ከሽሮ ሜዳ ቁልቁል ወደ ስድስት ኪሎ እየወረድኩኝ ነው። ከቀድሞ ተፈሪ መኮንን ከአሁኑ እንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት እልፍ ብሎ በስተቀኝ በኩል አስፋልቱ ዳር ጫማ የሚጠርጉ ሁለት ጎልማሶች በሥራ ተጠምደዋል። የሥራ ክቡርን በተግባር ያስመሰከሩ ታታሪዎችን አይቶ ማለፉ ስለከበደኝ አንዳቸው ጋር ቁጭ ብዬ ጫማዬን ማስጠረግ ፈለግሁ። ትልልቅ ሰዎች ጫማዬን እንዲጠርጉልኝ እንዴት እግሬን እሰጣቸዋለሁ በሚል ከራሴ ጋር ሞገትኩኝ። ግን ደግሞ ለእነርሱ ሥራ ነው። ሥራን አክብሮ የሚሰራን ሰው ማበረታታት ያስፈልጋል። ከሁለቱ በእድሜ ጠና ያሉናቸው ብዬ ወደአሰብኳቸው ሰው ጠጋ ብዬ ወረፋ ያዝኩኝ።
ሰውየው እንደ እድሜያቸው አይደሉም። ሲናገሩም ሲሰሩም ቅልጥፍ ያሉ ናቸው። ተራዬ ደረሰና ጫማዬን እያስጠረግሁ አንዳንድ ጥያቄዎችን አቀርብላቸው ጀመር። ከልጅነታቸው ጀምረው ከገጠር እስከ ከተማ በተለያዩ ሥራዎች ላይ በመሰማራት ኑሯቸውን ለማሸነፍ መድከማቸውን ነገሩኝ። ከሰሯቸው ሥራዎች ውስጥ ግብርና፣ ወጥ ቤት፣ እንጨት ቤት፣ ዲኮር፣ ሌስትሮ የመሳሰሉትን ጠቃቀሱልኝ። ችግርን በሥራ እንጂ በሌላ መንገድ ማለፍ የማይፈልጉት ጎልማሳ በዚህ እድሜያቸው ሌስትሮ እየሰሩ ቤተሰባቸውን በማስተዳደር ላይ እንደሚገኙ ገለጹልኝ። የጎልማሳው የሥራ ትጋትና የመንፈስ ጥንካሬ የሚያነቃቃ ሆኖ ሳገኘው የዚህ አምድ እንግዳ እንዲሆኑኝ አስፈቅጃቸው ወደ ወጋችን ገባን።
አለማየሁ ቦጋለ ይባላሉ። የሃምሳ ስድስት ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ናቸው። የተወለዱት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ ከተማ 01 ቀበሌ ነው። በልጅነታቸው ከሰፈር ልጆች ጋር እየተጫወቱ ማደጋቸውን ያስታውሳሉ። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በአካባቢያቸው በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ገብተው መማር ይጀምራሉ። ልክ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ገጠር ይኖሩ የነበሩት የአባታቸው አባት በቅሎ ላይ ተቀምጠው እርሳቸው የሚማሩበት ትምህርት ቤት ድረስ ይመጣሉ።
የያኔው ብላቴና የአሁኑ ጎልማሳ አቶ ዓለማየሁ አያታቸውን ሲያገኙ እጅግ ደስ ይላቸዋል። በዚያ የልጅነት እድሜ በቅሎ ላይ መቀመጥ ብርቅ ነገር ስለሆነባቸው ከኋላ እንዲያስቀምጧቸው አያታቸውን ይጠይቋቸዋል። ወትሮም ብላቴናውን አባብሎ ወደ ገጠር የመውሰድ ፍላጎት የነበራቸው አያት ሳያቅማሙ በቅሏቸው ላይ ያፈናጥጧቸዋል። ከዚያም እያጫወቱ ከወሊሶ ርቃ ወደ ምትገኘው ገደባኖ ወደምትባለው የገጠር መንደር ይወስዷቸዋል።
የአቶ አለማየሁ አባትም ልጃቸው ትምህርቱን አቋርጦ ገጠር አባታቸው ዘንድ መሄዱ ባያስደስታቸውም እምቢተኛ ላለመሆን እና አባታቸውን ላለማስቀየም ሲሉ ብቻ ሳይወዱ በግድ ዝምታን ይመርጣሉ። ከወሊሶ ከተማ ወጥተው ገጠር የገቡት የያኔው ታዳጊ የአሁኑ ጎልማሳ አቶ ዓለማየሁ በአያታቸው ቤት የሚደረግላቸው እንክብካቤ የከተማውን ህይወት እንዲረሱ ያደርጋቸዋል። አቶ ዓለማየሁ አዲስ አኗኗርን መላመድ ይጀምራሉ።
ከብት እያገዱ በለመለመው መስክ መፈንጠዝ፤ በቅሎ፣ ፈረስና አህያ መጋለብ፣ ወንዝ እየሄዱ መንቦጫረቅ፣ ማረም፣ መጎልጎል፣ አውድማ ላይ ማበራየት የመሳሰሉትን ተግባራት እያከናወኑ የገጠር ህይወትን ማጣጣም ይይዛሉ። የከተማውን ህይወት እረስተው ሙሉ ለሙሉ የገጠር ሰው ይሁናሉ፤ ገጠር በሚያይዋቸው ነገሮች እየተታለሉ ፊታቸውን ወደ ከተማ መመለስ ያስጠላቸዋል። ትምህርታቸውም እንደተቋረጠ ይቀራል። ከገደባኖ ወደ ወሊሶ ወላጆቻቸው ቤት በእንግድነት ሲመጡ የገጠሩ ህይወት ፊታቸው ላይ ድቅን እያለ ተመልሰው ወደ አያታቸው ቤት መሄድ ይዳዳቸዋል እንጂ እዚያው መቅረትን አይፈልጉም።
አቶ ዓለማየሁ አስራ ስድስት ዓመት ሙሉ ኑሯቸውን በአያታቸው ቤት አደረጉ። ኋላ ግን አያታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲያልፉ ልባቸው በሐዘን ይሰበራል። ገጠር የመኖር ተስፋቸውም ይደበዝዛል። እናም አያታቸው በህይወት እያሉ የሰጧቸውን አንድ ወይፈንና አንድ ፍየል ሸጠው ከአስራ ስድስት ዓመት የገጠር ቆይታ በኋላ ወሊሶ ከተማ ወላጆቻቸው ቤት ይመለሳሉ።
ተወልደው ያደጉበትን የወሊሶ ከተማ ኑሮ እንደ አዲስ መለማመድ ይጀምራሉ። አቶ ዓለማየሁ ገጠር ሲኖሩ ሥራ እየሰሩ የመኖር ልምድ አካብተዋል። ወሊሶ ከተማ ያለሥራ መቀመጡ ብዙም ምቾት ስላልሰጣቸው ሥራ ማፈላለግ ይጀምራሉ። ከዚያም ጌጤ ወሌ በሚባል ሆቴል በወጥ በቤት ሰራተኝነት ይቀጠራሉ። ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራው ከመግባታቸው በፊትም አስፈላጊው እግዛ እየተደረገላቸው ሙያውን መለማመድ ይጀምራሉ ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራውን ለምደው የሆቴሉ ወጥ ቤት ሰራተኛ ለመሆን ይበቃሉ።
በሆቴሉ ለአስራ አንድ ዓመት ያህል ከሰሩ በኋላ ድንገት ይታመሙና ወደ ሀኪም ቤት ይሄዳሉ። የጤና ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ የሚሰሩት ሥራ ለልብ ድካማ እንዳጋለጣቸው ተነግሯቸው የወጥ ቤት ሥራቸውን እንዲያቆሙና ሌላ ሥራ እንዲሰሩ ከሀኪም የተሰጣቸውን ትእዛዝ ተቀብለው ሥራውን ያቋርጣሉ።
ነገር ግን የቤተሰብ ጥገኛ መሆን ስላልፈለጉ ሌላ የሥራ አማራጭ መፈለግ ግድ ይሆንባቸዋል። አዲስ አበባ ቢሄዱ ጤናን የማይጎዱ ቀለል ያሉ ሥራዎችን እየሰሩ መኖር እንደሚችሉ ሰዎች ይመክሯቸዋል። የዛሬ ሃያ ስደስት ዓመት አካባቢ ከወሊሶ አዲስ አበባ ለመግባት ምክንያት የሆናቸውም ይሄው ጉዳይ እንደሆነ ይናገራሉ።
አቶ ዓለማየሁ አዲስ አበባ ሲመጡ የተቀበሏቸው አክስታቸው ነበሩ። የአዲስ አበባን መውጫ መግቢያ በደንብ እስኪያውቁትና የራሳቸውን ሥራ አግኝተው መስራት እስኪጀምሩ ለተወሰነ ጊዜ አክስታቸውን በሥራ እያገዙ እንደተቀመጡ ይናገራሉ። አክስታቸው የፈረንጅ ላሞች ነበሯቸው። አቶ አለማየሁ ላሞቹን እየተንከባከቡ፣ እያለቡና ኮንትራት ለያዙ ድርጅቶች ወተት እያደረሱ ይኖሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ከዚያ ግን እራሳቸውን ችለው ለመኖር በማሰብ ሥራ ማፈላለግ ይጀምራሉ። እንዳሰቡትም ፒያሳ አርሾ አካባቢ አንድ እንጨት ቤት በቀን ሰራተኝነት ይቀጠራሉ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ኮምፖርሳቶ የማሸግ፤ ማሽኖችን እየተጠቀሙ እንጨቶቹን በሚፈለገው ቅርጽ የመቁረጥ፣ ቁምሳጥንና ቡፌን የመገጣጠም ሙያን ይማራሉ። በቀን ከሃምሳ እስከ ሰባ ብር እየተከፈላቸው ጥቂት ወራት ከሰሩ በኋላ ቤት ተከራይተው መኖር ያስባሉ።
በዚህ አጋጣሚ ልክ እንደእርሳቸው ተሯሩጣ ከምታድር አንዲት ጠንካራ ሴት ጋር ተዋውቀው ስለነበር አብረው የሚኖሩበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ። እርሳቸው እንጨት ቤት እየሰሩ እርሷም ሰው ቤት በተመላላሽ ሰራተኝነት እየሰራች ቤት ተከራይተው መኖር ይጀምራሉ። እንድ ልጅም ይወልዳሉ። ይሁንና ኑሯቸውም ከእጅ ወደ አፍ ከመሆን አልዘል ይላቸዋል። የሚያገኙት ገቢ ከቤት ኪራይና ከምግብ የሚተርፍ ሳይሆን ይቀራል።
የእንጨት ቤቱ ሥራ ከጥቅሙ ይልቅ ድካም ይበዛበት እንደነበር የሚገልጹት አቶ ዓለማየሁ ሥራ የመቀየር ፍላጎት ያድርባቸዋል። ቀደም ሲል ወሊሶ እያሉ በጤና ምክንያት ያቋረጡትን የወጥ ቤት ሥራ መስራት ያምራቸዋል። ሰዎች አፈላልገውላቸው ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ በሚገኘው ትግራይ ሆቴል ተቀጥረው መስራት ይጀምራሉ። አሁንም ኑሮ ጠብ ሳይል ይቀራል። እንዲያውም ቀደም ሲል የገጠማቸው የጤና ችግር ይቀሰቀስባቸውና ታመው ይተኛሉ። አቶ አለማየሁ ትንሽ ካገገሙ በኋላ ተመልሰው እዚያው እንጨት ቤት መስራት ይጀምራሉ። ኑሯቸውን ፈረንሳይ አካባቢ ያደረጉት ባልና ሚስት ጠዋት ሁለቱም በየአቅጣጫው ወደ ሥራ እየተሰማሩ ማታ ወደ ቤታቸው ይገባሉ። አንድ ልጃቸውን እየተንከባከቡ ህይወታቸውን በዚህ መልክ እየገፉ ለዓመታት ያሳልፋሉ።
አቶ ዓለማየሁ ከኑሮ ጋር የሚያደርጉት ትግል ሳያንሳቸው ሌላ ፈተና ይገጥማቸዋል። ባለቤታቸው ይታመሙና የአልጋ ቁራኛ ይሆናሉ። ወትሮም ሁለት ሆነው እየተሯሯጡ እንኳን ጎዶሎ የበዛበት ኑሯቸው በአንድ ሰው ጫንቃ ላይ ይወድቃል። አቶ አለማየሁ በሚያገኟት ገንዘብ ባለቤታቸውን እያስታመሙ ከኑሮ ጋር ብርቱ ትግል ውስጥ ይገባሉ። ለረጅም ጊዜ በዚህ ሁኔታ ካሳለፉ በኋላ መጨረሻ ላይ ህመሙ እየጠናባቸው የሄደው ባለቤታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ።
የአቶ አለማየሁ የችግርና የመከራ ጊዜ እየበረታ ይሄዳል። ከሁሉ በላይ የልጃቸው ነገር ያስጨነቃቸዋል። ከአንድ ዓመት የስቃይ ህይወት በኋላ የሟች ባለቤታቸው ዘመዶች ልጅቱን ወደ ክፍለ ሀገር ወስደው ማሳደግ እንደሚፈልጉ ይገልጹላቸዋል። አቶ ዓለማየሁ ከልጃቸው መለየት ባይፈልጉም ካለባቸው ችግር አንጻር ልጃቸውን ወደ እናቷ ዘመዶች ዘንድ ልከው እራሳቸውን ለማውጣት ትግላቸውን ይቀጥላሉ። ከተወሰነ ቆይታ በኋላ ሌላ ሚስት አግብተው ተመሳሳይ የኑሮ አይነትን መግፋት ይጀምራሉ።
አቶ ዓለማየሁ ሁለተኛ ሚስት አግብተው ስለወለዷቸው ልጆችና ስለቤተሰባቸው ሁኔታ ማውራት ያልፈለጉበት ምክንያት እንዳለ ይናገራሉ። ግን ስለቤተሰቦቻቸው ሲሉ ዛሬም ድረስ ዋጋ እየከፈሉ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ከሃያ ዓመት በላይ ቤት እየተከራዩ ቤተሰብ ለማስተዳዳር መጣራቸውን ያስረዳሉ። ከልጅነት እስከ እውቀት ከገጠር እስከ ከተማ እራሳቸውን ችለው ለመኖር ሲሉ በተለያዩ ሥራዎች ላይ መሰማራታቸውንም ይናገራሉ።
አቶ አለማየሁ ዛሬ በሌስትሮ ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። የሌስትሮ ሥራን የመረጡት የሰው ቅጥረኛ ሆኖ ከመስራት በቀላል የመነሻ ገንዘብ የራስን ሥራ እየሰሩ ለመኖር እድል የሚሰጥ በመሆኑ ነው። በሌስትሮ ሥራ ከተሰማሩ ከአስራ አምስት ዓመት በላይ ሆኗቸዋል። ቀደም ሲል ለእንጨት ሥራ የሚሰማሩበትን ፒያሳ ትተው ስድስት ኪሎ አካባቢ ጎዳና ላይ እየሰሩ መዋል ጀምረዋል። በሌስትሮ ሥራ ቤት ተከራይተው ቤተሰብ እያስተዳደሩበት ነው። በቀን ከመቶ እስከ መቶ ሃምሳ ብር እንደሚያገኙ ይገልጻሉ። አብዛኛውን ጊዜ እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ ጫማ በመቀባት ያሳልፋሉ፤ ከዚያ በኋላ አስኪመሻሽ ጫማዎችን ይሰፋሉ።
የሌስትሮ ሥራ በክረምትና በበጋ ተመሳሳይ ገቢ እንደሌለው የሚጠቅሱት አቶ ዓለማየሁ በተለይም በክረምት ወቅት የደንበኞቻቸው ቁጥር ስለሚቀንስ እምብዛም ጥቅም እንደማያገኙ ያስረዳሉ። አንዳንዴ ሰርግ ሲኖር ደግሞ መኪኖችን እና አዳራሾችንና ስቴጆችን የማስዋብ ሥራ ይሰራሉ። አቶ አለማየሁ የዲኮር ሙያ የተማሩት ፒያሳ ይሰሩ በነበረበት ጊዜ እንደሆነ ይገልጻሉ። አንድ በአጋጣሚ የተዋወቋት ሴት ቅዳሜና እሁድ የሰርግ መርሐ ግብር በምታዘጋጅ ጊዜ እርሳቸውን ለመርዳት ያህል እየጠራች እንደምታሰራቸው ይናገራሉ። ይህም ቢሆን ወቅታዊ ሥራ በመሆኑ አስተማማኝ ገቢ የሚገኝበት አለመሆኑን ይጠቅሳሉ።
ሰው ሰርቶ የመኖር ፍላጎት እስካለው ድረስ የፈለገውን ሥራ እየሰራ እራሱን ማኖር አያዳግተውም ይላሉ። ትልቅ ሰው ሌስትሮ ሲሰራ ማየት እምብዛም ያልተለመደ በመሆኑ አንዳንድ ሰዎች በተለይም ወጣቶች እንዴት አባቴን ጫማ አስጠርጋለሁ በሚል ትልልቅ ሰው ጋር የማስጠረግ ፍላጎት እንደሌላቸው ይናራሉ። ይልቁንም ለትልልቅ ሰዎች የሚጨነቅ ሰው ደንበኛ በመሆን ሊያግዛቸው እንጂ ሊሸሻቸው አይገባም ነበር ይላሉ። አንዳንዶች ቋሚ ደንበኛ በመሆን አንዳንዴም መክፈል ከሚገባቸው ዋጋ በላይ በመስጠት እንደሚያበረታቷቸው ይገልጻሉ። ‹‹በህይወት ዘመኔ ቢርበኝም ቢጠማኝም ለምኜ አላውቅም የሚሉት አቶ ዓለማየሁ እጅ እግር ያላቸው ጤናማ ወጣቶች ሲለምኑ መመልከትም ያናድደኛል›› ይላሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ከሆኑ ከሃያ ስድስት ዓመት በላይ ማሳለፋቸውን ይናገራሉ። ለሚኖሩበት ቀበሌ የመኖሪያ ቤት ችግር እንዳለባቸው ደጋግመው ቢያመለክቱም እስከ አሁን ጥያቄያቸው አለመመለሱን ይገልጻሉ። የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንደ እርሳቸው አይነት ህይወት ለሚመሩ ሰዎች ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ያሳስባሉ።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2013