ሕይወት ብርቱ ሰልፍ ናት።በድካም፣ በልፋት በውጣ ውረድ የተሞላች።ደግሞም ብርሃን..ደግሞም ፈንጠዝያ እንዲህም አላት።ለበጎም ይሁን ለመጥፎ ተራችንን እየጠበቅን ነው።ፊትና ኋላ ሆነን ቆመናል…።ከዕለታት አንድ ቀን በሕይወታችን ላይ የሚመሽ ቀን ይመጣል።ከዕለታት አንድ ቀን ደግሞ እንደዚሁ በብርሃን ያሸበረቀ የሚነጋ ቀን ይመጣል።ሰልፈኛ ነን…በመጠበቅ ውስጥ የቆምን..ግን ደግሞ ለብኩርና የምንጋፋ፣ ለመብለጥ፣ ለመቅደም ፊተኛ ለመሆን ኋለኞችን የምንጥል..የምንገፋ እንደዚም።
የሚጠቅመን እያለ ለማይጠቅመን የምንለፋ ነን…የሚያስፈልገን እያለ ለማያስፈልገን የምንደማ እንዲህም ነን።ሕይወት አልገባንም…መኖርን አልተረዳንውም።ሁሉም ነገር በሩጫና በብልጠት የሚገኝ የሚመስለን ብዙዎች ነን።በመኖራችን ውስጥ ለሌሎች እንዲኖሩ እስካልፈቀድን ድረስ ለመቅደም የምናደርገው ሩጫ ከኪሳራ ባለፈ ትርፍ ይዞልን አይመጣም።ምክንያቱም ሕይወት በመልካምነት ቀመር የተሰራ ነውና።
ከዚያኛው ዓለም ወደዚህኛው ዓለም ስንመጣ ለሰው ልጅ ሁሉ አስፈላጊ እንድንሆን ስለሆነ ነውና።ብዙዎቻችን ራስ ወዳድ ነን።የእኛን እርዳታ የሚፈልጉ በርካታ ወገኖች በዙሪያችን እያሉ ስለራሳችን ብቻ የምንጨነቅ ነን።የእኛን ፈገግታ..የእኛን መልካምነት የሚሹ ብዙ ችግረኛ ወገኖች እየጠበቁን ወደ ራሳችን ብቻ ያተኮርን ነን።ብዙ ነገራችን የማይሳካው በሕይወታችን ውስጥ ጥሩነት ስለሌለ ነው።ቢኖር እንኳን በቂና ከወገንተኝነት የዘለለ ስላልሆነ ነው፡፡
ከእንግዲህ ባለው ጊዜአችሁ ውስጥ ስኬታችሁን መልካምነት ውስጥ እንድትፈልጉት አዛችኋለሁ።ለራሳችን እያሰብን ስለራሳችን ብቻ እየተጨነቅን በምንኖረው ሕይወት ውስጥ ስኬት የለም።ስኬት ለሌሎች ባሰብን ሰዓት፣ ለሌሎች መልካም በሆንን ቅጽበት የሚመጣ አምላካዊ ቀመር ነው።ምናልባት ክፉ ሆነን፣ ሰርቀንና ቀምተን ወይም ደግሞ ባልተገባ መንገድ ሄደን የምንፈልገውን ሀብትና ዝና ሥልጣንና ጌትነት አግኝተን ደስ ብሎን ሊሆን ይችላል።እመኑኝ እርሱ ዘለዓለማዊ ደስታችሁን የሚቀማችሁ ነው።እመኑኝ እርሱ ጊዜያዊ ደስታን ከመስጠት ባለፈ ለነገ የሚሆን ምንም ነገር የለውም።እንዲያውም መጥፊያችሁ ነው የሚሆነው።በሳቃችሁ ማግስት ራሳችሁን በከባድ ኀዘን ውስጥ ታገኙታላችሁ።ከዛሬ ቀጥሎ በሚመጣ ነጋችሁ ውስጥ ራሳችሁን በአሁኑ ልክ አታገኙትም።
ከአገር ሰርቃችሁ የበላችሁት፣ ሥልጣንና አለቅነታችሁን ተጠቅማችሁ ከድሀ የወሰዳችሁት እጅ መንሻ የሞታችሁ ምክንያት ነው።መልካም ሕይወት በመልካም ሀሳብ ውስጥ ነው።ለሌሎች መኖር ስትጀምሩ፣ ለሌሎች መልፋት ስትጀምሩ ያኔ በሕይወታችሁ ውስጥ መልካም ነገር መከናወን ይጀምራል።ስኬታችን ደስታችን ሁሉ ያለው ለሌሎች በምንሆነው በጎነት ልክ ነው።ብዙ ሰዎች የሕይወት ትርጉም አልገባቸውም ስለ ሮጡ፣ ስለበረቱ የሚያሸንፉ የሚመስላቸው ብዙ ናቸው።ስለ ለፉ፣ ስለደከሙ የሚረኩ፣ ስለ ተጫወቱ የሚያሸንፉ የሚመስላቸው እዚህም እዚያም በየሰፈሩ ሞልተዋል፡፡
ሕይወት ግን በልባችን..በነፍሳችን ውስጥ የእግዚአብሔር በዝቶ መኖር ነው።ሕይወት በእኛ መኖር ሌሎች እንዲኖሩ መፍቀድ ነው።ሕይወት የወደቁትን እያነሱ ያዘኑትን እያጽናኑ ከምንዱባን ጋር፣ ከተናቁት ጎን መቆም ነው።ተስፋ ካጡት ጋር ህብረት ፈጥሮ መጓዝ ነው።ያኔ ነው ሀሳባችን የሚከናወነው።ያኔ ነው የምንፈልገው ነገር የእኛ ሆኖ የምናገኘው።ብዙዎች በዓለም ታሪክ..በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራ የሌለን በሌሎች ታላቅነት ውስጥ ተደብቀን ያለን ነን።ዋጋችንን፣ ጸጋችንን ሳናውቅ እንዲያው ዝም ብለን የምንኖር ብዙዎች ነን።ተልዕኮአችንን ማወቅ አለብን።
ለምን ሰው እንደሆንን መረዳት አለብን..ሰውነቱን ያልተረዳ ሰው ለራሱም ሆነ ለአገሩ የሚፈጥረው አንዳች ጥቅም የለም።መኖር መተንፈስ ብቻ እየመሰለን መስራትና ማከናወን ያለብንን ታላቅ ነገር ሳናከናውን ያለፍን ሞልተናል።የተፈጠርነው ለሌሎች ብርሃን እንድንሆን ነው።የተፈጠርነው ካለን ላይ ለማካፈል ነው።አገራችን ድሀ አገር ናት በዙሪያችን እርዳታ የሚሹ ብዙ ወገኖች አሉ።እነርሱን ረስተን የሚኖረን ልዕልና የለም።ታላቅ መሆን የሚፈልግ መጀመሪያ ታናናሾቹን ወዳጅ ያድርግ።ብዙ ድሆች፣ ብዙ ችግረኞች በዙሪያችን እያሉ በራችንን የምንዘጋ ከሆነ ሰውነት ገና አልገባንም።ድሆች በራፋችን ላይ ቆመው ምጽዋት እየጠየቁን በጭካኔ የምናባርራቸው ከሆነ ሕይወት ምን ማለት እንደሆነ ገና አልተረዳናትም ማለት ነው።
ስኬታችሁ የሚመጣው፣ የምትፈልጉት ነገር የእናንተ የሚሆነው በልባችሁ ውስጥ ባለው ሰብዓዊነት ልክ ነው..ይሄን መቼም እንዳትረሱ።እስካሁን ድረስ ለፍተን..ለፍተን አንዳች ነገር ጠብ ሳይልልን የምንኖረው በልባችን ውስጥ መልካምነት ስለጎደለ ነው።ላባችን ጠብ እስከሚል ጥረን ግረን ከድካም በዘለለ በረከት የራቀን ክፉዎች ስለሆንን ነው።ፍቅርን ሳናውቅ የሚኖረን ስኬት የለም።ሳትወዱ ሳታፈቅሩ በጥላቻና በመገፋፋት እየኖራችሁ የምታገኙት የሕይወት ፍሰሀ የለም።
ፍሰሀችሁ ያለው ሰውነታችሁ ውስጥ ነው። ካለፍቅርና ካለመልካምነት ታላቅነት የለም።መልካም ነገሮች ሁሉ ለሚወዱና ለሚያፈቅሩ ልቦች ቅርብ ሆነው የተቀመጡ ናቸው።ሰውነት ፈጣሪን መምሰል ነው።ውብ ያደረገንን ባለቤታችንን በሥራ፣ በተግባር መምሰል ነው።የአምላክ ሀሳቦች ናችሁ..እጹብ ድንቅ ሀሳቡ ነው ሰው ያደረገን።በውስጣችን አምላክ ራሱን አስቀምጧል።ዓይኖቻችሁ ድሆችን እንዲያዩ፣ ጆሮዎቻችሁ የችግረኛውን የተማጽኖ ድምጽ እንዲሰሙ አራሯቸው።ልቦቻችሁ..ነፍሶቻችሁ ስለምስኪኑ አብዝተው እንዲጨነቁ አሰልጥኗቸው።ሰውነት በአካልና በአእምሮ መሰልጠን ብቻ ሳይሆን የፈጣሪን ታላቅ ሀሳብ መረዳትም ጭምር ነው።
የእውነት ሰው የምንሆነው ወደዚህ ዓለም ያመጣንን የፈጣሪን እውነተኛ ፍቃድ ስናውቅ ነው።የመፈጠራችንን ምክንያት ስናውቅ በሕይወት የሚባክን ጊዜ አይኖረንም። መኖራችን ለሌሎችም አስፈላጊ እንደሆነ ማሰብ እንጀምራለን።ለሌሎች አስፈላጊ እንደሆንን ማሰብ ስንጀምር በሀሳባችን ውስጥ በህልማችን ውስጥ ሌሎችን ማካተት እንጀምራለን ያኔ ወደምንፈልገው የደስታም ሆነ የስኬት ጫፍ እንደርሳለን።ብዙዎቻችን ራስ ተኮር ነን። ብዙዎቻችን ለራሳችን ብቻ ኖረን ያለፍን ነን። ብታምኑም ባታምኑም ሁላችንም ለሁላችን እናስፈልጋለን።
ባለማሰብ ባለማስተዋል ሌሎች ጠቃሚዎቻችን እንዳይደሉ እናስባለን እንጂ ስኬታችን ደስታችን ሁሉ አይጠቅሙም ያልናቸውን ሰዎች ታኮ የሚመጣ ነው።ስለዚህ የማይጠቅም ሰው ምድር ላይ አልተፈጠረም ማለት ነው። ዓይኖቻችንን ገልጠን ብናይ በዙሪያችን ብዙ ጠቃሚ ሰዎችን ማየት እንችል ነበር።በአጉል አመለካከት የማይጠቅመንን አመለካከት የምናራምድ ብዙዎች ነን።እውነተኛ ሰውነት ሁሉም ሰው ለሁሉም አስፈላጊ ነው ብሎ የሚያስብ ነው።አምላክ በውስጣችን ያስቀመጠው ሀሳብ ይሄ ነው።የቅድስና ሀሳብ፣ የእውነት የይቅርታ ሀሳብ፣ የደግነትና የበጎነት ሀሳብ፣ የይቻላልና የአሸናፊነት ሀሳብ..ይሄ ነው ሰውነት። ይሄ ነው ሙሉነት።
በሆነው በምንሆነው ነገር ላይ ሁሉ አምላክ በዳኝነት በስውር በእኛ ውስጥ አለ..እኛም በእሱ ውስጥ አለን።እኛ አምላክ ሰው ሆኖ ነን።እኛ የፈጣሪ መልኮች ነን..ጸዳሎቹ።እኛ የአምላክ የተአምራት መገኛዎች ነን።እኛ ቅኔዎቹ ነን..ውብ ዜማው።ስለዚህም ራሳችሁን ለመልካም ተግባር የተገባችሁ ሰዎች አድርጋችሁ ፍጠሩ።ሁሉም ነገር እንዳልኳችሁ ነው መልካም ሕይወታችሁ ያለው በመልካም ተግባራችሁ ውስጥ ነው።ብዙ ነገር የሚፈልግ ሕዝብ አለን። ብዙ ችግረኛ፣ ብዙ ኀዘንተኛ ወገን አለን። መጽናናት የሚፈልጉ፣ አይዞህ ባይ የሚሹ ብዙ ነፍሶች እዚህም እዚያም አሉ።
በተለያዩ የአገራችን ክፍል የእኛን እርዳታ የሚጠብቁ በርካታ ነፍሶች አሉ።የተራቡ፣ የተጠሙ፣ ምግብና መጠለያ የሚሹ ወገኖች አሉ።ወደነሱ እንይ ወደ ባዶነታቸው እንመልከት።ብዙ ነገር በሚፈልግ ሕዝብ መሀል ነን።አካባቢያቸው ላይ ትምህርት ቤት አጥተው ብዙ ርቀት በእግር እየሄዱ የሚማሩ አሉ፣ ንጹህ ውሃ አጥተው የወንዝ ውሃ የሚጠጡ ብዙ ኪሎ ሜትር ተጉዘው የሚቀዱ ድሀ ወገኖች አሉን።ጨለማ ውስጥ የሚኖሩ መብራት የሚፈልጉ፣ መንገድና ጤና ጣቢያ ሆስፒታልም የሚሹ በርካታ ወገኖች በየገጠሩ አሉን።እጆቻችንን በመዘርጋት ልንደርስላቸው ይገባል።
ወላጅ የሌላቸው፣ ጧሪ ያጡ አዛውንቶች፣ ጎዳና የሚኖሩ ብዙ ችግረኞች አሉን።እንድረስላቸው…መኖራችን ዋጋ የሚኖረው በሀብታችን አይደለም፣ በቤትና መኪናችን ወይም በፎቅና ቪላ ቤታችን አይደለም።መኖራችን ዋጋ የሚያገኘው በበጎ ሥራችን ነው።ሕይወት መልካምነት ናት…ቀደም ብዬ እንዳልኳችሁ መንገዳችን የሚቀናው፣ ነገራችን የሚከናወነው በመልካም ሥራችን ነው።ከመልካምነት ውጪ ሙሉ አድርጎ የሚያኖረን አንዳች ነገር የለንም።ለራስ ብቻ መኖር ይብቃን።
የዛሬ ጥፋታችን የነገ ህመማችን ነው።የዛሬ መልካምነታችን የነገ ሰላማችን ነው።አሁናችን ለነጋችን ዋስትና ነው።ካላችሁ ላይ ለሌለው አካፍሉ።ሁለት ካላችሁ አንዱን ስጡ ይሄን ስታደርጉ ብርሃናዊ ነጋችሁን እየገነባችሁ ነው።ደግሞም የፈጣሪ ስውር እጆች ሕይወታችሁን ሙሉ ሊያደርጉ ከበላያችሁ ይዘረጋሉ።በርካቶች አሉ በራስ ወዳድነት ኖረው በመጨረሻዋ የሞታቸው ሰዓት ላይ ሰብዓዊነትን የሰበኩ…ስለመልካነት የመሰከሩ።
ከዚህ ውስጥ አንዱ አሜሪካዊው ቢሊየነር ስቴፍ ጆንሰን ነው።ስቴፍ ጆንሰን በካንሰር በሽታ ሊሞት የመጨረሻዋ ደቂቃ ላይ ስለመልካምነት ነበር የተናገረው።ስለፍቅር፣ ስለጓደኝነት ስለቤተሰብ ነበር የተናገረው።በሕይወቴ ሁሉ ያለኝ ሰው ነኝ፣ ተመኝቼ ያጣሁት አንድም የለም ብዙ ወርቅና ብር፣ ብዙ ሀብትና ንብረት፣ ብዙ ቤትና መኪና አሉኝ።እነዚህ ሁሉ ግን ከሞት አላዳኑኝም።እነዚህ ሁሉ ግን የምመኘውን ሕይወት አልሰጡኝም።ገንዘብና ሀብት ለማግኘት የሮጥኩትን ያክል ለፍቅርና ለመልካምነት ብሮጥ ዛሬ ላይ በዚህ ልክ ከንቱ ሆኜ ራሴን አልጋ ላይ አላገኘውም ነበር ሲል የመልካምነትን ጥግ በሕይወቱ የመጨረሻ ሰዓት ላይ ሆኖ ተናግሯል፡፡
ባለጸጋ ሆነን የፈለግነውን አግኝተን ብንኖር ይሄ ምንም ነው።ሕይወት ለሌሎች መኖር እንደሆነ አሁን ነው የገባኝ።ሕይወት ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንደሆነ አሁን ነው የተገለጸልኝ።ዘመናዊ መኪና መንዳት፣ ሰማይ ጠቀስ ቤት ውስጥ መኖር፣ በሀብትና ገንዘብ መንበሽበሽ፣ ዝናና ክብር ሥልጣንና ጌትነት እኚህ ሁሉ ደስታን ሊሰጡን ይችላሉ የእውነተኛ ሕይወት መገለጫ ግን አይደሉም።እውነተኛ ሕይወት በእኛ በረከት ውስጥ ሌሎች እንዲኖሩ መፍቀድ ነው ሲል በመገነዣ አልጋው ላይ ሆኖ የመጨረሻ የስንብት ቃሉን ለመላው ዓለም አስተላልፎ ወደማይቀርበት ሄዷል።
ከስቴፍ ጆንሰን ሕይወት ብዙ መማር እንችላለን። ገንዘብ ደስተኛ እንድንሆን ቢያደርገንም የመልካምነትን ያክል ዋጋ ግን አለው ብዬ አላምንም።በሕይወታችን ውስጥ በገንዘብ የማይመለሱ ነፍሳዊ ጥያቄዎች አሉ።እኚህ ጥያቄዎች በገንዘብ ሳይሆን በፍቅር የሚመለሱ ናቸው። በመልካምነት ነው እልባት የሚያገኙት። ከእንቅልፋችን መባነን ካልቻልን አንድ ቀን በሕይወታችን ማምሻ ላይ እንደ ስቴፍ ጆንሰን መመለስ የማንችለው በሕይወታችን የሚቆጨን ጊዜ ይመጣል። ይሄ እንዳይሆን በመኖራችን ውስጥ ሌሎችን እናኑር። በሀሳባችን ውስጥ፣ በራዕያችን ውስጥ ሌሎችን እናስገባ። ያኔ የእውነት ትኖራላችሁ።ያኔ በድካምና በጥረት ያላገኛችሁትን ደስታና ስኬታችሁን ታገኙታላችሁ። ያኔ በብዙ በረከት፣ በብዙ መታደል ረክታችሁ ትኖራላችሁ..እናም መልካም ሁኑ።አበቃሁ..ቸር ሰንብቱ፡፡
ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2013