ወላጆች ልጆቻቸው እራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ እየተንከባከቡ የማሳደግ ተፈጥሯዊ ሃላፊነት እንዳለባቸው ይታመናል። አብዛኛዎቻችን ነፍስ አውቀን ለቁም ነገር እስክንበቃ ድረስ ሀሳባችንን በሙሉ በወላጆቻችን ላይ ጥለን ያደግን ነን። ስለምግብና ልብሳችን፣ ስለጤንነታችን፣ በሰላም ወጥተን ስለመግባታችን የሚጨነቁልን ወላጆቻችን ናቸው። የልጅነት አስተዳደጋችን ተቀራራቢነት ቢኖረውም እንዳደግንበት ቦታ፣ ሁኔታ እና የኑሮ ደረጃ ልዩነት ሊኖረው ይችላል። በቀላሉ በገጠርና በከተማ የሚያድጉ ልጆችን አስተዳደግ ብንመለከት እንኳ በርካታ ልዩነቶችን እናያለን።
የገጠር ልጆች ከከተማ ልጆች የበለጠ በልጅነታቸው የስራ ሃላፊነትን ይሸከማሉ። ገና ከሰባትና ከስምንት ዓመት እድሜያቸው ጀምረው ከብት የማገድ፣ ውሃ የመቅዳት፣ እንጨት የመልቀም፣ የመጎልጎል፣ አረም የማረምና የመሳሰሉ የጉልበት ስራዎችን በመስራት ቤተሰቦቻቸውን ያግዛሉ። ያን ያህል አይብዛ እንጂ የከተማ ልጆችም ቢሆኑ ለቤተሰቦቻቸው በመላላክ፣ በንግድ ስራ ውስጥ በመሳተፍና ቀለል ያሉ የቤት ስራዎችን በማከናወን ወላጆቻቸውን ያግዛሉ።
ለማንኛውም እንዲህ ያለው ተግባር ከአስተዳደግ ባህላችን ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ጉልበት ብዝበዛ ልንለው አንችልም። እንዲያውም ልጆች ስብዕናቸው በጥሩ ስነምግባር እንዲቀረጽ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ እሴቶቻችን አንዱ በስራ ተገርቶ ማደግ እንደሆነ የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው። ምክንያቱም ከልጅነታቸው ጀምረው ስራን እየሰሩ ያደጉ ልጆች ያካበቱት ልምድ በወደፊቱ ህይወታቸው ላይ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ይታመናልና ነው። አብዛኛዎቹ ስኬታማ ሰዎች ስኬታማ የመሆናቸው ምስጢር ደንገተኛ ሳይሆን በልጅነት እድሜያቸው ጥንስስ በማስቀመጣቸው ነው።
ከወላጆቻቸው እቅፍ መውጣት የማይገባቸው ታዳጊዎች ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውን ለማኖር ሲጥሩ ማየት እምብዛም የተለመደ አይደለም። በተለይም እራሳቸውን ችለው መኖር የሚገባቸው ወጣቶች ወይም ጎልማሶች የወላጆቻቸው ጥገኛ ሆነው በሚኖሩበት ሀገር የቤተሰብ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ታዳጊዎች የማይገመቱ ስራዎችን እየሰሩ ቤተሰባቸውን ሲረዱ መመልከት ሊያስገርም ይችላል።
የዛሬው እንግዳችን በልጅነቱ ይኖርበት በነበረው ገጠራማ ቦታ በግብርና ስራ ይተዳደሩ የነበሩ ቤተሰቦቹን በስራ እያገዘ ይኖር የነበረ ታዳጊ ነው። ቤተሰቦቹ በግብርና የሚተዳደሩ ናቸው ቢባሉም በቂ የእርሻ መሬት የሌላቸው በመሆኑ የሚያመርቱት ምርት የዓመት ቀለባቸውን እንኳ አይሸፍንላቸውም። የቤተሰቡ ችግር የሚያስጨንቀው ብላቴና ታዲያ የአቅሙን እየሰራ ሊረዳቸው በማሰብ በለጋ እድሜው ከትውልድ አካባቢው ተሰዶ ወደ አዲስ አበባ አጎቱ ዘንድ በመምጣት ሙያ ተምሮ ቤተሰቦቹን እያገዘ ይገኛል።
ታዳጊው ቀን ቀን እየሰራ ማታ ማታ እየተማረ እራሱንም ቤተሰቦቹንም ከችግር ለማውጣት እየጣረ ነው። ያም ብቻ ሳይሆን ሙያውን አሳድጎ ለሌሎችም የስራ እድል የመፍጠር ፍላጎት አለው። የፋሲካ ማግስት ነው። ከረፋዱ አምስት ሰዓት አካባቢ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አስራ ሁለት ካራ ፍተሻ ሰፈር እግር ጥሎኝ ተገኝቻለሁ። ከአስፋልቱ ባሻገር ከሚታየው የከብት መሸጪያ አጥር ጥግ እንዲት የሸራ ቤት ትታያለች። ቁጥራቸው አምስትና ስድስት የሚሆኑ ሰዎች ከቤቷ በር ላይ ቆመው በስራ የተወጠረውን ብላቴና እጅ እጁን ያያሉ።
ለስራዬ የሚጠቅም መረጃ አገኝ እንደሁ ብዬ ተጠጋሁ። ሰዎቹ ዓመት በዓሉን አስመልክቶ ቢላዋ እና የስጋ መከትከቻ ለማስሞረድ የቆሙ ናቸው። ታዳጊው አንጥረኛ ፋታ ያጣ ይመስላል። ወናፍ የጨበጡትን ሁለት እጆቹን ወደ ላይና ወደ ታች እያደረገ የምድጃውን ፍም አፍክቶታል። አልፎ አልፎ የወናፉን እንቅስቃሴ ቆም እያደረገ ትርክክ ባለው ፍም እሳት ላይ የተቀመጡትን ቢለዋዎች ያገለባብጣቸዋል። አንዳንዴም የጋሉትን ቢለዋዎች በመቆንጠጫ እየያዘ ወደ ዳር ካወጣቸው በኋላ የሚፈልገውን ቅርጽ እንዲይዙለት ብረት ላይ አጋድሞ ይቀጠቅጣቸዋል። በአንድ በኩል እድሜውና የሚሰራው ስራ አለመመጣጠን በሌላ በኩል ሰርቶ የማደር ጥረቱ እያስገረመኝ ቆሜ እመለከተው ጀመር። ደንበኞቹን ከሸኘ በኋላ የስራ ድርሻዬን ገልጬለት የህይወት ተሞክሮውን እንዲያካፍለኝ ጠየኩት። ፈቃደኝነቱን ካሳወቀኝ በኋላ ወደ ወጋችን ገባን።
አብዲ ባህሩ ይባላል። አስራ አምስት ዓመቱ ነው። ትውልዱና እድገቱ ኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ አካባቢ ነው። ያደገበት መንደር ልዩ ስሙ መኛቆ ይባላል። የአስራ አምስት ዓመቱ ታዳጊ ለቤተሰቦቹ የመጀመሪያ ልጅ ሲሆን ከእርሱ በታች ሁለት ወንድና አንድ ሴት በድምሩ ሶስት ታናናሾች እንዳሉት ይናገራል። ቤተሰቡ በግብርና የሚተዳደሩ መሆናቸውን የሚናገረው ብላቴና ገቢያቸው አነስተኛ በመሆኑ ተቸግረው እንደሚኖሩ ይገልጻል። አብዲ የቤተሰቡ መቸገር ከአብሮ አደጎቹ ጋር እንደልቡ እንዳይጫወት የስነ ልቡና ጫና እንደሚፈጥርለት ይናገራል። በአለባበሱም ሆነ በአመጋገቡ ከሰፈሩ ልጆች አንሶ መገኘቱ ያስቆጨው እንደነር ያስታውሳል። ሁል ጊዜ የቤተሶቹን በተለይም የታናናሾቹን ህይወት የመለወጥ ፍላጎት እንዳለው ይገልጻል።
አንድ ቀን ታዲያ አዲስ አበባ ይኖር የነበረው የእናቱ ወንድም ሊጠይቃቸው ወደ መኛቆ በሄደ ጊዜ አብዲ አዲስ አባባ ሄዶ ያገኘውን ስራ እየሰራ ቤተሰቦቹን የመርዳት ፍላጎት እንዳለው ለአጎቱ በማሳወቅ ይዞት እንዲሄድ ይማጸነዋል። አጎቱ ግን እድሜውን የሚመጠን የጉልበት ስራ እንደሌለ በመግለጽ በሀሳቡ ሳይስማማ ይቀራል። አርፎ ትምህርቱን እንዲማርና ወደፊት ሲያድግ ሊወስደው እንደሚችል ይነግረዋል። ልቡ ለስራ የተነሳሳው ታዳጊ ግን ባልተመቸ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ከመማር ይልቅ አርሱ እየሰራ ታናናሾቹ ሳይቸገሩ እንዲማሩ በማሰብ መሄድ እንደሚፈልግ አጥብቆ ይጠይቃል። ካልሆነ ግን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጠፍቶ በመሄድ ሀሳቡን ሊያሳካ እንደሚችል ለቤተሰቦቹ ያሳውቃል። ግትር አቋሙን የተረዱት ቤተሰቦቹ ጠፍቶ ከሚያስጨንቀን በሚል አጎቱ ይዞት ቢሄድ እንደሚሻል ተነጋግረው ይፈቅዱለታል። አጎቱም በአብዲ ሀሳብ ተሸንፎ ይዞት ወደ አዲስ አበባ ይመጣል።
አብዲ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ዋና ዓላማው ስራ እየሰሩ ቤተሰቦቹን መርዳት ቢሆንም እንዳሰበው ለእርሱ የሚመጥን ስራ አግኝቶ ቤተሰቦቹን መርዳት ሳይችል ይቀራል። ነገር ግን አዲስ አበባ ከመጣ ጊዜ ጀምሮ አጎቱ ጋር ቁጭ ብሎ እየዋለ ሙያ ይቀስም ነበር። አጎቱ አንጥረኛ ነው። ቢላዋ፣ ዲጅኖ፣ ጠገራ፣ ዶማ ወዘተ እየሠራ ይሸጣል። አብዲ እስር እስር እያለ ሙያውን መማር ይጀምራል። አንዳንዴ ወናፉን አየር ስቦ እያስተፋው የምድጃውን እሳት በማጋጋም አጎቱን ያግዛል። በዚህ አጋጣሚ ወናፍ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማታውቁ አንባቢዎቼ ትንሽ ነገር ብዬ ማለፍ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።
ወናፍ በድሮ ጊዜ ከፍየልና ከበግ ቆዳ የሚሰራ ሆኖ ብረታ ብረትን እያጋሉ እንደ ማረሻ፣ ዶማ፣ ቢላዋ ወዘተ የሚሰሩ አንጥረኞች ምድጃውን በትንፋሻቸው እፍፍፍ እያሉ ፍም እንዲወርደው በማድረግ ፈንታ ወናፉን አየር አስበው እያስተፉ ምድጃው ፍም እንዲኖረው የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው። ዛሬ በከተሞች አካባቢ የአንጠረኞችን ስራ ጋራዦች እየሰሩት በመሆኑ የወናፍ አገልግሎት እምብዛም ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም። ወደተነሳንት ጉዳይ እንመለስ።
አጎቱ ከስር ከስር የጋሉ ብረቶችን ከእሳት ውስጥ እያወጣ ቅርጽ ሲያሲዛቸው አብዲ በትኩረት ይመለከታል። አንዳንዴም እራሱ ቢለዋዎችን እየሞረደ ስለት እያወጣ ይደረድራል። እንዲህ እንዲህ እያለ በአጭር ጊዜ ውስጥ አጎቱ የሚሰራቸውን ስራዎች በሙሉ ይለምዳል። የስራ ፍላጎቱንና ፍጥነቱን የተረዳው አጎቱ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ስራውን ለአብዲ ትቶ እርሱ በሌላ ስራ ላይ ይሠማራል።
ታዳጊው ስራውን ተረክቦ መስራቱን ይያያዛል። የምግብ፣ የማረፊያ ቤትና የትምህርት ቤት ክፍያውን አጎቱ እየቻለው እርሱ ስራውን ብቻ እየሠራ የሚያገኛትን ሳንቲም ማጠራቀም ይጀምራል። በአጎቱ ሙያዊ ድጋፍና እገዛ የተበረታታው ታዳጊ በሙሉ አቅሙ የአንጥረኝነት ስራውን እየሰራ እንዳሰበው ቤተሰቦቹን የመርዳት እድል ያገኛል። በተለይም ለመስቀል፣ ለፋሲካ እና ለገና በዓላት ካጠራቀማት ገንዘብ ላይ ለቤተሰቦቹ በመላክ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ያደርጋል። ታናናሾቹ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲማሩ የአቅሙን ሁሉ እያደረገላቸው እንደሚገኝ የሚናገረው አብዲ በዚህም እጅግ በጣም ደስተኛ መሆኑን ይገልጻል።
እርሱም ቢሆን ያቋረጠውን ትምህርት ዳር ለማድረስ ቀን ቀን እየሰራ ማታ ማታ ይማራል። አሁን የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ታዳጊው ጠንክሮ በመስራት ወደፊት ሙያውን የማሳደግ ፍላጎት እንዳለው ይናገራል። በተለይም የቴክኒክና ሙያ ትምህርቶችን በመማር ማሺኖችን ተጠቅሞ የብረት ውጤቶችን የማምረት ፍላጎት እንዳደረበት ይገልጻል። እንደገራዥና ትልልቅ ወርክ ሾፖችን ከፍቶ ህይወቱን የመምራትና ለሌሎች ሰዎችም የስራ እድል የመፍጠር ምኞት እንዳለው ይናገራል።
አብዲ ወደ አዲስ አበባ የመጣው ከሶስት ዓመት በፊት ነው። የስራ ቦታውን የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አስራ ሁለት ካራ ፍተሻ ሰፈር አድርጎ ኑሮውን ለገዳዲ አድርጓል። ከለገዳዲ ጠዋት አስራ ሁለት ሰዓት ተነስቶ ስራ ቦታው አንድ ሰዓት ላይ ይገኛል። ማታ የትምህርት ሰዓቱ ከመድረሱ በፊት ወደ ቤቱ ይገባል። ገበያ አለ በተባለ ቀን እስከ ሁለት መቶ ብር የእለት ገቢ ያገኛል። አንዳንዴ ግን ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብሎ ሃምሳ ብር እንኳ የማያገኝበት ጊዜ እንዳለ ይናገራል። በየካ ካራ ከብት ተራ አጥር ስር ሸራ ወጥሮ እየሰራ ያለው ታዳጊ ማህበሩ ጊዜያዊ የስራ ቦታ ስለፈቀደለት ለቤት ኪራይ ወጪ አለማውጣቱ እንደረዳው ይገልጻል።
ከአብዲ ጋር የተገናኘነው በትንሳኤ በዓል ማግስት ነው። በዚያ ሰሞን ታዲያ በካራ ፍተሻ ሰፈር አካባቢ የሚገኙት ስጋ ቤቶች ወደ ስራ በመመለሳቸው በተለይም የቢላዋ እና የስጋ መከትከቻ ቁሳቁሶችን የሚያስሉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን አብዲ ነግሮኛል። ጾም ሲገባ ግን ድጅኖ እና ዶማ ከሚያሰሩ ጥቂት ሰዎች በስተቀር ቢላዋ የሚያስሞርዱ ደንበኞቹ ዝር አይሉም። በዚህ የተነሳ ገቢው ይቀንሳል።
አብዲ ለችግር እጁን ላለመስጠት ሲል እየሰራ መኖር እንደጀመረ የሰው እቃ ተሰርቆበት እዳ ውስጥ የገባበትን ሁኔታ እንዲህ ያስታውሳል። አራት እና አምስት የሚሆኑ ወጣቶች ቢላዋ በእጃቸው ይዘው እንዲሞርድላቸው ዋጋ ይጠይቁትና ይነግራቸዋል። ከመካከላቸው አንዱ ዋጋ ቀንስልን በሚል የውሸት ሲከራከር ሌሎቹ ከሰው የተረከበውን ድጂኖና ሌላ እቃ ሰርቀው ይሄዳሉ።
አብዲ በወቅቱ ምንም ስላልተጠራጠረ ትኩረት አላደረገባቸውም። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን የተሰጠውን እቃ ሲመለከተው የለም። የእቃው ባለቤቶች ሲመጡ እንደጠፋበት ይነግራቸዋል። እነርሱም የቀን ስራ የሚሰሩ በመሆኑ እቃውን ካላገኙ የእለት ገቢ እንደማይኖራቸው በመግለጽ ከየትም አምጥቶ እንዲሰጣቸው ወጥረው ይይዙታል። አብዲ በወቅቱ እቃውን የሚገዛበት ብር እጁ ላይ ስላልነበረ ግራ ይጋባል። በኋላም አጎቱ ጋር ደውሎ ብር ከተቀበለ በኋላ መርካቶ ሄዶ እቃውን በአምስት መቶ ብር ገዝቶ መስጠቱን ያስታውሳል። ከዚያ በኋላ ትምህርት አግኝቶ በጥንቃቄ እየሰራ መሆኑን ይገልጻል።
ስራ ሰርተው ማደር የሚችሉ ወጣቶች በስርቆት ተግባር ላይ መሰማራታቸው እንደሚያሳፍር የሚናገረው ስራ ወዳዱ ታዳጊ ከዚያ ይልቅ በተለያዩ ስራዎች ላይ በመሰማራት የወደፊት ህይወታቸውን ለመቀየር መጣር እንደሚገባቸው ይመክራል። እኛም እንደ አብዲ ያሉ ገና ለጋ ልጆች አጥንታቸው ሳይጠነክር ወገብ በሚያጎብጥ ስራ በመጠመድ ለችግር እጅ ላለመስጠት ሲፍጨረጨሩ ማዬት የሚያስቀና ባይሆንም ለሌሎች ስራ ፈት ጎልማሳዎች አርአያ የመሆን አቅም አላቸውና አብዲን በርታ፣ ጠንክር ብለን ተሰናበትን። ሳምንት ሌላ ባለታሪክ ይዘን እስከምንመጣ ቸር ይግጠመን።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2013 ዓ.ም