አዲስ አበባ፡- የኢፌዴሪ መከላከያና የደህንነት ተቋማት አባላት ከማንኛውም የፖ ለቲካ ፓርቲ አባልነትና ተሳትፎ ሙሉ ለሙሉ ነፃ መሆናቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ። በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ዳባ ለአዲስ ዘመን በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፣ የመከላከያና የደህንነት ተቋማት ከኃላፊዎች እስከታች ያሉትን አባላት ከማንኛውም የፓርቲ አባልነት ተሳትፎ ነፃ በማድረግ በህገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅና የአገራቸውን ልኡላዊነት የማስከበር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
እንደ ሊቀመንበሩ ማብራሪያ በመከላከያና በደህንነት ተቋማት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የነበሩ ሠራተኞችና ኃላፊዎች ሁለት አማራጭ ተሰጥቷቸዋል። የፖለቲካ አባልነታቸውን ትተው በተቋማቱ በአባልነታቸው መቀጠል ወይም ደግሞ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቋሙን ለቅቀው በመውጣት በፖለቲካ ፓርቲ አባልነታቸው መቀጠል ነው። አብዛኞቹ አባላት የፖለቲካ ድርጅት አባልነታቸውን ትተው በመከላከያና በደህንነት ተቋማት ውስጥ ሥራቸውን ቀጥለዋል።
የፖለቲካ ተሳትፏቸውን አቁመው በሥራቸው ከቀጠሉት መካከል የብሄራዊ መረጃ ደህንነት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸውን ትተው በኃላፊነታቸው ከቀጠሉት መካከል ይገኙበታል። በአጠቃላይ የተቋማቱ ሠራተኞች ወገንተኝነታቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ እንዲሆን ተደርጓል። በአሁኑ ወቅት የድርጅት መዋጮ የሚያዋጣ፣ በአዲስ ራዕይ ላይ የሚወያይና የድርጅት ስብሰባ የሚያደርግ የሠራዊትም ሆነ የደህንነት አባል የለም።
በኢህአዴግ ምክር ቤትም ሆነ በሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች በሥራ አስፈፃሚነትም ሆነ በሌላ ደረጃ በፖለቲካ የሚሳተፍ ሠራተኛም ሆነ ኃላፊ የለም ብለዋል። በተደረገው ማሻሻያ ተቋማቱ በህዝብ ዘንድ አመኔታ እየፈጠሩ ናቸው። ከህብረተሰቡ ጋር አብረው እየሠሩ ስለሆነ ህዝቡ የሚያውቀውን መረጃ ለተቋማቱ እየሰጠ ነው። ተቋማቱም ከህዝብ ጋር ለመሥራት በስፋት እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ