ሰውዬው ባህር ተሻግሮ ፣ ድንበር አቋርጦ ከሀገር ከወጣ ዓመታት ተቆጥረዋል። ካሰበው ደርሶ የስደት ህይወትን ‹‹ህይወቴ›› ማለት ከጀመረ አንስቶ ስለትናንት ፈጽሞ ማሰብን አይሻም።
ይህ ሰው የሰው አገር ሰው ከሆነ ወዲህ መለስ ብሎ ያለፈበትን መንገድ ላያስታውስ ከራሱ ተማምሏል። ላስብ፣ ላስታውስ ካለ ግን ከማንነቱ ጋር በዋዛ አይታረቅም። ከአዕምሮው ጓዳ የማይመዘው ክር፣ የማይጎትተው ገመድ የለም።
እንዲህ በሆነ ጊዜ የበረሀ ጉዞው በዓይኑ ውል እያለ ዕረፍት ይነሳዋል። የስደት ጓደኞቹ ስቃይና ሞት ፣የእሱ እንግልትና መከራ፣ የበርካቶች ለቅሶና ውሃጥም ትውስ እያለው ይጨነቃል። ምንጊዜም ቢሆን ትዘታዎቹ ሰላማዊና ጤናማ ሆነው አያውቁም።
ይህ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ጉዳዮቹን ባሰበ ቁጥር በትዝታ ወደ አገር ቤት ይመለሳል። ለእሱ የአገር ቤት ትዝታዎቹ ሰላም ሰጥተውት አያውቅም። ያለፈበትን የህይወት መንገዶች ሲያስታውስ የስቃይ ዘመኑን አይረሳም። ከትውልድ ቀዬው፣ከሚወዳት አገሩና ከሚሳሱለት ውድ ቤተሰቦቹ ነጥሎ በሰው አገር ሰማይ ስር ያቆመውን እውነት ጠንቅቆ ያውቀዋል። ይህ እውነት የማንነቱ ጥቁር ጥላ ሆኖ ሲጋርደው፣ሲከተለው ቆይቷል። ዛሬ ስሙን አስቀይሮ፣ ኢትዮጵያዊነቱን አስለውጦ ስደተኛ አስብሎታል።
ይህን አይረሴ ታሪክ ሲያስታውስ ውስጡ በጥላቻ ይመላል። በስመ ፖለቲካ በእሱ መሰሎች ላይ የደረሰው ስቃይ ውስጡ ድረስ ዘልቆ ያንገበግበዋል። ይሄኔ የተወለደባትን አገር ያደገባትን ቀዬ፣ አምርሮ ይጠላል። የራሱ ወገኖች በወገኖቻቸው ላይ የፈጸሙትን ግፍና በደል እያሰበ ስለማንነቱ ደፍሮ ለመናገር ያሳፍረዋል።
ይህ ሰው ያን ክፉ ዘመን ሲያስብ አገሩ ትውስ ትለዋለች። እሷን ሲያስብ እንደሌሎች ቀድሞ ናፍቆት አያሰቃየውም። በጎ ትውስታ መልካም ሥዕል አይታየውም። ሁሌም እንዲህ ሲል ይገልጻታል። ‹‹ያቺ አገር… ከዘራችው ማሳ የእጇን ፍሬ ያላገኘች ፣ ከሠሩላት ያሴሩባት ፣ከሞቱላት የገደሏት ፣ የሚኖሩባት ምድር ፣ በአብዮት፣በፖለቲካ፣በፓርቲ ሰበብ ልጆቿን በልጆቿ ያስበላች›› ሲል ያማርራታል፡፤
ደግሞም እንዲህ ሲል ይቀጥላል። ‹‹ በየዘመናቱ እንደ አዲስ ምንጭ ለሚፈልቁ ካድሬዎች እጇን የሰጠች፣በአፋዊ ልፈፋ፣ውል በሌለው ትርክት የሰለቸች፣በእስር ፣በእንግልት በስደት ታሪክ የደመቀች፣ ትውልዷን በባሌ፣በቦሌ ብላ ያባከነች፣የሰው አገር ጌጥና ሞገስ ›› ይላታል።
የትናንቱ ኢትዮጵያዊ የዛሬው ዳያስፖራ ካለበት ፣ ከቆመበት ምድር ሆኖ ያለፈበትን ጨለማ ይዳስሳል። ማንነቱን አገሩን ከከበቧት ጋሬጣዎች ጋር እየመዘነም ያወዳድራል። እሱን ከኢትዮጵያ፣ኢትዮጵያንም ከእሱ ባስተያየ ጊዜ ጉዳቱ፣ ቁስልና ህመሙ ይሰማዋል። ኀዘኑ ችግርና መከራው ያስለቅሰዋል።
ዳያስፖራው የራሱን መልክ በአገሩ መስታወት ውስጥ ባገኘው ቁጥር ኀዘን ከትካዜ ይወርሰዋል። ይሄኔ ከራሱ እያወራ ከህሊናው ይሟገታል። እየደጋገመም ለውስጠቱ መልስ አልባ ጥያቄን ያቀርባል። ‹‹እስቲ ቆይ ለዚህች አገር የማይድን ቁስል ተጠያቂው ማነው? የውጭ ኃይሎች ? የጎረቤት አገራት? የራሷ ልጆች ? ወይስ ሌላ … የዳያስፖራው ጥያቄ ሳይመለስ፣ የልቡ መሻት ሳይሞላ ቀን መሽቶ ይነጋል።
ወዳጆቼ ! ሰውዬው ብዙ ቢያስብና ያሻውን ቢናገር ፍርድ አለበት እንዴ? እኔ የለበትም ባይ ነኝ። በእሱ ህሊና የሚመላለሰው ሀቅም ውሸት ነው ብዬ አላምንም። በእርግጥ ይህ እሳቤ የእኔና የእኔ ብቻ ነው። ለምን ካላችሁኝ አገራችን በየዘመናቱ ከበቀሉ ሹል ጥርሶችና ሰፊ መንጋጋ አምልጣ እንደማታውቅ አስታውሳችኋለሁ።
አዎ! የእኛዋ ታላቅ አገር ሁሌም በእንዲህ ዓይነቶቹ ቀርጣፊዎች እጅ እንደወደቀች ነው። በየጊዜው አጋጣሚውን ተጠቅመው ብቅ የሚሉ በሊታዎቿ እንደጨቅላ ልጅ ከጉያዋ ተወትፈው ደሟን ሲመጧት ኖረዋል። እነዚህ አንጡራ መጣጮች ሁሌም በዋዛ ‹‹ ጠገብን ›› የሚሉ አይሆኑም። እንደጉሬዛ ከአንዱ ዛፍ ወደ ሌላው ዛፍ እየዘለሉ የዋርካዋን አገር ቅርንጫፍ ይገነጥላሉ። የአንዱን ግንድ ከአንዱ ቆርጠውም ልዩነትን ያሳፋሉ። ቅጠሉን መልምለው ሲያደርቁ የዛፉ ስር አይቀራቸውም። ዙሪያውን እየቆፈሩ ስራስሩን ከበቀለበት ካደገበት መሬት ሊነቅሉ ይታገላሉ።
በዚህ ሙከራቸው ለ‹‹ነበር›› የሚያስቀሩት አሻራ አይኖርም። ቀሪውን የዛፍ ጥሪት በእሳት እያጋዩ የአመድ ቁልል ይከምራሉ። እንግዲህ ለእነሱ ታሪክ ማለት ይህ ዓይነቱ ድርጊት መሆኑ ነው። ለእነሱ ድል ማለት የሌሎች ስቃይና መከራ፣ ለቅሶና ትካዜ ነው።
አንዳንዴ ዳያስፖራው እንዲህ ማሰብ በጀመረ ጊዜ የውስጡን ጉዳይ የሚጋሩት፣ ሃሳቡን የሚካፈሉት አይጠፉም። እነዚህ ሰዎች እንደሱ ከአገር ቤት በስደት የመጡና ዜግነታቸውን የለወጡ ዳስፖራዎች ናቸው። ካገሩ ልጆች በርካቶቹ በባህርና በበረሀ ያቋረጡ፣ ህይወት ያመሳሰላቸው፣ ኑሮ ያቀላቀላቸው ሆነዋል።
እነዚህ ወገኖች አብዛኞቹ ህይወታቸው ምቹ የሚባል ነው። ሁሌም ግን የወገናቸው በደልና ኀዘን ለቅሷቸው ነው። በየአፍታው ውድ አገራቸውን ያስባሉ። የህዝቧ ዕድገትና ስልጣኔ እንደሌሎች አገራት ቢሆን ምኞታቸው ነው። ለህዳሴ ግድቡ ሲሏቸው እጃቸው ይሰፋል። ለተቸገሩት ለመርዳት ላዘኑት ለማጽናናት ይፈጥናሉ፡፤
ኢትዮጵያ በሌሎች አገራት ተጽዕኖ እንድትወድቅ አይሹም። ስለሀገራቸው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይጮሀሉ። ጩኸታቸው የጉም ላይ ድምጥ እንዳይሆን ትግላቸው እስከጥግ ይጓዛል። የማንነታቸው ማሳያ የአገራቸው ሰንደቅ ፣ የአንድነታቸው መዝሙር ነው።
እነዚህ አገር ወዳድ ዳያስፖራዎች ብሄር ቋንቋ፣ ዘር ኃይማኖት ይሏቸው ክፍፍል ችግራቸው አይሆንም። በአማርኛ አዚመው ፣በኦሮምኛ ይጨፍራሉ፣በትግርኛ ዘፍነው በወላይትኛ ይደንሳሉ። ብሄርን በስም እንጂ በክፉ ድርጊት አይገልጹትም። የአገራቸው ሁሉም ቋንቋ መግባቢያ ፣መናገሪያቸው ነው። አንዱን ከአንዱ አይከፍሉም፣ አያወዳድሩም።
የስደትን፣ የችግርን፣ የርሀብ ጥማትን ስሜት ያውቁታልና ማንም በእነሱ መንገድ እንዲያልፍ አይሹም። ዛሬን የሰው አገር ሰው ቢሆኑም የነገ ተስፋቸው አገራቸው ብቻ ናት። ሁሌም የምድራቸው አፈር ካሉበት ይሸታቸዋል። እንደ እትብታቸው ሁሉ መቀበሪያቸው ውድ አገራቸው ብትሆን ይመኛሉ። ኢትዮጵያዊነት በእነሱ ማንነት ፣ የማይሞት ፣ የማይቀዘቅዝ ፣ህያውና ትኩስ ደም ነው።
ሌሎቹ ደግሞ በቦሌው አውሮፕላን በክብር የተሸኙ፣ በቂ ስንቅ የተቋጠረላቸው፣ለማስታወሻ የአበሻ ልብስ የተሰጣቸው፣ለትውስታ ፎቶ ከቪዲዮ፣ የተቀረጹ ቅንጡዎች ናቸው። በእነዚህ ዳያስፖራዎች ብዙዎች ስለነገ ተስፋ ጥለዋል። እንደተባለው ሆኖም በእነሱ ድልድይነት የበርካቶች ምኞትና ተሳክቷል። ለመሰል ዳያስፖራዎች ቁጥር ማደግም አንድ ርምጃ ጨምሯል።
አብዛኛው ዳያስፖራዎች አሁን ላይ በሀገራችን እየሆነ ያለው እውነት ያሳስባቸው ይዟል። በእጅጉ ከሚያስቡት መሀልም ጥቂት የማይባሉት ስለ ሰላምና ፍቅር፣ ስለሰብዓዊ መብትና አብሮነት አጥብቀው ይታገላሉ። ይህ ትግላቸው በተግባር መገለጽ ከጀመረም ሰነባብቷል።
ሁሉም ዳያስፖራዎች ሃሳብ ፍላጎታቸውን፣ ተቃውሞ፣ ድጋፋቸውን ለመግለጽ ለምን ባይ የለባቸውም። ፍቅርም ይሁን ጥላቻን ለማሳየት፣ የሚኖሩባቸው አገራት አደባባይን ተከልክለው አያውቁም። ለሚያካሂዱት ሰልፍ ፈቃድ አውጡ፣ አጀንዳ አስይዙ፣ ንግግር ምረጡ፣ የሚላቸው የአጥቢያ ዳኛ የለም። እንደኛ አገር ቢሆን እኮ የሊቀመንበሩ ፈቃድ በዋዛ ላይገኝ ይችላል። ቢገኝም የጠባቂዎቹ ዓይን ያስፈራል፤ ባያስፈራም ዕርምጃው ኮሽታው አይታመንም። ውይ…. ውይ… አንዳንዴማ… ሆ ! እናንተዬ ዝም ብልስ። አዎ! ዝም ዝም! ይሻላል ያ ሁሉ ሰቀቀን አልፏልና።
በእነሱ ምድር ግን ይህ ሁሉ ስጋትና ችግር ሆኖ አያውቅም። በስፍራው ሁሉም ባለመብት፣ ሁሉም የእኩል ተናጋሪ ነው። በባዕዳኑ አደባባይ ሁሌም የተለያዩ ድምፆች ይሰማሉ፤መልከ ብዙ መልዕክቶች ይነበባሉ፣በርካታ ባህርይና አስገራሚ ድርጊቶች ይታያሉ።
በጣም የሚገርመው የሰልፈኞቹ አደባባይ መውጣትና ሃሳብ መግለጽ ጉዳይ አይደለም። አስደናቂው ነገር የሁሉም መልዕክትና ቋንቋ እንደባቢሎንያኑ አንደበት መዘበራረቅ፣ መለያየቱ ነው።
ወዳጆቼ! የቋንቋ መለያየት ሲባል የትርጓሜ ለውጡን ለማለት ፈልጌ አይደለም። ሰልፈኞቹ ቢሻቸው በሀገሬው ቋንቋ ፣ አልያም በራሳቸው መግባቢያ መልዕክቱን ማስተላለፍ መብታቸው ነው። ይህ ደግሞ ለማንም፣ለምንም ብርቅ ሆኖ አያውቅም።
‹‹ነገሩ ወዲህ ነው ›› አለ ያገሬ ሰው። አዎ ! ነገሩ ወዲህ ነው። እነሱ አደባባይ ሲወጡ የራሳቸውን ሃሳብ ለማንጸባረቅ ብቻ አይደለም። ዋንኛው ግባቸው የሌላውን ሃሳብ ጭምር ለመቃወምና ለማጨናገፍ ነው።
እነዚህኞቹም ዳያስፖራዎች በሰው አገር እየኖሩ ዓመታትን ገፍተዋል። የእነሱ ህይወትና የኑሮ መንገድ ግን ከበርካቶቹ ይለያል። ‹‹እ.ህ.ህ.ህ…..›› አለ ብሶተኛው ፈረሰ። እነሱ ግን እንደፈረሱ አይደሉም። ባሻቸው ጊዜ አገርቤት መሄድ ፣መምጣት፣ መመላለስ ይችላሉ። እስከዛሬ ለራሳቸውም ይሁን ለቤተሰቦቻቸው የፈለጉትን አድርገዋል። በአገራቸው የበርካታ ሕንፃዎችና የዘመናዊ መኪኖች ባለቤት ናቸው። ይህን ሲያደርጉ እምብዛም አልደከሙም። ከቀኝ እጅ ወደግራ እጅ የማቀበል ያህል ነገሮቻቸው ቀላል ሆነው ዘልቀዋል። አመጣጣቸው እንደሌሎች በበረሀና በባህር አይደለም። እንግልትን አያውቁትም። ችግር፣ ስደት ይሉትን መከራ አልቀመሱም።
አብዛኞቹ የባለስልጣናት ልጆችና የቅርብ ዘመዶች እንደመሆናቸው አገር ውስጥ ስለሚሆነው አዲስ ጉዳይ የቀደመ መረጃ አላቸው። የእነሱን ጥቅም የሚነካና የሚገዳደር ነገር ከሆነ አደባባይ ወጥተው አፋቸውን ለመክፈት የሚቀድማቸው የለም።
‹‹ ራስ ደህና ›› እንዳለቸው እንቶኔ እነሱም ከራሳቸው በላይ ማንንም አያስቀድሙም። ለነገሩ አውነታቸውን ነው። ‹‹ለእኛ ሳይሆን ለእኔ›› ያሉ የእነሱ አጋሮች አገሪቱን በአጥንት ሲያሰቀሯት የጠየቃቸው የለም። የቤት አይጥ ከመሆን አልፈው የውጭ አገር ተናካሽ ጅቦች ሲሆኑም እንዴት ለምን ? ያላቸው አልተገኘም። ሙስና ይሉትን ቃል በሰው ጆሮ እየደገሙ ድሀውን ህዝብ ባዶ ሲያስቀሩት ታዛቢ አልነበራቸውም።
አዎ! እነዚህ ቡችሎቻውም በደህና ቀን በመሸጉበት አገር ተቀምጠው አገራቸውን ቢያዋርዱና ቢዘልፉ አይፈረድም። የአባቶቻቸውን ድርጊት ደግመው ምግባራቸውን በቃላቸው ቢያረጋግጡ አይደንቅም፣ አያስደንቅም። በእርግጥ መፈክር ብቻውን ታሪክ አይሠራም። አንድ አያደርግም። ፍሬ አልባ ተቃውሞም ውጤት አያመጣም፣ አያስከብርም።
ተቃወምን ባዮቹ የአደባባይ ሰዎች ሁሌም ተቃውሟቸው አገራዊ አጀንዳ ሆኖ አያውቅም። በምንም አጋጣሚ ቢሆን የወገን ጥቃት ይሉት ነገር ነገራቸው አይሆንም። ማንም በማንም ላይ ጨፈቃውን ቢያነሳ፣የትኛውም አገር በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ቢገባ ደንታቸው አይደለም።
እነዚህ አገር ጠል ፣ የአደባባይ አሽቃባጮች ላንቃቸው እስኪላቀቅ የሚጮሁት ለራሳቸው ጥቅም ብቻ ነው። ድርጊቱን ሲፈጽሙ አገራቸውን የሚገልጽ ሰንደቅ አይዙም። የራሳቸው ባንዲራና የስድብ መግለጫ ሰሌዳ አላቸው። እሱን አንግበው ያሻቸውን ይዘልፋሉ። አገር የሚያፈርስውን፣ወገን የሚከፋፍለውን መርዝም በመላው ዓለም ይረጫሉ፡፤
አንዳንዴ ስለሀገርና ህዝብ ከሚጮሁት ወገኖች ጋር ግንባር ለግንባር ይገጥማሉ። ሁለቱ ጎራዎች ውሃና ዘይት እንደማለት ናቸው። ሃሳባቸው ለየቅል በመሆኑ ኮከባቸው አይገጥምም። አንድን ጉዳይ በመደገፍና በመቃወም መሀል ሆነው ከተገናኙ ተአምር ይፈጠራል። ይህኔ በኢትዮጵዊነት ጀርባ፣ በአንድ ራስ ሺህ ምላሶች ይታያሉ። ያም ሆኖ አገራዊ ስሜት ይነግሳል። ጥላቻ፣ስድብና መርዛም ሃሳብ በእጅጉ ይዋረዳል።
መቼም ወገኖቼ! ሰው ህሊናውን ከሸጠና ማንነቱን ለጥቅም ካሳለፈ በበላበት ለመጮህ የሚቀድመው የለም። የጎረሰው ከሆዱ እስኪጠፋ፣የግንባሩን ወዝ እየጠረገ ፣ ስለውለታው ይጮሀል ‹‹እሪ ኡ ኡ …›› እያለም ‹‹ያዙኝ ልቀቁኝ›› ይላል፤በሌሎች ላይ በደል አድርሶ እንደተበደለ፣ ዘርፎ እንደተዘረፈ፣ ገድሎ እንደተገደለ ሲሆን ብዙዎችን ለማሳመን በዘዴ ተክኖ ተከሽኖ ነው።
‹‹ሆዳም ሰው ፍቅር አያውቅም›› እንዲሉ ስለሆድና ጥቅም፣ ዋጋ የተከፈለበት ጩኸት በየኤምባሲው ደጃፍ መሰሎችን ይኮለኩላል። በዚህም አሳፋሪ ማንነትን ያሳያል። ሁሌም አንድ ብሄርን መሰረት አድርጎ፣ የግለሰቦችን ስም እያወደሰ የተከበረችውን አገርን ያንቋሽሻል። የዜጎቿን ማንነት አሳንሶ ብሄራዊ ጥቅሟን ለድርድር ያቀርባል።
የብዘዎችን ዓይንና ጆሮ ለመሳብ በሚደረገው ጥረት እሪ ባዮቹ ተበድልን፣ተጎዳን ማለት ልማዳቸው ነው። ዛሬ ላይ በድንገቴው ለውጥ የቀረባቸው የማይነጥፍ ንዋይ እንደ እግር እሳት ያነዳቸዋል። ይህን እያሰቡ ልክ እንደ አህያዋ ለእኔ ያልሆነ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው ሁሉ እነሱም ለእነሱ ያልጠቀመች አገር ትፍረስ ፣ ትውደም፣ ትበተን ይላሉ።
እንዴ! አገር እኮ! ትቢያ አቧራ አይደለችም፡ እንደጭብጥ አፈር በዋዛ አትበተንም። አገር እኮ! የሰንደዶ ቤት አይደለችም በትንሹዋ ጣት ፍርስ ፈርስርስ አትልም። ‹‹እንዳማረሽ ይቅር›› አለ ሰውዬው። አዎ ሁሉም እንዳማራቸው ሊቀሩ ግድ ነው።
በሰው አገር ቆመው ክፋትን የሚዘሩ ዳያስፖራ ተብዬዎች በኢትዮጵያ ላይ ያነሱትን እጅ ሊሰበስቡ ይገባል። አንድነት ኃይል እንጂ የክፉ ስሜት መገለጫ ሲሆን ማየት በእጅጉ ያሳፍራል። በአንድ ራስ ሺህ ምላስን የሚዘረጉ ለፍላፊዎችም ለመጪው ትውልድ መልካምነት ቢያወርሱ ይከብራሉ እንጂ አይከስሩም። ነገ አገራቸው ለመግባት አያፍሩም። አንገት አይደፉም። ለማንኛውም ባሉበት ልቦና ይስጣቸው!
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2013