ማህሌት አዘነ የንግግርና ቋንቋ ቴራፒስት ስትሆን ለህፃናት እድገት ጠቃሚ መረጃዎችን በማህበራዊ ድረ- ገጿ ትፅፋለች። ለዛሬም “ልጆች ከጨዋታ ምን ይማራሉ” በሚል ማህሌት የሰጠችውን ምክረ ሃሳብ ልናካፍላችሁ ወደድን። መልካም ንባብ።
ጨዋታ ማለት ለልጆች ከመዝናኛ በላይ ነው። መጫወት ለልጆች ስለ ዓለም እንዴት እንደሚማሩ የሚያደርግ ነገር ነው። ጨዋታ ሰዎች ከሌሎች ጋር ለመግባባት፣ ለመማማር፣ ማህበራዊ ችሎታዎች ለማዳበር ይጠቀሙበታል። ጨዋታ ስሜትን ለመግለጽ፣ እርካታን ለማግኘት እና ሌሎች እንዴት እንደሚሰማቸው ለመረዳት ይጠቅማል። በሌላ አገላለጽ ጨዋታ ማህበራዊ እና ስሜታዊ ብልህነትን ይገነባል::
ልጆች በሚጫወቱበት ጊዜ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ የሚጠቀሙባቸውን ጠቃሚ ችሎታዎች እየተማሩ ያድጋሉ:: ልጆች ከጨዋታ ከሚማሩት ነገሮች መካከል የቋንቋ አጠቃቀም ችሎታቸው ያድጋል፣ ማህበራዊ መስተጋብራቸው ይሻሻል፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ያጎለብታሉ፣ ችግር ፈቺነትን ይማራሉ።
ልጆች ሲጫወቱ ፈጠራ ስራዎችን ይለማመዳሉ፤ የማሰብ ችሎታቸው ይጨምራል፤ ራስን የመቆጣጠር ስሜት ይኖራቸዋል፤ የድርድርና ስምምነት ችሎታዎችን ያዳብራሉ፤ የሚፈጠሩ አደጋዎችን ቀድሞ የመረዳት ችሎታ ያጎለብታሉ። በተጨማሪም በጎ ፈቃደኛነትን እና ተገቢ ሥራን የመከወን ክህሎቶችን ይማራሉ፤ እንዲሁም የሌሎችን አመለካከት የመውሰድ ብሎም ተራን መጠበቅና የመሳሰሉትን ማህበራዊ መስተጋብሮች ይማራሉ።
ለአብነት የአኩኩሉ ወይም ድብብቆሽ ጨዋታን ማንሳት ይቻላል። የድብብቆሽ ጨዋታ ለልጆች የተለየ ጥቅም አለው፤ የልጆቻችን አእምሮ፣ አስተሳሰብና አካላዊ እድገት ከማምጣት ረገድ ጠቃሚ ነው። ይህም የሚሆነው በአንድ በተወሠነ አካባቢ አንድ ልጅ ሲቆጥር ሌሎች ራሳቸውን ይደብቃሉ፣ እየተሯሯጡ ይፈልጋሉ፣ ያገኛሉ፣ አዕምሯቸውን ያሰራሉ።
ድብብቆሽ ወይም አኩኩሉ ለልጆች
ያላቸው ጥቅሞች
ትውስታ፦ ሌሎች እስከሚደበቁ ዓይናቸውን የሚጨፍኑት ልጆች ፍለጋውን እስከሚጀምሩ ድረስ ዓይናቸውን በሚጨፍኑበት ወቅት የተለያዩ መረጃዎችን ይሰማሉ፤ ከመረጃዎቹም ውስጥ አስፈላጊ የሆኑትን በአዕምሯቸው መያዝ ይጀምራሉ:: ፈላጊዎቹም ሆነ የተደበቁት ልጆች እየተጫወቱ የጨዋታውን መመሪያዎች እና ህጎች ያስታውሳሉ:: መጀመሪያ መደበቅ የእነሱ ተራ ይሆናል፤ ቀጥሎ ሲቆጥሩ የተደበቀውን ለማግኘት አይቸገሩም።
የስራ ተነሳሽነት፦ ልጆች የራሳቸውን ግብ ማሰብ ይጀምሩሉ። ለመደበቅ በጣም ጥሩውን ቦታ ይፈልጋሉ:: እቅድ ማውጣት እና ቅድሚያ መስጠት ይጀምራሉ፤ በዚህም ልጆች ግብ አውጥተው ማስፈፀም ይችላሉ::
ዕይታን መውሰድ፦ ልጆች ራሳቸውን በሌላ ሰው ቦታ ላይ ማስቀመጥ ይችላሉ:: “እናንተን ብሆን ኖሮ ወዴት እደበቃለሁ?” ዓይነት ሀሳቦችን ያመነጫሉ።
የተለያዩ አስተሳሰቦችን ይገነዘባሉ፦ ልጆች ባልተጠበቁ ወይም ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ይላመዳሉ። ስሜትን መቆጣጠር፣ ደስታን ከፍ ማድረግ፣ ድብቅ እና ሚስጥራዊ ብልህነትን ለማሳደግ ይማራሉ። ቅንጅት እና ሚዛናዊነት ይማራሉ።
ድፍረትን መለማመድ፦ ልጆች በዚህ ጨዋታ ድፍረትን ይለማመዳሉ፤ በተጨማሪም የመቋቋም ጡንቻዎቻቸው የበለጠ ጠንካራ ይሆናል::
የአካል እድገትን ማሻሻል፡- የአካል እድገትን እና ቅንጅትን ማሻሻል ይማሩበታል። አጠቃላይ የአካል ጡንቻዎችን ማጠንከር እና የመሳሰሉትን ነገሮች ያዳብራሉ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2013