ውስጥ ሆነን ተመሳሳይ የሆነን ህዝብ ለመምራት አቅደን በዚያ አገርና ህዝብ ጥቅም ላይ በአንድነት ካልተቆመ አገራዊ አንድነትንስ እንዴት ማጠንከር ይቻላል?
የዓለም ቁንጮ ነኝና የራሴን ፍላጎት ሌላው ላይ ልጫን፤ የበላይ ነኝና በጉልበቴ ሌላውን ልደፍጥጥ ባይዋ አሜሪካ ዛሬ በሉዓላዊ አገራችን ላይ ፍትህ አልባ ውሳኔ አሳልፋለች፡፡ ይህች አገር ስለኛ የምታሰላና የምትጨነቅ ሆና አታውቅም፤ ይልቁንም እሷ ለኔ ብላ በምታሰላው የራስዋ ጥቅማዊ ስሌት መሰረት አድርጋ ለኔ የቱ ይበጀኛል ብላ እንጂ፡፡ የእኛ ህዝብ ጉዳይ አሊያም ችግር ለእርሷ ምኗም አይደለም፡፡
ታዲያ የኛዎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህችን ፍርደ ገምድል አገር የምንረታበት ትልቁ ቁልፍ በእጃችን እንዳለ ስለምን አልተረዱም? ሁሉም ዜጎች ያለ ልዩነት በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመርኩዛ የወሰነችው ውሳኔና ተግባርዋ ተገቢ ያለመሆኑን ርምጃዋ ለራስዋ የማያዋጣት እንደሆነ መንገሩ እንዴት ተሳነን?
ነገ በምርጫ አሸንፋችሁ የምታስተዳድሩት ህዝብ በአገራዊ ጥቅም ላይ ያላችሁ አቋም በዚህ መሰሉ ጉዳይ ላይ አቋማችሁን ካላሳወቃችሁት እንዴት መረዳት ይቻለው ይሆን? የውስጥ ችግራችን በራሳችን የምንፈታው ዘርፈ ብዙ ችግሮቻችንን በሂደት የምንግባባባቸው መሆኑን ለይተን፤ ከእኛነታችን ጋር እጅግ የራቀውን የሩቁን አካል አገራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ላይ የሰጠውን የተሳሳተ ውሳኔ ላይ አብሮ ተቁሞ አይ! እዚህ ጋ ይበቃል ስለምን አልተባለም፡፡
ይህ ጉዳይ በዚህ ፅሁፍ ላይ በወል ስም የተጠቀሱት አካላት ሁሉንም የሚመለከት ላይሆን ይችላል፡፡ አገራዊጉዳይ ነውና የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን ሉዓላዊነት የሚመለከት ነውና በፅኑ እንቃወማለን፤ በዚህም ጉዳይ አገራዊ አንድነት አለን ያሉ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ነበሩ፡፡ ጉዳዩ አገራዊ ጉዳይ እንጂ የገዢው ፓርቲ ጉዳይ ብቻ አይደለም ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና አንዳንድ ግለሰቦች ያራመዱት አቋም ሊደነቅም ይገባዋል፡፡
ነገር ግን ይህ ጉዳይ ኢትዮጵያን የሚጎዳ የኢትዮጵያዊያን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ስለመሆኑ በአንድነት ቆመው ሌላውን አካል በቃህ ያላሉቱ ተግባር ነው የሚገርመው፡፡ ዛሬ እጅጉን የገዘፈ ድምፃቸውን አጉልተው ስለ ኢትዮጵያ እንጮሀለን ስለ ህዝብዋ እንናገራለን የሚሉት እነዚህ አካላትና ፓርቲዎች በዚህ ወሳኝ ሰዓት ለአገራቸው ካልቆሙ በየትኛው ምቾት ላይ ሆነው ነው ታዲያ ስለኛ የሚሟገቱት፡፡
ምንም ያህል የተለያየ ሀሳብና የራሳችን እቅዶች ቢኖሩንም፣ እቅዳችንን የምናስፈፅምባት አገራችንና እንዲለወጥ የምንፈልገው ህዝባችን ጥቅም ላይ ልዩነት እንዴት ይኖረናል? ይህ የመንግስት ጉዳይ ነው፤ ያለ ተፎካካሪ ፓርቲ ነገ መንግስት ቢሆን የሚጋፈጠው እሱ አይደል፡፡ ዛሬ እሟገትልሀለሁ የሚለው ህብረተሰብስ እንዴት ነው ስለሱ የሚሟገትና የአገሩን ጥቅም ለሌላ አሳልፎ የማይሰጥ ስለመሆኑ የሚያረጋግጠው?
በእያንዳንዳችን ጥረት መፃኢ ብሩህ ገፅታዋን የምትገነባውን አገራችንን በአንድ አላማ ቆመን ጥቅምዋን ማረጋገጥ ይገባናል፡፡ ለማንኛውም ባዕድ አገርም ሆነ አካል አገራዊ ጥቅምን አሳልፎ የማይሰጥ፣ የህዝቧን ለውጥና ሉዓላዊነት የሚያከብርና የሚያስከብር ተፎካካሪ ፓርቲ፣ ስለኢትዮጵያ መቆሙን በተግባሩ ማረጋገጥ አለበት፡፡ አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2013