የአዲስ ዓመት ጅማሬ …
የመስከረም ወር ከባተ ቀናት አልፈዋል። የአዲስ ዓመቱ ድባብ አሁንም እንዳለ ነው። ቀኑን በድምቀት የዋለው ከተማ ምሽቱ ያገደው አይመስልም። በየቦታው የሚታዩ ሱቆችና መደብሮች ደንበኞቻቸውን እያስተናገዱ ነው። መንገደኞች ትራንስፖርት ለመያዝ ከወዲያ ወዲህ ይላሉ። የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ሥራቸውን አልዘነጉም። ደንበኞችን ለመሳብ ከፍ ባለ ድምጽ ይጮኻሉ፤ ይጣራሉ።
ዕንቁጣጣሽን ተከትሎ የመጣው የመስቀል በዓል ድባቡን ትቶ ካለፈ ሁለት ቀናት ተቆጥረዋል። አውደ ዓመቱን አሳበው መዝናናትን የመረጡ አንዳንዶች በጊዜ አልገቡም። የብርጭቆ አንገት ጨብጠው ከመጠጡ ይደጋግማሉ። ከእነዚህ መሐል ጥቂት ጋባዥና ተጋባዦች የወጉን አድርሰው ወጥተዋል። ሌሎች አዲስ እንግዶች የእነሱን ቦታ ሊተኩ ወደ መዝናኛው እየገቡ ነው።
አሁን የጎዳናው ላይ ግርግር ቀንሷል። ወደቤታቸው የሚገቡ በርካቶች በጊዜ ተሸኝተዋል። መንገዱን ያጣበቡ ነጋዴዎች ጓዛቸውን ሸክፈው ስፍራውን ለቀዋል። ሱቆችና መደብሮች ደንበኞችን ማስተናገድ አቁመዋል። ሰዓቱ እየነጎደ ምሽቱ እየገፋ ነው። የመንገዱን ጠርዝ ይዘው የቆሙ የላዳ ታክሲዎች ጠያቂዎችቸውን መናፈቅ ጀምረዋል። ሾፌሮቹ በዕይታቸው ነቅተው የኮቴ ድምጽ ይጠብቃሉ። መሰሎቻቸው ደንበኞችን ይዘው ከጎናቸው ሲፈተለኩ እነሱን መሆን ይመኛሉ።
አሁን ለሊቱ እየተጋመሰ ነው። አልፎ አልፎ በመንገዱ ሽው ከሚሉ ጥቂት መኪናዎች በቀር የጎላ እንቅስቃሴ የለም። በየስፍራው ሁለት ሦስት ሆነው የሚዘዋወሩ ፖሊሶች አካባቢውን ይቃኛሉ። ሙቀት ለማግኘት የሻቱ የጎዳና አዳሪዎች በየቦታው እሳት አንድደው ይሞቃሉ። የመስከረም ቀዝቃዛ አየር በርትቷል። የእኩለ ለሊቱ ጭርታ ጨምሯል።
ተደርድረው ከቆሙ ታክሲዎች በአንደኛው የተቀመጠው ሾፌር ከፊትና ከኋላው የነበሩ ታክሲዎች ተሳፋሪዎችን ይዘው ሲንቀሳቀሱ አይቷል። እሱ ከቀን ይልቅ የምሽት ሥራ እንጀራው ከሆነ ቆይቷል። ሁሌም ቋሚ ደንበኞቹን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎትን ሲሹ በዋጋ ተነጋግሮ ካሰቡት ያደርሳል፤ ይመልሳል ።
ባለታክሲዎቹ ምሸት በገፋና ሰዓት በጨመረ ቁጥር ዋጋቸው ከፍ ይላል። አብዛኞቹ ደንበኞች የተጠየቁትን ይከፍላሉ። ሾፌሮቹም በታማኝነት ከተፈለገው ቦታ ያደርሳሉ። ባለታክሲዎቹ ያለአንዳች ሥጋት እንዲጓዙ ቋሚ ደንበኞች ቢያገኙ ይወዳሉ። ተሳፋሪዎቹም ቢሆኑ በሚያውቋቸው ሾፌሮች ቢገለገሉ ይመርጣሉ። እነሱ ከሆኑ ከደህንነት ችግር ይርቃሉ። ያለፍርሃት ያለጥርጣሬ ያሽከረክራሉ።
ብዙ ጊዜ የምሽት ባለታክሲዎቹ ምሽት ላይ የሚሠሩ ሴቶችና ደንበኞቻቸውን ያመላልሳሉ። በየትኛውም ሰዓትና ጊዜ ቢሆን ካሉበት ይደርሳሉና ጥቅማቸው የጋራ ነው።
በታክሲው የተቀመጠው ሾፌር የወቅቱ ብርዳማ አየር እየተሰማው ነው። እንዲህ በሆነ ጊዜ የመኪናውን ቴፕ ከፍቶ ሞቅ ያሉ ሙዚቃዎችን ያደምጣል። ቅዝቃዜውን ተቋቁሞ ጥቂት ከታገሰ ደግሞ የዕድሉን አያጣም። ምሽቱ እየገፋ ነው፤ እሱ ግን እስከመጨረሻው ተስፋ አይቆርጥም።
ባለታክሲው ሁለት እጆቹን ከመኪናው መሪ አስደግፎ በሐሳብ ይብሰለሰላል። ድንገት የእጅ ስልኩ አቃጨለ። ጆሮዎቹ ነቁ። ጥሪው እሰኪደጋግም አልጠበቀም። እየተጣደፈ አነሳው። ከአጭር የሰላምታ ልውውጥ በኋላ ሾፌሩ በስልክ ከሚወራው ሰው ትዕዛዝ ተቀበለ። ደዋዩ የዘወትር ደንበኛው ዘነበ ነው። ዘነበ ደንበኛው ብቻ አይደለም። የሰፈሩ ሰው ጭምር ነው። ሾፌሩ አሉኝ ከሚላቸው ቋሚ ደንበኞች መሐል አንዱ ነውና ሲያናግረው በተለየ ቅርበት ነው።
ወጣቱ ዘነበ መዝናናት ያስደስተዋል፤ ለዚህ ደግሞ ምሽትን ይመርጣል። ሰዓቱ በገፋ ጊዜ ለባለታክሲው ይደውላል። ባለታክሲው ጥሪው ሲደርሰው ለደንበኛው ትኩረት ሰጥቶ ከፈለገው ቦታ ያደርሰዋል። እሱም የልፋት ድካሙን አያሳጣውም። የተጠየቀውን ሰጥቶ ጉርሻን ከምስጋና አክሎ ይለየዋል።
የዛን ቀን መስከረም 19 2011 ዓ.ም የለሊቱ አጋማሽ ነበር። ባለታክሲው ስልኩን ዘግቶ ዘነበ ወደነገረው ስፍራ ለማምራት የመኪናውን ሞተር ቀሰቀሰ። እሱም እንደሌሎች ዕድል ቀንቶት ከፊት ከኋላው የከበቡትን ታክሲዎች ከጀርባው ትቶ ወደተባለው ስፍራ ተፈተለከ።
ባለታክሲው ዘነበ ወደ ነገረው ቦታ ሲደርስ ብቻውን አላገኘውም። አንድ ጓደኛው አብሮት ነበር። ሁለቱም ሲዝናኑ እንደቆዩ ያስታውቃል። በንግግርና ገጽታቸው ላይ ተመሳሳይ ስሜት ይስተዋላል። መጠጥ ሲጠጡ ነበርና ሁኔታቸው ከሞቅታ በላይ ነው። በተለይ ዘነበ ስካሩ በግልጽ ይለያል። ንግግርና ጨዋታው ጤናማ አይደለም። ባለታክሲው ሁለቱን ባልንጀሮች አግኝቶ ውስጥ እንደገቡ የተለመደውን ጥያቄ አነሳ። ‹‹ወዴት እንሂድ ?›› ሲል ምላሽ ጠበቀ።
ይህኔ ሁለቱም በአንድ ድምጽ ‹‹ወደ ቤቴል›› ሲሉ መለሱለት። ባለታክሲው የጉዞ አቅጣጫውን ቀይሶ የጦር ሃይሎችን መንገድ ያዘ። ጥቂት እንደተጓዙ የዘነበ ጓደኛ ወደቤቴል ሳይሆን ወደቤቱ መግባት እንደሚፈልግ ተናገረ። መኖሪያው አየር ጤና አካባቢ ነው። እስካሁን የተዝናናው የበቃው ይመስላል። ‹‹ቤቴ እገባለሁ›› ሲል ዘነበ አልተቃወመም። መጀመሪያ እሱን አድርሰው ወደ ቤቴል መሄድ እንደሚችሉ ተስማማ።
ሾፌሩ አሁንም በሚፈለገው ፍጥነት እየነዳ ነው። የለሊቱ ጭርታ ባሻቸው አካሄድ እንዲጓዙ እየረዳቸው ነው። የቀኑን ያህል የመኪኖች መጨናነቅ አይታይም። የዘነበወርቅ አደባባይን አልፈው ወደ አየር ጤና ሲያመሩ ጊዜ አልፈጀባቸውም። የዘነበ ጓደኛ መኖሪያ ደርሰው ከደጃፉ አወረዱት። ዘነበና ባልንጀራው ተሰነባበተው ተለያዩ። ሾፌሩ የመኪናውን አፍንጫ ወደመጣበት መልሶ ቤቴል ወደሚባለው ሰፈር አቀና።
ቤቴል በዛን ሰዓት…
የቤቴልና አካባቢው ነዋሪዎች እንደሁልጊዜው በጊዜ ወደቤታቸው ገብተዋል። ሰፈሩ መኖሪያ እንደመሆኑ ክስተቱ የተለመደ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስፍራው በታላላቅ የንግድ መደብሮች መሟሟቅ ጀምሯል። በርከት የሚሉት ነዋሪዎች አካባቢውን ሲያደምቁት ይውላሉ። ሆቴሎች፣ ቡና ቤቶች ካፌና ሬስቶራንቶች ለስፍራው መለወጥ ድርሻ አላቸው።
ምሽት ላይ በርካቶቹ አገልግሎታቸውን አጠናቀው ይዘጋሉ። ከእነዚህ መሐል አንዳንዶቹ ምሽቱን አጋምሰው ደንበኞቻቸውን ይሸኛሉ። ጥቂቶቹ ደግሞ ከምሽት አልፈው እሰከ ንጋት ይሠራሉ። እንዲህ አይነቶቹ ገበያ የሚደራላቸው ከዕኩለ ለሊቱ በኋላ ነው።
በእነዚህ ስፍራዎች የሚታደሙ ደንበኞች ዘና ማለት ምርጫቸው ነው። ያሻቸውን እየጠጡ መደነስ መጨፈር ይወዳሉ። በመጠጥ ቤቶቹ ከሚያስተናግዱ ሴቶች ጋር ጭውውት ደስ ይላቸዋል። ሲሻቸው አውርተው፣ አልያም ተስማምተው አብረዋቸው ያድራሉ። ብዙጊዜ በእነዚህ ቤቶች ጠብና ግርግር አይጠፋም። ሰክረው የሚደባደቡ፣ ተፈናክተው ፖሊስ ጣቢያ የሚጓተቱ በርካታ ናቸው። ሲነጋ የትናንቱ ተወርቶ የዛሬው መንገድ ይቀጥላል። ይህ እውነት የእነዚህ ቤቶች ልማዳዊ ገጽታ ሆኖ ጊዚያትን አስቆጥሯል።
ዘነበና ባለታክሲው ከእነዚህ ቤቶች በአንደኛው ተገኝተዋል። እነሱ ሲደርሱ ሙዚቃው ከውጭ እየተሰማ ነበር። አንዳንዶች ከመቀመጫቸው ተነስተው እየደነሱ ነው። አጫጭር ቀሚስ የለበሱ አስተናጋጆች የፈዘዘው መብራት ሳያግዳቸው ጠረጴዛዎችን ይቃኛሉ። አዲስ የሚገቡትን እየተቀበሉ አመቺ ወንበር ያሳያሉ። ጨርሰው ከሚወጡ ደንበኞች ሂሳብ አስበው፤ ይቀበላሉ።
አስተናጋጆቹ ብዙ ጊዜ በደንበኞች ለዳንስ ይጋበዛሉ። አንዳንዶች ጥያቄውን ተቀብለው እንግዶችን ያስደስታሉ። ጥቂት አረፍ ካሉ ተቆጪያቸው ይበዛል። በአሰሪያቸው ዓይን እንዳይገቡና ድርጊታቸው ከስንፍና እንዳይቆጠር ይጠነቀቃሉ።
በቡና ቤቱ …
ባለታክሲው ደንበኛውን ካሰበው ስፍራ እንዳስገባ ወደመጣበት ለመሄድ ተዘጋጀ። ይህን ያየው ዘነበ እሱ እንዳሰበው ሊሸኘው አልወደደም። አብሮት ቆይቶ ከግብዣው እንዲታደም ለመነው። ባለታክሲው ጥቂት እንደማመንታት ብሎ በሐሳቡ ተስማማ።
የሆቴሉ ሙዚቃ ደምቋል። በየመሐሉ እየተነሱ የሚደንሱ ደንበኞች ዘና ማለታቸውን ቀጥለዋል። የመጠጥ ሽታና የላብ ጠረን ከሙቀት ተዳምሮ መጨናነቁ ጨምሯል። ይህ ሁሉ ምንም ያልመሰላቸው አንዳንዶች ከሚጠጡት እያስጨመሩ፤ ከሚያወጉት እየቀጠሉ ነው።
ዘነበና ባለታክሲው ከአንድ ጥግ ተቀምጠው ቢራ መጠጣት ጀምረዋል። በቤቱ በተናጥል ካሉት ሌላ በቡድን ሆነው የሚዝናኑ ሰዎች ጠረጴዛ ከበው ይጫወታሉ። ጨዋታቸው በሳቅ የታጀበ ነው። ከእነሱ መሐል ለዳንስ የሚነሱ አይጠፉም። መወዝወዙ ሲበቃቸው ወደመቀመጫው ይመለሳሉ።
ዘነበ ከቢራው እየደጋገመ ነው። ሙዚቃውና ሙቀቱ ከመጠጥ ታክሎ ሰውነቱን መጋል ጀምሯል። ስካር ሲጀምረው ከሰዎች ጋር ሰላም አይፈጥርም። ሰበብና ምክንያት እየፈለገ ለጠብ ይጋበዛል። ክፉ እየተናገረ ሌሎችን ያስከፋል። ዓመል መሆኑ የገባቸው በትዕግስት ያልፉታል። ይህን የማይሞክሩት ሊጣሉት ይነሳሉ። ብርቱ ገላጋዮች ካሉ ጠቡ ውሃ ይፈስበታል።
ዘነበ ከመጠጡ እየደጋገመ የቤቱን ትዕይንት ያስተውላል። አሁን የሚጨፍሩትን መምሰል እየፈለገ ነው። ዳንሱን ለብቻው ማድረግ አልፈለገም። በዓይኖቹ እየቃኘ ባሻገር ተመለከተ። ዓይኑ ከአንዲት ወጣት አስተናጋጅ ላይ ከማረፉ ከነበረበት ተነስቶ ይጠራት ጀመር። አብራው እንድትደንስ ልብሷን እየጎተተ አስገደዳት። ልጅቷ አልፈቀደችም። አስተናጋጅ በመሆኗ ይህን ማድረግ እንደማትችል ደጋግማ ነገረችው።
ዘነበ በምላሽዋ ተናደደ። ጥያቄውን ያለመቀበሏን ከንቀት ቆጠረው። እየተጠጋት አብራው እንድትድነስ ደጋግሞ ጠየቃት፤ ልጅቷ ውሳኔዋ አልተለወጠም። መጨቃጨቅ ጀመሩ፤ ዘነበ ንዴቱ ጨመረ። መናቁ፣ አለመፈለጉ አንገበገበው ትዕግስት አጣ። ወዲያው ፈጥኖ አንድ ጉንጭዋን በጥፊ አነደደው። አስተናጋጇ ፊቷን እያሻሸቸ ጮኸች። እያለቀሰች አለቃዋን ልትጣራ ወደውስጥ አለፈች። በሁኔታው ያዘኑ በርካታ ዓይኖች ተከተሏት ።
እነ ዘነበ ከተቀመጡበት ወንበር ፊት ለፊት በቡድን ሆነው የሚዝናኑ ሰድስት ወጣቶች ሳቅና ጨዋታ ደምቋል። ጠረጴዛውን የሞላው የቢራ ጠርሙስ ስለነበሩበት ቆይታ ያሳብቃል። በድንገት ግን በመሐከላቸው የነበረው ጨዋታ ተቋረጠ። ሳቅና ሁካታው ቀርቶ የሁሉም ትኩረት ወደ አንድ ጉዳይ አዘነበለ።
በቡድን ከነበሩት ባልንጀሮች አንደኛው ከዘነበ ጋር አንገት ለአንገት ተያይዟል። የጠባቸው ምክንያት ባይታወቅም ሁኔታቸው ያሰደነግጣል። ሳቃቸው በአፍታ የደበበዘዘው ባልንጀሮች ሁለቱን ከተያያዙበት አላቀው የራሳቸውን ሰው ወደ ነበረበት መቀመጫ መለሱ።
ጓደኛቸው በዘነበ ድርጊተ ተበሳጭቷል። ሴትን ልጅ በጥፊ መምታቱ አብሽቆትም ሊጣላውና ሊመታው ከመቀመጫው ተነስቷል። ቆይተው እውነታውን የተረዱት ባልንጀሮች ጓደኛቸውን መክረዋል። ከንዴቱ እንዲመለስም በጨዋታ አዋዝተዋል።
ዘነበ በቤቱ ጋርድ እየተገፋ ከመዝናኛው እንዲወጣ ሆነ። ድርጊቱ ስህተት መሆኑን ሊያምን የፈለገ አይመስልም። ባለታክሲው ከጠቡ መሐል ገብቶ ከገላገለ በኋላ መክሮና ተቆጥቶ እንዲረጋገ አደረገ። ለብቻው እንዲሆንና ጠቡን እንዲረሳም ከአስፓልቱ ማዶ ከሚገኝ ነዳጅ ማደያ አጠገብ ወስዶ አቆየው። ለጊዜው ነገሩን ለማብረድ መሞከሩ ተሳካለት። ዘነበ አሁንም እንደበሸቀ ነው ። ከሰውዬው ጋር መጣላቱ አናዶታል። ድርጊቱን እንደዋዛ ማለፍ እንደሌለበት እያሰበ እጁን በእጁ ይመታል።
ከጠቡ በኋላ…
ከነበሩበት ቆይተው ሲመለሱ ነገሮች ተረጋግተው ነበር። ባለታክሲው ይህን እንዳየ ጠበኛውንና ጓደኞቹን ይቅርታ ጠየቀ። ባልንጀሮቹ ወደ ቤታቸው ለመሄድ ከውጭ ቆመው ነበር። ይቅርታውን በበጎ የተቀበሉት ባልንጀሮች ነገሩን አቅልለው ሰላም ፈጠሩ። እንደውም መኪና ከሌላቸው ሊሸኝዋቸው እንደሚችሉ ነገሩት።
አምስቱ ጓደኞች በያዙት ዳማስ መኪና ለመሄድ ወደ ውስጥ ገቡ። የዘነበ ጠበኛ እነሱን ተሰናብቶ በራሱ መኪና ለመጓዝ ቁልፉን ከፍቶ ሞተሩን አስነሳ። ይህ ሁሉ ሲሆን ዘነበ ጥርሱን ነክሶ ጠበኛውን ያስተውላል። ከደቂቃዎች በፊት የሆነውን አልዘነጋም። እየተናደደ ዓይኑን አፍጥጦ ተጠጋው። በእጁ ድንጋይ ይዟል። ሰውዬው መኪናውን ከማስነሳቱ በፊት ደረሰበት። ባልተዘጋው መስኮት ተጠግቶ ድንጋዩን ፊቱ ላይ አሳረፈበትና ወደፊት ሮጠ ።
ፊቱ በደም የተሸፈነው ወጣት የሆነውን አላመነም። በድንጋጤና በእልህ ፊቱን እየጠረገ ደቂቃዎችን አሳለፈ። በዚህ መሐል ዘነበ ከእሱ የመራቅ ዕድል አገኘ። ከአፍታ በኋላ ጠበኛው ከድንጋጤው ባነነ። እልህና ንዴት ወረረው። በደመነፍስ የመኪናውን ፍጥነት ጨምሮ ከኋላው ተከተለው፡፤
ዘነበ በስካር ድካም እየተንገላወደ ወደፊት ገሰገሰ። ከኋላው መኪና እንደሚከተለው አውቋል። ሩጫውን ሳያቆም መሮጡን ቀጠለ። አሁንም የመኪና ሞትር ይሰማዋል። ባለመኪናው ይፈጥናል ዘነበ ይሮጣል። በመንደሩ የኮብልስቶን ጥርጊያ ላይ እንደገባ ባለመኪናው ደረሰበት።
ብርሃን በዓይኑ ላይ ማረፉን እንዳወቀ የትም እንደማያመልጥ ተረዳ። ጥቂት ቆም ከማለቱ ባለመኪናው ደርሶ ገጭቶ ጣለው። ዘነበ ከወደቀበት ሆኖ እንዳይገድለው በእጁ ተማፀነ። ባለመኪናው አልሰማውም። በዓይኖቹ አንዳች ነገር መፈለግ ያዘ። ድንገት የመንደሩ መኪና ጠባቂ ደረሰ። የያዘውን ትልቅ ድንጋይ አይቶም ‹‹ይቅርብህ›› ሲል ለመነው።
ባለመኪናው በሁለት እጆቹ ያነሳውን ትልቅ ድንጋይ አልመለሰውም። የወደቀውን ሰው አንገት በእግሮቹ እየረጋገጠ ገጭቶ ከጣለው ቁስለኛ ላይ ድንጋዩን ደጋግሞ አሳረፈበት።
የፖሊስ ምርመራ…
ፖሊስ ጥቆማ ከደረሰው አካባቢ ሲገኝ የዘነበ ህይወት አልፎ ነበር። ከአካባቢው መረጃ ሰብስቦ የሟችን አስከሬን እንዳነሳ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር አውሎ ቃሉን ተቀበለ። ስሙን ‹‹ሳሙኤል አባይ›› ሲል ያስመዘገበው ተጠርጣሪ ድርጊቱን ስለመፈፀሙ አምኖ መፀፀቱን ተናገረ። ጉዳዩን የያዘው መርማሪ ኢንስፒክተር ሲሳይ በላይ በመዝገብ ቁጥር 408/11 ላይ ቃሉን አስፍሮ ዶሴውን ለዓቃቤ ሕግ አሳለፈ።
ውሳኔ…
የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሽ ሳሙኤል አባይ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮ ተገኝቷል። ተከሳሹ በተጠየቀበት ከባድና ሆን ብሎ ሰው የመግደል ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑ ተረጋግጧል። በዕለቱ በተሰጠው ብይንም እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራ አራት ዓመት ጽኑ እሥራት ይቀጣ ዘንድ ተወሰኗል።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2013