አዲስ አበባ፡-ግልፅና ወጥ የሆነ የሥነ-ህዝብ ፖሊሲ መኖሩ የህዝብ ብዛትን ለልማት ለማዋል ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የኢትዮጵያ ሥነ-ህዝብ ከሀገሪቱ ልማት ጋር ያለውን ግንኙነትና የፖሊሲን አንድምታ በተመለከተ ትናንት በሂልተን ሆቴል ከዘርፉ ምሕራን በአካሄደው ውይይት እንደተገለጸው፣ በኢትዮጵያ ህዝብና ልማት ተነጣጥለው የሚታዩ ጉዳዮች አይደሉም፡፡ ስለዚህም ህዝብን ከሀገሪቱ የልማት ፖሊሲ ጋር ቁርኝት እንዲኖረው ግልፅና ወጥ የሆነ የሥነ-ህዝብ ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡
የአካዳሚው አባል ዶክተር ሰዒድ ኑሩ እንደገለጹት፣ ግልፅና ወጥ የሆነ የሥነ-ህዝብ ፖሊሲ የህዝብ ብዛትን ለልማት ለማዋል ወሳኝ ነው፡፡ የህዝብ መብዛት እንደየሀገራት ፖሊሲዎች ሊጠቅምም ሊጎዳም ይችላል፡፡ ቻይናን እንደምሳሌነት በመጥቀስ የህዝብ ብዛት ለሀገሪቱ እድገት ከፍተኛ የሆነ ሚና ተጫውቷል፡፡
በኢትዮጵያ ህዝብን በማስተማር ለሀገሪቱ ልማት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዲኖረው ማድረግ ይቻላል ያሉት ዶክተር ሰዒድ፣ የአንድ ሀገር የህዝብ ፖሊሲ በትምህርትና በጤና ከተቃኘ ዜጎች ለሥራ ዝግጁ በመሆን ለሀገራቸው ስጋት ከመሆን ይልቅ ጠቀሜታቸው ከፍ ያለ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሥነ-ህዝብ ፖሊሲ ቢኖርም ግልፅ አይደለም፣ እንዲሁም ስጋቶችንና ትሩፋቶችን በተለየ ሁኔታ በግልፅ አቋም የያዘ አይመስልም ያሉት ዶክተር ሰዒድ ፤ ነገር ግን በሀገራችን የህዝብ ብዛት እየጨመረ ስለሆነ ግልፅ በሆነ መንገድ የፖሊስ አቅጣጫዎች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል፡፡
ከአቅጣጫዎቹ መካከል የህዝብ ብዛትን እንደ አቅም መጠቀም፣ አቅም እንዲሆን ለማድረግ ያለባቸው ዝግጅቶችን መለየት፣ የሥነ-ህዝብ ለውጥ ዕድልም ሥጋትም እንደሚያመጣ አውቆ ለትሩፋትነቱ መሥራትና በወሊድም ምጣኔው ላይ በሥጋትነት አቋም በመያዝ የህዝብ ብዛትን ለልማት ማዋል የሚሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከተቋቋመበት መጋቢት 2005 ዓ.ም ጀምሮ በፈጠራ፣ በሥነ-ጥበብ እና ምርምር እንዲጎለብት አስተዋፅኦ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ሙያዊና ሳይንሳዊ ምክረ ሃሳቦችን ለፖሊሲ አውጭዎች በማቅረብ ለኢትዮጵያ እድገት የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ ያለ ተቋም መሆኑም በውይይቱ ተወስቷል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2011
ሞገስ ፀጋዬ