‹‹አይጣልን ያቀሉታል›› ይሉት አባባል አሁን በደንብ እየገባኝ ነው። አዎ! አሁንም አይጣልባችሁ ! በነገራችሁ ሁሉ እንደ እርጎ ዘንብ ጥልቅ ከሚሉ ጉዶች ይጠብቃችሁ፣ አያገባቸው ገብተው ዕንቅልፍና ሰላም ከሚነሱ ፍጡሮች ይሰውራችሁ። ‹‹አሜን! ›› ባትሉኝም እኔ እንዲህ እቀጥላለሁ ፤ አይጣል እያድርስ ፣ እያልኩ። ከነገረኞች ፣ ከምቀኞች፣ ሴራ ትጠበቁ ዘንድ እየተመኘሁ።
ወዳጆቼ ! አጀማመሬ ነገሮችን እያነሳሁ ለመመራረቅ አይደለም። ቃላትን እየሞሸሩ የማስዋብ ፍላጎቱም የለኝ። እናንተ ግን መነሻዬን ያዙልኝ። አይጣል አያድርስ ያልኩበትን ጉዳይ። መቼም ሠው ያለ ወዳጅና ዘመድ፣ እንዲያም ሲል ያለጎረቤት አይኖርም። ይህን የማይሻ ፣ የማይፈልግ ቢኖር ደግሞ በእርግጥም ችግር አለበት እላለሁ። ለነገሩ አንዳንዱ ያለችግር አይፈጠርም። ክፉ አመልና የማይጸዳ ባህሪይው ከሌሎች በተለየ ይታወቅበታል። ‹‹አመል ያወጣል ከመሀል ይባል የለ››?
ወዳጆቼ ! አንዱን ጀምሬ ወደ አንዱ አይሁንብኝና የእነዚህ የነገረኞች ጉዳይ በእጅጉ ያሳስብኛና ያስገርመኝ ይዟል። ክፉ ጉዳይ ደግሞ ከጎረቤት አልያም ይቀርባል ከሚባል ወዳጅ ሲመጣ አይጣል ነው። አዎ! ሰላም ይነሳል፣ ዕንቅልፍ ያሳጣል። እንደጣት ቁስል ጠዋት ማታ ይጠዘጥዛል፣ ያንገበግባል፡፤
የጣት ቁስልና የመንደር ምቀኛ ፣
እየጠዘጠዘ እንቅልፍ አያስተኛ ።
ያለው ማን ነበር ? ማንም ይበለው ማን አባባሉ እውነትት አለው። እውነት ስለ መሆኑ ደግሞ እኔም፣ እናንተም፣ ሁላችንም አሳምረን ልናውቀው ግድ እያለን ነው። እንዴትና ለምን ላላችሁ ደግሞ ጉዳዩ የሁላችንም ስለመሆኑ አሳምሬ እነግራችኋለሁ።
አዎ! ጎበዝ ምቀኞች፣ ሴረኞች በጸጉራችን ልክ በዝተዋል። እንደጣት ቁስል ያለአፍታ እየጠዘጠዙ ሰላምና ዕንቅልፍ የሚነሱ። የእነሱን ለእኛ ሰጥተው ድህነትን የሚያውጁ። እኛን አስበው ሲያወጉ ሁሌም ቋንቋቸው አንድ ነው። በሀሜት ይዘለዝሉናል። በነገር ይነክሱናል። ዕቅድ አውጥተው፣ አጀንዳ ዘርግተው ይወያዩብናል። እኛን ፣ ኢትዮጵያውያኖቹን! እኛን፣ የጥቁር ህዝብ ተምሳሌቶቹን።
አዎ! የነገሬ ዳርቻ ‹‹ግልጽና ግልጽ›› ነው። ‹‹ግልጽና ግልጽ›› ማለቴ ያው ነገሩን ግልጽ ለማድረግ በማሰብ ነው። አሁን የባንላጣዎቻችን ማንነት እንደገባችሁ ልገምት፤ ርቃችሁ አትሂዱ፡፤እመት ግብጽና ወይዘሮ ሱዳን ናቸው። ‹‹እ.ህ..ህ.ህ.ህ ….›› አለ ፈረስ። ነገር በሆዱ እንደገባ ሰው። እኛ እንኳን እን አያ ፈረስ አንብከነከንም ፤ ስለነሱ እናወራለን፣ እንናገራለን።
እነዚህ አገራት በአካል ባይመጡ በድርጊት ተንኮላቸው ሁሌም አብረውን ናቸው። ለነገር ባሏቸው ጊዜ ወደጅነታቸው አይሎ ራት ምሳቸው በአንድ ገበታ ከሆነ ቆይቷል። አሂሂሂ… እስቲ ያዝልቅላቸው፣ እስከመጨረሻው እስከጥጉ……
እነዚህ አገሮች እኮ ስለኛ ካሏቸው ድካምን አያውቁም፡፤ ጠዋት ማታ እንደቡና እየተጠራሩ በሀሜት ሲቦጭቁን ይውላሉ። ደግሞ ብቻቸውን አይምሰሏችሁ። ከእነሱ ተሻልን በለጥን የሚሉ ሀብታም ተብዬ አገራት ጭምር የቡጨቃው ታዳሚዎች ናቸው።
ለቡና ሀሜታቸው ገምደል አድርገው የሚቆርሱት ዳቦ፣ ጭልጥ አድርገው የሚጠጡት ትኩስ ወተት የላብ የጉልበት ዋጋቸው አይምሰላችሁ ፣ ከእኛው ቤት ከሄደ፣ በእኛው ደጃፍ ካለፈ በረከት የተገኘ ነው። ለዛውም አይናችን እያየ ፣ውስጣችን እያወቀ በእንጉርጉሮ ከምንሸኘው አንጡራችን የ ‹‹አባይ›› ወንዝ ላይ የተቀዳ። የማንነታችን ግማድ ፣ የስማችን መነሻ ከሆነው ታላቁ የግዮን ደለል ላይ ዓይን በዓይን የተወሰደ በረከት።
አዎ ! እነዚህ ጉዶች ከራሳችን ሀብት የተገኘውን ታላቅ በረከት እየተቋደሱ ጠዋት ማታ በጋራ ያኝኩናል፣ የጎረሱትን ሳያላምጡ፣ ያላመጡትን ሳይውጡም ዓይናቸው ለሌላ ጉርሻ ይቀላምዳል።
እንዳሻቸው እየከመሩ፣ እንደፈለጉ የሚሰለቅጡት ሁሉ ከኢትዮጵያ ምድር የሄደ ፣ ከአባይ አካል የተከፈለ መሆኑን አሳምረው ያውቁታል። ለሺህ ዘመናት ያለአንዳች ጠያቂ ከግዮን ያጋቱ ጡቶች የመገመጉት ንጹህ ወተት መቼም አጥግቧቸው አያውቅም። የጨለጡት በቁንጣን እያስጨነቃቸው፣ የጠጡት እያስመለሳቸው፣ በቃኝ ይሉትን ሞክረውት አያውቁም።
ደግሞስ ለማን ብለው ይጨነቁ፣ ለማንስ ብለው የእጃቸውን ሲሣይ ይጣሉ፣ ምን ዕዳ ኖሯቸው ስለርሀብ ጥማት ያስቡ፣ እኛም አልነበርን አሳልፈን የሰጠናቸው እኛም አልነበር የበይ ተመልካች የሆን ነው። ዛሬን ተነስተው ጥግብ፣ ጥግብግብ ቢሉብን ፍርድ የላቸውም።
እኛ እኮ! በጋ ከክረምት ከሚፈሱ ወንዞቻችን አዋጥተን፣ ለሙን፣ ጥቁሩን ቀዩን ፣ አፈር ከደለል ከምረን፣ ከአባይ ወንዝ አክለን ስንልክ ፣ ስናዳብራቸው ኖረናል። ተዝቆ የማያልቅ ሀብታችንን በሚያጓጉዝ ወንዛችን እነሱን እያወፈርን፣ እያቀለምን፣ እያሰባን ዘመናትን አሻግረናል። እንዲህ ስናደርግ እኛ እየተራብን ፣እየተቸገርን፣ እየሞትን ነው።
ወዳጆቼ! ዛሬ ባለንበት ቆመን ስማቸውን እያነሳን መውቀሱ ፣ በድርጊታቸው ማዘን መገረሙ አይበጀንም። ትናንት እኮ ትርጉሙ ሳይገባን በሙዚቃ ስልታቸው እየተወዘወዝን አዚመናል ። አይ እኛ በጣም እንገርማለን ‹ምናአልባትም እኮ የእነሱ ዘፈን ትኩረት አባይ ሊሆን ይችላል። ሳይገባንና ሳንረዳ በራሳችን ወንዝ ስለነሱ ዘፍነናል። የሀገራቸውን ተፈጥሮና ውበት እያዳነቅን ባላቸው በረከት ምራቃችንን ውጠናል።
እነሱ እኮ ! ዛሬም ሆነ ጥንት ከቱርፋቱ ተጋርተው፣ ከእሸት ከማሩ ቦጥቡጠው ነው። እነሱ እኮ ! ከሞቀው ከተማቸው ቀን ከሌት በሚደምቅ ብርሃን ታጅበው ነው። እነሱ እኮ! ከእኛው ደጃፍ ከሚደርስ በረከት በአሳው፣ በአትክልትና ፍራፍሬው ዳብረው ነው። በነዳጅ በማዕድኑ ከብረው ነው።
እኛ ደግሞ የእጃችን እያረረብን የእነሱን ሀብት ባሻገር ስናይና እንደተአምር ስንቆጥር ኖረናል። እያለን እንደሌለን ታይተን በድህነት ተፈርጀናል። እንግዳ ተቀባይ ህዝቦች መባላችን ቀርቶ በእነሱ ቀዬና መንደር የሰው አገር ሰዎች፣ ተብለን ስደተኞች ሆነናል።
የዛኔ በእነሱ ሙዚቃ እየተወዘወዝን ስናደምቃቸው፣ በአደባባይ እጃቸውን ይዘን ከፍ ስንደርጋቸው በሚጢጢ ደስታ ብዙ በረከት እንደወሰዱብን ያውቁት ነበር። እኛ ግን ፈገግታቸውን ሰጥተው የእጃችንን ሲደፉብን እንኳን ተንኮላቸው አልገባንም። ሰው አማኝ ልባችን ወዳጅነትን እያሰበ በፍቅር ሲያከብር፣ ሲያነግሳቸው ኖሯል። ውይ! ውይ! ስናናድድ።
ይህ እውነት ለእኛነታችን ታሪክ ‹‹እሰይ›› የሚያሰኝ ምዕራፍ ሆኖ አያውቅም። በዕንቅልፍ ያሳለፍነው ጊዜ ፣ ባለማስተዋል ያባከነው ዘመን፣ ዛሬ ላይ ዋጋ ያስከፍለን ይዟል። ለዚህ አባባሌ ዝምታችን እንደ ወርቅ ሊቆጠር ይገባል ካላችሁኝም ፤ እኔ ደግሞ ዝምታ ወርቅ ሊሆን የሚችለው ተረት ላይ ብቻ ሲሆን ነው። እላችኋለሁ። ዋሸሁ እንዴ?
ዛሬ ግብጽና ሱዳን በአንድ ማዕድ መቅረባቸው ያላአንዳች ምክንያት አይደለም። ከእኛ የሚላክላቸው ስንቅ አንድ ቀን ባዶ አገልግል እንዳይሆን በመስጋታቸው ነው። እስከዛሬ ሀገራችን እየፈተፈተች በምትልክላቸው ወዝ ጠገብ እንጀራ ትውልዳቸውን ሲያጠግቡ፣ ለወደፊቱም ጥሪት ሲቋጥሩ ኖረዋል።
በእኛ ቤት ዛሬም የእናቶቻችን ትከሻ እንጨት ከመሸከም አላረፈም። አሁንም ከኩራዝ ጭስና ከሳር ጎጆ ያልወጣው አርሶ አደር ስለነገው ብርሀን ተስፋ ኖሮት አያውቅም። በግብጽና ሱዳን መንደሮች ደግሞ ምንአልባትም ይህ አይነቱ እውነት አይታወቅ ይሆናል። ጨለማ ይሉት ታሪክ ኩራዝ ይባል ቁስ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተበረከተ ይመስል።
አሁን ዛሬ ኢትዮጵያ ካለችበት ተነስታለች። እስከዛሬ በብልጦች የተሞኘችበት፣ የእጇን ፍሬ አሳልፋ የሰጠችበት ጊዜ አክትሟል። ይህ ሲገባት ደግሞ የራሷን አባይ ከስደት ልትመልስ፣ ለም አፈሯን፣ አንጡራ ሀብቷን ልትታደግ ጉዞ ጀምራለች። እና ታዲያ ምን ይደንቃል፤ አገርን መታደግ፣ ከተኙበት ጥልቅ ህልም መንቃት ምን ክፋት አለው። ምንም።
ኢትዮጵያ እኮ እስካሁን ጥለዋት ሲበሉ የነበሩ ጎረቤቶችዋን አብረን ተካፍለን እንብላ ነው ያለችው። የማር በረከት፣ የወተት ተፋሰስ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት የሚፈስላቸው እያየች በሯን አልዘጋችም፣ ፊቷን አላዞረችም። የመጀመሪያውን ዶማ አንስታ ቁፋሮውን አንድ ስትል ጀምሮ ዓላማዋን ተናግራለች ‹‹ ኑ ፣ አብረን እንብላ ፣ በአንድ እንደግ፣ እንመንደግ ብላለች። ዓላማዋን ያወቁ ስሜቷን የተረዱ በርካቶች የወደፊት ዕድገቷ ቢታያቸው ቁርጠኝነቷን በበጎ አላዩትም። ብድርና እርዳታቸውን አሳበው ጆሮ ነፈጓት። በሚሰጧት ዳረጎት እያስፈራሩም ሊያሸማቅቋት፣ ሞከሩ።
እሷ ግን ‹‹ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ›› ከዓላማዋ ሳትናጠብ፣ ከጅምሯ ሳትደናቀፍ በመንገዷ ቀጠለች። ታላቁን የህዳሴ ግድብ በህዝቦቿ ላብና ወዝ አንጻም ለፍሬ ልታበቃ ታገለች፡፤ተሳካላትም፡፤እሰይ ኢትዮጵያ እንኳን ደስ አለሽ። እሰይ!!
አዎ ! እውነታው ለገባውና በቅንነት ለሚያስብ፣ ይህ ሀሳብ ድንቅ ነበር። ያለንን ተካፍለን እንብላ፣ ከሰራሁት በረከት ላቃምሳችሁ በእጄ ካለው ሀብት ላጋራችሁ፣ የምትል የዋህ አገር ስትገኝም ቅድሚያ የከበረ ምስጋና በተገባት ነበር። ድንቄም ምስጋና! ነገሩ ወዲህ ሆነና ጥርስ ይፋጭባት፣ ከንፈር ይነከስባት፣ ጉባኤ ይዋልባት ከጀመረ ሰነባበተ።
እናንተዬ ! አሁን ከግዮን ያጋቱ ጡቶች ስር የበቀሉት ጥርሶች ስለት ጨምረዋል። እነዚህ ጥርሶች በላይና በታች ብቅ ብቅ እያሉ ናቸው። አንዳቸው በግብጽ ሌላቸው ደግሞ በሱዳን። ሁለቱም ቢሆኑ ጥርሶቹን ለፈገግታ አይሹዋቸውም። ጧት ማታ እየሞረዱ፣ ሌት ተቀን እየሳሉ ሾተል ያበጁላቸው ይዘዋል። ሾተሉ ደግሞ ሁሌም የሚነጣጥረው ስጋት ሆናብናለች ወደሚሏት ሀገራችን ኢትዮጵያ ሆኗል።
እኛስ ወዳጆቼ! ምን እየጠበቅን ነው? ዛሬም ምርጫችን በሱዳን ዘፈኖች መደመም ነው እንዴ ? አሁንም ህልማችን የአረብ አገር ስደት፣ ነው እንዴ? የሰው አገር ኑሮና የሌላው ዓለም ህይወት ይሆን የሚያጓጓን።
ዘንድሮማ እናየው አንሰማው የለም። የሱዳንና ግብጽ በእኛ ላይ ማበር ሲገርመን እነ አውሮፓ ህብረትና አሜሪካም ይነሱብን ጀምረዋል። ‹‹እ.ከ.ከ.ከ.ከ……›› አለች ዶሮ። ኢትዮጵያችን እኮ ጥርስ የገባች አገር ሆነች። ከዚህና ከዚያ እየጎነተሉ ከፊትና ኋላ መንገድ እየዘጉ ግራ የሚያጋቧት ጠላቶች በረከቱ።
እቴዋ አሜሪካማ በእኛ ጉዳይ ረጅም እጇን መስደድ ከጀመረች ሰነበተች። ‹‹ነገረኛ›› አንድ ሰሞን ዶናልድ ትራምፕ ይሉት አውቆ አበድ ልጇ የራሱን መጨረሻ ሳያውቅ አባይ አይገደብም ፣እንዲያውም ግድቡ ይፈርሳል፣ ይደረመሳል ሲለን ነበር፤ ‹‹አልሰሜን ግባ በሉት›› አሉ። ግድቡ ከተገነባ እኮ ቆየ። ለዛውም በራሳችን እጅ፣ በራሳችን አዕምሮና በእኛው ጥሪት።
መናገር ካለብን ደግሞ እናስታውሳቸው። ድሀዋ እናት ከመቀነቷ፣ የቀን ሰራተኛው ከዕለት ጉርሱ፣ አርሶ አደሩ፣ ሰራተኛው፣ ሊስትሮና ተማሪው ሁሉ ካለው እየሰጠ ፣ ከገቢው እያካፈለ ለግድባችን ዋጋ ከፍሏል። እነሱ ግን ይህ አልዋጥ፣ አልመች ቢላቸው መንገዳቸውን ቀየሩ። አገር ለማፍረስ ህዝብ ለመበጥበጥ ሌት ተቀን ባዘኑ። ‹‹ሞኝህን ፈልግ›› አለ ያገሬ ሰው። አገር የጭቃ አሻንጉሊት ይመስል ዝም ብሎ ይፈርሳል እንዴ ? በእነሱ ምኞትና ፍላጎት ብቻ ታላቂቱ አገር እናት ኢትዮጵያ ፈጽሞ አትፈርስም። በጭራሽ !
ዘመዶቼ ! የሰሞኑ ጉዳይ ደግሞ መልኩን ቀይሮ ብቅ ብሏል። እንደ አውሮፓ ህብረት ያሉ ድርጅቶች ምርጫውን አስመልከቶ በሚነዙት ወሬ ጣልቃ ገብነታቸውን ለማሳየት እየሞከሩ ነው። በየቀኑ እኛ ‹‹እናውቅላችኋለን፣ ይሉን ይዘዋል። ባገኙት አጋጣሚም በዓለም ማህበረሰብ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ጨፈቃቸውን አንስተዋል። ድንቄም ተጽዕኖ። ኢትዮጵያ ጥንትም ሆነ ዛሬ የማንንም ጣልቃገብነት አትሻም። ኢትዮጵያ እንደ አገር የራሷ ማሰቢያ አዕምሮ አላት፣ ታሪክና ማንነቷም ከሌሎች ጠባቂነትና ጥገኝነት የራቀ ነው። ስለጥቅም ስትል በክብሯ ፈጽሞ አትደራደርም።
አዎ! አሁን ሁላችንም ከገደሉ ጫፍ ቆመናል፤ አንድነታችን ከጠነከረ፣ አብሮነታችን ከተጋመደ የመጣብንን ፈተና በድል እንመክታለን። መግባባት ካቀተን፣ ጥቅም ካሸነፈንና ለጠብና ብጥብጥ ጊዜ ከሰጠን ደግሞ ጠላቶቻችን ወደ ገደሉ ይጨምሩናል። ‹‹አዲዮስ››!
ወዳጆቼ! ወደ ገደል ከገባን በኋላ ለመውጣት መንፈራገጡ ዋጋ የለውም። ዛሬ በመሀላችን የገባውን አዲስ ዓመል አላስወግድ ካልን ውጤቱ የከፋ ይሆናል። በእርግጥ አሁን ላይ አንዳንዶች ጠብ በደላላ ብዋል። ‹‹ሞኝ›› አለ ጋሽስብሀት አዎ! ስራቸው ሞኝነት ነው። በሀገር ላይ መነሳት፣ በወገን ህይወት መጨከን። ትርፍ የለውም። አያስከብር አያስሞግስ፣ምንም።
ወደ ቀደመው ጉዳዬ ተመለስኩ። ወደ ህዳሴው ግድባችን። ወደ ግብጽና ሱዳን አዲስ ፍቅር። ወደ አሜሪካና አውሮፓ ህብረት ጣልቃገብነት። ዛሬ እኛ በአንድ ቃል እንዲህ ልንላቸው ግድ ነው። ‹‹እናንት ከንቱዎች በከንቱ አትድከሙ ፣ ኢትዮጵያ ምንጊዜም ኢትዮጵያ ናት። ማንነቷን አትረሳም፣ መነሻዋን አትዘነጋም። እናም ከዚች ድንቅ አገር ወዲያ ራቁ፣ እጃችሁንም አንሱ።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2013