ትግራይ የተወለደው ግደይ ኪሮስ እስከ አስረኛ ክፍል ተምሯል። ልጅነቱን ያሳለፈው በወላጆቹ እንክብካቤ ነበር። ዕድሜው ከፍ ማለት ሲጀምር ግን አዲስ ሀሳብ ብልጭ አለለት ። የአዲሱ ሀሳብ ሚስጥርም ትምህርቱን አቋርጦ ሥራ መያዝ እንዳለበት ወሰነ። ለዚህ ዕቅዱ የመጀመሪያ ምርጫው የክልሉ ማረሚያ ቤት ነበር። የማረሚያ ቤቱ አባል ሆኖ ካሰበው ለመድረስ ደግሞ ወታደራዊ ስልጠና መውሰድ ግድ አለው። ግደይ የተጣለበትን ግዴታ ለመፈጸም አልሰነፈም። ስልጠናው ከሚሰጥበት ተቋም ገብቶ በፖሊስነት ተመርቆ ወጣ።
ግደይ ፖሊስ ከሆነ በኋላ በትግራይ ክልል ማረሚያ ቤት ተቀጥሮ ማገልገል ጀመረ። ይህ አጋጣሚ ከብዙ ሰዎች ጋር አገናኘው።በስፍራው ካሉ ሰራተኞች ይልቅ ከታራሚዎች ጋር ያለው ቅርበት እየጠነከረ ሄደ።ግደይ አብዛኞቹን የሚጠጋው በምክንያት ነበር ፤ እነሱ የሚሹትን ይጠይቁታል። እሱ ያሉትን ሁሉ ካሉበት ያደርሳል። ለዚህ ውለታው ታራሚዎቹ ዝም አይሉም። የተጠየቁትን ሁሉ ቆጥረው ይከፍላሉ።ፖሊሱ ግደይ ከሁሉም ታራሚዎች ሀብቶም ለተባለው ወጣት የተለየ ስሜት አለው። ሀብቶም ህጻን ልጅ በመድፈር ወንጀል ተከሶ የማረሚያ ቤቱ ፍርደኛ ሆኖ ዓመታትን ዘልቋል።
ሁሌም ግደይና ሀብቶም ሲገናኙ በዓይን ይናበባሉ። ግደይ ዙሪያ ገባውን ቃኝቶ፣ ሰዋራ ቦታ መርጦ የእጅ ስልኩን ያውሰዋል። ሀብቶም በሞባይሉ አውርቶ ምስጋናን ከብር አቀብሎ ይለየዋል። ግደይ በየጊዜው የሚፈጽመውን ሚስጥራዊ ሥራ ሌሎች እንዳያውቁ ይጠነቀቃል።ሀብቶምም የነገውን እያሰበ የሚጠየቀውን ይፈጽማል።የፖሊሱና የታራሚው ድብቅ ግንኙነት እንደቀጠለ ነው ። ሀብቶም የመፈቻ ጊዜው ቀርቧል። ግደይም ለህክምና ከሥራ መውጣትን አስቧል።
አዲስ ህይወት…
ፖሊሱ ግደይ ጤና የነሳውን ህመም ለመታከም ሥራውን ካቆመ ሰንብቷል።ከእንጀራ ገበታው ሲርቅ አለቆቹን ፈቃድ አልጠየቀም። ለክፍሉ አላሳወቀም ። በአጭር ጊዜ እንደሚጨርስ ገምቶ ነበር። እንዳሰበው ሳይሆን ቀርቶ ቀናት አልፈዋል። ወራት ያስቆጠረው ቆይታ ግደይን በአጭር ጊዜ ወደሥራ አልመለሰውም። በማረሚያ ቤቱና በወታደራዊ ህግ መመሪያ ደግሞ የእሱ ድርጊት ክህደት ሆኖ ይቆጠራል። ይህን የሚያውቀው ግደይ ፊቱን ወደሥራ አልመለሰም።፡ የሚከተለውን ቅጣት ሲረዳ ሌላ አማራጭ አቀደ ።
አሁን የቀድሞው ፖሊስ ሥራ አጥ ሆኗል። ወጣትነቱን በዚህ ስሜት ማሳለፍ ያልፈለገው ግደይ ይጠቅሙኛል ያላቸውን ሰዎች እያፈላለገ ነው።አንድ ቀን ግን ከዚህ ፍላጎቱ የሚያደርሰው መንገድ ተሳካለት። ቀድሞ በማረሚያ ቤት ከሚያውቀው ሀብቶም ጋር ተገናኘ።ሀብቶም ከእስር ከተፈታ በኋላ ኑሮውን አዋሳ አድርጓል።የግደይን ሁኔታ እንዳወቀ በእንግድነት ተቀብሎ አስተናገደው።ጥቂት ቆይቶ ለቀጣይ ህይወቱ ይበጃል ያለውን አቅጣጫ ሊያሳየው ሞከረ። ግደይ የሀብቶምን ዕቅድ አልናቀውም። በቀረበለት ሀሳብ ላይ ደጋግሞ ሲያስብበት ቆይቶ ልቡ ተማርኳል። የሀብቶም የኑሮ ለውጥ ያለአንዳች ምክንያት እንዳልመጣ በገባው ጊዜም ለውሳኔ መስማማቱን አሳውቋል።
ሀብቶም አንዳንዴ አዲስ አበባ ብቅ እያለ ይመለሳል። አዲስ አበባ እሱና ባልንጀሮቹ ለጀመሩት ሥራ አመቺ የሚባል ከተማ ነው። ሀብቶምና የሥራ አጋሮቼ የሚላቸው ወዳጆቹ የሚንቀሳቀሱት የዘረፋ ዕቅድና መላ ዘይደው ነው። እነሀብቶም ሁሌም አዲስ አበባ በዘለቁ ጊዜ አመቺ ጊዜና ቦታ ለይተው ይዘርፋሉ። ይህን ሲያደርጉ የሚታገላቸው ካለ ጭካኔያቸው ይበረታል። ያሻቸውን ነጥቀው ህይወት ሊያጠፉ፣አካል ሊያጎድሉ ይችላሉ። ይህ አይነቱ ድርጊት ለእነሱ የዘወትር መተዳደሪያ ሆኖ ጊዜያት አስቆጥሯል።
አንዳንዴ ሀብቶምና ጓደኞቹ የንግድ ሱቆችን መኖሪያ ቤቶችንና ድርጅቶችን ይዘርፋሉ። ግደይ ከሀብቶም ጋር ብዙ አውርቷል። በአዲስ አበባ ማጅራት እየመቱ ከሚገኝ ገንዘብ ተንደላቆ መኖር እንደሚቻል አውቋል ።ሀዋሳ በቆየባቸው ጊዜያት ሀብቶምና ባልንጀሮቹ ከሄዱበት ሲመለሱ ለውጣቸውን አስተውሏል። ይህን ሲያውቅ እነሱን መሆን ተመኘ ።
ምኞቱን ለማስመር ከዘራፊዎቹ መከረ። ቡድኖቹ ከቡድናቸው ደመሩት ። እነሱን ሊመስል ተስማምቶ ከእጃቸው በላ ። አብሯቸው እየቃመ ፣ እየጠጣ ዕቅድ አወጣ ። የቀደመ ሙያውን ያወቁት ቡድኖች ለዓላማቸው መለመሉት ። ለሥራቸው እንደሚበጅ ገምተውም ከልብ አመኑበት ። ሥራውን ለይተው ስለድርሻው ሲነግሩት አልተቃወመም ። ሁሉን ሰምቶ የተባለውን ሊፈጽም ቃል ገባ ።ቡድኑን ተቀላቀለ።
ደጉ ሽማግሌ …
ግደይ አዲስ አበባ የአባቱ አጎት እንዳሉ ያውቃል። ሰውዬው ደግና ቸር ናቸው።እንግዳ ተቀባይና ዘመድ ወዳድ እንደሆኑ ሰምቷል። በርካቶች በቤታቸው አድገው ተምረዋል።ጥቂት የማይባሉ በእሳቸው መልካምነት መፍትሄ አግኝተዋል። በሰውዬው ዘንድ ባዕድነት ይሉት ስሜት የለም ።ማንም እንግዳቸው ሆኖ እንዳሻው ይስተናገዳል። የታመሙ፣የተቸገሩ፣ ሥራ ያጡ ዘመዶች በቤታቸው ይቆያሉ።፡ ሰውዬው ይህ በመሆኑ ደስተኛ ናቸው ።
ግደይ ስልካቸውን አፈላልጎ ደወለላቸው። ታሞ እንደቆየና ሥራ እንደሌለው ነገራቸው። ይህን ሲሰሙ ከልብ አዘኑ ።አዲስ አበባ መሆኑን ሲያውቁ ቤታቸው መጥቶ እንዲያርፍ ነግረው አድራሻ ጠቆሙት ።ግደይ ታክሲ ይዞ ከግቢያቸው ደረሰ።አጎት በፈገግታ ተቀብለው ‹‹ቤትህ ቤቴ ነው›› አሉት ። እንደወጉ አስተናገዱት ።የራሱን ክፍል ሰጥተው ያሻውን እንዲሆን እንዳይሳቀቅ ነገሩት።
ጡረተኛው አዛውንት በትልቁ ቤታቸው ይኖራሉ። ከጎናቸው ሚስትና ልጆች የሉም። የቤት ሰራተኛቸው ትዕግስት ታማኝና ታዛዥ ሆና ዓመታትን ዘልቃለች። እንግዳና ዘመድ በማያጣው ቤት ግደይን ስትቀበል አልተከፋችም። የእሱን ዝምድና ስታውቅ ለሽማግሌው ብቸኝነት መፍትሄ እንደሚሆን ገመተች። ልብሱን እያጠበች ምግቡን በሰዓቱ እየሰጠች አከበረችው።ግደይ እንግድነቱን ረስቶ ቤተሰብ ሆነ።ከሽማግሌው እየመከረ ከጨዋታቸው እየታደመ ቀናትን ቆጠረ።
አዲስ አበባን ከምቾት ጋር ያገኛት ወጣት ዋል አደር ሲል የአዋሳ ወዳጆቹን አሰበ። እነሱም ካሉበት ሆነው ያሰቡትን ጠየቁት ። ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት አልዘገየም ።የሚሉትን ሰምቶ ትዕዛዝ ተቀበለ።ግደይ ተኝቶ በነቃ ቁጥር ከባልንጀሮቹ የተሰጠውን መመሪያ ያስባል።እያሰበ ቤት ጓሮውን ፣ሳሎን ጓዳውን ይቃኛል። እየቃኘ የሚመጣ የሚሄደውን ዘመድ አዝማድ ይቆጥራል ። ጭር ባለ ጊዜም አለፍ ብሎ ይራመዳል። ዓይን የሚገቡ ዕቃዎችን እያየ ዋጋቸውን ይተምናል።ሰራተኛዋ ትዕግስት እንደሁልጊዜው እንግዶችን እየተቀበለች ትሸኛለች።
አንድቀን ግደይ ከባልንጀሮቹ በሰፊው መከረ።የቤቱን ይዞታ ፣የንብረቱን አይነት፣ የወዳጅ ዘመዱን ሁኔታ ዘርዝሮ ነገራቸው። ጓደኞቹ በመኖሪያው ዋጋ የሚያወጣ ዕቃ ስለመኖሩ ጠየቁት ።ወርቅ፣ላፕቶፕ ፣ካሜራ፣ሞባይል ሽጉጥና ሌላም ንብረት እንዳለ ነገራቸው።እነሀብቶም ይህን ሲያውቁ ምራቃቸውን ዋጡ፡፤ንብረቱን በእጃቸው የሚያስገቡበትን ቀን እያሰቡ ለድርጊቱ ተጣደፉ። ቀጣዩ የዘረፋ ዕቅድ የአጎቱ ቤት መሆኑን ነግረው ተልዕኮውን አሳወቁት።
በቀጠሮ ሲገናኙ። ስለዘረፋው ዕቅድ አውጥተው መምከር ያዙ። ግደይ የግቢውን አቀማመጥ፣የቤቱን በርና መስኮት አቅጣጫ በዝርዝር ነገራቸው። እነሀብቶም መግቢያ መውጫውን፣ ማምለጫ መደበቂያውን እየለዩ የሥራ ድርሻና ግዴታ ወሰዱ።ቀን ቆርጠው ሰዓት ለይተው ዝርፊያውን ሊፈጽሙ ተስማሙ።ሁሌም የሰዎች አጀብ የማያጣው ቤት ሰሞኑን በእንግዶች ተሞልቶ ቆይቷል። በቅርቡ ከወላይታ ዩኒቨርሲቲ ለእረፍት መጥቶ የነበረውን የዘመድ ልጅ ጨምሮ ሌሎችም ሲስተናገዱበት ከርመዋል።
ግደይ እንግዶቹ እንደተሸኙ ከጓደኞቹ ተገናኘ። ዝርፊያው ለሊት መሆን እንደሚገባው ሊያሳምኑት ሞከሩ። የዛን ቀን ከሩቅ የመጡ አንዲት እንግዳ መኖራቸውን ነግሮ ዕቅዱ እንደማይከወን አሳወቃቸው ።በማግስቱ ተገናኝተው የትናንቱን ጉዳይ አነሱ ።ግደይ አሁንም ዝርፊያው በዕለቱ መፈጸም እንደማይችል ምክንያት ሰጠ። ይህ በሆነ ጥቂት ቀናት በኋላ ዘራፊው ቡድን የመጨረሻውን ስብሰባ ተቀመጠ። በዕለቱ በታሰበው ቦታ ድርጊቱ እንዲፈጸም ተወስኖ በድምጽ ብልጫ ጸደቀ። ሀብቶምና ግደይን ጨምሮ አራት የቡድን አባላት የሥራ ድርሻ ወስደው የሰዓቱን መድረስ ናፈቁ።
ጥር 16 ቀን 2006 ዓም
አራቱ ሰዎች በአንድ ሆቴል ተገናኝተው ቢራ እየጠጡ ነው።አሁንም ወሬና ጨዋታቸው ስለምሽቱ ሥራ ሆኗል።ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ጀምሮ የሚመክሩበት ጉዳይ በቀላሉ አልተቋጨም ። ዘለው ስለሚገቡበት አጥር ፣ስለሚይዙት ገጀራና ጩቤ፣ ስለሚወስዱት ጥንቃቄና ሚስጥር ሁሉ ተነጋግረዋል ። በሆቴሉ እስኪመሽ መቆየት ነበረባቸው ።ምሽት ሁለት ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ ሲል፣ ግደይ የእጅ ስልኩን አውጥቶ ወደ ሰራተኛዋ ትዕግስት ደወለ። ስለአጎቱ ሲጠይቅ ከመኝታቸው አረፍ እንዳሉ ነገረችው ።ሁሉም ከነበሩበት ተነስተው ወደታሰበው ስፍራ አቀኑ። ግደይ ቤቱን ከሩቁ አሳይቶ ወደፊት ተራመደ። ከኋላው በአጭር ርቀት ተከተሉት። ምልክት እያሳያቸው የውጪን በር በራሱ ቁልፍ ከፍቶ ገባ። ወደሳሎኑ ሲዘልቅ አጎቱ ቆሎ እየበሉ ቴሌቪዥን ያዩ ነበር።
ሰላም ብሏቸው ከመቀመጡ የተለመደውን ምክር አደረሱት። አምሽቶ መግባት እንደማይበጅና ሲመሽ ዘራፊዎች ሊጎዱት እንደሚችሉ በስጋት አስጠነቀቁት። ምክራቸውን እንደሰማ ሆኖ እራሱን ወዘወዘ። ጥቂት ቆይቶ አጎት ቀን ለልብስ መግዣው የሰጡትን ብር አስታውሰው ጠየቁት። በተሰጠው ገንዘብ ሱሪና ሸሚዝ እንደገዛ ነግሮ አመሰገናቸው። ሽማግሌው ምስጋናውን ተቀብለው ወደመኝታ ሊያመሩ ተነሱ።ይህን ያስተዋለው ግደይ ሽማግሌውን በአይኑ ሸኝቶ ልቡን ደጅ ጣለ።
ምሽቱ ገፍቷል።ግደይ ከግቢ ውጭ ያሉት ሰዎች በጉጉት እንደሚጠብቁት ያውቃል።ሌሊቱ ጭር ማለት ሲጀምር በሱሪው ሥር የያዘውን ገጀራ እያመቻቸ ወደ ውጭ ወጣ። ጓደኞቹን ባሉት ቦታ ደርሶ ሲያገኛቸው አልተረጋጉም ። ከእሱ ከተለዩ በኋላ ከአንድ መደብር ስምንት ሞባይል ዘርፈው ከፖሊስ እጅ አምልጠዋል።
ወዲያው ትንፋሻቸውን ውጠው ለቀጣዩ ሥራ ተዘጋጁ።ሁሉም ግቢውን አልፈው ወደ ሳሎን ዘለቁ። ትዕግስትና አሰሪዋ በየክፍላቸው ተኝተዋል። ግደይ ከመታጠቢያ ቤቱ ገብቶ ውሀውን ከፈተ።ኩሽና አልፎም አጭር የአጥንት መከትከቻ አወጣ። ሀብቶም የሽማግሌውን በር ሲያንኳኳ ግደይ ስማቸውን እየጠራ የሻወሩ ውሀ እየፈሰሰ መሆኑን በትግርኛ ነገራቸው።
ሽማግሌው ከእንቅልፋቸው ተነሱ። ቢጃማ ለብሰው ፎጣ ደርበዋል። የተከፈተውን ውሀ ለመዝጋት አለፍ ከማለታቸው ከመጋረጃው ስር የተደበቀው ሀብቶም በያዘው ገጀራ ጭንቅላታቸው ላይ አሳረፈ።ሸማግሌው ሸርተት ብለው ግደይ እግር ስር ወደቁ ።ግደይ እንደመደገፍ ቀና አድርጎ አናታቸውን በገጀራ መታቸው።ወለሉ በትኩስ ደም ተሸፈነ። ሁለቱ የእጁን ገጀራ ተቀብለው ሰውዬው ላይ ተረባረቡ። ጡረተኛው ሽማግሌ በመታጠቢያ ቤቱ ደጃፍ ላይ በቁመናቸው ተዘረሩ ። ህይወታቸው አለፈ።
ዘራፊዎቹ በግደይ እየተመሩ የቤቱን ዙሪያገባ ቃኙት። ጥቂት ቆይተውም የሰራተኛዋን መኝታ ቤት አንኳኩ። ትዕግስት ብንን ብላ ማነው? ማነው? አለች። የሆነውን አላወቀችም።ግደይ ፈጠን ብሎ ‹‹እኔነኝ›› አላት። ተጣድፋ በሩን ከፈተች።
በሩ እንደተከፈተ እንዳትጮህ ሀብቶም አፏን በጨርቅ አፈነ።በድንጋጤ የራደችው ሴት ግደይንና የሽማግሌውን ሬሳ እያየች በለቅሶ ተማጸነች።የሰማት የለም። ሁሉም እንድትገደል ተስማሙ። ይህ ከመሆኑ በፊት ሀብቶም አስገድዶ ደፈራት። ጉዳዩን እንደጨረሰ የግድያው ትዕዛዝ ተፈጻሚ ሊሆን ግድ አለ።ሀብቶም የመጀመሪያውን ገጀራ አሳረፈባት ። ግደይ እሱን ተከትሎ ድርጊቱን ደገመ። ወደ ውስጥ ዘልቀው የእጇን ሞባይል ወሰዱ። በደም የተሸፈኑ ሬሳዎችን ተራምደውም ቤቱን መበርበር ጀመሩ። ያሰቡትን አላጡም።
ሌሊቱን የጀመሩት ፍተሻ ሲያበቃ ወርቆችና ብሮች፣ ላፕቶና ሞባይሎች፣ ሽጉጥና ካሜራ፣ አንድ መቶ አስራ ስምንት ሺህ ጥሬ ብር ከጫማና ልብሶች ጋር በሁለት ሻንጣዎች አጭቀው ሲወጡ ከሌሊቱ አስር ሰዓት ሆኖ ነበር ።
የፖሊስ ምርመራ
ሲነጋ ላፍቶ የባንክ ሰራተኞች ማህበር የደረሰው የፖሊስ ቡድን በመኖሪያ ቤቱ የተፈጸመውን ወንጀል አይቶ የሟቾችን አስከሬን አነሳ። ግደይ የጎረቤት ባለሱቅ ቀስቅሶ እንደሸኘው ደረሰበት። መረጃውን ይዞ ተጠርጣሪዎችን ማሰስ ጀመረ።ግደይና ጓደኞቹ የድርሻቸውን ይዘው ኬንያ ለመግባት እንዳልተሳካላቸው አወቀ። አዋሳና መቀሌ የቆዩት ቡድኖች ከፖሊሶች ዓይን አላመለጡም። ግደይ ማይጨው አባቱ ቤት ገብቶ ኑሮ ጀምሯል። ሌሎችም በዝርፊያ ሥራቸው ቀጥለዋል።
የፖሊስ መርማሪው ዋናሳጂን መንግሥቱ ታደሰ በመዝገብ ቁጥር 731/091 በተከፈተው ፋይል በቂ መረጃዎችን እየሰነደ ቆየ። በመጨረሻም ጉዳዩን ለዓቃቤ ህግ አሳልፎ ክስ እንዲመሰረት አደረገ።
ውሳኔ…
ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነግደይ ገብረህይወት ላይ የተከፈተውን የክስ ፋይል ሲመረምር ቆይቶ ለመጨረሻው ውሳኔ ደርሷል። ተከሳሹ ለዝርፊያ ሲል በቅንነት ያስጠጉትን አጎቱንና የቤት ሰራተኛቸውን በግፍ በመግደል ከግብረ አበሮቹ ጋር በፈጸመው ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑ ተረጋግጧል። በመሆኑም እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የሀያ ሶስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
ከችሎት በኋላ
የውሳኔው መዝገብ እንደተዘጋ አንድ ደብዳቤ ከዓቃቤህግ ለፍርድቤቱ ችሎት ደረሰ። ደብዳቤው በምስክርነት የቀረበው የሟችና ገዳይን ታዳጊ ልጅን ጉዳይ ይመለከታል። በምስክር አሰጣጥ ጊዜ ልጁ የአባቱን ስም ቀይሮ በአያቱ ስም መጠራት ጀምሯል ።ልጁ ለዚህ ያቀረበው ምክንያትም አባቱ ወላጅ እናቱን በሽጉጥ ሲገድል ማየቱንና ከዚህ በኋላም በስሙ መጠራት ያለመፈለጉን ነው።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2013