ፍሊፒናዊቷ ጋዜጠኛና ደራሲ ማሪያ ሬሳ በስም ማጥፋት ወንጀል ታስራ በዋስ መፈታቷ የፕሬዚዳንት ሮድሪጎ ዱቴርቴ መንግሥት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ላለማክበር የሚያደርገው ትግል ማሳያ እንደሆነ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ገልጸዋል፡፡ ‹‹ራፕለር (Rappler)›› የተባለው ድረ-ገፅ ተባባሪ መስራችና ስራ አስኪያጅ የሆነችው ሬሳ ከትናንት ወዲያ የፍሊፒንስ ፍትህ መስሪያ ቤት አካል በሆነው በብሔራዊ ምርመራ ቢሮ ባልደረቦች በቁጥጥር ስራ ውላ እንደነበር ተዘግቧል፡፡
ጋዜጠኛዋ በቁጥጥር ስር በዋለችበት ወቅት ‹‹የፍሊፒንስ መንግሥት የቱንም ያህል የውሸት ክስና ፕሮፖጋንዳ ቢያቀርብም ትክክለኛውን መስመር የያዙ ፍሊፒናዊያን ጋዜጠኞችን ከመንገዳቸው ሊያስተጓጉላቸው አይችልም፡፡ እርምጃው መንግሥት መገናኛ ብዙኃንን ለማፈን ምን ያህል እርቀት እንደሚጓዝ አመላካች ነው›› ብላለች፡፡ የፍሊፒንስ ብሔራዊ ምርመራ ቢሮ ባልደረቦች ሬሳን በቁጥጥር ስር ያዋሏት የመንግሥት የሥራ ሰዓት ተጠናቆ ቢሮዎች በሚዘጉበት ምሽት ላይ መሆኑ ሬሳ ዋስትና እንዳትጠይቅ ታስቦበት የተደረገ ነውም ተብሏል፡፡ የፍሊፒንስ ጋዜጠኞች ብሔራዊ ማኅበር (National Union of Journalists of the Philippines – NUJP) ‹‹እርምጃው አሳፋሪ ተግባር ነው›› በማለት የጋዜጠኛዋን እስራት አውግዟል፡ ፡
የፍሊፒንስ መንግሥት ተቃውሞንና ቅሬታን ለማስተናገድ ፈቃደኛ ባለሆነ ሰው የሚመራ በመሆኑ መገናኛ ብዙኃንንና ሃሳብን በነፃነትን የመግለፅ መብትን ለማዳከም ረጅም እርቀት መጓዙ እንደማያጠራጥር ኅብረቱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ ከፍሊፒንስ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው አክባያን (Akbayan) ፓርቲ የማሪያ ሬሳን መታሰር ኮንኗል፡፡ ፓርቲው ባወጣው መግለጫ፣ የጋዜጠኛዋ መታሰር መንግሥት የፕሬስ ነፃነትን በኃይል ለማፈን ከሚወስዳቸው እርምጃዎች መካከል አንዱ በመሆኑ እርምጃውን በጥብቅ እንደሚኮንነው አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ‹‹የማሪያ ሬሳ መታሰር እውነትን ለሚናገሩ ሁሉ የተሰጠ የማስፈራሪያ ምልክት ነው፡፡ የዱቴርቴ መንግሥት እውነተኛና ፍትሃዊ የጋዜጠኝት ስራን እንደሚፈራም ማሳያ ነው›› ብሎታል፡፡
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የፍሊፒንስ ቅርንጫፍ(Amnesty International Philippines) የጋዜጠኛዋ እስራት ፖለቲካዊ ዓላማ ያለውና የፍሊፒንስ መንግሥት በማሪያ ሬሳና በባልደረቦቿ ላይ የጀመረው የማስፈራያና የአፈና እርምጃ አካል እንደሆነ ገልጿል፡፡ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ኢንስቲትዩት (International Press Institute – IPI) የተባለው የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበርም የጋዜጠኛዋን እስራት አውግዟል፡፡ የማሪያ ሬሳ መታሰር ፍሊፒንስ ውስጥ የሚፈፀሙትን የሙስናና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በድፍረት የሚያጋልጠውን የዜና አውታር ለማዳከም የተወሰደ የተሳሳተ እርምጃ ነው በማለት ከጋዜጠኛዋና ከድረ-ገፁ ጎን እንደሚቆም ይፋ አድርጓል፡፡ ራቪ ፕራሳድ የተባሉ የተቋሙ የስራ ኃላፊ ‹‹ሬሳ የታሰረችበት ምክንያት አሳፋሪ ብቻም ሳይሆን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና የፕሬስ ነፃነት ላይ የተፈፀመ የመብት ጥሰት ነው›› ብለዋል፡፡
የፍሊፒንስ መንግሥት የጋዜጠኛዋ እስራት ፖለቲካዊ ይዘት አለው መባሉን አስተባብሏል፡፡ የፕሬዚዳንት ሮድሪጎ ዱቴርቴ ቃል አቀባይ ሳልቫዶር ፓኔሎ እንደተናገሩት፣ ጋዜጠኛ ማሪያ ሬሳ የፕሬዚዳንት ዱቴርቴ አስተዳደርን መተቸቷ አሁን ከታሰረችበት ጉዳይ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ አስተዳደሩ የፍርድ ቤት ውሳኔን እንደሚያከብርና በውሳኔው ላይ ጣልቃ እንደማይገባም ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንት ሮድሪጎ ዱቴርቴ ‹‹ራፕለር››ን ጨምሮ በአስተዳደራቸው ላይ የሰላ ትችት የሚያቀርቡ ሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትን በታክስ ማጭበርበር ሊከሰሱ እንደሚችሉ አስፈራርተዋቸው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት የፍሊፒንስ ዓቃቢያነ ሕግ ማሪያ ሬሳን እስከ አስራ ሁለት ዓመታት እስር ቤት የሚያቆይ የስም ማጥፋት ክስ እያዘጋጁ እንደሆነ ተናግረው ነበር፡ ፡ ጋዜጠኛዋ በቁጥጥር ስር የዋለችበት የስም ማጥፋት ጉዳይ አጅግ አወዛጋቢ በሆነው የሳይበር ወንጀል ሕግ (Cybercrime Law) በተባለው የአገሪቱ ሕግ የሚታይ ነው ተብሏል፡፡ ይህ ሕግ ድንጋጌ በማሬያ ሬሳና በድረ-ገፁ ላይ ተጨማሪ ጫና የሚፈጥር እንደሆነና ጋዜጠኛዋን ለእስራት ሊዳርግና የድርጅቱን ሕልውናም አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ተገልጿል፡፡ ‹‹ራፕለር (Rappler)›› የተባለው ድረ-ገፅ የፕሬዚዳንት ሮድሪጎ ዱቴርቴን አስተዳደር ድክመቶች ነቅሶ በማውጣት የሚታወቅ የዜና አውታር ነው፡፡ በተለይ ድረ-ገፁ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት በዳረገው የፕሬዚዳንቱ የድረ-ገፅ ዘመቻ ላይ የሰራቸው
ዘገባዎች ከመንግሥት ጋር ክፉኛ ያቃቃሩት ስራዎቹ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ማሪያ ሬሳን ለእስር የዳረጋት ጉዳይ እ.አ.አ በ2012 የድረ-ገፁ የቀድሞ ባልደረባ ከነበረው ከሬናልዶ ሳንቶስ ጋር ከሰሩት ዘገባ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
በወቅቱ በአንድ የአገሪቱ ፍርድ ቤት ዳኛና በአንድ ባለሀብት መካከል የነበረውን ግንኙነት ያጋለጡበት ዘገባ የአገሪቱ የሳይበር ወንጀል ሕግ ተጠቅሶ በስም ማጥፋት ወንጀል እንዲፈለጉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ የሳይበር ወንጀል ሕጉ የወጣውና ተፈፃሚ መሆን የጀመረው ሬሳና ሳንቶስ ዘገባውን ሰርተው ለሕዝብ ይፋ ከሆነ በኋላ ነው፡፡ የፍሊፒንስ ጋዜጠኞች ብሔራዊ ሊቀ-መንበር ፕሬዚዳንት ኖኖይ እስፒና የሳይበር ወንጀል ሕጉ እጅግ አደገኛና የፕሬስ ነፃነትን ለማፈን ሆነ ተብሎ የተዘጋጀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ማሪያ ሬሳ በዋስ ከተለቀቀች በኋላ በሰጠችው አስተያየት፣ ‹‹እርምጃው ስልጣንን አላግባብ ከመጠቀምና ሕግን ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ መሳሪያ ከማድረግ ጋር ይያያዛል፡፡ የፍሊፒንስ ዴሞክራሲ በየዕለቱ እየሞተ ነው›› ብላለች፡፡
የ55 ዓመቷ ፍሊፒናዊቷ ጋዜጠኛና ደራሲ ማሪያ ሬሳ ዝነኛና አወዛጋቢ ከሆኑ ፍሊፒናዊያን ጋዜጠኞች መካከል አንዷ ስትሆን፣ ዝነኛውና አንጋፋው ‹‹ታይም (Time)›› መጽሔት ‹‹የ2018 የዓመቱ ሰው (Person of the Year)›› ብሎ ከመረጣቸው ግለሰቦች መካከል አንዷ ከመሆኗ በተጨማሪ የጋዜጠኞች ጥበቃ ኮሚቴ (Committee to Protect Journalists – CPJ) የ2018 የዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ሽልማት (International Press Freedom Award) አሸናፊ ናት፡፡
በስራ አስኪያጅነት የምትመራው ‹‹ራፕለር›› ድረ-ገፅ በሙስናና በፀረ-አደንዛዥ እፅ ዘመቻ ጉዳዮች ላይ በሚሰራቸው ዘገባዎች ምክንያት ለተደጋጋሚ እስራት ተዳርጋለች፡፡ እ.አ.አ በ2016 ዓ.ም የደቡብ ምስራቅ እስያዊቷ አገር ፍሊፒንስ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ሮድሪጎ ዱቴርቴ መንበረ ስልጣኑን ከጨበጡ በኋላ በአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪዎችና ተጠቃሚዎች ላይ በሚወስዱት እርምጃ የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱ ጉዳዩ ከሀገሪቱ ፖለቲከኞች አልፎ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ጭምር እያወዛገበው ይገኛል፡፡ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች በበኩላቸው የፕሬዚዳንት ሮድሪጎ ዱቴርቴ ፀረ-አደንዛዥ እፅ ዘመቻ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል እንዲጣራ ጠይቀው ነበር፡፡
የፕሬዚዳንት ሮድሪጎ ዱቴርቴ አስተዳደር በአደገኛ እፅ አዘዋዋሪዎች ላይ በሚወስዳቸው እርምጃዎች ምክንያት ተደጋጋሚ ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከነዚህም መካከል ‹‹አስተዳደሩ አደገኛ እፅ አዘዋዋሪዎች ናቸው የተባሉ ግለሰቦች ላይ የሚወስደው እርምጃ ሕጋዊ አሰራርንና ማጣራትን የተከተለ ሳይሆን ቀጥተኛ የሆነ የግድያ እርምጃ ነው›› የሚለው ክስ ይጠቀሳል፡፡ የግድያ እርምጃ ከተወሰደባቸው ግለሰቦች መካከል ጥፋተኛ ያልሆኑ እንደሚገኙበትም የፕሬዚዳንቱ ተቃዋሚዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሲገልፁ ቆይተዋል፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት አልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ በፕሬዚዳንት ዱቴርቴ ፀረ አደንዛዥ እፅ ዘመቻ ላይ ሰራሁት ያለው የምርመራ ዘገባና ዘጋቢ ፊልም አስተዳደሩ በአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪዎች ላይ የሚወስደው እርምጃ ጥያቄ እንዲነሳበት ያደርጋል፡፡ የአገሪቱ ፖሊስ መሳሪያ ያልታጠቁና እጃቸውን ለፖሊስ በሰጡ ግለሰቦች ግድያ ላይ እንደተሳተፈ የምርመራ ዘገባዬ ያመለክታል ሲል ጣቢያው ይፋ አደርጎ ነበር፡፡ በፖሊስ የሚገደሉ ልጆችን የተመለከቱ ሌሎች ሪፖርቶችም፣ የአደንዛዥ ተጠቃሚ ሳይሆኑ አይቀሩም የተባሉ ልጆች በአገሪቱ ፖሊስ አባላት መገደላቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ‹‹ፍሊፒንስ ውስጥ በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል›› ነው እየተባለ የሚነገረው የዱቴርቴ ፀረ አደንዛዥ እፅ ዘመቻ፣ መቀመጫውን ሄግ ካደረገው ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (International Criminal Court)ም ከወቀሳ አልዳነም፡፡
‹‹ሂውማን ራይትስ ዎች (Human Rights Watch)›› የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የፕሬዚዳንት ዱቴርቴ የፀረ አደንዛዥ እፅ ዘመቻ ከ12ሺ በላይ ለሆኑ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት እንደሆነ ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ የፀረ አደንዛዥ እፅ ዘመቻቸውን አስመልክቶ ከተለያዩ አካላት ለሚቀርብባቸው ወቀሳ የሚሰጡት ምላሽ እስራት፣ ግድያና አፈና እንደሆነ ድርጅቱ በሪፖርቱ ገልፆ ነበር፡፡ ለአብነት ያህልም ፕሬዚዳንት ሮድሪጎ ዱቴርቴን በመተቸት የሚታወቁትና ከፀረ-አደንዛዥ እፅ ዘመቻው ጋር በያያዘ የተገደሉ ሰዎች ጉዳይ በአገሪቱ ሴኔት እንዲጣራ የምርመራውን ጉዳይ ይመሩ የነበሩት ለይላ ዴ ሊማ የተባሉ ሴናተር ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮችና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ተቃውሟቸውን አጠንክረው ቢገልፁም፣ የፕሬዚዳንት ዱቴርቴ አስተዳደርና የአገሪቱ ፖሊስ ኃይል ‹‹ሁሉም ግድያዎች የተፈፀሙት ሕጋዊ የሆኑ የፀረ-አደንዛዥ እፅ ዘመቻዎች በተካሄዱበት ወቅት ነው›› በማለት ደጋግመው ተናግረዋል፡፡
እ.አ.አ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም የደቡብ ምስራቅ እስያዊቷ አገር ፕሬዚደዳንት ሆነው የተመረጡት ሮድሪጎ ዱቴርቴ፣ በአገሪቱ የተንሰራፋውን የአደንዛዥ እፅ ዝወውር ለመግታት እንደሚሰሩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቃሳ ዘመቻቸው ወቅት አፅንኦት ሲናገሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2011
አንተነህ ቸሬ