አሁን ላይ ሀገራችን በብዙ መሰናክሎችና ፈተናዎች እየተናወጠች ትገኛለች። ፈተናዎቿና መስናክሎቿ እየበዙ፣ ሰላሟ እየተናወጠ የሚገኘው በአንዳንድ ፀረ ሰላም ኃይሎች ሴራ፣ እንደሆነም ይታወቃል ። የቀደሙት ጀግኖች አርበኞች ከወራሪ ጠላት ለማዳን ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉባት ይህች ሀገር ፤ ዛሬ ላይ በውስጥና በውጭ ሀይሎች በሚያጋጥሟት ሴራ ታሪኳን የሚያጎድፍ ፈተና ውስጥ ገብታለች ።
የቀደሙት ጀግኖች አርበኞች ሀገርን ለትውልድ ያስረከቡበትን እውነት ሳስብ በአእምሮዬ እየተመላለሰ እረፍት የሚነሳኝ ሀሳብ ውስጥ እገባለሁ ። ሀገር ተረካቢዎቹ እኛስ ! ለቀጣዩ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ምን እናስተላልፍ ይሆን? የሚለው ጥያቄም በውስጤ ይመላለሳል ። ‹‹አልሰሜን ግባ በለው›› አለ የሀገሬ ሰው›› ይሄኔ ነው! ቀኙና ግራውን፤ ፊትና ኋላውን በአጠቃላይ ዙሪያ ገባውን መማተር የግድ የሚሆነው።
ወዳጆቼ ! ይህንን ስላችሁ ስለማታወቁት ነገር ላወጋችሁ ፈልጌ አይመስላችሁ ። የቀደሙትን ፈለግ በመከተል ሀገር ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ለማድረግ የእኛን ሚና በምን ሚዛን ይመዘን ይሆን ለማለት ነው! ይህን ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም ። ‹‹ውሻ በቀደደው ጅብ —- ይባል የለ› ›። የቀደሙት እንደ እንቁ ተንከባክበው ያቆዩዋትን ይቺን ሀገር! አንዳንዶች የሀገር አሳቢ ነን ባዮች አንድነቷን ያስጠበቁ መስለው ሲንከባከቧትና ሲያንቆለጳጵሷት መመልከቴ ድንቅ ብሎኝ ፤ እጅግ ብገረም ትንሽ ላወጋችሁ ብዕሬን ከወረቀት አገናኘሁ!።
ወዳጆቼ! አሁንማ እድሜ ለዘመነ ቴክኖሎጂ ይሁንና! አንዳንድ ጀብደኞች ከያሉበት ሆነው ከቀደሙት ልቀውና መጥቀው፣ ለሀገር ተቆርቆሪ መስለው ሲታዩ ማየትን ለምደነዋል። ታዲያ ሁኔታቸው አያስገርምም ትላላችሁ ፤ እንክት! በደንብ ነዋ የሚያስደምመው።
በእነዚህ ለሀገር ተቋርቆሪ ነን ባዮች የሚፈጸሙ እኩይ ተግባር ደግሞ ዘመኑን የማይመጥን መሆኑ ቁልጭ ብሎ ይታያል። በዚህ በሰለጠነ ዓለም ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት መፍታት በሚቻልበት ወቅት ላይ ሆነን እንኳን ሀሳብን በሀሳብ ብልጫ ከማሽነፍ በዘለላ በአረጀ ባፈጀ አስተሳሰብ በመታጠር ሀገር ማተራማስ ከጊዜው ጋር የሚጣጣም ተግባር አይደለም።
በዚያን ዘመንና አሁን ላይ ለሀገር ሉአላዊነትና ለህዝብ አንድነት ሲባል የሚከፈለው ዋጋ ለየቅል መሆኑም መገንዘብን ይሻል። የያኔዎቹ አይረሴ ጀግኖች የሀገር ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ጦር ግንባር ድረስ ዘልቀው ከጠላት ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው ተፋልመዋል ። የአሁኖቹ ጀበደኞች ደግሞ ጦር ሜዳ መዝለቅ ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ቦታ ሆነው በፈለጉት የመሳሪያ አይነት ተጠቅመው፣ ተፋልመው እያፋለሙ መሆናቸው አይረሴ ያደርጋቸዋል ። ማንነታቸውን ደብቀው ፊትለፊት ከመጋፈጥ ይልቅ በውስጥ ደባና ሴራ ያሰቡበት ለመድረስ የሚያልሙ እንደሆነ ነጋሪ የማይሻው ተግባራቸው ምስክር ነው።
ወይ ጉድ አሉ እማማ! ሁሉን ቢናገሩት ፤ ሆድ ባዶ ይቀራል እንዲሉ ። እነ እንቶኔን ለየት የሚያደርጋቸው እንደ ቀደሙቱ ጦር ሜዳ መሰለፍ ሳያስፈልጋቸው ካሉበት ቦታ ሆነ መሳሪያቸው ሰብቀው በመዋጋት የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር ሳይሆን ሀገርን ለማፍረስ ታጥቀው መነሳታቸው ነው። ሀገር እንደሀገር እንዳይቀጥል የማይሸርቡት ሴራ፣ የማይፈነቀሉት ድንጋይ የለም።
የቀደሙቱ ጀግኖች በአዋጅ ነጋሪ በተላለፈ የክተት ጥሪ መሠረት ከያሉበት ተጠራርተው ‹አለሁልሽ ሀገሬ› ያሉበትና የሀገር ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ ፣ በአንድነት ሆ ! ብለው የተመሙበትን እያወሳን ኖረናል። ምን ያደርጋል ቅሉ፤ ዛሬ ላይ በማህበራዊ ሚዲያ ሀሰተኛ ወሬን በማራገብ ለሀገር መፈራረስ እየሰሩ ለሀገር አንድነት ከኛ ወዲያ ለአሳር ይሉናል እነ እንቶኔ! ። እውነት ነው! ዓለም በቴክኖሎጂ በዘመነበት በዚህን ጊዜ ያለው ጥበብና ዘዴ ከሌላው ጊዜ ይለያል። እንዲህ ዓለም በአንድ መስኮት በሚተያይበት በዚህ ዘመን ያለ ጀግነት ግን እውን ለየት ይላል ። ሁሉ በእጄ፣ ሁሉ በደጄ ፤ አይነት ነው። በቴክኖሎጂ በይነ መረብ በመጠቀም በሴኮንድ ውስጥ አይደለም ኢትዮጵያ ፤ ዓለም በአንድ እግሯ ለማስቆም የሚቻል እንደሆነ ይታወቃል። ችግር ምናአባቱ ከነምናምንቴው ገደል ይገባ ያሰኛል ! በቴክኖሎጂ መታገዝ መሳሪያን በእጅ አቀባብሎ መተኮስ ብቻ ነው የሚጠይቀው። ታዲያ እነ እንቶኔ! ለዚህ ማን ብሎአቸው፤ ስንፍና ብሎ ነገር አይታሰብም። በሀገር ሉአላዊነትና በህዝቦች አንድነት በኩል የመጣን ጠላት አፈር ከመሬት ለመደባለቅ ትርምስመሱን ለማውጣት ቀን ከሌት እየደከሙ አይደል ?
ወዳጆቼ! እንግዲህ እነዚህ የሀገር ባለውለታ ብንላቸው ያንስባቸው ይሆን ? ። በዚህ ዘመን ከእነዚህ በላይ ማን ተግባረ ሰናይ ይገኝ ይሆን!። የእነ እንቶኔን ሥራ ከጥንስሱ ጀምሮ ቆጥረን አንጨርሰውም በጥቂቱ ግን ከእፍታው ጀባ ለማለት ወደደኩ ። በተለይ ከሦስት ዓመታት ወዲህ ሀገራችን በአራቱም አቅጣጫ ከድጡ ወደ ማጥ እንድትገባ በማድረግ ሀገር የማፍረስ የደረጉት ጥረት የጀብደኞቹ ልዩ ገድል ስለ መሆኑ የሚዘነጋ አይኖርም ።
በመከራ ላይ መከራ በመደራረብ ፤ ሀገር እንዳትረጋጋ በማድረግ ፤ህዝብን ለስደትና ለእንግልት በመዳረግ፤ በየቦታው ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶ በስጋት ውስጥ እንድንዋትት አብክረው እየተጉ መሆናቸውስ እንዲያው በቀላሉ የሚረሳ ነው? በየማህበራዊ ሚዲያ በሚያሰራጩት መርዝ ሀገርን በማተራመስ፤ ህዝብን ከህዝብ ፤ ብሄርን ከብሔር ፤ ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በሚያሴሩት ሴራስ የሚያገዳደራቸው ይኖር ይሆን ? ያለ፣ የሌላ ኃይላቸውን ተጠቅመው ሀገር ለማፍረስ እየሰሩ መሆናቸው እኮ የአደባባይ ሚስጥር ነው ።
ኧረ ስንቱን እናወጋው! በአራቱ ማዕዘናት እሳትን በመጫር ትርምስ በመፍጠር ህዝቡን ወደአልተፈለገ ግጭት እንዲገባ አድርጎ ሀገርን ለማፍረስ እጅግ ስውርና ጥልፍልፍ ሴራን የመፈጸም ተልዕኮን አንግበው የመነሳት የእኩይ ተግባር ማሳያ አይደለም እንዴ? ይህንን ልማድና ተግባር ከወዴት ይሆን ያመጣነው ? ከዚህ የሚልቀው እጅግ በሚገርም ሁኔታ መላቅጡ የጠፋበትን ነውረኛ ተግባር ይፈጸማሉ ። ከውጭ ባላንጣዎች ጋር መተባበር ሀገር ለማፈራረስ ማለም ምን የሚሉት ድንቁርና ይሆን! የነውር ሁሉ ነውር ፤ የሀገር ክህደት። በአራቱንም ማዕዘናት መረባቸውን ዘርግተው የወገኖቻቸው ደም ከማፈሰስ የበለጠ ምን የጨካኔ ድርጊት ሊገኝ?።
በቅርብ እንኳን የብሔራዊ የመረጃና ደህነት እንዳስታወቀው በተለያዩ ጊዜያት ሀገርን የማፍረስ ሴራን አንግበው ከውስጥ እስከ ውጭ ሀገራት በፈጠሩት ሰንሰለት የሚካሄድ የሸብር ድርጊትን ለመፈጸም የተሰማሩ አካላት ሴራ እየከሸፈ መሆኑ ተነግሯል። በዚህ ጉዳይ የተገለጹት አካላት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ናቸው። በወገኖቻቸው ላይ የጭካኔን ተግባር ለመፈጸም አልመው የተነሱ እንደነበርም ዕሙን ነው።
ወዳጆቼ! የኢትዮጵያን ትንሳኤ ከማይፈልጉ አካላት ጋር መተባበር እብደት አይደለም እንዴ? ። የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እንደ ጀርባ ቅማል ጥብቅ ብለው ከትከሻዋ ላይ አንወርድም ያሉት የግብጽና ሱዳን ተልዕኮ ማስፈጸሚያ አሽከር መሆንስ ለማመን የሚከብድ አይደለም? ይህ ተግባርስ የአሁኑ ትወልድ ብቻ ሳይሆን የመጪውን ትወልድ እጣ ፈንታ የሚጎዳ መሆኑን ለመገንዘብ የሚከብድ ነው ወይ? ‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› አሉ እማማ ! በቅርቡ ሱዳን የእውር ድንብር በሆነ ምኞቷ በቤንሻንጉል ጉምዝ ድንበር የይገባኛል ጥያቄ ለማቅረብ ድፍረት ማግኘቷ እንኳን የውስጥ ችግሮቻችንን በመመልከት በደካማ ጎናችን ለመግባት ያሰበች ስለ መሆኑ ማሳያ ነው።
የጉድ ሀገር ገንፎ…. አያሰኝም ታዲያ ! እነዚህ ሀገር ውስጥ ቁጭ ብለው በሀገራቸው እጣ ፈንታ ላይ የሚጣጠሉ፤ በፖለቲካ ሴራቸው በወገኖታቸው ደም በማፍሰስ ስልጣን የሚመኙ ሀይሎችን ምን እንላቸው ይሆን ? እውን ይቺ ምድረ ገነት፤ ማህጸነ ለምለም የሆነችው ሀገር ነች እነሱንም ያፈራችው። በእርግጥ አንድነቱንና ነጻነቱን አስጠብቆ፤ በመቻቻልና በመከባበር ከኖረው ከዚህ ኩሩ ህዝብ መካከል ነው የወጡት ብሎ ለማሰብ የሚከብድ ነው ።
ከእነ እንቶኔ ተግባር እጅግ መራራ የሚያደርገውና ይበልጥ ግርምት የሚፈጥረው ደግሞ ለእነዚህ የውጭ ኃይሎች ስውር ዓላማ አስፈጻሚ ሆኖ መገኘት ነው። ከላይ ሀገር ወዳድ ለሀገር ተቆርቆሪ መሆናቸውን እየሰበኩ ውስጥ ውስጡን ግን እንደምስጥ እየማሱ ሀገርን ለማፍረስ ያሴራሉ። በተከታዮቻቸው አማካይነት በራሳቸው ሀገርና ህዝብ ላይ ደባ እየፈጸሙ ወገኖቻቸውን ለእልቂት የሚዳርጉ ተግባራትን በመፈጸም የሚረኩ ናቸው። እነዚህ አይናቸውን ጨፍነው፤ ሆዳቸውን ከፍተው፤ የሀገር ህልውናን ለባዕድ ሸጠው የሚኖሩ ራስ ወዳዶች ናቸው።
የራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ ይፈጸምላቸው ዘንድ እንጂ! ስለ ሀገርና ህዝብ አያገባንም ፤አይመለከተንም ባዮች ዓላማቸው አንድና አንድ ሀገርን ማፈረስነውና በሚፈጸሙት እኩይ ተግባር በርካታ ዜጎች መሰዋዕት ሆነዋል። ለዚህም ነው ያሰቡትንና ያለሙትን መፈጸም እንጂ ስለምንም ነገር ደንታ የለሽ መሆናቸው።እነሱ በህዝብ ላይ የፈጸሙት እኩይ ተግባር ቅንጣት ታህል ሳይሰማቸው ፤ ሌላ እኩይ ተግባር ለመፈጸም ያልማሉ። ሀገር በማተራመስ ፤ ህዝብ ለዛውም የራስ ወገንን ለችግር በመዳረግ የሚደሱት ናቸው። ለዚህም ነው እኩያ ተግባራቸው ከሰብዓዊነት የወጣው ስለመሆኑ , እያየን ያለነው።
የእነ እንቶኔ! ዓላማ፣ ድብቅ ሴራውም ጥልቅ ነው። በፖለቲካ ሀሳባቸው ህዝብ ከህዝብ ፤ ሃይማኖት፣ ከሃይማኖት እስካልተላተመ ድረስ ተቀባይነት የሚያገኙ አይመስላቸው። ለሚሰሩት ደባ ማህበራዊ ሚዲያዎች ዋንኛ መሳሪያቸው ናቸው። ለዚሁ ተግባር የመለመሏቸው የእኩይ ተግባራቸው ደጋፊዎች ጫፉን አሲዘው እንዲያረግቡት ያደረጋሉ። እያንዳንዱን ጉዳይ አጀንዳ አድርገውም ለሀገር አሳቢና ተቆርቋሪ ሆነው ይቀርባሉ። አሁንም አንዱን ከአንዱ እያምታቱ መኖርን ተያይዘውታል።
አንድን ሃይማኖት ወግነው አንዱን ላይ እያጥላሉ ብጥብጥና ሁከት ለመፍጠር ይጣጣራሉ። ፍጹም ፍላጎታቸው ሀገር በማተራመስ ትርፍ ማግኘት ነውና ሰላም እንዲሰፈን የሚደረገውን ጥረት ውስጥ ጋሬጣ በመሆን እያደናቀፉ ይገኛሉ። የፌስ ቡክ ካምፓኒ ባለፈው እንዳሳወቀው ውጭ ሆነው ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ ክፉ ተግባር የሚፈጸሙ አካላትን ለመመልከት ችለናል። ኢትዮጵያ ባለንጣዎቿ እየበዙባት ያለች ሀገር ስለመሆኗ ይህ እውነታ ምስክር ነው።
ይህን አይነቱን መርዝ የሚረጩ አካላት ዞሮ ዞሮ የጀርባው መጋረጃ ሲገለጥ ድብቁ ሴራቸው ይፋ ሆኖ ተጠያቂ መሆናቸው አይቀሬ ነው። ዛሬ የነገዱበትን ሀገርና ህዝብ በፍርድ ፊት አደባባይ የሚቆሙበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። አዎ! የእንቶኔን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወት ተብሎ ነበር።ሰሚ ጆሮና አስተዋይ ልቦና የት ይገኝና። አሁን ኢትዮጵያ ወደከፍታ እያደረገች ያለውን የለውጥ ጉዞ ለመቀልበስ የሚጥሩ ቢኖሩም ፤ መቼም ቢሆን አይሳካለቸውም።
የእነንቶኔ እኩይ ተግባር ተሸሽጎ አይቀርምና ህዝቡ፤ የእያንዳንዱ ሀገር ወዳድ ዜጋ የዜግነት ግዴታ መወጣት ይጠበቅበታል። ‹‹ሀገሬ ለእኔ ምን ስራችልኝ›› ሳይሆን ‹‹እኔ ለሀገሬ ምን ሰራሁላት ›› ማለትን ነውና ከቀደሙት የተማርነው። የቀደሙት አባቶቻችን ያቆዩልን ሀገር ተንከባክበን ለትውልድ የማስተላለፍ አደራ አለብን። አደራውን በአግባብ መወጣት ቢያቅተን እንኳን ሀገርን ለማፍረስ ያለመ ሴራን የሚፈጽሙ አካላት ፈጽሞ አላማቸው እንዲሳካ አንፍቀድላቸው። ትውልድ ያልፋል ሀገር ግን ይቀጥላል። በሀገራችን የተጀመረውን ፈጣን ለውጥ ማገዝ ባንችልም የለውጥ ጉዞው እንቅፋት ላለመሆን እንሞክር ።
እየሩስ አበራ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2013