“ትእዛዝ” ወይም “ትእዛዛት” ቀላል ጽንሰ ሀሳቦች አይደሉም፤ ከቃላት ባለፈ እምነት ናቸው፤ ፍቅርና አብሮነት፤ ወንድማማችነትና ጉርብትናም ጭምር። ይህን ስንል ከምንም ተነስተን ሳይሆን ከምንጩ፣ ከኃይማኖት፤ በተለይም ከታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ (በሌሎቹ ቅዱሳን መፃሕፍትም እንደሚኖር ይታመናል) ተነስተን ነው – ከ”አስርቱ ትእዛዛት”።
ምናልባት “ለአስርቱ ትእዛዛት የሚታዘዘው ቁጥር አንሶ የማይታዘዘው ቁጥሩ በበዛበት በዚህ ወቅት ስለ እነሱ ማውራቱ ለምን አስፈለገ?” ሊባል ይችል ይሆናል። ከተባለ ትክክል አይደለም ማለት አይቻልም፤ ነው። ይሁንና ግን የኛ አነሳስ የደራሲ ከበደ ሚካኤልን ሥራዎች፣ ውለታቸውንና የተወጡትን አገራዊ ኃላፊነት፤ የደራሲነት ሚና፤ በተለይም ከአገር ግንባታ አኳያ ከሰሯቸው በርካታ ሥራዎች መካከል “አስርቱ ትእዛዛት”ን በመውሰድ በእነሱ አማካኝነት አንዳንድ ሀሳቦችን (እንድገመውና ከአገር ግንባታ አኳያ) መለዋወጥ ነው።
(አገር ግንባታ ማለት የረዥም ጊዜ እቅድ፣ የአስተሳሰብ ልማትና ብስለት፣ የሥነ ምግባርና ሞራል እሴትን መጠበቅና ማስቀጠል፤ እንዲሁም ትውልድን ከአገራዊና ሕዝባዊ አመለካከት አኳያ መቅረፅና ወጣቱ ከአያት ቅድመ አያቶቹ በአደራ የተረከባትን አገር ጠብቆና አቆይቶ ለሚቀጥለው ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ከማስገንዘብ አኳያ መረዳት ተገቢ ሲሆን፤ ጽንሰ- ሀሳቡ ከ”አገረ መንግሥት ግንባታ” የተለየ፣ እንደውም አገረ መንግሥት ግንባታ ለአገር ግንባታ ግብአቱ መሆኑን መረዳት ጠቃሚ ነው።) ወደ ርእስ ጉዳያችን እንመለስ።
“ትእዛዝ” ወይም “ትእዛዛት” ከመንፈሳዊው ዓለም ባለፈም በምድራዊው ላይም ያለው ዋጋ የሚቀመስ አይደለም፤ በአስተዳደር መዋቅሩ ከቀበሌ እስከ ቤተ መንግሥት ድረስ “ትእዛዝ” ሰጪና ተቀባይ አለ፤ “ትእዛዛት” (በእኛ አገር ከላይ ወደታች) ሲወርዱ፣ ሲወራረዱ ነው ኑሯቸው። በማህበራዊ ሕይወትም ከታላቅ ጀምሮ እስከ ትልቁ የዕድሜ ጣሪያ ድረስ ያሉ ሁሉ ተዋረዳቸውን ጠብቀው ትእዛዝ ይሰጣሉ፤ ይቀበላሉም። ደራሲና ባለ ቅኔው ከበደ ሚካኤልም ይህንን ቀዳዳ ተጠቅመው ነው እንግዲህ እኛ “አስርቱ ትእዛዛት” ያልንላቸውን “እነሆ” ያሉት፤ ትውልድ በአግባቡ ይቀረፅ፣ አገር ተረካቢ በአስረካቢው እግር ይተካ፣ ሥነምግባርና ሞራል በሁሉም ዘንድ ይሰርፅ፣ በሁሉም ልብና አእምሮ ውስጥ ፈሪሀ እግዚአብሔር ይኖር፤ በሁሉም ልብ ውስጥ የአገርና የወገን እንዲሁም የሰንደቅ ዓላማ ትርጉም ይገለፅ፣ ፍቅር ይንቀለቀል ዘንድ ቆጥረው ያስረከቡን (‘ሰሚ የለም እንጂ ሰሚ ቢኖር …” በማለት ግጥምና ዜማ የሚሞክር ካለ ምንም ሳንሰስት እንመክረዋለን – ያዋጣል!!!)።
ዛሬ በተለመደውና በተቀደደው መንገድ እንሄድ ዘንድ አልፈቀድንም። አቶ ከበደ ሚካኤል (የክብር ዶክተር) እዚህ ተወለዱ … አደጉ … ተማሩ … ማለትንም የመልዕክታችን አካል ማድረግን አልፈለግንም፤ ስለ ግጥሞቻቸውም ሆነ ሌሎች ሥራዎቻቸው አንድ … ሁለት … ሦስት … እያልን መቁጠሩንም ለጊዜው ዘልለነዋል። ለዛሬ የመረጥነው “አስርቱ ትእዛዛት”አቸውን ለትውልድ ማሻገሩንና በባለውለተኛነታቸው ማስታወስ ነው።
እርግጥ ነው ከበደ ሚካኤል (1907 – 1991) ያላሉት የለም። ስብሀት ገብረእግዚአብሔር ማርክስ፣ እየሱስና ሼክስፒር (አንዳንዴም ጥላሁን ገሠሠን ይጨምራል) ያላሉት የለም ሲል ይሰማ፤ ጽፎትም ይነበብ ነበር። እኔም እላለሁ – ከበደ ሚካኤል ያላሉት ያላስተማሩት የሥነ-ምግባርና ሞራል ትምህርት፤ ያልቀመሩት መርሆና ኃልዮት የለም!!! (ሁሉ ነገር በዚህ ጽሑፍ በስተግርጌ እንደጠቀስነው የግጥም አንጓ ካልሆነ በስተቀር።)
መቸም ከሥነ-ምግባርና ሞራል፤ ወይም ትምህርት ጋር በተያያዘ ቀዳሚ ትዝታ ቢኖር የትምህርት ቤት ሕይወት ነው፤ ቀጥሎ ትምህርትና አስተምህሮቱ። በእነዚህ ተያያዥ ሂደቶች ውስጥ የመማሪያ መፃሕፍቱ አሉ፤ አጋዥ የምንላቸው፤ ሲያሻንም መርጃ መሣሪያ። እነዚህ ሲጠቀሱና ሲታወሱ ደግሞ (ልክ አባባ ተስፋዬን በ”ልጆች የዛሬ አበባዎች፤ የነገ ፍሬዎች” እንደምናስታውሳቸው ዓይነት አባታዊ ትውስታ ማለት ነው) የማይረሱ ስብእናዎች አሉ፤ ለምሳሌም ደራሲ ከበደ ሚካኤል።
በንጉስ ኃይለሥላሴም ሆነ በደርግ መነሻ አካባቢ ትምህርት ቤት ውሎ የሚገባ ሰው መቸም “ከበደ ሚካኤልን አላውቅም” ሊል አይችልም። ቢልም፣ የሆነ አንዳች ዓይነት ችግር ካልሆነ በስተቀር፣ የሚያምነው የለም፤ ወይንም በዛሬው ቋንቋ “አልሰማህም” እንለዋለን እንጂ “እሺ”፣ “ይሁን” ልንለው አይታሰበንም። ባጭሩ ማለት የፈለግነው ከበርካታ ሥራዎቻቸው መካከል “’ታሪክና ምሣሌ’ የጋራ ቋንቋ ነበር” ነው።
ታዋቂውን የእንግሊዝ ባለ ቅኔ ዊሊያም ሼክስፒርን ወደ አገራችን በማስገባት የመጀመሪያው አስተዋዋቂ በመሆን የሚታወቁት ከበደ ላገራቸው ያልሰሩበት ዋና ዋና ዘርፍ የለም። ሹም ሆነው አገልግለዋል፤ በፀሐፊነት ሰርተዋል፤ አገራቸውን ወክለው (በተለይ ከንጉሱ ጋር) አገራትን ዞረዋል። ይህ ሁሉ እያለም ዋና ሥራቸው የሆነ እስኪመስል ድረስ በርካታ ዘመን ተሻጋሪ የሥነጽሑፍ ምርቶችን አምርተው አልፈዋል።
ሥራዎቻቸው በዓይነታቸው ብዙ ሲሆኑ በዓላማቸው ግን ተቀራራቢዎች ናቸው፤ ስለ አገር ብልፅግና በጃፓን ማሳያነት ጽፈዋል፤ ስለ ቅኔ ብዙ ብለዋል፤ በዚህ ጽሑፍ በምናተኩርበት “ታሪክና ምሳሌ” አማካኝነት ለሁሉም የሚጠቅም ትምህርት ያስተላለፉ ሲሆን፤ በተለይ ትውልድን ከመቅረፅና ማነፅ አኳያ ከቤ የሄዱበት መንገድ እሩቅ ነው።
ከሥራዎቻቸው ሁሉ ለዛሬ “ታሪክና ምሳሌ ፩ኛ መጽሐፍ”ን ስንመርጥ በምክንያት መሆኑን መግለፅ ተገቢ ሲሆን፤ እሱም መጽሐፉ በተለይ ለማስተማሪያነት መዘጋጀቱና በማንኛውም መስፈርት ቢመዘን የተዋጣለት ሆኖ መገኘቱ፤ በተለይም አቀራረቡ (በቅርፅም በይዘትም) ከታተመበት ዘመን አንፃር ሲታይ ከጊዜው የቀደመ መሆኑና የይዘት ምርጫው ወቅቱንና ወደፊትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
ከበደ ሚካኤልንና ሥራዎቻቸውን ስናነሳ፤ ብዙውን ጊዜ ገጣሚነታቸው (በእንግሊዝኛ የፃፉት መጽሐፍ መኖሩን እንኳን ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን?) ላይ እናተኩራለን። እርግጥ ነው ገጣሚነታቸው ጎልቶ ይሰማል፤ በተለይ ከላይ እንዳመለከትነው በትምህርት ቤት ውስጥ ያለፈ ሰው ይህ ዓይነቱ የደራሲው ሥነጽሑፋዊ ስብእና ነው ቶሎ ብሎ ወደ አእምሮው ጓዳ የሚመጣው። ይሁን እንጂ ግን ከበደ ከዚያም በላይ ናቸው።
የከበደን ሥራዎች ስንመለከት በአንድ ሥራ ውስጥ እንኳን በርካታ ከበደዎችን ነው የምናገኘው። ገጣሚ፣ ታሪክ ፀሐፊ፣ መካሪ፣ ተርጓሚ፣ አስተማሪ ወዘተ ከበደዎችን። ይህንን በ”ተረትና ምሳሌ ፩ኛ መጽሐፍ” አማካኝነት እንመልከተው።
“ታሪክና ምሳሌ ፩ኛ መጽሐፍ” ከልቡ የማስተማሪያ መጽሐፍ ነው። ከበደም ትምህርትንና የመምህርነት ሙያን ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው፤ ይህንን (የተጋነነ መስሎ ከታየ) ከመጽሐፉ “መቅድም” እና ሌሎች ክፍሎቹ መረዳት ይቻላል።
“ታሪክና ምሳሌ ፩ኛ መጽሐፍ” በሚገባ ታስቦበትና ሙሉ ዝግጅት ተደርጎበት የተዘጋጀ ሲሆን፤ አላማውም (በአሁኑ ዘመን አነታራኪ በሆነው ቋንቋ ስንገልፀው) “አገር ግንባታ” ላይ ያተኮረ ነው።
“አገር ግንባታ” ለ”አገረ መንግሥት ግንባታ” ካለው የጎላ (እንደውም ወሳኝ) አስተዋፅኦ አኳያ ስንመለከተው የከቤ ምርጫ የሚደነቅና የሚያስመሰግናቸው ነው የሚሆነው። እንደ ልፋታቸው ተሳክቶላቸዋል አልተሳካላቸውም የሚለው ሌላ ጉዳይ ሆኖ ሥራዎቻቸው ለባለውለታነታቸው ግን ቀዳሚው ማረጋገጫዎቻችን ናቸው።
የ”ታሪክና ምሳሌ ፩ኛ መጽሐፍ”ን አገር የመገንባት ሚና የምናገኘው ከመጀመሪያው፣ ከሽፋኑ ጀምሮ ሲሆን እሱም በጋራ እውቀት፣ ማንነት፣ መለያ ላይ የተመሰረተ መሆኑና እሱም በውስጥ ገፆች በሚገባ ተብራርቶ መገኘቱ ነው።
“ተረትና ምሳሌ ፩ኛ መጽሐፍ” ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ሲሆን በይዘት ምርጫውም ከአገር፣ ሰንደቅ ዓላማ፣ ሕዝብና የመሳሰሉት ግዙፍና ረቂቅ ሀሳቦች ተነስቶ፤ እነሱን በሚያሰርፅ ብልሀት ላይ የተመሰረተ ሆኖ ነው የምናገኘው። በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናና ተቀባይነት ያላቸው ስብእናዎችንና ሥራዎቻቸውን በጥንቃቄ በመምረጥ ወደ እዚህ ያሻገረው ይህ መጽሐፍ የታዋቂ ፈላስፎችን አስተማሪ የሆኑ ሀሳቦችም በእቅፉ በመያዝ ነው።
ሌላው ይህንን መጽሐፍም ሆነ ደራሲውን ለየት የሚያደርጋቸውና ሥራው ከጊዜው የቀደመ ስለመሆኑ ማረጋገጫው ከማውጫው ቀጥሎ (ገጽ አልተሰጠውም፤ ርእስም የለውም) ያለው ገጽ ሲሆን፤ የዚሁ ገጽ የመጀመሪያ መስመር የሚጀምረው “እኛ ኢትዮጵያውያን . . .” የሚል መሆኑና ከአንዳንድ አገራት አወዛጋቢ ሕገ-መንግሥታት መግቢያ አንቀፆች የተሻለ (እንድገመው የተሻለ …) አቃፊ ሆኖ መገኘቱ ነው።
የዛሬ የዚህ ጽሑፍ ትኩረትም በዚሁ ገጽ ላይ ሲሆን የ”አስርቱ ትእዛዛት” ጉዳይም ከዚሁ ገጽ የሚጀምር በመሆኑ ገጹ መነሻችን ይሆናል ማለት ነው።
ይህ ገጽ አልባው ገጽና ጀርባው በዚህ ጽሑፍ አማካኝነት ወደ አንባቢ የምናሸጋግራቸውን የከበደን “አስርቱ ትእዛዛት”ን የያዘ ሲሆን ትእዛዛቱም ከላይ ጀመር ያደረግነው፣ የጥሩና አካታች (“አቃፊ”ም ብንለው ይሆናል) ሕገ-መንግሥት መግቢያ ይሆን ዘንድ በማሳያነት የተጠቀምንበትን “እኛ ኢትዮጵያውያን . . .” በሚል የሚጀምር “መመሪያ” (“መመሪያ” ያልነው እኛ መሆናችን ይታወቅ) የተቀነበበ ሲሆን እኛ ትእዛዝ እንል ዘንድም “ያስገደደን” ይሄው በ”መመሪያ”ው ውስጥ የተገኘው “በግድ” ነው። ሙሉ መመሪያውም፤
“እኛ ኢትዮጵያውያን ባሁኑ ጊዜ በግድ ልንከተለውና ልንፈፅመው የሚገባን ዐሳብ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ነው።” የሚል ነው።
በዚህ “መመሪያ” ውስጥ ካሉት 13 ቃላት መካከል ልዩ ትኩረትን የሚስቡ ያሉ ሲሆን በተለይ “እኛ”፣ “ኢትዮጵያውያን”፣ “በግድ”፣ “ባሁኑ ጊዜ”፣ “ልንከተለው” እና “ልንፈፅመው” “የሚገባ” የሚሉት ጥልቅና መጠነ ሰፊ ትርጉም ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ ለሰፊ ጥናትና ምርምር የሚጋብዙ፣ የወቅቱን (እና ያሁኑን) የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ታሪካዊ ሁኔታ የሚያመለክቱ ናቸው። በመሆኑም “ነው” ደራሲው ይህን ልዩ ልዩ የጽሑፍ ዓይነቶችን (“ትእዛዛቱ”፣ ምክሮች፣ ጥቅሶች ከታዋቂ ሰዎች፣ የፈላስፎች ንግግር፣ ግጥሞች – ፋኖስና ብርጭቆ፣ የብረት ድስትና የሸክላ ድስት …፣ የፊደል ገበታ ወዘተ) የያዘ የማስተማሪያ መጽሐፍ በማዘጋጀት ለአገር ግንባታ ተግባር ያነሳሳቸው። አሁን በቀጥታ ወደ “አስርቱ ትእዛዛት” (ከአንድ እስከ አስር የዘረዘሯቸው)፤ ትእዛዛቱን ለትውልድ ማሻገሩ ተግባራችን እንሂድ፤
አንደኛ፡- ኢትዮጵያዊ የሆንህ ሰው ሁሉ ንጉስህ፣ሰንደቅ አለማህ፣ አገርህና ነፃነትህ የሚጠቁበትን ነገር ለማስወገድ ወይም ደግሞ እነሱ የሚጠቀሙበትን ሥራ ለመፈፀም ብለህ በሞትህ ጊዜ በሰማይና በምድር ስምህ በወርቅ ቀለም የሚፃፍበትን የሰማእትነት ሥራ መስራትህን ልብህ ተረድቶ ደስ ይበለው።
ሁለተኛ፡- አገርን መውደድ ማለት አገርህ የምትጠቀምበትንና የምትከበርበትን ሥራ መሥራት ማለት ነው።
ሦስተኛ፡- አገርህንና ወገንህን የሚያስንቅ ወይም የሚጎዳ ሥራ ከመሥራት መሞት ይሻልሀል።
አራተኛ፡- እኛ ኢትዮጵያውያን የምንሰራው ሥራ መልካም ቢሆን አገራችን ኢትዮጵያ እንደምትከበር የምንሰራው ሥራ መጥፎ ቢሆን ግን እንደምትዋረድ አትርሳ።
አምስተኛ፡- ኢትዮጵያ አገርህ ከሌሎቹ ከማንኛቸውም አገሮች ሁሉ ይልቅ የምትበልጥብህ መሆንዋ ቀንም ሆነ ሌሊት በዐሳብህ ውስጥ ሳይረሳና ሳይዘነጋ ተጽፎ ይኑር።
ስድስተኛ፡- ማንኛውም የውጭ አገር ሰው ለተወለደባት አገሩ የሚያስብላት መልካም ዐሳብ ወይም የሠራላት መልካም ሥራ ሲነገር በሰማህ ወይም ተጽፎ ባየህ ጊዜ አንተም ደግሞ እንደዚሁ ይህንኑ ያህል ላገርህ ለኢትዮጵያ ልታስብላትና ልትሰራላት የሚገባህ መሆኑን እወቀው።
ሰባተኛ፡- አንድ ኢትዮጵያዊ ሲበደልና ሲጠቃ ባየህ ጊዜ የተበደለችውና የተጠቃችው እናትህ ኢትዮጵያ መሆኗን ተረዳው።
ስምንተኛ፡- ኢትዮጵያ አገርህ በእውነት ትልቅ ሳትሆንና ወንድሞችህም ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሳይደላቸው አንተ ብቻህን የምታገኘው ደስታ፣ ገንዘብና ተድላ በህልም እንደ ተገኘ ወርቅ መና፤ ባዶ ሆኖ የሚቀር መሆኑን ልብህ አይዘንጋው።
ዘጠኝኛ፡- ብዙ ገንዘብና ብዙ ርስት ከማግኘት ይልቅ ለአገሩ ትልቅ ሥራ የሠራላት ሰው ስሙ ለዘለአለም በታሪክ ሲጠራ ይኖራል።
ዐስረኛ፡- ሌሎቹ የዓለም ነገሥታት ከደረሱበት የሥልጣኔ ደረጃ ላይ አገራችን ኢትዮጵያ በቶሎ እንድትደርስ እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ማሰብና መጣጣር ይገባናል። ድካማችንና ትጋታችንም በተለየ ለዚሁ ዐሳብ ብቻ እንዲሆን ያስፈልጋል።
“የከበደ ሚካኤል አስርቱ ትእዛዛት” ያልናቸው እንግዲህ እነዚህ ናቸው። እያንዳንዳቸውን ወስደን እንመርምር፣ እንተንትን ብለን ብንነሳ የምንደርስበትን አስገራሚ ማጠቃለያ ከወዲሁ ማሰብ ይቻላል። በተለይም ከጊዜ አኳያ ከተመለከትናቸው፤ ከዘመን መንፈስ አንፃር ከመረመርናቸው መደምደሚያችን ምን እንደሚሆን ካሰብን የ”ዘንድሮ”ና “ድሮ”ን ልዩነትና አንድነት ከመረዳታችንም በላይ ደራሲው ምን ያህል ወደ ፊት ቀድመው ሁሉ ማየት (መስማትም ብንል አንወቀስም) እንደቻሉ ሳንረዳና ሳናደንቅ ማለፍ አይቻለንም።
ብዙ ጊዜ ግጥሞቻቸው ብቻ እየተጠቀሱላቸው የምናውቃቸው ደራሲ ከበደ ከግጥሞቻቸው ባለፈም እንዲህ ዓይነት ለአገር ግንባታ (Nation building) ተግባር የሚውሉ፤ ትውልድን የሚቀርፁና የማህበረሰቡን እሴት የሚያጎለብቱ፣ ከምድራዊው ደስታ ባለፈ የመንፈሳዊ ሕይወትንም አስፈላጊነት የሚያስተምሩ፤ ከሁሉም በላይ አንድነትን የሚያፀኑ ሥራዎችን የሰሩ መሆናቸውንና በሥራዎቻቸውም በዚህ ደረጃ ላገርና ሕዝባቸው ባለውለታ መሆናቸውን ብዙዎቻችን የተረዳን አይመስልም።
ባጠቃላይ፣ ምናልባት ነገሩ፤
በልቶ ለሚከሳ
ተመክሮ ለሚረሳ፤
ለዚህ ምግብ
ለዚህም ምክር ንሳ።
እንዳይሆንና መካሪ እንዳናጣ እንጂ ከበደ “. . . ባሁኑ . . .” ጊዜ እንዳሉት ሁሉ “የበለጠ …”ን ጨምረንበት “የበለጠ ባሁኑ ጊዜ . . .” እንደዚህ ዓይነት፣ የከበደ ሚካኤልን ዓይነት ምክሮች፣ ትእዛዛት፣ አስተያየቶች፣ ተግሳፃት ወዘተ ያስፈልጉናል የሚል ሀሳብ ብናነሳ ብዙዎች “ከጎናችን እንደሚቆሙ” እንደሚባለው በሃሳባችን እንደሚስማሙ መጠራጠር አይቻልም።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2013