አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 17 የሚገኝ አንድ ቤት በሶስት የቤት ቁጥሮች የተከፈለ ስያሜ ተሰጥቶታል ። ቤቱ አንድ ጣራና ሶስት ግዳግዳዎች አሉት። በሶስቱ በሮች የግል መግቢያና መውጫም ተሰርቶለታል።
በቤቱ የሚኖሩ ሶስት አባወራዎችና ቤተሰቦቻቸው በአንድ ጣራ አድረው በሶስት የተከፈሉ ግድግዳዎችን ይጋራሉ። ይህን ቤት ጨምሮ ሌሎች መኖሪያዎችን የማስተዳደር ሃላፊነት ያለው የቀበሌ አስተዳደር ቤቱን ይገባቸዋል ላላቸው ሶስት ሰዎች አካፍሎ በጋራ ይጠቀሙበት ሲል ከወሰነ ጊዜያት ተቆጠረዋል።
ይህ ቤት በወረዳው በሚገኝና በቀበሌ 20 ክልል በተመዘገበ 32221 የካርታ ቁጥር ይታወቃል። በቁጥር 17/31791 መዝገብም በባለቤትነት መብት ደብተር ያወጡበት አንድ ግለሰብ ናቸው። የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ነጋሽ ዱባለ ሶስቱ ደጃፍ ቤቶች በስማቸው ተይዘዋል።ቤቶቹ በአንድ ጣሪያና ግድግዳ ተያይዘው የተሰሩ ናቸው። በቤት ቁጥር 1304፣1305፣እና 1306 መለያ የሚታወቁትን ባለ ሶስት ክፍል ቤቶች የቀበሌው ጽህፈት ቤት ላሰበው ዓላማ ሊያውላቸው ለሶስቱ አባወራዎች እኩል በማካፈል ሆኗል።
ሙግት…
አቶ ነጋሽ ይህን ውሳኔ ከቀበሌው ጽህፈት ቤት እንደተረዱ ድርጊቱን በእጅጉ ኮነኑ። ቤቱን በባለቤትነት የያዙት እሳቸው መሆናችውን ጠቅሰውም ለሚገባቸው ሁሉ አቤት አሉ። ግለሰቡ ‹‹አሉኝ›› ያሏቸውን የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነዶችን ይዘዋል። የፍርድ ባለመብት የሆኑበትና ርክክብ የፈጸሙበት ማስረጃም አብሯቸው ነው።
ግለሰቡ ቀናትን በፈጀ ምልልስ ቤቱ የእሳቸው እንጂ የሌሎች መሆን እንደማይገባው ሞገቱ። በእሳቸው ላይ እየሆነ ያለው ድርጊትም የዜግነት መብትን የሚጥስ፣ በህግ የተሰጣቸውን ህጋዊ አግባብ የሚቃረን ነው ሲሉ ተቃወሙ።
የአቶ ነጋሽና የቀበሌ ጽህፈት ቤቱ ሙግት ቀጠለ። በይገባኛል ጥያቄ ክርክር የፈጠረው ጉዳይም ቀጠሮን በቀጠሮ እያከለ ጊዜያት አስቆጠረ። የአቶ ነጋሽ አቤቱታና ክስ ለቀበሌውና ለሚመለከታቸው ሃላፊዎች ብቻ አልሆነም። ቅሬታቸው የቤቱ ተካፋይ ባለመብቶች በተባሉት ላይም ቀጠለ።
ነጋሽ ሶስቱን የቤት ተካፋዮችና የቀበሌ ጽህፈት ቤቱን እየወቀሱና ማስረጃ እያጣቀሱ መከራከሩን ቀጠሉ። ቀበሌው በበኩሉ የእሳቸውን ሃሳብ ሊቀበል አልወደደም። አሁንም ቤቱ ለሶስት ሰዎች በእኩል ሊሰጥ እንደሚገባ እያስረዳ ሞገታቸው። የአቶ ነጋሽና የቀበሌ ጽህፈት ቤቱ ክርክር ያለአንዳች መፍትሄ ተራዝሞ ጊዜያት ወሰደ።
ቤቱ ለእናንተ ይገባል የተባሉት ተከራዮች የ ‹‹ይገባናል›› መብታቸውን ጠየቁ። እነሱ መኖሪያውን ሲረከቡ ህጋዊ ማረጋጋጫን ይፈልጋሉ፤ ቤቱ በባለቤትነት ሲሰጣቸውም መኖርን የሚሹት ያለአንዳች ስጋት ነው።
አቶ ነጋሽ እስከዛሬ በቤቱ ላይ የከወኑትን ሁሉ እያስረዱ ነው። የቤትና የአፈር ግብርን ሳያቋርጡ ገብረዋል። በስማቸውም የቤት ካርታና የባለቤትነት ማረጋገጫ አግኝተዋል። የግብር ደረሰኞቻቸው ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ ክፍያ መፈጸሙን ይጠቁማሉ። እነዚህንና ሌሎች ሰነዶችን ዋቢ አድርገው የሚመለከታቸውን እየከሰሱ፣ መብታቸውን እየጠየቁ ነው።
በአቶ ነጋሽ፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 17፣ ቀበሌ 20 እና በቤቱ ተከራዮች መካከል የተጀመረው ውዝግብ ቀጥሏል። ቀበሌው ውሳኔው እንዲተገበር ይጠይቃል። ተከራዮች በቤቱ የመኖር መብትን ይሻሉ፣ አቤት ባዩ በጽህፈት ቤቱ የተላለፈው ውሳኔ ተገቢ አለመሆኑን እያነሱ ይሞግታሉ።
ያለአንዳች ስምምነት ጊዜያት ያስቆጠረው ውዝግብ መፍትሄ የሚጠቁም መላ አልተገኘለትም። አቶ ነጋሽ በቀበሌው ጽህፈት ቤት የተሰጣቸው ውሳኔና ጊዜያት የፈጁበት ክርክር እንዳልበጃቸው አውቀዋል። ነገሮችን በይሁንታ መቀበልን አልፈለጉም።
አቶ ነጋሽ መፍትሄ ያላገኙበት ውዝግብ እንደማያዋጣ በገባቸው ጊዜ ሌላውን አማራጭ ሊሞክሩ ተነሱ። አሁን
ባሰቡት አማራጭ የራሴ የግሌ፣ የሚሉትን ይዞታ በእጃቸው እንደሚያስገቡ አምነዋል። አመኔታቸው በርትቶም አቤቱታቸውን ሊቀጥሉ ወስነዋል።
የመጀመሪያው ክስ…
አሁን አቶ ነጋሽ ከፍርድ ቤት ችሎት ቆመዋል። የክስ አቤቱታቸውን ማየት የጀመረው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድቤት ግለሰቡ ያቀረቡትን የሰነድና ተያያዥ ማስረጃዎች እያጤነው ነው። አመልካቹ በህግ የተሰጠኝን መኖሪያ ቤት የቀበሌው ጽህፈት ቤት ለሶስት ግለሰቦች አካፍሎ ሰጥቶብኛል ሲሉ ባቀረቡት ክስና አቤቱታ ፍርድ ቤቱ ይመለከታቸዋል የተባሉትን ሁሉ መጠየቅ አስፈልጎታል።
ፍርድቤቱ አመልካቹ ያቀረቡትን አቤቱታ መሰረት አድርጎ ባደረገው ማጣራት ለውሳኔ የሚያደርሰውን በቂ መረጃ አግኝቷል። በሰነድ ተረጋግጠው የቀረቡለት ማሳያዎችም ግለሰቡ በትክክል ቤቱ እንደሚገባቸው የሚያሳዩና የሚጠቁሙለት ሆነዋል። በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ አቶ ነጋሽ የቤት ባለቤትና ባለመብት እንዲሆኑ በመወሰን ይዞታው እንዲለቀቅላቸውና የሚመለከታቸው አካላት እንዲያስረክቧቸው በማለት ብይኑን ሰጥቷል።
ከውሳኔው በኋላ …
የአቶ ነጋሽና የተጠሪዎቹ ጉዳይ በብይን እንደተጠናቀቀ አመልካቹ የውሳኔ ግልባጩን መውሰድ እንደሚችሉ ተነገራቸው። ነጋሽ ውሳኔውን በአክብሮት ተቀብለው ቀጣዩን የቤት መረከብ ሂደት ለመከወን ራሳቸውን አዘጋጁ። ቤቱን ከሚመለከታቸው አካላት በአግባቡ ተረክበውም በሚፈልጉት መልኩ ማደስና መጠገን ጀመሩ።
እንዲህ በሆነ ጥቂት ቀናት በኋላ ግን አቶ ነጋሽ ፈጽሞ ባልገመቱት ሁኔታ ራሳቸውን ከፍርድ ቤት ችሎት አገኙት። እሳቸው ጊዜያት በፈጁበት ውዝግብ ብዙ አሳልፈዋል። ሲናፍቁት በቆዩት ቤታቸውም አዲስ ኑሮና መልካም ህይወትን ሲያቅዱ ቆይተዋል። ነጋሽ ድንገቴ ሃሳብ ዋጣቸው ፣ አለቀ ያሉት ጉዳይ ዳግመኛ ሲመለስ ከልብ ተከፉ። ዳኛው የተጠሩበትን ጉዳይ ጠቅሰው ሁኔታውን አስረዷቸው። ቀድሞ በፍርድ ውሳኔ እንዲረከቡት የሆነው መኖሪያ አሁን ሌላ ተቃዋሚ መጥቶበታል። የስራና ከተማ ልማት ቢሮ ጣልቃ ገብ ሆኖ ውሳኔውን እየተቃወመ ነው።
አቶ ነጋሽ ቢሮው በክሱ ጣልቃ ገብ ሆኖ እየሞገታቸው መሆኑን አወቁ። አሁን በስማቸው የተመዘገበው የቤቶቹ ካርታና ደብተር ዋነኛ ርዕስ ሆኖ እያከራከረ ነው። የስራና ከተማ ልማት ቢሮ በጣልቃ ገብ ሂደት ግለሰቡን በመሞገት ክርክር ጀምሯል። ግለሰቡ ቤቱ ሊመለስላቸው አይገባም በሚል ያያዘው አቋም ውሳኔ እያስቀየረ ነው። ቢሮው እስካሁን በስማቸው ተመዝግቦ የቆየው ካርታና ደብተር እንዲመክን ያደረገው ጥረት ተሳክቶለታል።
አቶ ነጋሽ በስማቸው የተመዘገበው የይዞታ ባለ መብትነት ተሰርዟል። ቤታቸውን ለማስመለስ ያደረጉት ልፋትና ድካም ውሃ ፈሶበታል። አሁን ባለቤት ስለመሆናቸው የሚጠቁም አንዳች መረጃ በእጃቸው የለም። ቀድሞ ካርታና ደብተር ያወጡበት ፣ ቁጥርና መለያ የወሰዱበት አግባብ ተቀባይነት አጥቷል። ነጋሽ የሆነውን ሁሉ ማመን አቃታቸው። ሰዎቹን አስወጥተው ማደስ የጀመሩት ቤታቸው የሌሎች ሲሳይ መሆኑን እያሰቡ አዘኑ፣ ተጨነቁ።
ዳግም አቤቱታ …
አቶ ነጋሽ የስራና ከተማ ልማት ቢሮ በጣልቃ ገብ ሂደት ተከራክሮ የይዞታ ማረጋጋጫ ካርታቸውን እንዳመከነ ባወቁ ጊዜ ጉዳዩን በህግ አግባብ ለመፍታት መፍትሄ ፈለጉ። አሁንም በፍትህ መንገድ ከመሄድ ሌላ ምርጫ የላቸውም።
አቶ ነጋሽ ዘወር ብለው እስካሁን የሆነውን አስታወሱ። ቤታቸውን ለማስመለስ ቀላል በማይባሉ ውጣ ውረዶች አልፈዋል። ቀድሞ በፍርድ አፈጻጸም ቤቱን እንዲለቁ የተገደዱት ተከራዮች የተላለፈውን የፍርድ ውሳኔ አውቀዋል። ይህን ሲያውቁ ውለው አላደሩም። ከቤቱ ያወጡትን ጓዝ በቦታው መልሰው ኑሯቸውን ቀጠሉ።
አቶ ነጋሽ እኖርበታለሁ ሲሉ ማደስ የጀመሩት መኖሪያ ቤት ዳግም በተከራዮቹ መያዙን አወቁ። ለዚህ ድርጊት የቀበሌው ጽህፈት ቤትና የሚመለከታቸው ሃላፊዎች እጅና ትብብር እንዳለበት ገባቸው። ተስፋ አልቆረጡም። መልሰው ከፍርድ ቤት ችሎት መቆም እንዳለባቸው ወሰኑ።
አመልካች አቶ ነጋሽ ዱባለ በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተገኝተው ክስ መሰረቱ። በክሳቸውም ቀድሞ በባለቤትነት የተሰጣቸው ህጋዊ ካርታ እንዲመክን መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ጠቀሱ። ከክሱ አያይዘው ባቀረቡት ጥቆማ ሶስቱ ግለሰቦች መልሰው የያዙትን ቤት ለቀው እንዲወጡ የፍርድ ቤቱን አስቸኳይ ውሳኔ ጠየቁ። የስራና ከተማ ልማት ቢሮ በህግ ይጠየቅልኝ ሲሉም አቤት አሉ።
ፍርድ ቤቱ በድጋሚ የአመልካችን ክስና አቤቱታ መመርመር ጀመረ። በዚህ የክስ ሂደት ሶስቱን ግለሰቦች ጨምሮ የስራና ከተማ ልማት ቢሮን የሚመለከት ሃሳብን በማጤን መረጃዎችን መፈተሽ፣ ማጣራት ያዘ። ፍርድ ቤቱ ይመለከታቸዋል ያላቸውን ተጠሪዎች በማቅረብ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ የቤት ማረጋገጫ ሰነድ ያለበቂ ምክንያት ሊሰረዝ እንደማይገባ አምኖ የቀረቡ ማስረጃዎችን በጥልቀት መረመረ።
መኖሪያ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 47/67 መሰረት ለመወረሱ የቀረበ ማስረጃ የለም ያለው ፍርድ ቤት አመልካች ቤቱን በፍርድ አፈጻጸም ከተረከቡ በኋላ ሰነዱ በከተማ ልማት በኩል እንዲመክን መደረጉ አግባብነት የሌለው ስለመሆኑ አሳወቀ። አመልካች ሌላ ቤት አላቸው በሚል በተጠሪዎች በኩል የተሰጠውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ ምክንያት ነው ያለውን መነሻ አስታወቀ።
ፍርድ ቤቱ በወቅቱ የነበረው አዋጅ ቁጥር 47/67 አሁን በስራ ላይ ላይ አለመሆኑን አስታውቆ የመከነው የቤት ሰነድና ካርታ ቁጥር 3221 እና የደብተር ቁጥር እንዲሁም ለመኖሪያዎቹ የተሰጡ የተለያዩ የቤት ቁጥሮች እንደቀድሞ ሆነው ተፈጻሚነታቸው እንዲቀጥል በማለት ውሳኔውን አሳለፈ። አመልካች የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተቀብለው ለአፈጻጸሙ የቀናት ጊዜን ጠበቁ።
የፌዴራል ከፍተኛ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተመሳሳይ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትን ውሳኔ ተቀብሎ አጸደቀ። ግለሰቡ የፍርድ ቤቱን ይሁንታ ተቀብለው የተወሰደባቸውን መኖሪያ ቤት በህግ አግባብ ሊያስመልሱ ራሳቸውን አዘጋጁ።
ችሎት በሰበር …
አቶ ነጋሽ በስር ፍርድ ቤቶቹ የተሰጣቸውን ውሳኔ ተቀብለው በክርክር ሂደቱ ተሟግተው ያሸነፉት ችሎት መልካም በመሆኑ ውሳጣቸው ረክቷል። ይህ እፎይታ ግን እምብዛም አልቆየም። ጉዳያቸው በተጠሪዎቹ ይግባኝ ባይነት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ዳግም ሊፈተሽ ግድ አለው።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የአመልካቾችንና አሁን ተጠሪ ሆነው የቀረቡትን ግለሰብ ሰነድ መመርመር ጀምሯል። በዚህ ሂደትም የስራና ከተማ ልማት ቢሮ የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ መስጠት፣ መከልከልና መሰረዝ በህግ የተሰጠው ስልጣን ስለመሆኑ አረጋግጧል።
አመልካቹ አቶ ነጋሽ ዱባለ በአሁኑ ጊዜ በህግ የተፈቀደ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ በእጃቸው ሳይኖር በፍርድ ቤት ቀርበው መከራከራቸው አግባብ አይደለም በማለት እስከአሁን የተሰጠውን የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በውሳኔው በመሻር መዝገቡን ዘግቷል።
አቤቱታ በፌዴሬሽን ምክር ቤት …
አቶ ነጋሽ አለአግባብ የተወሰደብኝ መኖሪያ ቤት ይመለስልኝ ሲሉና ሲከራከሩበት የነበረው ጉዳይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ መረታታቸው ተረጋግጧል። እሳቸው አሁንም በፍትህ ሂደቱ ተስፋ አልቆረጡም። ጉዳዩን ዳግም አንቀሳቅሰው አሸናፊትን ለማግኘት ታገሉ።
አመልካች በአዋጅ ቁጥር 47/67 መሰረት በህግ ያልተወረሰ መኖሪያ ቤቴን ግለሰቦች በኃይል ነጥቀው እየተጠቀሙበት ስለሆነ የህገመንግስት ትርጉም ይሰጥልኝ ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ። የአመልካቹን አቤቱታና የስር ፍርድ ቤቶቹን የቀደመ ውሳኔ የተመለከተው ጉባኤ መዝገቦችን አንድ በአንድ መረመረ።
ጉባኤው ለክርክሩ መነሻ የሆኑትን ባለሶስት ደጃፍ ቤቶች አመልካች የፍርድ ባለመብት ሆነው በአፈጻጸም ከተረከቡ በኋላ በስራና ከተማ ልማት ቢሮ ካርታውና ሰነዶቹ እንዲመክኑ መደረጉን በማስረጃዎች አረጋገጠ። ይህ ሲሆንም በፍርድ አፈጻጸም ሂደት ተገደው እንዲወጡ የተወሰነባቸው ግለሰቦች ቤቱን መልሰው በኃይል ለመያዝ እድል እንዳገኙ ምክርቤቱ መረዳት ቻለ። በማጣራት ሂደቱም ቢሮው ሰነዱን ለመሰረዝ ምክንያት ያደረገው አመልካች ከሚጠይቁት ቤት ሌላ መኖሪያ ያላቸው መሆኑን ነው።
ማስረጃዎች…
ጉባኤው ከቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ስለግለሰቡና ክርክር ስለተነሳበት ቤት ተገቢውን የሰነድ ማስረጃ እንዲሰጠው ጠየቀ። ክፍለ ከተማው ለጉባኤው በሰጠው ምላሽም በአመልካች ስም የቤት ካርታና የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ያለመኖሩንና በ1988 ዓ.ም ግን የተከፈለ የግብር ደረሰኝ መገኘቱን አስታወቀ።
የኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 40/8 / የግል ንብረት ባለቤነት መብት ለህዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ መንግስት የሚወስድበት አግባብ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል። የተጠሪዎች ድርጊት ግን በህግ ከተቀመጠው ድንጋጌ በተቃራኒ መሆኑን ጉበኤው ተረድቷል። በእነዚህና ሌሎች ምክንያቶችም በጉዳዩ ላይ የህገመንግስት ትርጉም እንደሚያስፈልግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
የመጨረሻው ውሳኔ…
ምክርቤቱ ለአቤቱታው ምክንያት የሆነው ቤት ላይ በየደረጃው ያሉ ፍርድ ቤቶች ክርክር አካሂደው አመልካች የቤቱ ባለቤት እንደሆኑ በተለያዩ ማረጋገጫዎች ተረድቷል። ንብረቱንም በህግ አፈጻጸም ተረክበው እንደነበር አውቋል። ይህ ሆኖ ሳለ ያለምንም የፍርድ መሻሪያ ቢሮው ሰነዶቹን እንዲመክን ማድረጉ የህግ አካሄዱን የሚቃረን በመሆኑና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔም አግባብ ባለመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም ሲል ውሳኔውን አሳውቋል።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2013