አዲስ አበባ፡- የመንገድ ግንባታ፣ የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ እና የቴሌኮም ሥራዎች አንዱ የሌላውን ሳያበላሽ እና ሳያፈርስ ተቀናጅተው እንዲሠሩ የሚያስገድድ ደንብ መዘጋጀቱ ተገለፀ፡፡
የተቀናጀ የመሰረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ እስክንድር ይማም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደገለጹት፤ ተቋማቱ በቅንጅት እንዲሠሩ ዓመታዊ ዕቅዳቸውን እንዲያናብቡ ከማገዝ ባሻገር ተቀናጅተው እንዲሠሩ አስገዳጅ ደንብ ተዘጋጅቷል፡፡
ኤጀንሲው ደንቡን አዘጋጅቶ ለከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያስተላለፈ ሲሆን፤ ሚኒስቴሩም በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የላከው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የደንቡ መፅደቅ ኤጀንሲው ተቋማቱ ደንቡን ሲተላለፉ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ እና ተጠያቂ እንዲሆኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት እንዲያሳውቁ የሚያስችል መሆኑን አቶ እስክንድር አመልክተዋል፡፡
ተቋማቱ በዓመቱ መጀመሪያ ዓመታዊ ዕቅዳቸውን ተናበው እንዲያዘጋጁ ኤጀንሲው ሁኔታዎችን ቢያመቻችም፤ ተቋማቱ ግን ከተቀናጀው ዕቅድ ውጪ እየሠሩ በመሆኑ ችግሩን መቀነስ እንዳልተቻለ አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ እስክንድር ገለፃ፤ መንገዶች ባለሥልጣን መንገድ ለመሥራት ሲያቅድ በመንገዱ የተዘረጋ የውሃ መስመር፣ ኤሌክትሪክም ሆነ የቴሌኮም ገመድ ያለበትን ሁኔታ ሳያጣራ ከተቋማቱ ጋር ሳይነጋገር ግንባታውን እንዲያካሂዱ ከተቋራጮች እና ከአማካሪዎች ጋር ውል በመፈፀም ወደ ግንባታ መገባቱ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ይገኛል፡፡
ለአብነት ከአዲስ አበባ ወደ ቡራዮ እና ጊንጪ የሚካሄደውን የመንገድ ግንባታ ሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ብዙዎቹ ግንባታዎች የሚጓተቱት አንድም ባለመናበብ ችግር ሳቢያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኤጀንሲው ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ቢቋቋምም ራሱን ከማደራጀት ጎን ለጎን ላለፉት ሁለት ዓመታት ተቋማቱ ተናበው ባለመሥራታቸው መሰረተ ልማቶች ሲጎዱ ጉዳቱ እንዳይስፋፋ በቦታው በመገኘት ጉዳት የመቀነስ(እሳት የማጥፋት) ሥራ እየሠራ ቆይቷል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2011
ምህረት ሞገስ