• 8ኛው የኢትዮጵያ ፎረም ዛሬ ይጀመራል
ጅግጅጋ፡- 8ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም የጅግጅጋን ከተማ ገጽታ ለመቀየር በሚያስችል መልኩ እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ፡፡ ፎረሙ ያለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲጠናቀቅ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተጠቁሟል፡፡ ዛሬ በጅግጅጋ የሚጀመረውን 8ኛውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም አስመልክቶ ትናንት በተሰጠ መግለጫ እንደተነገረው፤ ጅግጅጋ ቀደም ሲልም ሆነ አሁን ላይ የጸጥታ ችግር የሌለበት ቢሆንም በ2010ዓ.ም ሐምሌ መጨረሻ ላይ የተከሰተው ተግባር ገጽታዋ ላይ መጥፎ ጥላ አጥልቷል፡፡ በመሆኑም ፎረሙን ይሄን ገጽታዋን ለማደስና ተግባሩም የህዝብና የመንግስት እንዳልሆነ ለማሳያነት እንደሚጠቀሙበት ተነግሯል፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎንፌ እና የሶማሌ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብዱልፈታህ ሼክቢሂ በጋራ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ ፎረሙን በድምቀት ለማካሄድ የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀቀው ጅግጅጋ እንግዶቿን ተቀብላለች፡፡ እንግዶችም የተዘጋጀላቸውን ቦታ ተረክበው ለበዓሉ ድምቀት የድርሻቸውን ለመወጣትና ራሳቸውንም ለማስተዋወቅ የሚያስችሏቸውን ተግባራት በማከናወን የበዓሉን መጀመር እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡
በዓሉም የጅግጅጋ ከተማን ገጽታ ለማደስና ቀድሞ የተፈጠረውም ነገር የህዝቡ ተግባር አለመሆኑን በሚያሳይ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ዶክተር አብዱልፈታህ በመግለጫው ወቅት እንዳሉት፤ ፎረሙን ለማከናወን የሚያስችሉ ዝ ግ ጅ ቶ ች ሙ ሉ በ ሙ ሉ ተጠናቅቀዋል፡፡ የፌዴራል የሥራ ኃላፊዎችና የድርጅት ተወካዮችም ወደከተማዋ ገብተዋል፡፡ ህብረተሰቡም እንግዶቹ በሚገቡባቸው ቦታዎች እየተገኘ አቀባበል አድርጓል፡፡ ይህ ፎረም በስኬት እንዲጠናቀቅም የክልሉ ህዝብና መንግሥት እንዲሁም የክልሉና የመንግሥት መዋቅሩ አብረው እየሠሩ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን ጅግጅጋ ከዚህ ቀደምም ሆነ አሁን ላይ ሰላም ብትሆንም በ2010ዓ.ም ሐምሌ 28 የደረሰች ችግር የከተማዋን ገጽታ እንደጎዳው የጠቆሙት ዶክተር አብዱልፈታህ፤ በዚህ ፎረም የከተማዋን ገጽታ ለማደስና እውነተኛ ገጽታዋን ለማሳየት እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል፡፡ በተለይ ችግሩን የፈጠሩት ህዝቦችና መንግስት አለመሆኑን ለማሳየት እንደሚያውሉትና ህዝቡም ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹን የሚወድ እንደመሆኑ በህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት፤ በጸጥታ ኃይሉ ጥምረትና የቀን ከሌት ትጋት ታጅበው ፎረሙን በስኬት እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
አቶ ካሳሁን በበኩላቸው እንዳሉት፤ የበዓሉ ዝግጅት ከመጠናቀቁም በላይ 168 የኢትዮጵያ ከተሞችና 9 ድርጅቶች ጅግጅጋ ላይ ከትመዋል፡፡ ጅቡቲ፣ በርበራና ሐርጌሳ ከተሞችም የሚሳተፉ ይሆናል፡፡ በከተማዋም አስተማማኝ ጸጥታ ያለ ሲሆን፤ እስኪጠናቀቅም የክልሉና የፌዴራል አካላት በጋራ እየሠሩ ናቸው፡ ፡
ፎረሙም የከተማነትና የከተሜነት ልምድ የሚለዋወጡበት እንደመሆኑ፤ በከተሞች የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና፣ በመሬት ልማትና አስተዳደር፣ በአረንጓዴ ልማትና አካባቢ ጥበቃ፣ እንዲሁም በቤትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጽሑፎች ቀርበው ይመከርባቸዋል፡፡ ትናንት በዋዜማው ‹‹የጅግጅጋ ከተማ ከየት ወደየት›› በሚል ርዕስ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲና በጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ቅንጅት የተዘጋጀ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ የጅግጅጋ ከተማ የባህልና ታሪክ ባለቤትነቷ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት አመቺነቷ በስፋት ተነስቶበታል፡፡ ፎረሙ ከየካቲት ዘጠኝ እስከ የካቲት አስራ አራት ድረስ የሚቆይ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2011
ወንድወሰን ሽመልስ