ጤናማ ወሲብ ለሰው አስፈላጊ እና ዘርን ለመተካት የሚጠቅም እንዲሁም ሥጋዊ እርካታን የሚያስገኝ የተፈጠሮ ስጦታ ነው። ጤናማ ወሲብ የሚባለው በሁለት ሰዎች የጋራ ፍላጎት ላይ የተመሠረተና ለ2ቱም የተላላፊ በሽታዎች የማያስከትል እንዲሁም ሁለቱም ወሲብ የማድረግ ፍላጎታቸው የተነሳሳ ለተፈለገው ጊዜ ያህል የሚቆይና በእርካታ የሚጠናቀቅ ሲሆን ነው።በሁለቱም ፆታዎች ላይ የሚከሰቱ የለያዩ አይነት ከወሲብ ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉ። በዚህ ፅሁፍ በወንዶች ላይ የሚከሰቱ ወሲብ ተያያዥ ችግሮችን እናያለን።
ወሲብና ተያያዥ ችግሮች
– ብልት መቆም ጋር የተያያዙ
– የስፐርም ፈሳሽ መፍሰስ/መጨረስ ጋር የተያያዙ
– የወሲብ ፍላጎት መቀነስ/ማጣት
እነዚህም ችግሮች እድሜን ተከትለው የሚጨምሩ ሲሆን ብዙ ወንዶች ከ40 ዓመት ዕድሜ በኋላ የሆነ ዓይነት ወሲብ ተያያዥ ችግር እንደገጠማቸው ይናገራሉ።
1. የወሲብ ፍላጎት መቀነስ/ማጣት – 5-15% የሚገመቱ ወንዶች ላይ የሚታይ ሲሆን አንዳንዴ በሌሎች ወሲብ ነክ ችግሮች ምክንያት ይከሰታል ።ሌሎች እንደ ምከንያት የሚጠቀሱት የሚከተሉት ናቸው
– መድሀኒቶች (የድብርት, ህመም ማስታገሻ, ዕፅ የመሣሠሉት)
– አልኮል
– ድብርት, ከፍተኛ ድካም
– የፍቅር ግንኙነት ችግሮች
– የቴስቴስትሮን ሆርሞን እጥረት
– ሌሎች የጤና ችግሮች መኖር
አብዛኞቹ ከላይ የጠቀስናቸው ችግሮች መወገድ/መታከም የሚችሉ ናቸዉ።
2. ብልት መቆም ጋር የተያያዙ – በብዛት ወንዶች ላይ የሚከሰተው ነው (16%)
እነዚህም ብልት አልቆም/በደንብ አልቆም ማለት ወይም እስከመጨረሻ ቆሞ አለመቆየት ናቸው።
መንስኤዎች
– ዕድሜ መጨመር
– ከፍተኛ ውፍረት
– ሲጋራ, መድሀኒቶች
– ሌሎች ህመሞች (ስኳር, የልብ, ከፍተኛ ደም ግፊት, የደም ስብ/ኮሌስትሮል መብዛት) የአካል እንቅስቃሴ ማድረግና ክብደት ማስተካከል ችግሩን ሲያሻሽል ታይቷል።
3. የስፐርም ፈሳሽ መፍሰስ/መጨረስ ጋር የተያያዙ
3.1. የስፐርም ቶሎ መፍሰስ (Premature Ejaculation)
ወሲብ ሳይጀመር ወይም ተጀምሮ ከ1 ደቂቃ በታች በሆነ ጊዜ ውስጥ የወንድ ፈሳሽ ሲፈስ ይህ ችግር አለ ይባላል።
ይህ ሁኔታ በወንዶቹ ላይ መጨነቅ መረበሽና ከሴት ጋር ግንኘነት እንዲተው የሚያደርጋቸው ቢሆንም ጥቂቶች ብቻ የህክምና ዕርዳታ ይጠይቃሉ። በቀጥታ ይህ ነው ተብሎ የተጠቆመ የችግሩ መንስኤ የለም።
ህክምናው በአብዛኛው የመድሀኒትና የስነልቦና ጥምር ህክምና ነው።
3.2. የስፐርም ፈሳሽ ከተገቢው ጊዜ በላይ መዘግየት ወይም ከነአካቴው አለመፍሰስ/እርካታ ላይ አለመድረስ
– ሌሎች ውስጥ ደዌ ህመሞች መድሀኒቶች የነርቭ ሲስተም ወይም የሽንትና ብልት አካላት ቀዶ ጥገናዎች እና የሆርሞን ችግሮች እንደመንስኤ ይጠቀሳሉ።
ወሲብ ነክ ችግሮች በግለሰቡ ላይ የሚያስከትሉት ችግሮች
– ድብርት ጭንቀት መረባበሽና ዝቅተኛ በራስ መተማመን
– የትዳር/ፍቅር ግንኘነት ችግሮች
– መውለድ አለመቻል
አጠቃላይ መከላከያ እና ህክምና
አጠቃላይ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጤንነት መጠበቅ ወይም ህመም ሲኖር መታከም/መቆጣጠር ያስፈልጋል።
የሰውነት ክብደት ማስተካከል እና የአካል እንቅስቃሴ ወሳኝ ናቸው። አልኮል መቀነስ/መተው ጫት ሲጋራና ሌሎች ዕፆችን መተዉ ያስፈልጋል። ድካምና ጭንቀት/ውጥረት መቆጣጠርም ይበጃል።ሌላው ሊሰመርበት የሚገባው ይህም እንደማንኛውም የጤና እክል ታይቶ ህክምና መውሰድ ይገባል። በገሀዱ አለም የምናየው ግን ብዙ ወንዶች ህክምና ለማድረግ እንደማይደፍሩ ወይም ሊታከሙ መጥተው ፈርተው ሀሳብ ቀይረው ሌላ ነገር ተመርምረው እንደሚመለሱ ነው። ይህ ታካሚ በተጨባጭ በግሌ የነገረኝ ነው። በተጨማሪም በቀን ከመታከም ይልቅ ማታ ላይ ወደ ሀኪም ቤት ጎራ የሚሉ ሲሆን ይህም ተገቢውን የህክምና ባለሙያ ከማግኘት ያግዳቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሰዎች ሌሎች መንፈሳዊና ባህላዊ ትርጓሜዎች ይሰጣሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘም ወሲባዊ ጤንነታቸውን ለማረጋገጥ ከሴተኛ አዳሪ ወይም ሌላ ሴት ጋር በመሞከር እራሳቸውን ለተላላፊ በሽታዎች የሚያጋልጡ አሉ።በግል ከሚደረጉ ጥንቃቄዎች በተጨማሪ የመድኃኒትና የስነልቦና ህክምና መፍትሄዎች አሉ።
ምንጭ ፦ከጤና ሀብት ነው
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2013