አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለማህበረሰብ ችግር ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚሠራውን ሥራ ውጤታማ ማድረግ የሚችለው ክልሎችም ኃላፊነታቸውን ሲወጡ እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡ አስተዳደሩ ባለፈው ሳምንት ከጎዳና ላይ ያነሳቸውን ሦስት ሺ ዜጎች በአምስት ማዕከሎች ውስጥ የምግብ፣ የጤናና የሥልጠና አገልግሎቶች እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ የማህበራዊ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለሙ አሰፋ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉት ዜጎች 92 በመቶ የሚሆኑት ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ናቸው፡፡አዲስ አበባ ከተማ ከሌሎች በተለየ የተፈጠረላት አደረጃጀትም፣ አሰራርም ሆነ ምቹ ሁኔታ የለም፡፡ለማህበረሰብ ችግር ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች ማቋቋሚያ የሚውል ተዘዋዋሪ ፈንድና የዓለም ባንክም የሚያደርገው የጎዳና ፕሮጀክት ድጋፍ ለሁሉም እኩል ሲሆን፤ ችግሩ ቁርጠኝነት ነው፡፡
ክልሎች የከተማ አስተዳደሩ በሚሰራው ልክ ካልተንቀሳቀሱ ለማህበረሰብ ችግር ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚሰራውን ሥራ ውጤታማ ማድረግ ያስቸግራል፡፡ ዜጎች መደበኛ ህይወት የመኖር መብት እንዳላቸው እንዲሁም ፀጥታና ደህንነት ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች መጠቀሚያ እንደሚያደርጓቸው መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ እያከናወነ ያለው ሥራ ከጎዳና ላይ ያነሳቸውን ዜጎች የምክር አገልግሎት፣ የኑሮ ክህሎት እና የሰዕብና ግንባታ ሥልጠና በመስጠት ወደ መጡበት እንዲመለሱ ማድረግ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ዓለሙ፣ ክልሎች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ዳግም ወደጎዳና እንዳይወጡና ሊወጡ የተዘጋጁትንም በመመለስ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስረድተዋል፡ በጉዳዩ ላይ የፌዴራል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የፌዴራል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከክልሎች ጋር የጀመሩትን ውይይት በማጠናከር ለውጤት ማብቃት ካልቻሉ ጥረቱ ከንቱ እንደሚሆን አቶ ዓለሙ ገልጸው፤ አብዛኞቹ ወደ የመጡበት ለመመለስ ፍላጎት ቢኖራቸውም ስጋታቸው የሥራ ዕድል ያለማግኘት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በዘላቂነት እስከ አምስት ሺ ሰዎች የሚይዝ በጤና፣ በሥልጠና እና በሌሎችም አገልግሎቶች የተደራጀ ቋሚ ማዕከል በማዘጋጀት ዜጎችን በማብቃት መደበኛ ህይወት እንዲኖሩ የማስቻል ሥራ ለመሥራት ማቀዱን የጠቆሙት አቶ ዓለሙ፤ ለማህበረሰብ ችግር ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች የሚውል በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ዜጎች በቁጥር (100272444726) የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉበት ትረስት ፈንድ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ዓለሙ ማብራሪያ ቢሮው በበጀት ዓመቱ አጋማሽ በያዘው እቅድ ሦስት ሺ ዜጎችን ከጎዳና ላይ በማንሳት በላፍቶ ንፋስ ስልክ፣ በኮልፌ፣ አራዳ፣ አቃቂ፣ ልደታና ቦሌ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ማዕከሎች ውስጥ የሥልጠና እና የተለያዩ አገልግሎቶች እየሰጠ ሲሆን፤ ለ45ቀናት ቆይታ ያደርጋሉ፡፡የልየታ ሥራ ከተሠራ በኋላ ወደ የአካባቢያቸው የመመለስ ሥራ ይከናወናል፤ ቤተሰብ ለሌላቸው አማራጮች ተዘጋጅቷል፡፡ የተለየ ጥቅም ይገኛል ብለው የገቡትን በመለየት እንዲወጡ እየተደረገ ነው፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2011
ለምለም መንግሥቱ