አዲስ አበባ፡- ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በሚካሄደው አራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራው ላይ የሚሳተፉ ባለሙያዎች ወደ ሥራው ከመግባታቸው በፊት ቃለ መሃላ እንደሚፈፅሙ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ገለፀ፡፡ ቆጠራውን በተመለከተ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተርና የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ፀሐፊ አቶ ቢራቱ ይገዙ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በቆጠራው የሚሳተፉ ባለሙያዎች ወደ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት ቃለ መሃላ እንዲፈጽሙ ይደረጋል፡፡ እንደ አቶ ቢራቱ ገለጻ ቃለ መሃላ እንዲደረግ የተፈለገው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የየራሱ እምነት ያለው በመሆኑ መረጃውን የሚሰበስበው ትክክለኛ መረጃ እንዲሰበስብ ነው፡፡ በቆጠራ ሥራው ላይ የሚሰማሩትና ተቆጣጣሪዎች ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ የጠቆሙት አቶ ቢራቱ ወደ 150 ሺ የሚገመት የቆጠራ ቦታ ካርታ እንዲሁም ከ37 ሺ በላይ የመቆጣጠሪያ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን እና በእያንዳንዱ ቦታም አንድ ተቆጣጣሪ እንደሚመደብ ገልጸዋል፡፡
አቶ ቢራቱ እንዳስረዱት በቆጠራው የሚሳተፉት የመንግሥት ሠራተኞች ሲሆኑ፣ በአብዛኛው ከመምህራን የሚመለመሉ ናቸው፡፡ ከእነርሱ በተጨማሪ የግብርና ባለሙያዎችና የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችም በምልመላው የሚካተቱ ይካተታሉ፡፡የመመልመያ መስፈርትም ተዘጋጅቷል፡፡ ከመስፈርቶቹ መካከል በቴክኖሎጂው እውቀት ያላቸው፣ በሥራ ምስጉን የሆኑ እንዲሁም በሥነ ምግባርም ችግር የሌለባቸው የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡ አራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ ከቀደምት ሦስት የህዝብና ቤት ቆጠራዎች በተሻለ ሁኔታ ቆጠራውን ለማካሄድ እና ውጤቱም የበለጠ ጥራትና በህዝብ ዘንድም ተዓማኒነት እንዲኖረው ሰፊ ሥራ በመሠራት ላይ ነው፡፡ ተደራሽነቱም ሁሉም ቦታ የሆነ፣ መረጃ አሰባሰቡ ላይም እያንዳንዱ ሰው ሳይቆጠር እንዳይታለፍ በሚያስችል መልኩ ዝግጅቶች በመገባደድ ላይ ናቸው፡፡ ቆጠራው ከተካሄደ በኋላም ውጤቱ በእያንዳንዱ ክልል ከቀበሌ ጀምሮ ያለውን የህዝብ ብዛት በትክክል ሊያሳይ በሚችል መልክ ዝግጅት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
በቴክኒክ ረገድ ያለውን ግብዓት ውጤታማ ለማድረግ በመስክም ፍተሻ ተደርጓል በዚህም ለቆጠራው ስኬታማነት ጥሩ ግብዓት መገኘቱን አቶ ቢራቱ አመልክተዋል፡፡ በቆጠራ ላይ ይከሰታል ተብሎ የሚገመተው የቁጥር ስህተትና አይነቱን ቀድሞ ማስወገጃ ሥርዓትም ተነድፏል፡፡ በቆጠራው እንቅስቃሴ ላይ በስጋትነት ከሚነሱት መካከል አንዱ የማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚራገበው ተዓማኒነት የሌለው ወሬ መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህ በህዝቡ ላይ ውዥንብር እንዳይፈጠር እውነትን ከሐሰት መለየት የሚጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በቆጠራው ወቅት ተፈናቃዮች ወደ መደበኛ ቦታዎች ተመልሰው እንደሚቆጠሩም ጠቁመው፤ ይህ ካልተቻለ ደግሞ ባሉበት ሁኔታ ቆጠራው ሊካሄድ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
‹‹የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን መረጃውን በመተንተን ከውሳኔ ሐሳብ ጋር በቴክኒክ እይታ እናቀርባለን፡፡ ያን የቀረበለትን የቴክኒክ እይታ በራሱ መርምሮ የመቀበል፣ እንደገና እንዲታይ የማድረግ እንዲሁም ወደ ምክር ቤት ከመቅረቡ በፊት ውድቅ የማድረግ ሥልጣን አለው፡፡ ውድቅ ማድረግ ማለት ሁለተኛ ቆጠራ እንዲካሄድ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ምክር ቤቱም በተመሳሳይ የማድረግ ሥልጣን አለው›› በማለት ያስረዱት አቶ ቢራቱ፤ ውጤቱም ቆጠራው ከተጠናቀቀ በኋላ ከአራት እስከ ስድስት ወራት ውስጥ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
በርካታ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ ኤጀንሲው የሠራው ትንበያ እንዳመለከተው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ 98 ሚሊዮን ይጠጋል፡፡ ተቆጥሮ ሲመጣ ግን ሊቀንስ አሊያም ሊጨምር እንደሚችል መታሰቡን አቶ ቢራቱ ገልጸዋል፡፡ ቃለ መሃላው ቀደም ሲል በተካሄዱ ሦስት ቆጠራዎች ተግባራዊ እየተደረገና በአራተኛው ቆጠራ ላይ የሚጀመር እንደሆነም ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2011
አስቴር ኤልያስ