ኢትዮጵያ አገራችን ለዘመናት ዳር ደንበሯን አስከብራ፤ ነፃነቷንም ጠብቃ ተከብራና ታፍራ የኖረች፤ አኩሪ ታሪክ ያላት መሆኑን ወዳጅም ጠላትም የሚመሰክረው ሐቅ ነው። ይህ የረጅም ዘመን ነፃነትና አኩሪ ታሪክ በተአምር የተገኘ አይደለም።
በየጊዜው ከሚነሱ ወራሪዎችና የቅኝ ግዛት የማስፋፋት ዓላማ ከነበራቸው ቅኝ ገዥዎች ይሰነዘርብን የነበረውን ጥቃት እንዲሁም ከአባይ ወንዝ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ግብጾች ሲያካሂዱብን የኖረውን ሥውር ደባ አባቶቻችን በመመከታቸው ነው። አባቶቻችን በመካከላቸው ሊኖሩ የሚችሉ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው አንድነታቸውን አጠንክረውና ኃይላቸውን አስተባብረው ለብሔራዊ ጥቅማቸውና ለነፃነታቸው ቅድሚያ በመስጠት ወራሪ ኃይሎችንም ሆነ ሥውር ደባ ፈፃሚዎችን እንደ አመጣጣቸው በጀግንነት እየተዋጉ አሳፍረው መልሰዋል። ይህም አኩሪ ታሪክ በመስዋዕትነት የተመዘገበ ነው።
ከዚህ ላይ በአሁኑ ጊዜ በህይዎት ያለነው ኢትዮጵያውያን በጥልቀት ልንረዳውና ልናሰምርበት የሚገባን ቁም ነገር አለ። በየዘመኑ የነበሩ አባቶቻችን በየወቅቱ በነበሩት ገዥዎች አመራር ላይ ቅሬታ ወይም የሃሳብ ልዩነት ሳይኖራቸው ቀርቶ ሳይሆን የአገር ሉዓላዊነትን በማስቀደማቸው ነው። ለህዝብ የጋራ ደህንነትና ለአገር ዳር ደንበር መከበር ቅድሚያ በመስጠት ልዩነቶቻቸውን አቻችለው የጋራ ጠላታቸውን በጋራ ለመቋቋም ተባብረው በመሰለፋቸው ይሰነዘርባቸው የነበረውን ጥቃት ሁሉ በአቸናፊነት ሲወጡ መኖራቸውን ጭምር ነው፤
ከታሪክ እንደምንረዳው ኢትዮጵያ አገራችን በአንዱ ወይም በሌላው ምክንያት ከውጭ ኃይሎች ተጽዕኖና ሥውር ደባ ነፃ ሁና የራሷን የልማት አጀንዳ በሰላም ለማከናዎን የቻለችበት ዘመን አልነበረም ቢባል ማጋነን አይመስለኝም። በየጊዜው የነበሩት መሪዎቻችንም አገሪቱን ለማልማትና የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል ቢጥሩም በዚሁ ከላይ በገለጽኩት ምክንያት ሳይሳካላቸው እየቀረ አገራችን አሁን ባለችበት የዕድገት ደረጃ ላይ ለመገኘት ተገዳለች።
በእነዚሁ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ተጽዕኖና ሥውር ደባ አገራችን በልማት ለማሳደግና የህዝባችንም ኑሮ ለማሻሻል አባቶቻችን ያደርጉት የነበረውን ጥረት እንዳይሳካ ሲያደርግ ቢቆይም ብሔራዊ አንድነታችን ለማናጋትና ዳር ደንበራችን ለመድፈር የነበራቸው ዓላማ ግን አልተሳካላቸውም። አርቆ አስተዋይ በሆኑት ጀግኖች አባቶቻችን የተባበር ትግልና በተከፈለ አኩሪ መስዋዕትነት እያሳፈሩ ሲመልሷቸው እንደቆዩ የጀግኖች አባቶቻችን አኩሪ ታሪክ የሚያረጋግጠው ሐቅ ነው፤
ይህን የአባቶቻችን ብሔራዊ ጥቅማቸውንና ነፃነታቸው ለማስከበር ልዩነቶቻቸውን ትተው በአንድነት በመቆም ጠላቶቻቸውን አሳፍረው ይመልሱበት የነበረውን የትግል ስልት አሁን ያለነው ትውልዶች እንደህይዎት መመሪያችን አድርገን ልንከተለው እንደሚገባ ለማሳሰብ እወዳለሁ፤ በረጅሙ የታሪክ ዘመናችን በተለያዩ ጊዜያት በአውሮፓ ወራሪ ኃይሎች የተሰነዘሩብንን ጥቃቶችና በጀግኖች አባቶቻችን የተባበረ አንድነትና ፅኑ ተጋድሎ በኢትዮጵያ አቸናፊነት የተደመደሙትን ጦርነቶች መጥቀስ ይቻላል። በቅርቡ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ እንኳን በግብጾች የተካሄደብንን ሥውር ደባና የእጅ አዙር ጦርነት እንደምሳሌ ብንወስድ፤
1. ኤርትራውያን ወንድሞቻችን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን መዋሃዷ ቀርቶ ፌዴሬሽኑ እንዲፈርስና እንደ አንድ ክፍለ አገር ሁና እንድትዋሐድ በህዝበ ውሳኔ አረጋግጠው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሐድበት ጊዜ በሥልጣን ክፍፍል ያልተደሰቱ ግለ ሰቦችን ግብጽ አስከድታ በመውሰድና ካይሮ ከተማ ውስጥ የተቃዋሚዎች ቢሮ በመክፈት ጀብሃ የሚባል ተቃዋሚ ድርጅት እንዲያቋቁሙ በማድረግ በሞራልና በማቴሪያል ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገች ኢትዮጵያን የመውጋት ሥውር ደባዋን እንደጀመረች አንዳንድ የታሪክ መዛግብት ያስረዱናል፤
2. ግብጽ በኤርትራ ክፍለ አገር ውስጥ የምታካሂደውን ኢትዮጵያን ሰላም የመንሳት ሥውር ደባ ወደ መሐል ኢትዮጵያም ለማስፋፋትና ኢትዮጵያን የማዳከም አላማዋን የበለጠ ለማጠናከር በማሰብ ከአዲስ አበባ ዩኒበርሲቲ ተማሪዎችና ከሌላም ሴክትር አንዳንድ ለእነሱ አላማ ማስፈፀሚያ ሊያገለግሉ ይችላሉ ብለው የገመቷቸውን ዜጎች በመመልመል ሌሎች የትግራይ ተገንጣይ ቡድኖችን አቋቁማ ኢትዮጵያን የማዳከም ሥራዋን እንደቀጠለች ይታወቃል፤
3. ህውሓትና ሌሎችም አንጃዎች በግብጽ ቀጥተኛ ዕርዳታና ድጋፍ በኢትዮጵያ ላይ የእጅ አዙር ጦርነት ያካሂዱ እንደነበር ለማረጋገጥ ከተፈለገ የህወሓት ታጋይ የነበሩና ወያኔን ከድቻለሁ በማለት በደርግ አስተዳደር ተቀባይነት ያገኙትን ሰው መጥቀስ ይቻላል። እኚህ ሰው የወያኔ የውስጥ አርበኛ በመሆን ምን ያህል አፍራሽ ሥራ ይሠሩ እንደነበርና ግብጻዊው የአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ሥራ አስኪያጅ እንዴት ይተባበሯቸው እንደነበር በማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ቴሌብዥን /ለዋልታ ከወራት በፊት የሰጡትን ቃለ ምልልስ ማየቱ / መስማቱ በቂ ማስረጃ ነው።
በዚሁ ቃለ ምልልስ ታጋዩ በሂልተን ሆቴል በስልክ ኦፐሬተር የሥራ መደብ ተቀጥረው ደመወዝ እየተከፈላቸው የሥራ ሽፍታቸውም ሌሊት ሌሊት እንዲሆንና በሆቴሉ የስልክ መስመር ጫካ ለነበሩ የወያኔ መሪዎች የአገሪቱን ምስጢር በነፃነት ሲያስተላልፉ ነበር።ቀን ቀን ደግሞ ከመደበኛ ሥራቸው ነፃ ሁነው በከተማ ውስጥ እየተዘዋወሩ የስለላ ሥራ ሲያከናውኑ እንዲውሉ የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ግብጻዊ አመቻችተውላቸው እንደነበር ገልፀዋል፤ ግብጻዊው ባለሙያም ለሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ ሁነው ከግብጽ የመጡበትና የተመደቡበት ሁኔታ ቢጣራ የሴራው አካል መሆኑን እንደሚያረጋግጥ አልጠራጠርም፤
ይህ እንግዲህ እንዲሁ በአጋጣሚ የሆነ ግጥጥሞሽ ሳይሆን ታስቦበትና በተደራጀ መልኩ ይፈፀም የነበረ ሴራ ነው። ይህን ለምሳሌ ያህል ጠቀስኩ እንጅ የደርግን መንግሥት ለመጣል በተደረገው የተባበረ ሴራ በሌሎች የአገሪቱ መንግሥታዊ ተቋማትና የሥራ ዘርፎች ውስጥም በተጠናከረ መልኩ ይከናዎን እንደነበር ይገመታል።
ይህም የግብጾች ሥውር ደባ ምን ያህል ውስጣችን ድረስ ዘልቆ ገብቶ እንደነበር ያሳያል፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ለዚህ ሥውር ደባቸው መሳካት አንዳንድ እራስ ወዳድና ከግል ጥቅማቸው ውጭ ስለሌላ የአገር ጉዳይ የሚያስብ ህሊና ያልነበራቸው ወይም ሥውር ደባው ሳይገባቸው በአስመሳዩ የጠላቶቻችን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የተታለሉ ወገኖቻችንም በመሣሪያነት እያገለገሉ ሲጎዱን የኖሩ መሆናቸውንም ጭምር የሚያስረዳን ነው፤ ውድ ወገኖቼ ከሁሉም የሚያሳዝነው በሥውር ደባ በተቀነባበረው ጦርነት ኢትዮጵያውያን ጎራ ለይተን ባደረግነው መቆራቆስ በሁለቱም ጎራ የሞትነው እኛው ኢትዮጵያውያን ነን። ሳናውቅ ያሳካነው ግብ ደግሞ የጠላቶቻችን ዓላማ የሆነውን የአገራችን የኢኮኖሚ አውታሮች ማውደም፤ ብሔራዊ አንድነታችን ማናጋት፤ በዘር፤ በባህልና በአኗኗር፤ በሥነ ልቡና አንድ የሆነውን፤ ተጋብቶና ተዋልዶ የነበረውን የአንዲት አገር ዜጋ መለያየት ነበር። ኢትዮጵያ አገራችንም ወደብ አልባ ማድረግ ነበር።
ለዚህ የጠላቶቻችን ሥውር ደባ መሳካት ደግሞ አብዛኛዎቻችን ኢትዮጵያውያን ሥውር ደባውን በአግባቡ ተረድተንም ይሁን ሳንረዳ በጠላቶቻችን ለተቀነባበረው የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ልባችን በመስጠት በመንግሥት ከሚሰጠን መረጃና ማሳሰቢያ ይልቅ በሥውር የሚተላለፍልንን የጠላቶቻችን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እንደ እውነት አድርገን በማመናችንና በመከተላችን የበኩላችን አፍራሽ አስተዋጽኦ እንዳደረግን የሚካድ አይመስለኝም።
ይህንን ጉዳይ ከዚህ ላይ ለማንሳት የፈለግሁት ባለፈው ስህተት ማንንም ለመውቀስ ሳይሆን ከለፈው ስህተት ተምረን አሁን ባለንበት በዚህ ፈታኝ ወቅት ተመሳሳይ ስህተት እንዳንፈጽም የበኩሌን የጥንቃቄ ማሳሰቢያ ለመስጠት ስለአሰብኩ መሆኑን በጥሞና እንድትረዱልኝ በትህትና አሳስባለሁ፤ በአሁኑ ወቅት ይኸው ሥውር ደባና ተጽዕኖ ከምንጊዜውም በበለጠና በተጠናከረ መልኩ ቀጥሎ ይገኛል፤ እኛም ሁላችን የአገሪቱ ዜጎች ከአባቶቻችን በበለጠና በተጠናከረ ሁኔታ ክንዳችን አስተባብረን የተቃጣብንን አደጋ መመከት ወቅቱ የጠየቀን ታሪካዊና ብሔራዊ ሃላፊነታችን ሁኗል፤ ይህን ታሪክ የጣለብንን ኃላፊነት እንደ አባቶቻችን ሁሉ በተባበረ ክንዳችን መመከትና ማክሸፍ ካልቻልን ግን ብሔራዊ ጥቅማችን ሊያሳጣን፤ ብሔራዊ አንድነታችንም ሊያናጋና ለመላው ጥቁር ህዝብ የትግል አርማና የነፃነት ፋና የሆነውን ነፃነታችንም ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባና እኛንም የታሪክ ተጠያቂ ሊያደርገን ይችላል።
ከሁሉም በላይ የሚያሳስበውና የሚያሳዝነው ደግሞ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ አንዳንድ የራሳችን ወገኖች በዚህ ሥውር ደባ አስፈፃሚነት ግንባር ቀደም ሚና ሲጫዎቱ ማየታችን ነው። ከታሪክ እንደምንረዳው በየጊዜው አገራችን ፈተና በገጠማት ጊዜ ሁሉ አንዳንድ እራስ ወዳድ ግለሰቦች በግልና ጊዜያዊ ጥቅም እየተደለሉ ለጠላት ያገለግሉ የነበረበት አጋጣሚ እንደነበረ ይታወቃል።
በአሁኑ ጊዜ የሚደረገው ሥውር ደባና ተጽዕኖ የህዳሴ ግድባችን ሥራ ለማስቆምና በብሔራዊ የግዛት ክልላችን ውስጥ የሚገኙ የሀብት ምንጮቻችን አልምተን የመጠቀም መብታችን የሚጋፉ ናቸው። ሁላችንም የአገሪቱ ዜጎች የግል ፍላጎታችንና ስሜታችን ለጊዜው እንደሌለ ቆጥረን በመተው ለብሐራዊ ጥቅማችን በአንድነት ቁመን ልንዋጋውና ልናከሽፈው ይገባናል እላለሁ።
ከዚህ ላይ በግልጽ ለመናገር የምፈልገው ባለው የመንግሥት አመራር ስልት ላንደሰት እንችላለን፤ ወይም የሃሳብ ልዩነት ሊኖረን ይችላል፤ ከዚህም በባሰ በአመራሩ ጉዳትም ደርሶብን ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ሃላፊ ከሆነው የመንግሥት ሥራ አፋፃፀም ጋር ያለንን የሃሳብ ልዩነትም ሆነ የደረሰብንን በደል ዘለዓለማዊ ከሆነችው አገራችን ጥቅም ጋር በምንም በልኩ ልናወዳድርው አይገባም የሚል እምነት አለኝ።
መሪዎቻችን የሁላችንም ፍላጎት ባሟላ መልኩ አመራር ቢሰጡ ጥሩ ነበር። ነገር ግን ሰዎች ናቸውና ጉድለት ይኖራቸዋል ፍፁምነት ያለው አመራር ሊሰጡ አይችሉም፤ ፍፁምነት ይኖራቸዋል እንኳን ብንል አሁን አገራችን ባለችበት የኢኮኖሚ አቅምና የፖለቲካ ሁኔታ የ110 ሚሊዮን ህዝብ/ ዜጎችን ፍላጎት ማሟላት በእኔ እምነት የማይቻል መሆኑም ግምት ውስጥ መግባት ያለበት ይመስለኛል።
ይህን ስል ለመንግሥት ጥብቅና ለመቆም አስቤ ሳይሆን አገራችንን አሁን ከተቃጣባት የተቀነባበረ ጥቃት በአቸናፊነት ለማውጣት ያለን አማራጭ ልዩነቶቻችንን ወደጎን ትተን በጋራ በመቆም ሴራውን ለማክሸፍ መታገል የተሻለ አማራጭ ነው ብዬ ሰለማምን ነው። አሁን ባለንበት ወቅታዊ ሁኔታ ከመንግሥት የተሻለ የትግላችን ማዕከል ሁኖ ሊያገለግል የሚችል ተቋም ወይም አማራጭ የለም ብዬ ስለምገምትም ጭምር እንደሆነ በጥሞና እንድትረዱልኝ አሳስባለሁ።
በዚህ ወቅት ይህን አለማድረግ ግን ባለቤቷን የጎዳሁ መስሏት አካሏን በጋሬጣ ወጋች እንደሚባለው የሞኝነት ሥራ ነው የሚሆነው። ቋሚ ብሔራዊ ጥቅማችን የሚያሳጣና ዘለዓለማዊ የህሊና ቁስል ሁኖ የሚኖር፤ በታሪክ ፊትም የሚያሳፍር ተግባር መፈፀም ነው እላለሁ፤ ውድ ወገኖቸ አንዳንድ ዜጎቻችን አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ወይም በግል ጥቅም ተታለው ምንም ወንጀል ያልሰሩ ወይም የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባላት ያልሆኑ ሰላማዊ ነዋሪና ደሃ የሆኑ ወገኖቻቸውን ሀገር ሰላም ነው ብለው በሚኖሩበት ቦታ በጥይት በመደብደብ መግደል፤ ንብረታቸውን ማቃጠልና ከመኖሪያ ቦታቸው በማፈናቀል ለረሃብና ለችግር እየዳረጉ ይገኛሉ። እነዚህ ሽብር የሚፈጥሩ ወንድሞቻችን የሥውር ደባው መገለጫና የሥውር ደባውንም በአስፈፃሚነት እያገለገሉ መሆናቸውን ከሚያስረዳ በስተቀር ሌላ ምንም ምክንያት ሊሰጠው የሚችል ተግባር ሊሆን አይችልም የሚል እምነት አለኝ፤
ስለዚህ ውድ ወገኖች የአገራችን ታሪካዊ ጠላቶች ዳር ደንበራችን ለመድፈርና ብሔራዊ ጥቅማቸን ለማሳጣት በተሰለፉበት በዚህ ወቅት ምንም ዓይነት የደረሰብን በደል ወይም የፖለቲካ ጥያቄ ቢኖረን ለጊዜው አቆይተነው አባቶቻችን ያደርጉት እንደነበረው የኢትዮጵያን ጥቅም በማስቀደም በአንድነት ተሰልፈን የተሰነዘረብንን የተቀነባበረ ጥቃት በአቸናፊነት ለመወጣት በሚያስችለን መልኩ ሁላችንም የበኩላችንን ያልተቆጠበ ጥረት እናድርግ። ይህ ሳይሆን ቀርቶ የጠላቶቻችን ሥውር ደባ ለመቋቋም ባንሰለፍ ግን በውጤቱ የምንጎዳው ሁላችንም የአገሪቱ ዜጎች በጋራ እንደሆነ ሁላችንም በጥሞና እንድናጤነውና አሰላለፋችን እንድናስተካክል ከአደራ ጭምር ለማሳሰብ እወዳለሁ፤
ወሃቤ ሰላም ዋለልኝ ሲሳይ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2013