ወ/ሮ ምንአለሸዋ በርሄ በአራዳ ክፍለ ከተማ ግንፍሌ አካባቢ በቆዳ ጫማ ሥራዎች ተሠማርታ ትሠራለች። የስራ ቦታዋ ጃንሜዳ አካባቢ አራዳ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ ግቢ ውስጥ ባሉ ህንፃዎች የሚገኝ ሲሆን፣ በሥፍራው የተለያዩ የጫማ፣ የልብስ ስፌትና የባህል ጥበብ አልባሳት ሥራዎች በብዛት ሲሠሩ ይታያል።
ሥራውን በራስዋ ተነሳሽነት ከጀመረችው አምስት ዓመታት ሆኗታል። መንግሥት ሥራውን እንድትጀምር ከሌሎች ሰዎች ጋር በቆዳ ጫማ እና ተያያዥ ሥራዎች ላይ ሥልጠና የሰጣት ሲሆን፣ በ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጁ ግቢ ውስጥ ለመሥሪያ የሚሆን ቦታ ተሰጥቷት ነው እየሠራች የምትገኘው።
የመሥሪያ ቦታው የመንግሥት ስለሆነ ቅናሽ ነው የምትለው ምንአለሸዋ፤ ከውጪ ዲዛይኖችን በማፈላለግ ለገበያ የሚቀርቡ ጫማዎች ዲዛይን አድርገው ወቅትንና ፋሽንን የተከተሉ ምርቶች እንደሚያመርቱ ጠቁማለች። አንዳንዴም በጫማ ዲዛይን የሰለጠኑና ልምድ ያላቸው የተማሩ ፕሮፌሽናል ሞዴሊስቶች የሚያወጡትን የጫማ ዲዛይን በመጠቀም ጫማዎቹን እንደሚያመርቱ ትናገራለች። የጫማው ዲዛይን ሲወጣ ዲዛይኑን ለሚያወጡ ፕሮፌሽናል ሰዎች ክፍያ እንደሚፈጽሙም ነው የምታብራራው ።
የምታመርተው ጫማዎች በብዛት የወንዶች መሆናቸውን ገልጻ፣ ዲዛይን ቀያይረን እናመርታለን እንጂ ገበያው እንደ ሴቶቹ ጫማዎች አይደለም ትላለች። የወንድ ጫማ ዲዛይንና ፋሽን ዐይቶ የሚረባረበውና የሚገዛው ጥቂት መሆኑንም የምትጠቁመው። በተቻለ መጠን ወቅቱን የጠበቀ ለየት ያለ ዲዛይን በመጠቀም ጫማዎችን እናመርታለን ስትል ምንአለሸዋ ገልጻለች። መጪው ክረምት ከመሆኑ አንፃር ከወዲሁ ለክረምት የሚሆኑ ጫማዎች ለማምረት እየተዘጋጁ መሆኑን አስታውቃለች።
በኮረናም ወረርሽኝ ዓመት ሙሉ አልሠራንም በሚባልበት ደረጃ ነን የምትለው ምንአለሸዋ ቀደምሲል በገበያ ትስስር የተዋወቁዋቸው የጫማ ነጋዴዎች አዘው ምርቱን ይወስዱ እንደነበረ ታስታውሳለች።
በዘርፉ የተሰማሩትን ሁሉ ፋሽን ለመከተል ዲዛይን ለመቀያየር ጥረት እያረጉ ባለበት ወቅት ኮረና የገበያ ትስስራቸውን ሰብሮባቸዋል። “ የእኛ ሥራችን ከሰዎች ጋር ብዙ ግንኙነት ስላለው፤ ኮረና ደግሞ ግንኙነት ማድረግን ስለማይፈቅድ እቃችንን ብናመርትም ማስተዋወቅና መሸጥ አልቻልንም። ” ስትል ዘርፉ ያለበትን ችግር ትጠቁማለች።
እንደ እሷ ገለጻ፤ አካባቢው ለጫማ ግብአት የሚሆኑ ቁሳቁስ የማይገኝበት ነው። መርካቶና ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች ሄዶ መግዛት የግድ ነው። ግብአቱን ለማምጣት ሲኬድ ሥራ ሊቋረጥ ይችላል። በሥራ ቦታው ለጫማ ቆዳ የሚሆኑ ቁሳቁስ የሚሸጡ ቢኖሩ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል ።
ምንአለሸዋ እንደምትለው፤ በክፍለ ከተማው በዓመት ሦስት ጊዜ የገበያ ትስስር ይደረግላቸዋል። ምርቶቻቸውን በአራዳ ክፍለ ከተማ ባሉ ዋና ዋና አደባባዮች በሚዘጋጁ ዐውደ ርዕይና ባዛሮች ላይ ያሳያሉ። አውደ ርዕዩ ምርታቸውንና ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ ይረዳቸዋል። ይህ ደግሞ በግል የሚገዙንም ዐይተው ሲገዙን በጅምላም የሚገዙ ነጋዴዎች ጫማዎቹን ዐይተው አድራሻና ስልክ ወስደው የገበያ ትስስር እንደሚፈጠር ጠቁማለች። መንግሥት መሥሪያ ቦታውን ከመስጠት ባለፈ ሥልጠና በመሥጠትና የገበያ ትስስር እንድንፈጥር ትብብር እንደሚያደርግላቸው ትናገራለች ።
ምርታችንን በዓመት ሦስት ጊዜ ታስተዋውቃላችሁ ቢባልም ለሌሎች ዕድል ሲሰጥ የሚያመልጠን ነገር ይኖራል የምትለው ምንአለሸዋ ዕቃዎቹም ሲሸጡ እንደ ኤግዚቢሽንና ባዛር ትውውቅ ስለማይደረግ ሰው እግረመንገዱን በአካባቢው ሲያልፍ ሲያገድም በአደባባይ ዳር ከእግረኛ መንገድ ጥግ ድንኳን ተደኩኖ በክፍለ ከተማው የሚመረቱ አልባሳትን ጫማዎችን ሲያይ ነው ገበያ የምናገኘው፣ ትሥሥር የምንፈጥረው በማለት ታብራራለች። በግላቸው ጫማ የሚገዙ ይኖራሉ፤ የበለጠ ግን ለጅምላ ንግድም አድራሻ ወስዶ የሚሄድም አለ። የክፍለ ሀገር ነጋዴዎች ይመጣሉ፤ ባዛሩ የበለጠ የሚጠቅመን ለንግድ ምርቱን የሚፈልጉ ሰዎች ሲያገኙን ነው። የምናመርተውን የጫማ ዓይነት አይተው ይወስዳሉ፤ አንዳንዴም እነሱ ፋሽን ብለው በሚያመጡትና በሚያሳዩን ዲዛይን ጫማውን እናመርታለን ነው የምትለው።
በሥፍራው ያገኘናት ወይዘሮ ወይንሸት ኮስትሬ የጫማ ሥራውን ከጀመረች አምስት ዓመቷ ነው። የሴቶች ጫማዎችን ስለምትሠራ የተለያዩ ዲዛይኖችንና ፋሽኖችን መከተል ገበያ ለማግኘት እንደሚረዳት ከሥራ ልምዷ ተረድታለች። የጫማ ፋሽን ዲዛይን በራስዋ ትሰራለች፤ ለዚህም በመረጃ መረብ ከምታያቸው የሴት ጫማዎች በመጠቀም ገበያ ላይ ያምራል ብላ የምታስበውን ትሰራለች። አንዳንዴም እንዲሠራላቸው የሚፈልጉ ሰዎች ዲዛይኑን እና ሞዴሉን ይዘው መጥተው ያሰሯታል፤ ለእነሱ ከሠሩ በኋላ ለሌላ ገበያተኞች እንዲሆን እንደገና ሠርታ ትሸጣለች።
በሴቶች ጫማ ላይ ገበያ ለማግኘት ዲዛይን መቀያየር የግድ ነው የምትለው ወይዘሮ ወይንሸት፤ በየጊዜው ዲዛይኑንና ፋሽኑን ተከትለን አዳዲስ ጫማ የማንሠራ ከሆነ ገበያ አናገኝም ትላለች። ሞዴሉን ተቀይሮ የማይመረት ጫማ ከሆነ ሴቶች ጫማውን ሊገዙት ቀርቶ ዞር ብለውም አያዩትም ትላለች።
አዳዲስ ዲዛይን ጫማ ስንሠራ በብዛት ተወስዶ በተደጋጋሚ ሥሩልን ብለው የሚጠይቁ አሉ። የሴቶች ጫማ ላይ አንዳንዴ ሪሳይክል የተደረጉ ቁሶች፣ የጫማ ሶሎችን እንጠቀማለን ስትል ትገልጻለች።
ወይዘሮ ወይንሸትም የኮረና ወረርሽኝ በጫማ ገበያው ላይ መቀዛቀዝ ማስከተሉን ትጠቁማለች። ሠራተኞችም የተበተኑበት ሁኔታ እንደነበርም ታስታውሳለች። በአሁኑ ወቅት ገበያው እያንሠራራ መሆኑንም ትናገራለች። የምታመርተው የሴት ጫማ መሆኑን ጠቅሳ፣ የኮሮና በሽታ በእንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ባሰረፈበት ወቅት እንኳ በየጊዜው እየቀያየረች የምትሠራቸው ጫማዎች ገበያ እንደነበራቸው ጠቁማለች።
ከኮረና በፊት ለባዛርና ኤግዚቢሽን ወደ ተለያዩ ክልሎች ምርታቸውን ይዘው ይሄዱ የነበረበት ሁኔታ ከነጋዴዎች ጋር ትስስር ለመፍጠር እና ገበያ ለማግኘት እንደረዳቸው አስታውሳ፤ ጫማዎችን ለማምረት የግብአት መሸጫ በሥራ ቦታቸው አለመኖሩ ወደ መርካቶ በየጊዜው እንዲሄዱ እንዳስገደዳቸው በመግለጽ የምንአለሸዋን አስተያየት የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥታለች። የጫማ ሶልና ጥሬ ዕቃ ስንገዛም 25 ደርዘንና ከዚያ በላይ ስለሚሉን ጥሬ ዕቃዎች ለመግዛት በገንዘብም እንቸገራለን። መንግሥት የዘወትር ድጋፉና ትብብሩ አይለየን ትላለች።
ያነጋገርናቸው በጫማ ሥራ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሥራ ቦታው ለትራንስፖርትና አድራሻውን ለመጠቆም አስቸጋሪ መሆኑንም ይናገራሉ። ቦታው ለደንበኞች መጥተው እንዳያዩ ምቹ አይደለም፤ በምልክት ተነግሮአቸውም ሰዎች ለመምጣት ይቸገራሉ። በዚህም የገበያ ውልም ተዋውለው የሚፈርስበት ጊዜ አለ ስትል ታመለክታለች። ራሳችን የግድ ወደ እነሱ መሄድ አለብን፤ ራሳችን ስንሄድ ደግሞ በእኛ ላይ እምነት ያጣሉ፤ ከሌላ ቦታ አምጥተን አትርፈን የምንሸጥ ይመስላቸዋል ስትል ታመለክታለች። በቆዳ ጫማ ሥራችን አልፎ አልፎ ሠራተኛ እጥረት ቢያጋጥመንም ከመርካቶ የጫማ ምርት የተሻለ እናመርታለን ስትል በስራዋ ያላትን መተማመን ትናገራለች።