- ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ
ኢትዮጵያ አገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከምትታወቅባቸውና ከምትከበርባቸው አገራዊ ልዩ እሴቶቿ ውስጥ አንዱ የዘርፈ ብዙ ልዩነቶች የመቻቻል ምድር መሆኗ ሲሆን ሕዝቦቿ በፈሪሃ አምላክ የሚመሩ ናቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ አገራችን የሃይማኖት ብዝሃነትን በመቻቻል፣ በአብሮነትና በመከባበር የሚያስተናግድ ማህበ ረሰብ ያላት ታሪካዊ ተምሳሌት መሆኗ ነው።
የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን
ሙስሊሞች!
የእስልምና ኃይማኖትና አገራችሁ ኢትዮጵያ ከከተማችሁ አዲስ አበባ ጋር ያላቸው ታሪካዊ ትስስር በማይናወጥ መሠረት ላይ የተጣለው ገና ከጅምሩ በመሆኑ ከእምነት ጋር ተያይዞ ለዘመናት ሲያጋጥሙን ለኖሩት የውስጥና የውጭ ተግዳሮቶች ሳንበገር አንድነታችንን፣ አብሮነታችንን፣ ሉዓላዊነታችንን ተቻችሎ በፍቅር የመኖር እሴቶቻችንን በጥበብና በጀግንነት አስጠብቀን ኖረናል።
የዚህ ማንነታችን ቀጣይ የሆነውን ዛሬያችንን በፍቅርና በክብር አብረን በማሳለፍ ላይ እንገኛለን። ዘንድሮ የታላቁን የረመዳን ፆም ወቅት በታሪካችን ከእናትና ከአባቶቻችን የወረስነውን እሴት በማስጠበቅ በተለያየ መልኩ በየቦታው አብረን አሳልፈናል። ለአብነትም በቅርቡ የሰጠነው የማምለኪያ ቦታዎች ይህንን ይመሰክራሉ። በስካይ ላይት ሆቴል ሁሉም ሃይማኖቶች በተገኙበት ከሙስሊም ወንድሞቻችን ጋር አብረን አፍጥረናል። ከሶሪያውያን ተፈናቃይ ወንድምና እህቶቻችን ጋር እንዲሁ። በቤተ-መንግሥት፣ በሆቴሎችና በየክፍለ ከተሞቻችን ማዕዶችን ተጋርተናል። በፍቅርና በመከባበርም አብረን አሳልፈናል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የዘንድሮውን የረመዳን ፆም ልዩ በሚያደርግ ሁኔታ በተለያዩ የአገራችን ከተሞች ሰፋፊ የጎዳና ላይ የአፍጥር ፕሮግራሞች እጅግ በሚያስደስትና ጠላቶቻችንን በሚያስቀና ሁኔታ በመንግሥት አካላት እና በሁሉም ነዋሪዎች ትብብርና አብሮነት ሲካሄዱ ቆይቷል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በከተማችን አዲስ አበባ ብዙ ቁጥር ያለው የሙስሊሙን ማህበረሰብና ሌሎችን ያሳተፈ የጎዳና ላይ አፍጥር ለማካሄድ የተዘጋጀው ዕቅድ ባዘጋጁ አካላትና ግለሰቦች እንድናውቀው ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ፕሮግራሙ በተሳካና የዓለም ሪከርድ በሚሰብር ሁኔታ እንዲፈፀም ከፍተኛ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል። ከአዘጋጆቹ ጋር በተደጋጋሚ እየተገናኘን ለፕሮግራሙ ውጤታማነት በሙሉ ልባችን ስንሰራ ቆይተናል። ለስኬቱም እስከመጨረሻዋ ድረስ በሙሉ አቅማችን ሠርተናል። ይህን ትልቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለአብሮነትና ለአገር አንድነት ለማዋል የተሰራው ሥራ የሃሳቡን አመንጪዎችና አዘጋጆቹን የሚያስመሰግን ታላቅ ተግባር መሆኑን እናምናለን። በእርግጥም ዛሬም በከተማዋ የተለያዩ ጎዳናዎች ላይ የአፍጥር ፕሮግራሞች ተካሂደዋል።
የተከበራችሁ የከተማችን የእስልምና እምነት ተከታዮች፣
አብሮ አንድ ማዕድ በጋራ የተቋደሰ አደባባይ የኔ ያንተ ብሎ አይጣላም። ነገር ግን በአንድ በኩል የአደባባዩ የመጨረሻ የግንባታ ሥራዎች አለመጠናቀቃቸው፣ ከሥነ- ሥርዓቱ መከናወን ጋር ተያይዞ ተገቢ ያልሆነ የደብዳቤ ልውውጦች ካደረጉት አካላት ጋር በመወያየት በጋራ ግንዛቤና በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተና ያለንበትን አጠቃላይ ሀገራዊ ሁኔታ ከግምት ባስገባ መልኩ ፕሮግራሙ በታቀደው መሠረት የአፍጥር ቦታው ስፋቱና ርዝመቱ እንዲያሳትፈው ከታሰበው የታዳሚ ብዛት አንፃር እንቅፋት እንዳይፈጠር እዛው በውስን አካባቢ እንዲካሔድ እንደመፍትሔ ተወስዶ ነበር።
እንደፍላጎታችን ቢሆን ኖሮ ዛሬ በመድረኩ ላይ ተገናኝተን በባህላችናና በታሪካችን መሠረት ፕሮግራሙን በአብሮነትና በፍቅር ባከበርን ነበር፡ ሆኖም አዘጋጆቹ የአፍጥር ቦታው ስፋቱና ርዝመቱ ውስንነት ላይ ስላልተስማሙ የመሰረዝ አማራጭን ወስደዋል። በሌላ በኩል ይህን ለሌላ አላማቸው ለማዋል በማህበራዊ ሚዲያ ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንዲራገብ ያደረጉ አካላት እንዳሉ አስተውለናል። ይህም የተወሰነ ቅሬታን መፍጠሩን እንገነዘባለን።
ውድ ሙስሊም ወገኖቻችን
በተለያዩ ድምር ምክንያቶች በተፈጠረው የፕሮግራሙ መስተጓጎል ቅሬታ ሊፈጥር የሚችል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ቅሬታችንን የምንገልጽበት መንገድም በሰላማዊና በሰከነ አግባብ መሆን ይኖርታል። ከሌሎች እምነት ተከታይ ወንደሞቻችን ጋር ሆነን ለዘመናት ነብሳችንን ገብረን ያቆየናትን አገራችንን ለጥቃት ማጋለጥ አይገባንም።
ስለሆነም ሌሎች ተመሳሳይ ፕሮግራሞችን ለሺ ዓመታት የምናከብርባትን ታላቋን ዲሞክ ራሲያዊትና የበለጸገች አገር ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ርብርብ ለማደናቀፍ እየሰሩ ላሉ አካላት ዕድል እንዳንሰጥ እንደ እምነቱ አስተምህሮት ታጋሽነታችሁን ታጸኑ ዘንድ አደራ እንላለን።
የተፈጠረውን ከፍተት በመጠቀም የግል ጥቅማችሁንና ፍላጎታችሁን ለማሳካት ሲባል ጨዋውን ህብረተሰብ ለማሳሳትና በማይገባ ተግባር ላይ ለማሳተፍ የምትጥሩ ግለሰቦችና አካላትም ከድርጊታችሁ ትቆጠቡ ዘንድ እናሳስባለን።
ወቅቱ በእልህና ለጠላቶቻችን ክፍተት በሚፈጥር መልኩ መሆን የለበትም በማለት ይሄንኑ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ጉዳዩ በሠላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ላደረጋችሁ ህዝበ ሙስሊሞች በሙሉ የከተማ አስተዳደሩ ምስጋናውን ያቀርባል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2013