አዲስ አበባ:- የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች በዓመታዊ ጉባኤያቸው ተወያይተው የሚያሳልፏቸውን ውሳኔዎች ሥራ ላይ በማዋል በኩል ክፍተት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂ ጥናት ኢንስቲትዩት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ገለፁ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ መላኩ ሙሉዓለም በ32ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤና አጠቃላይ በህብረቱ አሰራር ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለፁት፣ መሪዎቹ በአጋርነት፣ በንግድ ልውውጥ፣ በሰላምና ፀጥታ፣ በአሸባሪነት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በፋይናንስ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በእዳ ስረዛ እና በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ተወያይተው ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ፡፡ ውሳኔዎቹን ሥራ ላይ ማዋል ወይንም መተግበር ላይ ግን ክፍተቶች አሉባቸው፡፡
መሪዎች የተስማሙባቸውን ጉዳዮች ከተፈራረሙ በኋላ በየሀገሮቻቸው በፓርላማ ማጸደቅ የሚጠበቅባቸውን የማይፈጽሙበት ሁኔታ መኖሩን የጠቆሙት አቶ መላኩ፤ ለአብነትም መሪዎች በልዩ ልዩ ጉዳዮች ዘርፍ ለመረዳዳት እ.ኤ.አ. በ1975 ቢፈራረሙም እስከ ዛሬ በየሀገራቸው በፓርላማ ባለማጸደቃቸው 44 ዓመት ተንጠልጥሎ መቆየቱን አመል ክተዋል፡፡
እንደ ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ ገለፃ አንድ አዋጅ ከወጣ በኋላም ተከታትሎ የማስፈጸም ክፍተት ይታይባቸዋል፡፡ በህብረቱ 34ተኛ ጉባኤ ላይም የክትትልና ግምገማ ሥርዓት ጠንካራ መሆን እንዳለበት ተወያይተዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2011
ለምለም መንግሥቱ