የመጨረሻው መጀመሪያ …
የፍርድቤቱ ችሎት ተሰይሟል። ዳኞች ቦታቸውን ይዘዋል። በርካታ የፍርድቤቱ ታዳሚዎች የመጨረሻውን የፍርድ ውሳኔ ለመስማት አዳራሹን ሞልተውታል። ተከሳሹ በችሎቱ አንድ ጥግ በተዘጋጀ ስፍራ እንደቆመ ነው። ዓቃቤህግና ጠበቃው ጥቁር ካባቸውን እንደለበሱ በተቃራኒ አቅጣጫ ቆመዋል ።
ዛሬ የምስክሮች ቃል አይሰማም ። ሁሉም የሚጠበቅባቸውን እማኝነት አጠናቀዋል። ከችሎቱ ትይዩ ካሉ አግዳሚዎች በአንደኛው ሁለት ወንድ ልጆች ይታያሉ። በሁለቱም ፊት ያጠላው ሀዘን ከጥላቻ ጋር ይነበባል። ተከሳሹን በተለየ ስሜት እያስተዋሉት ነው። ሰውዬው ዙሪያ ገባውን እየቃኘ የችሎቱን መጀመር ይጠብቃል። አዳራሹ አሁንም በዝምታ ተውጧል። ድንገት ከዳኛው አንደበት ቃል መሰማት ጀመረ። ይህኔ የሁሉም ታዳሚ እይታ ወደ ችሎቱ አተኮረ።
ቅድመ -ታሪክ
ጎበና ሰሜንሸዋ ቡልጋ ከተባለ ስፍራ ተወለደ። በልጅነቱ እንደ እኩዮቹ ትምህርትቤት አልገባም። ሌሎች ቀለም ለመቁጠር ዕድል ሲያገኙ እሱ ለዚህ አልበቃም። የፊደል ሀሁን ሳይለይ አዲስ አበባ ጣልያን ሰፈር መጣ። ወላጅ አባቱ እንደልጅ ተቀብለው የትምህርትቤትን ደጃፍ አሳዩት።
ጎበና ደብተር ይዞ አንደኛ ክፍል ገባ። የጀመረውን የትምህርት አመት ሲጀምር ወደ ሁለተኛ ክፍል አለፈ። ቀጣዮቹ ሶስት አመታት። በዕውቀት እያሻገሩ አምስተኛ ክፍል አደረሱት። ከዚህ ደረጃ በላይ መቀጠል አልቻለም።ትምህርቱን አቋርጦ ሀሳቡን ቀየረ። መንጃ ፈቃድ ለማውጣት አቅዶ ተሳካለት።
አትክልት ተራ አካባቢ እየሮጠ ደህና ገንዘብ አገኘ። ጥቂት ቆይቶ የራሱን መኪና ገዛ። በመኪናው ከወዲያወዲህ እያለ ብዙ ተግባሮች ከወነ ። እንዲህ መሆኑ ከብዙዎች አገናኘው። ይህ ግንኙነት ገንዘብ ለማግኘት የላቡ ወዝ ፣የጉልበቱ ድካም ብቻ በቂ እንዳልሆነ ጠቆመው።
ይህ አይነቱ ሀሳብ በጎበና ውስጠት መዋል ማደር ጀመረ። ካወቃቸው ሰዎች ጋር በየቀኑ የገንዘብ ማግኛውን ዘዴ አወቀበት። ውስጡ ያደረ ፍላጎቱን ለመሙላት በሌሎች ዘንድ ህገወጥ የሚባለውን ስራ ሞከረው፣ ተሳካላት። በአዲሱ ስራው አልከሰረም። ረብጣ ገንዘብ ኪሱ አስገባለት። እሱን እየቆጠረ ቢዝነስ ባለው ድንቅ ውሎ ገፋበት ። ትዳር ይዞ ሶስት ልጆች ወልዷል። ኑሮውን አዲስ አበባና አዳማ አድርጎ በመኪናው ያሻውን ሁሉ ይፈጽማል።
ቢዝነሱ ያሰበውን ጥቅም ሲሰጠው ገንዘብ እየቆጠረ፣ ጥሪት እየቋጠረ በጅምሩ ቀጠለ። እንዳሰበው ብዙ አልተጓዘም ። አንድ ቀን ይህ ድርጊቱ ተነቃና ከህግ ፊት አቆመው። በፈጸመው የማታለል ወንጀል የቀረበበት ክስ ቀላል አልሆነም። ጉዳዩ በማስረጃና በምስክር ተጠናክሮ ወንጀለኛነቱን አረጋገጠ። ጎበና ለፈጸመው የጦር መሳሪያ ዝውውርና የማታለል ወንጀልም ችሎቱ ይገባዋል ያለውን የአስራአምስት አመት ጽኑ እስራት በየነ።
ጎበና የእስራት ፍርዱን ሊቀበል ደብርብርሃን ማረሚያቤት ገባ። የአስራአምስት አመቱን እስር አንድ ብሎ ሲጀምር ፣ ባለቤቱና ህጻናት ልጆቹ መፈተን ያዙ። ትናንት ሙሉ የነበረ ቤት ዛሬ መጉደል ጀመረ። ልጆች በአባታቸው ናፍቆት ተሳቀቁ። ሚስት የጎደለ ጎጆዋን ልትሞላ፣ በድካም ባዘነች። ለእሷ የታሰረ አባወራዋን ለመጠየቅ አገር አቋርጣ መጓዙ ቀላል አልሆነም። የህጻን ልጆቿ ፍላጎትና ስለአባታቸው የሚያነሱት ጥያቄ በእጅጉ ፈተናት።
አንዱ አመት አልፎ ሁለተኛው ተተካ። እሱም አልፎ ሶስተኛው የእስር ጊዜ ቀጠለ። በዚህ ሁሉ መሀል የወይዘሮዋ ህይወት ከአጣብቂኝ ውስጥ ገባ። ስንቅ ማዘጋጀት፣ ልጆች መንከባከብና የጎደለን መሙላት የእሷ ብቻ ሆነ። ሶስተኛው አመት እንደጀመረ ግን አባወራው ከደብረብርሃን ማረሚያ ፣ወደ አዳማ የመዞር ዕድል አገኘ። ይህ አጋጣሚ ለቤተሰቡ መልካም ሆኖ ነገሮችን አቀለለ።
ታራሚው አባት አዳማ እንደገባ ካለፉት አመት በተሻለ ልጆቹ ጎበኙት። ሚስት ርቃ ከመሄድ መንገዱ አጠረላት። እንዲህ ከሆነ ጥቂት ጊዜያት በኋላ ሌላ እድል ተፈጠረ። ታራሚው እስካሁን የታሰረው እንዳለ ሆኖ በምህረት እንዲለቀቅ ሆነ ።
ህይወት ከእስር በኋላ…
ጎበና አሁን ከማረሚያ ቤቱ ተለቆ ከቤተሰቡ ተቀላቅሏል። በናፍቆት የከረሙ ልጆቹ ፣ በብቸኝነት የተፈተነችው ባለቤቱ በደስታ ተቀብላው እያስተናገዱት ነው። ሁሉም አስራ አምስት አመት በ3 አመት ብቻ መቋጨቱ አስደሰቷቸዋል። የቤተሰቡ ሠላምና የቀድሞ ህይወት ተመልሷል ። አሁን እፎይታ የሠፈነበት ኑሮ እየታየ ነው።
ወይዘሮ አበባ ከአቶ ጎበና ጋር በትዳር ከተጣመረች አመታት ተቆጥረዋል። ሶስቱ ልጆች የትዳራቸው በረከት ሆነው ህይወታቸውን አድምቀዋል። ጎበና ከእስር ከተፈታ በኋላ መተዳደሪያ ባለው ስራ ተሰማርቷል። አባወራው ስራ ከጀመረ ወዲህ በባለቤቱ ላይ ባህሪው ተቀይሯል። ዘወትር በእሷ የሚያድርበት ጥርጣሬ ቅናት ፈጥሮ ሠላም እንደነሳው ነው።
የጠዋት ማታ ጭቅጭቅ የቤቱን ሠላም ማናጋት ጀምሯል። ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ ጣሊያን ሰፈር የገባው ቤተሰብ ኑሮን እንደቀድሞ ቀጥሏል። የትናንቱ ጎደሎ በአባወራው መምጣት ቢሞላም በሰላም እጦት እንደተናጋ ውሎ ያድራል። ባለቤቱን በጥርጣሬ እያየ ባለመታመን የሚፈርጃት ጎበና እሷ የምትለውን ለአንድም ቀን ሰምቶ አያውቅም። በየቀኑ ፀያፍ ቃላት እየጣለ በጭቅጭቅና በስድብ እልሁን ይወጣል። አንዳንዴ ጎበና አምሽቶ ይመጣና ሚስቱን ፊት ለፊት ሲያገኙት በጥፊ ይመታታል። ይህንን የሚያደርገው በልጆቹ ፊት ነው።
ድርጊቱን የሚያዩት ህጻናት በአባታቸው ሁኔታ ይሳቀቃሉ። ሁሉን በትዕግስት ማለፍ ልምዷ የሆነው ወይዘሮ በባሰባት ጊዜ ታመራለች። አባወራው ይህንን ሲረዳ እግሯ ስር ተንበርክኮ ይቅርታ ይጠይቃል። ዳግም መጠጥ እንደማይቀምስ ምሎ ተገዝቶ ቃል ይገባል። እንዲህ በሆነ ጊዜ ለጥቂት ቀናት በቤቱ ሠላም የሰፈነ መስሎ ይቆያል። መልሶ አባወራው ከመጠጡ ይታዳማል እንደገናም ባለቤቱን ጠርጥሮ ጠብና ዱላ ያነሳል።
ሠላም የቆየው ቤት ጭቅጭቅ ሲነካው የቤተሰቡ ውሎ አደር ወደ ጭንቅ ይቀየራል። ሚስት ለልጆቿ የምትከፈለው ዋጋ ፤ ከአቅም በላይ ሆኖ ፤በምሬት ትንገሸገሻለች። ይህንን የሚያወቁ ሽማግሌዎች በመሀል እየገቡ ችግሩን በእርቅ ይፈታሉ። ለአፍታ ሰላም ወርዶ የጠቡ ዱላ ይነሳል።
ወይዘሮ አበባ በየቀኑ የሚደርሰባት በደል ከጭንቀት ቢጥላት አዳማ ፀበል መመላለስ ይዛለች ። ፀበል የምትጠመቀው ወላጆቷ ባሉበት አካባቢ ነው። ሁሌም መከፋቷን የሚያወቁት እናት አባት በዚህ አጋጣሚ በጎውን መክረው ሁሉን እንድትችል አሳምነው ወደ ትዳሯ ሸኝተዋታል። ይህንን ሲያደርጉ አባወራውን አልዘነጉም። ካለበት ጠርተው ፤ ክፉ ደጉን አንስተው እጁን ከሚስቱ እጅ አጨባብጠዋል። በዕለቱ የወረደውን እርቅ አይተውም የቆየ ስጋታቸው ተወግዷል። ልጆች በእናት አባታቸው እርቅ ተደስተዋል። ዳግመኛ ጠብ እንዳይመጣ እየተመኙ የቤታቸውን ሠላም ይናፍቃሉ።
ጅምሩ ሠላም እንደነበረው አልቀጠለም። ጥቂት አረፍ ያለው ቤተሰብ ዳግመኛ በፍቅር እጦት ተመታ። ጭቅጭቁ፣ ጠቡ፣ ድብዳባው ቀጠለ። ታማሚዋ ወይዘሮ ከበሽታዋ እየታገለች ለመታገስ ሞከረች ። በቅርቡ ሆስቲታል ተኝታ ነበር ። የኩላሊት ህመሟ አስጊ መሆኑ በሀኪሞች ተነግሯታል።
አባወራው ይህንን ቢያወቅም ፣ጥርጣሬውን አልተወም። በወጣ በገባ ቁጥር፣ ሴትነቷን እያረከሰ ፀያፍ ስድብ ያወርድባታል። ልጆች ሁሉን እያዩ ልባቸው ይሰበራል። ውስጣቸው ይደማል፤ አይናቸው ያነባል።
አንዳንዴ አባወራው በጊዜ ይገባል። በጊዜ ቢገባም ጥላቻውን አይተውም። ባመሸ ጊዜ ሚስቱን ጨምሮ መላው ቤተሰብ ይጠብቀዋል። ደጁ ደጁን የምታይ እናታቸውን ከበው ልጆች የአባታቸውን ሠላም መግባት ይጠብቃሉ። ጎበና አምሽቶ በገባ ቀን የስካሩ መጠን ይጨምራል። እየተንገዳገደ ይሳደባል። እየተሳደበ ሚስቱን ያንገላታል። ሁሉን ቻይዋ ወይዘሮ እንደአመጣጡ ፣ ድርጊቱን ችላ ታሳልፋለች።
ጎበና ሁሌም ከጎኑ የሚሽጠውን ሽጉጥ ቤተሰቡ አያውቅም። ከቤት በወጣ ጊዜ ከራሱ አይለየውም። ውሎ ሲመለስ፤ ከእይታ ደብቆ ያስቀምጠዋል። የብቻውን ሚስጥር በእጁ እየዳሰሰ አሻግሮ ያስባል። እያሰበ ጥርሱን ይነክሳል።ሁሌም ከአእምሮው የማትጠፋውን ሚስቱን ቤት ሲገባ እየፈለገ፣ ሰበብ እየፈጠረ ይጠላታል። ሶስቱ ልጆቹ የአባታቸውን ባህሪ ችለው የእናታቸውን ችግር ይረዳሉ። ሰላም ሲኖሩ እየሳቁ፣ ጠብ ሲፈጥር ይጨነቃሉ።
ታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም …
ምሽት አራት ሰዓት እንደሆነ ከውጭ ወደቤት የገባው አባወራ አፍታ ሳይቆይ ተመልሶ ወጣ። ወደቤት ገብቷል ያለችው ወይዘሮ መልሶ መውጣቱን እንዳየች ሀሳብ ያዛት። እንዲህ ማድረጉ ለበጎ እንዳልሆነ ገምታም በትካዜ ተዋጠች።
መሽቷል። ሰዓት በጨመረ ቁጥር ጭንቅ የሚይዛት ወይዘሮ ዛሬም በተለመደው ስሜት ሆና የበሩን መንኳኳት ትጠብቃለች። ገና በጊዜ የልጆቿን ገላ አጣጥባ ራት ሰጥታቸዋለች። ሁሌም ከጎኗ የማይጠፉት ህጻናት ዛሬም በሳሎን ካለችው እናታቸው ጋር ሲጨዋወቱ አምሽተው ትንሹ ወደ መኝታው አምርቷል።
አሁንም ሰዓቱ እየገፋ ነው። በዕንቅልፍና ድካም የሚናውዘው ቤተሰብ ወደቤቱ ያልገባውን አባወራ መጠበቅ ይዟል። ከለሊቱ ስድስት ሰዓት ማለት እንደጀመረ። የሳሎኑ በር በሀይል ተንኳኳ። ይህኔ እናትና ትልቁ ልጇ ከነበሩቡት ድካምና እንቅልፍ ነቅተው ወደበሩ አተኮሩ።
ወይዘሮ አበባ ጋደም ካለችበት ሶፋ በፍጥነት ተነስታ የሳሎኑን በር ከፈተች። በሩን ያለቅጥ እየደበደበ ያለው ባለቤቷ ጎበና ነበር። መዝጊያውን ወደ ኋላ እንደከፈተች ወደ ጎን ዞር ብላ አሳለፈቸው። ጎበና አሁን በተለየ ስካር ውስጥ ነው ። ባለቤቱን ፊት ለፊት እንዳየ የተለመደውን የስድብ ውርጅብኝ አደረሳት ።ሚስት ይህን ባህርይ ብትለምደውም የዛሬው ባስ እንዳለ ገብቷታል።
ስድቡን እንደቀጠለ ወደመኝታ ቤቱ አለፈ። ይህ ሁሉ ሲሆን ህጻኑ ክፉኛ ተረብሾ እያስተዋለው ነበር ። ጎበና ከመኝታ ቤቱ ሆኖ ባለቤቱ ወደእርሱ እንድትመጣ ጠራት። ጥሪው ጩኸትና ቁጣን አዝሏል። ወይዘሮዋ እየተንቀጠቀጠች ትዕዛዙን ተቀብላ ያለውን ፈጸመች ።
ልጁ መረበሽ ጀመረ። ጭቅጭቅ እየተሰማው ነው። ድምጹ እያየለ ሲመጣ ወደ እናት አባቱ መኝታ ክፍል አመራ፡ ፡በሩ አጠገብ ቆም ብሎም ወደ ውስጥ ማየት ጀመረ። አባቱ ከአልጋው ጫፍ እግሩን አነባብሮ ተቀምጧል። እናቱን አንበርክኳት፤ በለቅሶ እየተማጸቸው ነው ። እየደጋገመ የተለመደውን ጸያፍ ቃል ይናገራል።
ከጎኑ ያስቀመጠው መሳሪያ ድንገት ከልጁ ዓይን ገባ።ምን እንደሆነ ባይገባውም እናቱ እሱን እያየች መደናገጧን አውቋል። አባት ልጁን አላየውም። እናት አምርራ እያለቀሰች ነው። ለቅሶና ልመናዋን መስማት ያስጠላው ጎበና ያስቀመጠውን ሽጉጥ አንስቶ ወደእሷ አነጣጠረ። ማጅራቷን በግራ እጁ ይዞ፣ ጸጉሯን ወደኋላ ጨምድዶ እየሳበ ሲያንገላታት ልጁ በቅርበት ተመለከተ። ወዲያው የያዘውን ሽጉጥ አስተካክሎ ጭንቅላቷ ላይ ተኮሰ። ከባድ የመሳሪያ ድምጽ የለሊቱን ዝምታ አናወጠ።
ልጁ ቤቱ በደም ሲሞላና እናቱ ተዝለፍልፋ ስትወድቅ ተመለከተ። አባትዬው እየተጣደፈ ወደሳሎኑ ሄደ። ሸጉጡን ከሱሪው ቀበቶ ሽጦ በሩን ከፍቶ ወጣ። ህጻኑ እየተንቀጠቀጠ በዓይኖቹ ተከተለው። ከጥቂት ቆይታ በኋላ ቤቱ በሰዎች ግርግርና ጨኸት ተሞላ።
የፖሊስ ምርመራ…
ፖሊስ ለሊቱን ጣልያን ሰፈር ከሚገኘው መኖሪያቤት ሲደርሰ የወይዘሮዋ ህይወት አልፎ ነበር። የትንሹ ልጅ ልብስ በደም መበከሉን ያዩ ሰዎች ልብሱን አውልቀው ገላውን አጠቡ። ፖሊስ ሙሉ መረጃ ሰብስቦና አስከሬኑን በወጉ መርምሮ ስለተጠርጣሪው ጠየቀ። ረዳት ኢንስፔክተር ሲሳይ ተሾመ በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 842/11 በየቀኑ የሚገኙ መረጃዎችን እየሰነደ ተፈላጊውን አባወራ ማሰስ ጀመረ።
በችሎት ፊት…
ጥር 5 ቀን 2012 ዓ.ም የልደታ ከፍተኛ ፍርድቤት ችሎት ተሰይሟል። ባልተገባ የቅናት ስሜት ተነሳስቶ የልጆቹን እናት ህይወት በሽጉጥ ያጠፋው አባወራ ከችሎት ፊት ቀርቧል። ፍርድቤቱ ግለሰቡ የፈጸመውን ከባድ ሰው መግደል ወንጀል በማስረጃዎች አያይዞ ጥፋተኝነቱን አረጋግጧል። የአዳራሹ ታዳሚ በዝምታ እንደተዋጠ ነው። ዳኛው የመጨረሻውን የፍርድ ውሳኔ ማንበብ ጀመሩ። ግለሰቡ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የሃያ አመት ጽኑ እስራት ይቀጣ ሲሉም ብይን አሳለፉ።
ከችሎት በኋላ
የውሳኔው መዝገብ እንደተዘጋ አንድ ደብዳቤ ከዓቃቤህግ ለፍርድቤቱ ችሎት ደረሰ፡፡ ደብዳቤው በምስክርነት የቀረበው የሟችና ገዳይን ታዳጊ ልጅን ጉዳይ ይመለከታል፡፡ በምስክር አሰጣጥ ጊዜ ልጁ የአባቱን ስም ቀይሮ በአያቱ ስም መጠራት ጀምሯል ፡፡ልጁ ለዚህ ያቀረበው ምክንያትም አባቱ ወላጅ እናቱን በሽጉጥ ሲገድል ማየቱንና ከዚህ በኋላም በስሙ መጠራት ያለመፈለጉን ነው፡፡
መልካም ስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም