ጎረቤታሞች የትንሳኤን በዓል እንደወትሮው ሁሉ ቁርስ፣ምሳ፣ እራት በተራ እየተጠራሩ በመገባበዝ በሰላም አሳልፈዋል::በዓሉ እስከ ዳግም ትንሳኤ ይቀጥላል:: የክርስትና ልጅና እናት ወይንም አባት በዚህ ወቅት ነው የሚጠያየቁት :: ዳቦና የተለያዩ መጠጦችን በመያዝ አንዳቸው ሌላኛው ቤት ይሄዳሉ::ለክርስትና ልጅ ልብስ ማልበስም የክርስትና እናትና አባት ወግ ነው::
ተነፋፍቆ የተገናኘው ዘመድ፣ በተለያየ መንገድ ዝምድና ወዳጅነት የፈጠረው ሁሉ በዚህ መልኩ ተሰብስቦ በሳቅ በጨዋታ ያሳልፋል:: የአብሮነት፣ የአንድነትና የማህበራዊ ግንኙነቱ ማሳያ በሆነው በዚህ በዓል ብዙዎች ደስታቸውን በማጣጣም ላይ ናቸው::
ከቀናት በኋላም ሙስሊም ወገኖችም እንዲሁ በተመሳሳይ ያለው ለሌለው በማካፈል በደስታ በዓላቸውን ያከብራሉ::ሁሉም እንደእምነቱ በዓሉን ቢያከብርም ክርስቲያኑ ሙስሊም ጎረቤቱን፣ ሙስሊሙም እንዲሁ ክርስቲያን ጎረቤቱን ጠርቶ ያለውን በወንድማማችነት መንፈስ ተካፍለው በደስታ በዓል የሚያሳልፉት:: ሰርግም ሲደግሱ እንዲሁ አይለያዩም::ስጦታቸውን ይዘው በመሄድ ይታደማሉ::
እንዲህ ባለ መልኩ ዓውዳመቱንም፣ሰርጉንም አብረው ቢያሳልፉም በአሁኑ ጊዜ የሰዎችን መተሳሰብና አንድነት በማይፈልጉ ኃይሎች ህይወታቸውን በመነጠቃቸው፣ለአካል ጉዳትም በመዳረጋቸው፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ውስጥም የሚገኙ በመኖራቸው የአውድ ዓመት ደስታው ምሉዕ ነው ማለት አይቻልም::
እንዲህ በበዓል ወቅት ትስስሩ ይጠነክራል ለማለት እንጂ ሰዎች በጉርብትና አብረው ሲኖሩ አንዳቸው ለሌላኛው የሚያሳዩት ፍቅርና መተሳሰብ ጠንካራ ነው::ጩኸት እንኳን ሲሰማ ጎረቤት ቀድሞ ይወጣል:: ፀብም ከሆነ መሃል ገብቶ ይገላግላል::ድረሱልኝ ብሎም ከተጣራ ሰምቶ የሚተኛ ጎረቤት የለም:: ከነአባባሉም ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት ይሻላል ይባላል::
መተሳሰቡ ከዚህም አልፎ ልጅን በጉዲፈቻ ወስዶ እንደራስ ልጅ አድርጎ በማሳደግ ይታወቃል:: እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለብን አንድ ሰው ልጅ በጉዲፈቻ ለማሳደግ ሲወስድ ዘር ጠይቆ ወይንም ቆጥሮ አይደለም:: በደም ከማይተሳሰረው ሰው ጋር በልጁ አማካኝነት ዝምድናውን ለማጠናከር ሲል የሚያደርገው ተግባር ነው:: ጉዲፈቻ መልኩን ቀይሮ ባህርማዶ ዘልቆ የኢትዮጵያዊውን የቆየ የጉዲፈቻ ባህል ሳያደበዝዘው በፊት የሚደነቅና የኢትዮጵያውያን ብቻ ባህል ተደርጎ የሚወሰድ ነበር::
ልጅ ቀጥቶ ማሳደግም የወላጅ ብቻ ሳይሆን የጎረቤትም ኃላፊነት በመሆኑ እኔ አያገባኝም ብሎ አያልፍም::ጎረቤት ከመጥፎ ድርጊቱ በመመለስ ለወገን ለሀገር የሚጠቅም ዜጋ እንዲሆን በኃላፊነት ስሜት ይገስጻል:: ከመጥፎ መንገድ ይመልሳል:: ልጆችም ቢሆኑ ለጎረቤቶቻቸው ትልቅ አክብሮት አላቸው:: በጉርምስናቸው አንዳንድ ነገር ሲያደርጉ እንኳን ጎረቤቶቻቸው ጭምር እንዳያዩዋቸው በጣም ይጠነቀቃሉ:: ሊያንጓጥጧቸው ቀርቶ ቀና ብለው አያዩዋቸውም::መከባበሩና መተሳሰቡ በአዋቂዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በልጆችም መካከል ተመሳሳይነት አለው::
በኀዘንና በደስታ ጊዜም ያለው መረዳዳት ጠንካራ ነው::የአውድ ዓመቱም ሆነ ጉርብትናው አብሮነታችንን አጠናክሮ እዚህ ላይ አድርሶናል::ለሌላው ዓለም በተምሳሌትነት የሚጠቀስ፣ጠንካራ ማህበራዊ ትስስርን የሚፈጥር በዓል እንዲደበዝዝ ያደረጉ ኃይሎች በዚህ ባህል ውስጥ ያደጉ ኢትዮጵያውያን ናቸው ለማለት ይከብዳል:: ለሰው ህሊና የሚከብድ ኢሰብአዊ ድርጊት በመፈጸም ከሞቀቤታቸው እንዲወጡ በማድረግ በዓልን ቀርቶ የዕለት ተዕለት ኑሮአቸውን እንዳይኖሩ በማድረግ እኩይ ተግባራቸውን ቀጥለዋል::
እነርሱ ልባቸው ታውሮ ለእኩይ ተግባር ሲነሳሱ ያ በጉርብትናና በአውድ ዓመት ብዙ መገለጫዎች ያሉት የጠነከረው አንድነትና መተሳሰብ የት ደረሰ? ለምንስ ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው አይነት እንዲሉ ልዩነታችን በውይይት መፍታት ለምን አልቻልንም? የኢትዮጵያን ውድቀት ለሚፈልጉ ኃይሎች በራችንን እየከፈትንላቸው እንደሆነስ ስንቶቻችን ተገንዝበናል? የሚሉት ጥያቄዎች መልስ መስጠት መቻል አለብን::
ዘመናዊነትና ስልጣኔ አንዱ በሌላው ህይወትና አኗኗር ላይ ጣልቃ እንደመግባት ተቆጥሮ ያ ለጎረቤቱ ልጅ ይጨነቅ የነበረና ከመጥፎ ተግባሩ ለመመለስ ጥረት ሲያደርግ የነበረ ጎረቤት ኃላፊነቱን እርግፍ አድርጎ መተው አሁን ለሚስተዋለው ውጥንቅጥ መንገድ ከፍቷል የሚሉ ወገኖች ጥቂት አይደሉም::
ሰሞኑን ያከበርነው የጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች በዓል በምክንያት ነው:: ኢትዮጵያን ከወራሪው ፋስሽት ጣሊያን ተከላክለው ታፍራና ተከብራ ለዛሬ ትውልድ ኩራት የሆነች ሀገርን ያስረከቡት::ወራሪውን አሸንፈው ለድል የበቁት በታጠቁት የጦር መሳሪያ ብቻ አልነበረም:: የጠነከረው አንድነታቸው ጭምር እንጂ:: ትናንት ጀግኖች አባቶች አጥንታቸውን ከስክሰውና ደማቸውን አፍስሰው ዳርድንበራቸውን ያስከበሩት የውጭ ወራሪ ኃይልን በመጣበት አሳፍረው በመመለስ ነው::
ቅኝ ያልተገዛች፣ ለጥቁር ህዝቦችም መኩሪያ የሆነች ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ ተብላ በዓለም እየተነገረላት ግን ወገን በወገኑ እጁን ማንሳቱ ፍጹም የማይገናኝ አሳፋሪ ድርጊት ነው:: የሚገርመው ደግሞ በሀገሩ ላይ ሰርቶ መለወጥ አቅቶት ድህነትን ሸሽቶ በሰው ሀገር ላይ ሰርቶ ያራሱንም የቤተሰቡንም ኑሮ ለማሻሻል የወላጆቹን ጥሪት አሟጥጦ ኢትዮጵያዊ የሚል ዜግነት ይዞ ከሀገር ተሰዶ የወጣው ሁሉ ዓላማውን አሳክቶ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ወገኑን መጥቀም ሲገባው እትብቱ የተቀበረባትን፣አፈር ፈጭቶ የቦረቀባትን ሀገሩን ለመበታተን መነሳቱና ጡት ነካሽ መሆኑ ነው::
ስደት ላይ ያለውን ሁሉ በተመሳሳይ መፈረጁ አግባብ ባይሆንም ጥቂቶች ግን በስመ ስደተኛ ወይንም ዲያስፖራ እየተባለ የሚጠራውን ሁሉ እያጠለሸው ይገኛል:: የሌላው ዓለም ዜጋ ሰርቶ ያገኘውን ገንዘብ ወደ ትውልድ ሀገሩ በመላክ ሀገሩን በመለወጥ ስሙ ሲጠራ ኢትዮጵያዊው ወደ ሀገሩ የላከው የገንዘብ መጠን እንኳን በአግባቡ አይታወቅም:: ለቤተሰቡ የሚልካትን ጥቂት ገንዘብ እንኳን በጥቁር ገበያ መላክ ነው የሚመርጠው::በሰው ሀገር ሆኖ ጥቁር መባሉን ዘንግቶት እራሱን አገር ለማተራመስና ሰላም መንሳት በየማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ዘመቻ ማድረጉ የሚያስብ አዕምሮ አለው ለማለት አያስደፍርም:: ምንም እንኳን የዚያ ሀገር ዜጋ እንደሆነ በወረቀት ቢረጋገጥለትም ደሙ ግን ኢትዮጵያዊ መሆኑን ሊፍቀው አይችልም::
ዲያስፖራው በሰው ሀገር ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ ሲኖር ሰብአዊና ቁሳዊ መብቱ ተከብሮለት ከዜጋው እኩል በሰላም እየኖረ፣እዚህ ከነችግሩ ጥሎት የሄደው ወገኑ ከድህነቱ እንዳይላቀቅ ይበልጥ ማጥ ውስጥ እንዲገባ፣ እንዲሰቃይ፣ እንዲንገላታና እንዲሞት ማድረግ ምን ይሉታል?አዙሮ የሚያየው አንገቱና ህሊናው ታውሮ እኩይ ተግባሩ ቢያሸንፈውም ታሪክ ይፋረደዋል::
በሀገር ውስጥም ሆኖ በጊዜያዊ ጠቅም ተደልሎ በወገኑ ላይ ስለት በማንሳትና ተረጋግቶ እንዳይኖር የሚያደርገውም በለው እያለ የሚደግፈው አካል እጁ ያጠረ ዕለት መግቢያ አይኖረውም:: ከብዙ ከብቶች መካከል አንድ በጥባጭ ካለ ሁሉም ይታመሳል::በጥባጩ ከመሀከላቸው ሲወጣ ግን ሌሎቹ ሰላማቸውን ያገኛሉ::ጥቂት አዋኪዎችም እንዲሁ እንደ ከብቶቹ ከብዙዎች መካከል ተለይተው መውጣታቸው አይቀርም::
ዛሬ በቀላሉ በእጁ በገባው ቴክኖሎጂ አሉና ተባለ እያለ በሀሰት ወሬ አገር ለማተራመስና በዜጎች ደም ሊነግድ የሚሯሯጡ ሀይሎችን በጋራ መታገል ያስፈልጋል::በተለይ ህዝባችን ማህበራዊ ትስስሩን አጠናክሮ በማስቀጠል ለእነዚህ አፍራሽ ሀይሎች እጅ ሊሰጥ አይገባም::በዓውድ ዓመት እየተጠራራ የሚገባበዘውና ዝምድናውን ለማጠናከር የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ባህል ስለሆነ ብቻ መሆን የለበትም:: እንደቀደመው ሁሉ በእውነተኛ ማንነቱ ጭምር መሆን ይኖርበታል::የነበረው የአንድነትና የመተሳሰብ ጥንካሬ ካልተመለሰ ለእኩይ ተግባር ለተነሳሱ እጅ ሰጥተን የማንወጣው ችግር ውስጥ እንዳንገባ እያንዳንዳችን ኢትዮጵያውያን አብሮነታችን እንደዓውዳ መታችን ይሁን::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2013 ዓ.ም