አዲስ አበባ፡- በምዕራብ ኦሮሚያና ደቡብ ምስራቅ ጉጂ አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው ችግር እየተቀረፈ በመምጣቱ ነዋሪው ወደ ሰላማዊው እንቅስቃሴ መመለሱ የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ ፡፡ አንድ ሺህ የኦነግ ሠራዊት አባላት ወደ ካምፕ መግባታቸው ተጠቆመ፡፡ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምዕራብ ኦሮሚያና ደቡብ ምስራቅ ጉጂ አካባቢ ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር በአካባቢው የነበረው ሰላማዊ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ባለፉት ሳምንታት በመንግሥት በተሠሩ ሰላም የማስጠበቅ ሥራዎች ሁኔታዎች እየተሻሻሉ በመምጣታቸው በአሁኑ ወቅት ተዘግተው የቆዩ ትምህርት ቤቶች ወደ መማር ማስተማሩ እንቅስቃሴ እየገቡ ሲሆን፣ ተስተጓጉለው የነበሩ መንግሥት ሥራዎችም ወደ ቀደመ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው እየገቡ ነው ፡፡
በአካባቢው ተቋርጠው የነበሩ መሰረተ ልማቶች ሥራም ተጀምሯል ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ ተጀምረው የነበሩ የጤና መንገድና የትምህርት ቤት ፕሮጀክቶች ግንባታዎችም እየተካሄዱ መሆኑን ጠቁመዋል። አጠቃላይ የነበረው ሰላም ከወራት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በርካታ ለውጦች የታዩበት እንደሆነ በመግለጽም፣ መንግሥት የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ዜጎችን ሰላም ለማስጠበቅ የሚሠራውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል ፡፡
ምክትል ኃላፊው ጨምረው እንደተናገሩት በሀገሪቱ የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ በኤርትራ በኩል ከገቡት 1 ሺ 300 የኦነግ ሠራዊት አባላት በተጨማሪ በሀገር ውስጥ በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ የኦነግ ሠራዊት መካከል ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑት በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን ለመቀጠል ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ማሠልጠኛ ካምፕ ገብተዋል፡፡ እነዚህ ወታደሮች የሚሰጣቸውን ሥልጠና ካጠናቀቁ በኋላ እንደየፍላጎታቸው የክልሉ የፖሊስ አባል መሆንን ጨምሮ በተለያዩ ሥራ መስኮች የሚሰማሩ ይሆናል፡፡ ለዚህም መንግሥት አስፈላጊውን የሥራ እድል ያመቻቻል፡፡
ሥልጠናውም እንደ ሀገር ሆነ በክልል የተጀመረውን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማስቀጠልና በሰላማዊ መንገድ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለማጠናከርና ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲችሉ የሚያበቃ ይሆናል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ሌሎቹ በትጥቅ ትግል እየተንቀሳቀሱ ያሉት የኦነግ ጦር ሠራዊት አባላት የቀደሙትን የትግል ጓዶቻቸውን ፈለግ ተከትለው በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን እንዲቀጥሉ በመንግሥት በኩል ፍላጎት መኖሩንና ለዚህም እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከየካቲት 6/ 2011ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የኦነግ ሠራዊትን ወደ ካምፕ የማስገባት የመስክ ስምሪት እንቅስቃሴ ከአባ ገዳ፣ ሀደ ስንቄና ምሁራን በተውጣጡ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት የተጀመረ ሲሆን፤ የአቀባበል ሥነ ሥርዓቱም በክልሉ በሚገኙ 12 ዞኖችና 22 ወረዳዎች እንደሚከናወን መገለፁ የሚታወቅ ነው፡፡ በተመሳሳይ የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከዚህ በኋላ የሠራዊቱ አባላት ተጠሪነት ለሳቸው ሳይሆን ለኦሮሞ ሕዝብና ለአባ ገዳዎች ስለሆነ ሠራዊቱም ይህንን በመገንዘብ የአባገዳዎቹን ትእዛዝ በሙሉ ልብ መቀበል እንዳለበት ማስገንዘባቸው ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ