በዓለማችን በአብዛኛው የሰለጠኑ አገራት ዛሬ ለሚያመርቷቸው ዘመናዊ መኪናዎች፣ አውሮፕላኖችና አጠቃላይ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መነሻቸው መሰረታዊ ሸቀጦችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች መሆናቸው እሙን ነው።ዓለማችን የስልጣኔ ካባ የተከናነበችው፤ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ስትሸጋገር ነው የሚባለው ለዚህ ነው። በእጅ ከሚሰሩ የዕድ ጥበብ ውጤቶች በፋብሪካ የተመረቱ ምርቶች ሲተኩና በገጠር ከሚኖር አብዛኛው ህዝብ ወደ ከተሜነት ሲሸጋገር ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ መምጣቱ የዘመናዊ አኗኗር ዘይቤ እየተለመደ መሄዱን በዓለም የበለጸጉ አገራት የኋላ ታሪክ ያሳየናል።
አገራት የተለያዩ ዘመናዊ አዳዲስ መሳሪያዎችን፣ የኃይል አማራጮችና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ጥቅም ላይ ማዋል መጀመራቸውን ተከትሎ የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ዘመናዊ መሆን ቻለ።የትራንስፖርት፣ ኮሙኒኬሽንና የባንኮች ዕድገትም እንዲሁም የሸቀጦች ምርታማነትና ትርፋማነት ማሳደግ ኢንዱስትሪ ዕድገቱ እንዲያፋጠን አስችሎታል። በየጊዜውም ሳይንስ የፈጠራቸው አዳዲስ ግኝቶች ተግባራዊ በመደረጋቸው የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶች በአግባቡ እሴት ተጨምሮባቸው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
ለአብነት እንደ ጃፓን፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋንና ኢንዶኖዢያ የሰሉ አገራት ደግሞ አሁንም የኢንዱስትሪ ልማት ለኢኮኖሚያቸው የብረት ምሶሶ ሆኖ ዘልቋል። እንደ ቲዮታና ሳምሰንግ ያሉ ዓለም አቀፍ ግዙፍ ኩባንያዎች ዛሬ ላይ የደረሱት ከትንሽ ተነስተው ነው።ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያም የብልፅግና ጉዞዋን ለማሳለጥ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በማስፋፋት ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ ግብ ይዛ እየሰራች ትገኛለች።
አልባሳትን፣ መሰረታዊ ሸቀጦችን፣ የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችና ሌሎች መገልገያ መሳሪያዎችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማውጣት ከውጭ ታስገባላች።በተለይ መድሃኒቶችን፤ ማሽነሪዎችን፤ ተሽከርካሪዎችንና መሰል ሸቀጦችን ከውጭ ለማስገባት አሁንም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ታወጣለች። ይህን የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት ለማሟላት መንግስት አንደኛ ከውጭ የሚገቡትን ዕቃዎች አገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማድረግ ኢንቨስትመንትን በስፋት ለመሳብ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው።
ሌላው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በአይነት፤ በጥራትና በመጠን ለመጨመር ግብ ይዞ እየሰራ ነው። በተለይ የውጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፤ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚደረገውን ጉዞ ለማፋጠንና የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማስቀጠል የማኑፋክቸሪንግ መስክ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ የኤክስፖርት ሸቀጦችን አቅርቦት በአይነት፣ በመጠንና በጥራት ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።
በአገራችን ኢንዱስትሪዎች እያቆጠቆጡ በመምጣታቸው ቀደም ሲል ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶች በአገራችን ውስጥ በመመረታቸው ተጨባጭ ለውጥ እየታየ መሆኑን ያሳያል። በተለይ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ ምርቶች ለዚህ ተጨባጭ ማሳያ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ፣ በሃዋሳ፣ በአዳማ፣ በጅማ፣ በመቐሌ፣ በባህዳር፣ በደብረ ብርሃን፣ በድሬድዋ፣ በኮቦልቻና በሌሎች አካባቢዎች የተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዛሬ ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በአገር ውስጥ ከመተካታቸው በተጨማሪ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ ናቸው፡፡
በቅርቡ ግንባታው ተጠናቆ ኢንቨስተሮችን በመጠባበቅ ላይ የሚገኘውን የሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጨምሮ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋትና ማደግ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ሁለተናዊ ዕድገት ግንባር ቀደም ድርሻ እያበረከተ ይገኛል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ የምርት ውጤቶች የውጭ ምንዛሬና የንግድ ተወዳዳሪነትን ከማሳደግ በተጨማሪ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል። እነዚህ ባለሙያዎችም ቴክኖሎጂ የመፍጠርና የመቅሰም አቅማቸው በየጊዜው እየጎለበተ በመምጣቱ ነገ ለሚስፋፉት ኢንዱስትሪዎች ምቹ መደላድል ይፈጥራሉ።
በኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች 13 ሲሆኑ፤ ለእነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በአጠቃላይ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ሁኗል።ወደ ማምረት ስራ የገቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርታቸውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ በ2012 በጀት ዓመት 485 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል።እንዲሁም መጪው ሰኔ በሚጠናቀቀው በጀት ዓመትም ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚገኙ ሲሆን ከ80 ሺህ በላይ ዜጎች ቀጥታ የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን መረጃ ያመለክታል።ይህ የሚያሳየን የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በአገር ውስጥ ምርቶች ከመተካታቸው ባሻገር ምርታቸውን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ መሆኑን ጭምር ነው።እንዲሁም ለበርካታ ዜጎች ቀጥታና ቀጥተኛ ያልሆነ የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ጭምር ነው፡፡
ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማስፋፋት ለአገሪቷ ፈርጀ ብዙ ጥቅም እያስገኙ ናቸው።በዚህም ከውጭ አገሮች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገቡትን ምርቶች በአገር ውስጥ ምርቶች መተካት ተችሏል፤ የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምሮ ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እየተገኘ ነው።ሌላው በተበታተነ መልኩ እዚህም እዚያም የሚገነቡትን የኢንዱስትሪዎችን በአንድ አካባቢ በማድረግ በተቀናጀና በተናበበ መልኩ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችንና አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜና በአነስተኛ ወጪ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።አገር በቀል ኩባንያዎችም በቀላሉ ከውጭ ኩባንያዎች ልምድና ክህሎት እንዲቀስሙ መልካም ዕድልን እየፈጠሩ ነው፡፡
ስለዚህ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በየጊዜው አቅማቸውን እያጎለበቱና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ክህሎታቸው እያሻሻሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ማምረት ይኖርባቸዋል። ለእዚህም የሚበጀውን ስንቅና ትጥቅ አዘጋጅተው ጉዞቸውን ወደ ፊት ሊቀጥሉ ይገባል። መንግስትም ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከማስፋፋት ጎን ለጎን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርታቸውን እያመረቱ ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ለሚያቀርቡ ኩባንያዎች የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ወዲያው እየፈታ ምርታማ እንዲሆኑ ማገዝ ይጠበቅበታል፡፡
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2013