ውዶቼ ! ከእናንተ አሜን (አሚን) የሚል ተመሳሳይ መልስ ስለምፈልግ ፤ ሰላማችሁ ብዝት ይበል። ማለትን መርጫለሁ። ሰላም ነው? ከማለት ሰላማችሁ ይብዛ በእጅጉ ይልቃል። ሰላምታ ላይ ጥያቄ ግን ያስዋሻል አይደል? እቤቴ እየተበጠበጥኩ አድሬ ከቤት ስወጣ ጎረቤቴ እንዴት አደርክ ቢለኝ ልለው የሚችለው “ሰላም ነው” የሚል ነው። አያችሁ አስዋሸኝ ማለት አይደል። ሰላም ካልሆናችሁ አልያም ከሆናችሁም የምትሰጡኝ መልስ ተመሳሳይ ሊሆን አይችልም። ስለዚህም ከመጠየቅ ይልቅ ሰላማችሁ ይብዛ ማለትን መርጫለሁ።
ብልጠት ማደሪያቸው ፣ እያታለሉ መኖር ተለምዷዊ ተግባራቸው የሆኑ ሰዎችን አንስተን ስለነሱ እናወራ እስኪ ጎበዝ። እርግጥ ነው ብልጥ አይደለን ይሆናል ፤ ነገር ግን በእነዚህ በብልጣ ብልጦች የምንታለል ሞኝ እንዳልሆን ለእነሱ ማስረዳት ግድ ይለናል ወገን። የቀን ብርሃናማነትን አይተው የሚቀርቡን ጭጋጉን ደግሞ ጠርጥረው የሚርቁንን መለየት ግድ ይላል። አገር የማህበረሰብ ድምር ውጤት አይደለች። እያዳንዳችን የምንሰራበትና የምናስገኘው ውጤት ድምር ነው አገራዊ እይታን ሁለንተናዊ ማንነታችንን የሚገልጸው።
በየእለት እንቅስቃሴና ሁነታችን ውስጥ የምናደርገው ተግባርና የምንቀረጽው አስተሳሰብ ለነገ ማንነታችን መሰረት ነው። እውናዊ ጽናት መላበስና ከማስመሰል መራቅ ደግሞ እውነተኛ ለውጥ ላይ አገርንም ብሎም እያንዳንዱን ዜጋም ያዳርሳል። ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ድረስ ላመነበት ተግባርና አቋም የሚገዛ ዜጋ የመኖሩን ያህል በሁኔታዎች መለዋወጥ መጣ ሄድ የሚል አስመሳይ ደግሞ ሞልቷል።
የድል አጥበያ አርበኛ ታውቃላችሁ። ሌላው ተዋድቆ ባቀረበው ድል ላይ ተገኝቶ ዘራፍን የሚደጋግም ጉደኛ። እኔ ነኝ የድሉ ሰበብ እኔ ነኝ የዚህ ሁሉ መነሻ ብሎ የሚፎክር። እነዚህ መሰል የድል አጥቢያ አርበኞች ድል አድራጊዎችን በስተመጨረሻ ቀርበው ባለድል መሆናቸውን የሚያውጁ ናቸው። እነሱ በጥሞና ይመለከቱናል፤ ሁኔታና አካሄዳችንን አጢነው ይቀርባሉ፤ አልያ በብዙ መልክ ይርቁናል። እነዚህ አርበኞች ባለ ድል መሆናችንን ሲያረጋግጡ በስተመጨረሻ የሚቀላቀሉን በስልት የሚንቀሳቀሱ አስመሳዮች ናቸው።
ዛሬ ላይ እነዚህን መሳይ ጉደኞች ተበራክተው ኧረ እንደውም ሙልት ብለው በየመንደሩ ይገኛሉ። እውነት ምንድነው? ሀቁ የቱ ጋ ነው? ብለው ለይተው ከመነሻው እስከመጨረሻው መታገል ሳይሆን አያያዝን አይተው ባለድሉን የሚቀላቀሉ ቀላዋጮች ናቸው። በነገራችን ላይ የሚረግጡት እዚያም እዚህም ስለሆነ አስተውሎ ለረግጣቸው በቀላሉ ለመለየት አያስቸግሩም። እነሱ በጉዳዩ ላይ ቋሚ በነገሩ ላይ ዘውታሪ አለመሆናቸውን ለመለየት ብዙም ጊዜ አይፈጁም።
ባሉበት ቦታ ላይ ጸንተው የሚቆሙ አይደለም። ምክንያቱም መጀመሪያም ሁኔታውን አይተው እንጂ አምነውበት አይቀላቀሉም። እውነተኛ ድሉን ያቃረቡ የዚያ ተግባር ባለቤቶች ተግባር በእነዚህ ቢዋጥም በሂደት እውነታው መጋለጡ አይቀርም። ጎበዝ ገጥሟችሁ ያውቃል? የእናንተን አያያዝ አይቶ ሊደግፋችሁ አልያም ሊቃወማችሁ የሚያኮበኩብ ውል አልባ ሰው። አያያዛችሁና የመጨረሻ ስኬታችሁን አይቶ ቀርቦ አብሯችሁ የሚፎክር ሰው። ይህንን ነው የድል አጥቢያ አርበኛ የምንለው።
በዚህች አገር ዛሬ ላይ የተገኘን ሁሉ በአንድ ሃሳብ ላይ ባንግባባም ማመን ያለብን ባንቀበለውም እውነት የሆነ ጉዳይ አለን። የቆምንባት ምድር፣ የምንሰየምበት ዜግነት፣ የምንለይበት ማንነት በዚህች አገር ላይ የጸና ነው። ሀገር ለማጽናት ደግሞ ጽኑ ሆኖ መቆም ግድ ይላል ፤ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው። አገራዊ ስጋት ሲመጣ ወደ ኋላ አፈግፍገን የተለየ ድል ሲገኝ ወደፊት መጣ የምንል የድል አጥቢያ አርበኛ አስመሳይ ወዳጅ ፈጽሞ ልንሆን አይገባም።
ጽናት የሁሉ ነገር ስኬት መሰረት ነው። ጸንቶ ስለ አንድ ዓላማ በአንድነት መቆም የሚከብደው ውጤት ላይ መድረስ ይሳነዋል። የጽናት ዋንኛ ግቡ ደግሞ የሚፈለገውን ዓላማ ለማሳካት የሚያቃርብ ወኔን መላበስ ነው። እርግጥ አንድ ነገር ላይ ጽኑ ሆኖ ለመዝለቅ ውስጣዊ ማንነትና የተሰራንበት ሥነ ልቦና ወሳኝ ነው። የምናራምደው ሃሳብ ልክነት በትክክል መረዳት እውነተኝነቱን ማረጋገጥና ስለዚያ ተግባር እና እውነት ራሳችንን እስከመጨረሻው ማስገዛት ግድ ይላል።
ዛሬ ላይ አገራችን ያለችበትን ዘርፈ ብዙ ችግርና ያለንበትን እውናዊ ሁኔታ ተረድተን ከዚህ ለመውጣት በሚደረገው ጥረት በጎ ተጽዕኖ መፍጠር ከተሳነን፣ ነገ ላይ ታግለው ለውጥ ካመጡት ጋር እኩል ተሰልፈን ዘራፍ እያልን መፎከር ፈጽሞ ሊያምርብን አይችልም። ዛሬ አገር የልጆችዋን ጠንካራ አንድነትና ብርቱ ትግል በምትፈልግበት ጊዜ ተኝተን ነገ ላይ ሁኔታዋን አይተን አለሁልሽ ማለት ፈጽሞ ከእኛ አትጠብቅም።
አዎ ዛሬ ላይ ያለውን ሁለንተናዊ ችግር ለመቅረፍ አቅደን በጋራ ተነስተን ኢትዮጵያችንን ለሁላችንም ምቹ ቤት፣ ሰላምዋን የጠበቀችና ለሌሎች የተረፈች እንድትሆን በማድረግ ጥረት ጽኑ ተሳታፊ፣ ጀምሮ ጨራሽ ፣ተግብሮ በተግባሩ ውጤታማ ልንሆን ይገባል።
ሁለት ጊዜ ሰው ይከብራል ፤ ውስጡም ሀሴት ይላበሳል። አንድም በቆመበት እውነት ላይ ጸንቶ ለቆመለት ዓላማ ራሱን ሰጥቶ ስለ እውነት በመቆሙ የህሊና እረፍትን ይላበሳል። ወዲህም ደግሞ ያ በጽናት የቆመለት ዓላማ እና እውነት ዘግይቶም ቢሆን መሳካቱ ስለማይቀር ባገኘው ድል ፍስሀን ይላበሳል።
ታዲያ ነገ የኢትዮጵያ ትንሳኤ እውን መሆኑ አይቀርም። በዚያ ትንሳኤዋ የእኛን በጎ አሻራ ማሳረፍ ደግሞ የእያንዳንዳችን ሃላፊነት ነው። አገር ዛሬ በእጅጉ ስትፈልገን እጃችንን አጣጥፈን ልንቀመጥ ደግሞ አይገባም። ነገ የማይቀረውን ትንሳኤዋን ስታረጋግጥ የትንሳኤዋ መረጋገጥ ተዋናዮች በመሆናችን የምናገኘው የህሊና እረፍት ብሎም አገራዊ ኩራት የምር ይሆናል።
እኛም ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ድረስ በአገራዊ ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ የራሳችንን ያልተቆጠበ ጥረት አድርገን ነገን በናፍቆት መጠበቅ ግድ ይላል። ሌሎች በተጋደሉበትና እኛ ባልተሳተፍንበት ትግል ገብተን የድል አጥቢያ አርበኛ ከመሰኘትም እንወጣለን። ከሁሉም በላይ ግን ለእኛም እረፍት ለአገራችንም ለውጥ ከመነሻው እስከመዳረሻው በጽናት መቆም የእኛ የዜጎች ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን መረዳት ይገባል። አበቃሁ ፤ ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2013