የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ከሜክሲኮ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ ለመገንባት ላሰቡት ግንብ ገንዘብ ለማግኘት በማሰብ ‘ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ’ ሊያውጁ እንደሆነ ዋይት ሃውስ ማስታወቁን ቢቢሲ የወሬ ምንጭ አስነብቧል።
ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ቀደም በውጭ ከሚኖሩ ወታደሮቻቸው ጋር በቪዲዮ ኮንፍረንስ ለገና በዓል የ‹እንኳን አደረሳችሁ› ቆይታ ባደረጉበት ወቅት፤ ‹‹አሁንም ቢሆን በአሜሪካ ሜክሲኮ ድንበር ላይ ለሚገነባው ግንብ የጠየቁት ብር ካልተፈቀደ ተቋማቱ ዝግ ይሆናሉ›› ማለታቸውን ሮይተርስ የወሬ ምንጭ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕን ለ17 ወራት ሲያማክሩ የቆዩት ተሰናባቹ አማካሪ ጆን ኬሊይ ለኤል.ኤ ታይምስ በሰጡት ቃል፤ ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ የሚሻገሩ ስደተኞችን ለመቆጣጠር የትራምፕ አስተዳደር ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች ምክርን ተቀብሎ ነበር።
‹‹ባለሙያዎቹ ያሉት፤ ተሰናባቹ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ‹‹አዎን በአንዳንድ ቦታዎች የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚገድቡ አጥሮች ያስፈልጉናል። ቴክኖሎጂ እና በርከት ያለ የሰው ኃይል ነው የሚያ ስፈልገው።›› ብለዋል
‹‹ፕሬዚዳንቱ አሁንም ስለ ‹ኮንክሪት ግንብ› ነው የሚያወሩት። ወደፊት ግን ‹የብረት አጥር› የሚለውን ሃረግ መጠቀም ይጀምራሉ። አስተዳደሩ የኮንክሪት ‹ግንብ ሃሳብ›ን ውድቅ ካደረገው ወራት ተቆጥ ረዋል›› በማለት አስረግጠው ተናግረዋል።
የወሬ ምንጩ በዘገባው እንዳስታወሰው፤ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደረገ ባቸው የፖለቲካ ጫና በመሸነፋቸው በሀገሪቱ ታሪክ ረጅም የሆነውን የመንግ ሥት ተቋማት በከፊል መዘጋት እንዲያበቃ የሚያስችል ስምምነት ፈርመዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ የፈረሙት ሰነድ የተዘጉ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ለሶስት ሳምንታት ከፌዴራል መንግሥት በጀት
እንዲያገኙ የሚያስችል ስምምነት ነው፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ፤ የፕሬዚዳንቱን ይሁንታ ያገኘው ውል ፕሬዚዳንቱ በአሜሪካና በሜክሲኮ መሃል ለመገንባት ላሰቡት ግንብ የሚውል ማንኛውንም አይነት ገንዘብ አያጠቃልልም፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከዚህ ቀደም በአሜሪካና በሜክሲኮ መሃል ግንብ ለማስገንባት የሚውል የ5 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር የበጀት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ነገር ግን አብላጫ መቀመጫ ያላቸው ዲሞክራቶች የፕሬዚዳንቱን ጥያቄ ውድቅ አድርገውት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ፕሬዚዳንቱ፣ የበጀት ጥቄያቸው ውድቅ መሆኑን ተከትሎ ነበር ጥያቄያቸው ተቀባይነት እስኪያገኝ ድረስ ‹‹ማንኛውንም አይነት የበጀት ውሳኔ አልቀበልም›› ሲሉ የቆዩት፡፡
በወቅቱም በትዊተር ገፃቸው በአሜሪካና በሜክሲኮ መሃል ግንብ የመገንባቱን እቅድ በፍፁም እንደማይተውት እና ነገር ግን እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት በተቋማቱ መዘጋት የተጎዱ ሰዎችን ከችግር ለማውጣት መሆኑን አስፍረዋል፡፡
በአሜሪካ ዜጎች ላይ የተደቀኑ የጤና እና የደህንነት ስጋቶችን በመደበኛ ሕጎች መግታት ሳይቻል ሲቀር ፕሬዚዳንቱ ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ ወይም ‘ናሽናል ኢሜርጀንሲ’ የማወጅ ስልጣን አላቸው። የድንበር አጥሩ ጉዳይ ትራምፕ እ.ኤ.አ በ2016 የምርጫ ዘመቻ ወቅት ሊፈጽሟቸው ቃል ከገቧቸው ዋነኛ ጉዳዮች መካከል መሆኑ ይታወሳል፡፡
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ እንዳሉት፤ ፕሬዚዳንቱ በሚያውጁት ብሔራዊ አደጋ ጊዜ አዋጅ ህጋዊ ተግዳሮት እንደሚገጥማቸው ይናገራሉ፡፡
ልክ እንደ ምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ሁሉ የዴሞክራክቲክ መሪ የሆኑት ቹክ ሹመር በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ፕሬዚዳንቱ እየሄዱት ያለው አካሄድ እጅግ የተሳሳተ እና ፓርቲያቸውም እንደሚያወግዘው ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሰረት የአሜሪካ ጦር በጀትን ለግንቡ መስሪያ ሊጠቀሙት እንደሚችሉ የዋይት ሃውስ መግለጫ አስታውቋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህን የሚወስኑት ከዴሞክራቶች ፍላጎት እና ውሳኔ በተጻረረ መልኩ ነው።
በርካታ ዴሞክራቶች ትራምፕ ‹‹ስልጣንን ያለ አግባብ እየተጠቀሙ እና አገሪቱን ህግ አልባ እያደረጓት ነው፡፡›› ሲሉ አምርረው እየወቀሷቸው ነው።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ቸው ወቅት ግንቡን መገንባት ዋነኛ እቅዳቸው እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ሲንቀሳቅሱ ነበር። ይሁን እንጂ እስካሁን ግንቡን የሚገነቡበት በጀት ማግኘት ቀላል አልሆነላቸውም።
ኮንግረሱ፣ ትራምፕ ለግንቡ ግንባታ የጠየቁትን ገንዘብ የሚከለክል ረቂቅ አዋጅ አሳልፏል። ይሁን እንጂ ይህ ረቂቅ አዋጅ ሕግ ሆኖ የሚጸድቀው የፕሬዚዳንቱ ፊርማ ሲኖርበት ብቻ ነው።
የዋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክረተሪ ሳራ ሳንድረስ በበኩላቸው፤ ‹‹‘ፕሬዚዳንቱ አሁንም ቢሆን ግንቡን ለመገንባት ቃላቸውን እየጠበቁ ነው፤ አዋሳኝ ድንበሩ ይጠበቃል፡፡ ትልቋ ሀገራችን ደህንነቷ የተጠበቀ ይሆናል›› ማለታቸውን አስታውቀዋል።
ሳራ ሳንድረስ አክለውም፤ ‹‹ፕሬዚዳንቱ በድንበሩ አማካኝነት የሚከሰተውን ብሄራዊ የደህንነት ስጋት እና ሰብአዊ ቀውስ ለማስቆም የተለያዩ እርምጃዎችን ይወስዳሉ፤ ከእነዚህም መካከል ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ይገኝበታል፡፡›› ሲሉ ተደምጠዋል።
ኮንግረሱ ትናንት ለድንበር ደህንነት ያጸደቀው ገንዘብ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ትራምፕ ለግንቡ ግንባታ 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ጠይቀዋል።
በአሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር ላይ ይገነባል ተብሎ የነበረው የኮንክሪት ግንብ መነጋገሪያ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ እንዳሉት፤ ፕሬዚዳንቱ በሚያውጁት ብሔ ራዊ አደጋ ጊዜ አዋጅ ህጋዊ ተግዳሮት ይገጥማቸዋል፡፡
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤን ጨምሮ የዴ ሞክራቲክ መሪ የሆኑት ቹክ ሹመር በጋራ በሰጡት መግለጫ ፕሬዚዳንቱ እየሄዱበት ያለው መንገድ እጅግ የተሳሳተ እና ፓርቲያቸውም እንደሚያወግዘው ተናግረዋል፡፡
እንደ በርካታ ዴሞክራቶች ፕሬዚዳንት ትራምፕ ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ አወጁ ማለት ፕሬዚዳንቱ ‹‹ስልጣንን ያለ አግባብ እየተጠቀሙ ነው፡፡ በተጨማሪም ድርጊቱ ህግን የጣሰ ነው፡፡›› ሲሉ እየወቀሷቸው ነው።
አክለውም እንደገለፁት፤ ፕሬዚዳንቱ በጉዳዩ ዙሪያ ሜክሲኮዊያንን ማሳመን ይሳናቸዋል፤ አሜሪካዊያንም ቢሆን አዋጭ እና ጠቃሚ ላልሆነው እንዲሁም የሚከፍሉት ግብር እጅግ ውድ ለሆነ ግንብ እንዲውል አይፈልጉም፡፡ ስለዚህም ፕሬዚዳንቱ እንዲህ ያለውን ረብ የሌለውን ጉዳይ ይዘው ወደ ሴኔቱ መሄዳቸውን ቢያቆሙ ይመረጣል፡፡
አሜሪካ ከላቲኖች ጋር ያላት ብቸኛ የየብስ ድንበር ከሜክሲኮ ጋር ነው። 2 ሺህ ማይል ወይም 3 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር ከሚሆነው ወሰን ትራምፕ ቢያንስ ግማሹን ያጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል። 8 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር ከሚረዝመው የቻይና ግንብ ቀጥሎ ከዓለም በርዝማኔው ሁለተኛ ይሆናል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ‹‹ግዙፍ ግንብ እገነባለሁ፤ ማንም ሰው ከእኔ የተሻለ ግንብ መገንባት አይችልም፤ እመኑኝ። ከሜክሲኮ በሚያዋስነው ደቡባዊው ድንበር ላይ እጅግ ግዙፍ የሆነ ግንብ፤ በጣም አነስተኛ በሆነ ወጪ እገነባለሁ። የግንቡን ግንባታ ወጪ ሜክሲኮ እንድትሸፍን አደርጋለሁ።›› ያሉት ከሶስት ዓመት ገደማ በፊት የምርጫ ቅስቀሳቸውን ባስጀመሩበት ጊዜ እንደነበር ይታወሳል።
ትራምፕ ‹‹አሜሪካ ትቅደም›› በሚለው ፖሊሲያቸው መሰረት ‹‹ሜክሲኮን አስ ከፍላለሁ›› ቢሉም ሜክሲኮ ምንም እንደማትከፍል ማስታወቋ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2011
አብርሃም ተወልደ