በሥራ ዓለም ፔሮል ላይ ፈርሞ የወር ደመወዝተኛ መሆን የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዕጣ ፈንታ ነው።በዚህ ዕጣ ፈንታ እሽክርክሪት ውስጥም በወር የሚገኘው ገንዘብ ከባለቤቱ ጋር ሊቆይ የሚችለው ቢበዛ በወሩ የመጀመሪያ ሳምንት ብቻ ነው።ምክንያቱም የቤት ኪራዩን ጨምሮ የምግብ ፍጆታዎችና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች በሙሉ ለወር እንዲበቃ ተደርጎ ይሸነሸናል።ሸመታውም ቢሆን ገበያው ባቀረበው መጠንና ዓይነት ሳይሆን የወሩ ገቢ አቅም በሚፈቅደው መጠን ነው።ይህም ሆኖ ለወር የተባለው ፍጆታ ደመወዝ መዳረሻ ላይ ተገባድዶ ብድር ሊያስገባ ይችላል፤ ስለዚህ የደመወዝተኛ ኑሮ ሁልጊዜም ከእጅ ወደ አፍ ዓይነት ነው።
ይሁን እንጂ የወር ደመወዝተኛ መሆን ላለፉት በርካታ ዓመታት በማህበረሰቡ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሆኖ ቆይቷል።በተለይም በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ተቀጥሮ መሥራት የቻለ ሰው ተቀባይነቱ የጎላ እንደነበር ይታወሳል። ይህን ተከትሎም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከከፍተኛ የትምህርተ ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ በርካታ ወጣቶች የተለያዩ ሥራዎችን በራሳቸው አቅም ፈጥረውም ሆነ ከመንግሥት ውጪ የሆኑ ሥራዎችን ለመሥራት በራቸውን ዝግ አድርገው ሥራን ከመንግስት ብቻ መጠበቅ የመጨረሻ ግባቸው አድርገው ቆይተዋል።
አሁን አሁን ደግሞ መንግሥት ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠሩ እንዲሁም ቀጣሪ ድርጅቶች እየተበራከቱ በመምጣታቸው ከመንግሥት ውጪ ያሉ በርካታ የሥራ በሮች ተከፍተዋል።ዜጎችም የተከፈቱትን በሮች ይበልጥ በመከፋፈት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁን ወቅት ዜጎች ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ የግል ሥራ መሥራት አዋጭና ተመራጭ መሆኑን በተጨባጭ ማረጋገጥ ችለዋል።በመሆኑም ብዙዎች ከመንግሥት ሥራ ጎን ለጎን እንዲሁም ሙሉ ለሙሉ የመንግሥት ሥራን በመተው በግል ሥራ ተሰማርተው የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ ችለዋል።
በዛሬው የስኬት ገጻችን አንግዳ አድርገን የመረጥናቸው።በመምህርነት የማገኘው ደመወዝ ቤተሰቤን በአግባቡ መምራት አላስቻለኝም።በማለት በትርፍ ጊዜያቸው ተጨማሪ ሥራ ሠርተው ገቢያቸውን ማሳደግ የቻሉና ኑሯቸውን ያሻሻሉ ሴት ሥራ ፈጣሪ ናቸው።ትውልዳቸው አዲስ አበበ ከተማ ሲሆን፤ እድገታችው ሃዋሳ ከተማ ነው።በቀድሞው አጠራሩ ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርታቸውን ተከታትለው በዲፕሎማ ተመርቀዋል።የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር ሆነውም በተመደቡበት ይርጋለም ከተማ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።እያስተማሩ ተምረውም የትምህርት ደረጃቸውን ወደ ዲግሪ አሳድገዋል።
በመምህርነት ሲያገለግሉበት ከነበረው ይርጋለም ከተማ ወደ ሃዋሳ በዝውውር በመጡበት ወቅት ሃዋሳ ከተማ ያለው የኑሮ ሁኔታ ይርጋለም ላይ ከነበረው ጋር የሚመጣጠን አልነበረምና በመምህርነት ደመወዝ ብቻ መቀጠል የማያዋጣ እንደሆነ ተረድተው በወቅቱ ተጨማሪ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ወሰኑ።ውሳኔያቸውን ወደ ተግባር ከማሳደጋቸው አስቀድሞ ምን መሥራት እንዳለባቸው አጥንተዋል።አካባቢያቸውን ባስተዋሉበት ወቅት የዳቦ ቤት እጥረት ስለመኖሩ በመገንዘብ ዳቦ ቤት ከፍተዋል፡፡
ወደ ሥራው በገቡበት ወቅት፡፡ደመወዝተኛ ሆናችሁ እንዴት ዱቄት ታቦናላችሁ፤ ምን አጣችሁ፡፡የሚሉ አስተያየቶች ገጥመዋቸዋል፤ ብዙዎችም አልተቀበሏቸውም።ይሁንና አትስሩ የሚሏቸውን ሰዎች አስተያየት ወደ ጎን በመተው እንዲሁም በሥራው የገጠሟቸውን ውጣ ውረዶች በመቋቋም ከመምህርነት ሥራቸው ጎን ለጎን ዳቦ ቤት ከፍተው ውጤታማ መሆን የቻሉት ወይዘሮ ጽጌ ጥላሁን በሃዋሳ ከተማ የቅድስት አርሴማ ዳቦ ማምረቻ ባለቤት ናቸው።
የቀድሞዋ መምህርት የአሁኗ የዳቦ ቤት ባለቤት ወይዘሮ ጽጌ፤ የመምህርነት ሥራቸው የሚጠናቀቀው በግማሽ ቀን መሆኑ ተጨማሪ ሥራ ለመሥራት ይበልጥ እንዳነሳሳቸው ይናገራሉ።መነሻቻቸውን ከመምህራን ቁጠባና ብድር ማህበር 30 ሺ ብር ያደረጉት ወይዘሮ ጽጌ፤ የሚኖሩበት ኮንዶሚኒየም አካባቢ ዳቦ ቤት አልነበረም።በተለይም ልጆች ለያዘ ቤተሰብ ዳቦ የየዕለት ምግብ ነው። የእርሳቸውም ልጆች ዳቦ በጣም የሚወዱ በመሆናቸው ዳቦ ይገዙ የነበረው ከዳቦ ቤት ሳይሆን ከሻይ ቤቶችና ከሸቀጥ ሱቆች ነበር።እዚህ ቦታ ላይ የሚገዛው ዳቦ ደግሞ ንጽሕናው የተጠበቀ አልነበረምና የሥራ ፍላጎታቸው ወደዚሁ አዘነበለ፡፡
በብድር 30 ሺ ብር ላይ ብድር ጨምረው የመስሪያ ቁሳቁሶችን አሟልተው ዱቄት በችርቻሮ ገዝተው በኪራይ ቤት ዳቦ ማምረት ጀመሩ።በወቅቱ የነበረው ገበያ ሞቅ ያለ ነበርና ኮንዶሚኒየም መግዛት ቻሉ።ኮንዶሚኒየም ውስጥ እየሠሩም እየኖሩም ቆይተው ገበያቸው እየተስፋፋ ሲመጣ ፍላጎታቸውም እያደገ በመምጣቱ ተጨማሪ ሰፋ ያለ ማምረቻና መኖሪያ ቦታ መፈለግ ጀመሩ።የገዙትን ኮንዶሚኒየም ቤት ሽጠውም ከሃዋሳ ከተማ ወጣ በማለት ገጠራማ ቦታ ላይ መሬት ገዝተው ቤት መሥራት ችለዋል።
በዚህ ጊዜ ገበያው የመቀዛቀዝ ሁኔታ የገጠመው በመሆኑ ለጊዜው በሚል ሥራውን አቁመዋል።ከተወሰነ ጊዜ ቆይታ በኋላም ከልማት ባንክ ጋር ባደረጉት ስምምነት በአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የዳቦ መጋገሪያ፣ ማቡኪያ፣ መቁረጫና ሁሉንም ነገር የያዘ ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነ ሥራ ለመሥራት ቁሳቁሶችን አሟልተው በአዲስ መልክ ወደ ሥራ ተመለሱ።ልማት ባንክ ገዝቶ ላቀረበላቸው መስሪያ ቁሳቁሶች ክፍያቸውን በወቅቱ እየከፈሉ ሥራቸውን ቀጠሉ።
ምንም እንኳን ሰፊ መሬት ገዝተው መኖሪያቸውንና ዳቦ ማምረቻቸውን በአንድ ቦታ ላይ መሥራት የቻሉ ቢሆንም አካባቢው ከከተማው ወጣ ያለ በመሆኑ ገበያቸው እንደቀደመው ጊዜ አልሆነም።ይሁንና ወደ መሀል ከተማ አምስት ቦታዎች ላይ ዳቦ መሸጫ ሱቆችን በመከራየት ተጨማሪ የሥራ ዕድል በመፍጠር ሥራቸውን ቀጠሉ።በአምስት መሸጫ ሱቆቹ ውስጥ የሚሸጡትን የሽያጭ ሠራተኞችን ጨምሮ ለ17 ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።
ዳቦ የሚያመርቱበትም ሆነ የሚኖሩበት በመኖሪያ ቤታቸው ከከተማው ወጣ ያለ ቦታ በመሆኑ ርቀቱን መሸፈን የሚቻለው በትራንስፖርት ነው።በመሆኑም ዳቦውን ከመኖሪያቸው ወደ መሸጫ ሱቆች ዳቦ ለማከፋፋል መኪና ገዝተዋል።መኪና መግዛት የቻሉትም በዳቦ ሽያጭ ሲሆን፤ በአሁን ወቅትም በፈለጉት መጠንና በተለያዩ አካባቢዎች እንደልብ ተዘዋውረው ዳቦ ለማከፋፈል ተጨማሪ መኪና የመግዛት ዕቅድ አላቸው።
የሚያመርቱት ዳቦ ጥራቱንና መጠኑን የጠበቀ በመሆኑ ተመራጭ ዳቦ ስለመሆኑ ያላቸው ሰፊ ገበያ ምስክር ነው።ይሁንና በአሁን ወቅት ያላቸውን ሰፊ ገበያ በሙሉ አቅማቸው አምርተው ተደራሽ ለማድረግ ለዳቦ ዋና ግብዓት የሆነው የስንዴ ዱቄት እጥረት ሀገሪቷ የገጠማት ችግር በመሆኑ ለጊዜው ሥራው ቢቀዛቀዝም ተስፋ ባለመቁረጥ አቅምን አጠናክሮ መሥራት የግድ እንደሆነ ወይዘሮ ጽጌ ያምናሉ።ሥራው እየተስፋፋ ሲመጣ ሙሉ ጊዜያቸውን የፈለገ በመሆኑ ከመምህርነት ሥራቸው ተሰናብተው ሙሉ ለሙሉ የዳቦ ምርታቸው ላይ ትኩረት አድርገዋል፡፡
ወይዘሮ ጽጌ፤ ለሥራ ካላቸው ትጋትና ጥረት የተነሳ ከዳቦ መጋገር በተጨማሪም ዶሮ በማርባት ሥራ ላይም ይሳተፋሉ።ዳቦ በሚያመርቱበት ጊዜ በርካታ የዳቦ ፍርፋሪ የሚገኝ በመሆኑ ይህ ተረፈ ምርት እንዳይባክን በማለት በሰፊው ግቢያቸው ውስጥ ዶሮም ያረባሉ።በዶሮ እርባታም እንቁላል በመሸጥ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ማንኛውንም ሥራ ለመሥራት የውስጥ ፍላጎትና ዕውቀት ያስፈልጋል የሚል እምነት አላቸው። ባለቤታቸውን ጨምረው ሁለታቸውም ከዲፕሎማ ተነስተው በዲግሪ ትምህርቸውን የተከታታሉ ሲሆን፤ ባለቤታቸው ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ወይዘሮ ጽጌ፤ በዲፕሎማ ትምህርት መምህርት ሆነው ሲያገለግሉ የቤት ውስጥ ሥራን ጨምረው እየሠሩና ሌሊት እያጠኑ የዲግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።ልጆች እያሳደጉ የመንግሥት ሥራ በመሥራት እንዲሁም በቤት ውሰጥ ያለውን ኃላፊነታቸውን በብቃት ተወጥተዋል። ጎን ለጎን ዳቦ ጋግረው በመሸጥ ዛሬ የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሰዋል።ለዚህ ሁሉ ውጤት ዋናው ጥረት እንደሆነም ይናገራሉ።በ150 ሺ ብር መነሻ ካፒታል ወደ ሥራው የገቡት ወይዘሮ ጽጌ፤ በሥራቸው ውጤታማ ሆነው ከኪራይ ቤት በመውጣት የራሳቸውን መኖሪያና ዳቦ ማምረቻ ሠርተው በአዲስ መልክ ደግሞ ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ በአሁን ወቅት የሁለት ሚሊዮን ብር ካፒታል ደርሰዋል።ድርጅታቸውም ቀድሞ ከነበረው ስሙ አቤል ዳቦ ቤት ቅድስት አርሴማ የዳቦ መጋገሪያና ማከፋፋያ በሚል ተከፍቷል፡፡
አሁን ባለው የሀገሪቷ ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ የስንዴ ዱቄት እጥረት ያጋጠመና የጠፋ በመሆኑ በስፋት በተመጣጣኝ ዋጋ ማምረት አልተቻለም። ነገር ግን ህይወት ይቀጥላል፤ ከሥራው ጋር የተገናኙ የተለያዩ ነገሮች በመኖራቸው ባለው የገበያ ዋጋ እንሠራለን ያሉት ወይዘሮ ጽጌ፤ እርሳቸውን ከሌላው ነጋዴ ለየት የሚያደርጋቸው ነገር እንዳለ የናገራሉ። በአሁን ወቅት ጡረታቸውን አስከብረው ወርሐዊ ገቢ ማግኘት ችለዋል።
በቀጣይም የዳቦ ማምረት ሥራውን ይበልጥ አጠናክሮ የመቀጠልና ከዚሁ ጎንም ኩኪስ ለማዘጋጀት የኩኪስ መስሪያ ማሽን ለመግዛት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።ማሽኑን ሲያገኙ ኩኪስ በማምረት እንዲሁም የተለያዩ ተያያዥ የሆኑ ምርቶችን የማምረት ፤ምርቶቻቸውንም ሃዋሳ ከተማ ላይ በስፋት ተደራሽ የማድረግና በሃዋሳ ከተማ አካባቢ ባሉ ሌሎች ከተሞች ጭምር ተደራሽ ለማድረግ ዕቅድ አላቸው፡፡
ወይዘሮ ጽጌ፤ ወደ ሥራው ሲገቡ በሃዋሳ ከተማዋ የነበረው የዳቦ ፍላጎትና አቅርቦት የሚመጣጠን አልነበረም።ካለመመጣጠኑም በላይ የሚቀርበው ዳቦ ጥራቱ ጥያቄ ውስጥ የገባ ነበር። በእነዚህ ምክንያቶች ተገፍተው ወደ ዘርፉ የተቀላቅለዋል። በአሁን ወቅት በከተማዋ በርካታ ዳቦ ቤቶች ተከፍተው ተወዳዳሪው በዝቷል።ምንም እንኳን ተወዳዳሪ እየበዛ ቢመጣም በጥራት መሥራት ከተቻለ ሁልጊዜም ውድድሩን ማሸነፍ እንደሚቻል ያምናሉ።
በአሁን ወቅትም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተወዳዳሪ ከመኖሩ ባሻገር የተለያዩ የጥራት ደረጃና የምርት ዓይነቶች አሉ።ስለዚህ ውድድሩን ለማሸነፍና ውጤታማ ለመሆን የነበረውን ነገር ብቻ ይዞ መቀጠል የማይቻልና አዋጭ አይደለም።ስለዚህ በየትኛውም መስመር ቢሆን ጊዜው የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ተወዳዳሪ መሆን አስፈላጊ እንደሆነ ወይዘሮ ጽጌ ያስረዳሉ፡፡
ዳቦ ማባያ ሳያስፈልገው በሻይ መበላት የሚችል እንደመሆኑ ፍላጎቱ ሰፊ ነው የሚሉት ወይዘሮ ጽጌ፤ በተለይም በአሁን ወቅት ጤፍ ከመወደዱ ጋር በተያያዘ ዳቦ ተፈላጊነቱ ጨምሯል።ነገር ግን የስንዴ ዱቄትም እጥረት አለ።በመሆኑመ መንግሥት የተቻለውን ሁሉ ያድርግ ሲሉ አሳስበዋል።በተያያዘም ዳቦ ለመጋገር ከዱቄት በተጨማሪ ዘይትና ስኳር ያስፈልጋል የሚሉት ወይዘሮ ጽጌ፤ ስኳር በወር አንድ ኩንታል እያገኙ ጣፋጭ ዳቦዎችንም ይጋግራሉ።
መንግሥት በአሁን ወቅት አጠቃላይ በአምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል ያለውን ችግር ለይቶ ለመፍታት እንዲያስችለው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ግንኙነት እያደረገ ይገኛል።እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ በመሆኑ ቀጣይነት ቢኖረው ብዙ መማር ይቻላል በማለት በመንግሥት በኩል እየተደረገ ስላለው እንቅስቃሴ ተናግረዋል።
በመጨረሻም አሁን ላይ እየከበደ መጣውን የኑሮ ውድነት ለማሸነፍ አልቻልንም የሚለውን ከውስጡ አውጥቶ መጣል አለበት።ሰዎች እችላለሁ ብለው ከተነሱና ጥረት ካደረጉ የማይሠሩት ነገር አይኖርም።በተለይም ሴት ልጅ መሥራትና የራሷ የሆነ ገቢ ሊኖራት ይገባል።ሠርታም መለወጥና ሕይወቷን ማሻሻል ይገባታል።ወጣቱም ሥራ የለም ብሎ ጸጉሩን እያሻሸ ተቀምጦ ሥራ ከመጠበቅ ያገኘውን ነገር ሁሉ ሥራ ሳይንቅ መሥራት አለበት።ቤተሰብም ለሥራ ያለውን አመለካከት አስተካክሎ ለልጆቹ አርአያ በመሆን ወጣቱን ሥራ ፈጣሪ ማድረግ ይጠበቅበታልም ብለዋል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2013