በአገራችን በዓልና ቀጤማ ቁርኝታቸው ጠንከር ያለ ነው:: ቀጤማ /ለምለም ሳር/ በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የምስራች መገለጫ ተደርጎ ይታመናል:: ወቅቱ የትንሳኤ በዓል የሚከበርበት እንደመሆኑ ይህንኑ እሳቤ ተከትሎ ቀጤማ በሰፊው ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል:: በተለይም የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ከበዓሉ ሀሴት ጋር በተያያዘ የምስራች መግለጫ የሆነውን እርጥብ ሳር በቤታቸው ውስጥ በመጎዝጎዝ ተስፋቸውን ያለመልማሉ::
የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ስለቀጤማ ጥቅምና አስፈላጊነት ማስረዳት አይደለም፤ አንዲት በቀጤማ ንግድ ቤተሰቦቿን ከምታስተዳድር ምስኪን እናት የህይወት ተሞክሮ መማር ላይ ያነጣጠረ ነው::
ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ ነው:: አግር ጥሎኝ የካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አጠራር ካራ ፍተሻ ሰፈር ተገኝቻለሁ:: የትንሳኤን በዓል በተመለከተ ይመስላል ከአስፋልቱ ግራና ቀኝ ቀጤማ የሚሸጡ እናቶች ተኮልኩለዋል:: እንዳንዶቹ ቀና ለማለት እንኳ ጊዜ የላቸውም፤ ደንበኞቻቸውን አሰልፈው ይቸበችባሉ፤ ትንሽ ጠውለግ ያለ ቀጤማ የያዙትም ቢሆኑ የመጣላቸውን አድል እየተጠቀሙበት ነው:: ብቻ የቀጤማ ንግዱ ተጧጡፏል:: አንድ እፍኝ የማትሞላ እርጥብ ሳር እየተቋጠረች አስር አስር ብር ትሸጣለች::
ከአጨዳና ከሸክም ውጭ ምንም ወጪ ያልወጣባት ጭብጥ የማትሞላ እርጥብ ሳር አስር ብር እየተሸጠች አንድ ኪሎ ሽንኩርት ሰላሳ ብር ተሸጠ ብዬ ማጉረምረሜ ትክክል እንዳልሆነ ተሰማኝ:: ሽንኩርት ተመርቶ ገበያ እስኪደርስ ድረስ ከፍ ያለ የገንዘብና የጉልበት ወጪ ይጠይቃል:: ቀጤማ ግን ከጨፌ ቦታ ወይም ከወንዝ ዳር በቀላሉ ታጭዶ የሚመጣ መሆኑን ሳስብ እንዲህ ዋጋ ማውጣቱ ቢያስገርመኝ የሚገርም አይሆንም::
ትዝብቴ ሌሎች ሌሎች ነገሮችንም እንዳነሳ አደረገኝ:: የሸቀጦች ዋጋ ግሽበት ሲነሳ የውጭ ምንዛሬ እድገትና የነጋዴዎች አሻጥር እንደምክንያት ሲጠቀሱ እሰማለሁ:: የቀጤማ ዋጋ ጭማሬስ ምክንያቱ ምን ይሆን? ይህንኑ እያሰላሰልኩ ላነጋግራቸው የፈለግኳቸው እናት ፋታ እስኪያገኙ ድረስ ቆሜ እጠባበቅ ጀመር::
እዚያው እንደቆምኩ ልጅ እግሮቹ ነጋዴዎች የያዙትን ጨርሰው ማዳበሪያቸውን እያጣጠፉ ወደ ቤታቸው መሄድ ጀመሩ:: አዛውንቷ እናት ግን የያዙትን አልጨረሱም:: ግር ግር ሲፈጥሩ የነበሩ ገዢዎችም ቁጥራቸው ቀንሷል:: በዚህ መሃል ስለቀጤማ ንግዱ አንዳንድ ጥያቄዎችን ለአዛውንቷ አቀረብኩላቸው:: ስለህይወት ታሪካቸው በጨረፍታ ነግረውኝ ሲያበቁ ስለስራቸውና አሁን ስለሚኖሩት ህይወት ጠቆም ጠቆም አደረጉኝ::
ምስኪኗ እናት በትዳርና በኑሮ ምሬት ምክንያት ይኖሩባት ከነበረው አንዲት የገጠር ቀበሌ ጠፍተው ወደ አዲስ አበባ ከተማ ከመጡ ከሃያ ዓመት በላይ ሆኗቸዋል:: በአዲስ አበባ ከተማ ትዳር መስርተው አዲስ ህይወት መኖር ቢጀምሩም የሁለት ልጆቻቸው አባት ለስራ ወደ ክፍለ አገር እንደሄዱ በዚያው የውሃ ሽታ ሆነው ቀርተውባቸዋል:: እስከ አሁን ድረስ ይኑሩ ይሙቱ አያውቁም::
በዚህ የተነሳ ልብስ እያጠቡና እንጀራ እየጋገሩ ሁለት ልጆቻቸውን ለማሳደግ ይገደዳሉ:: አቅማቸው እየደከመ ሲመጣ ደግሞ እንደየወቅቱ ሁኔታ ጎመን ቀጤማና የወይራ ስንጥር እየሸጡ ለመኖር መገደዳቸውን ነገሩኝ:: ምስኪኗ እናት ቤት ተከራይተው እየኖሩ የእለት ጉርሳቸውን ለመሸፈንና ልጆቻቸውን ለማስተማር የሚያደርጉት ጥረት ለሌሎች አስተማሪ በመሆኑ የዚህ አምድ እንግዳ ላደርጋቸው ወደድኩ:: የህይወት ታሪካቸውን ሊያካፍሉኝ ስለፈቀዱ አመስግኛቸው ወደ ወጋችን ገባን::
ወይዘሮ መሬማ መኮንን ይባላሉ:: ተወልደው ያደጉት ወሎ ክፍለ አገር ወረ ሂበኖ ወረዳ በአንዲት አነስተኛ የገጠር መንደር ውስጥ ነው:: በልጅነታቸው በግብርና ስራ የሚተዳደሩ ቤተሰቦቻቸውን በስራ እያገዙ ማደጋቸውን ይናገራሉ:: ከቤት እስከ ውጭ ስራዎችን ሰርተዋል:: ትምህርት የመማር እድል አላገኙም:: የያኔዋ ኮረዳ እድሜያቸው ለአቅመ ሄዋን ሲደርስ በቤተሰቦቻቸው አስገዳጅነት የመጣላቸውን ባል እንዲያገቡ መገደዳቸውን ይናገራሉ::
በመልክም ይሁን በባህሪ ከማያውቁት ሰው ጋር ተጋብተው መኖር ይጀምራሉ:: አንድ ልጅ ከወለዱ በኋላ ባለቤታቸው በሚያደርስባቸው በደል ምክንያት ትዳራቸውን ትተው ወደ ወላጆቻቸው ቤት ይመለሳሉ:: ወላጆቻቸው እያስታረቋቸውና እየተቆጧቸው ተመልሰው እንዲሄዱ ጫና ያደርጉባቸው እንደነበር ይገልጻሉ::
በተደጋጋሚ ከባለቤታቸው ጋር እየተጋጩ ወደ ቤተሰቦቻቸው ይሄዱ የነበሩት ወይዘሮ አንድ ቀን ላለመመለስ ወስነው እዚያው መኖር ይጀምራሉ:: ትዳር ፈቶ ወላጆች ቤት መቀመጥ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ እንደነውር እንደሚቆጠር የሚናገሩት ወይዘሮ መሬማ ለሁለተኛ ጊዜ ከሌላ ሰው ጋር ትዳር መስርተው ከወላጆቻቸው ቤት ይወጣሉ:: የመጀመሪያ ልጃቸውን ወላጆቻቸው ጋር ትተው አዲስ ጎጆ ይመሰርታሉ:: ከሁለተኛው ባለቤታቸው ጋር እራቅ ወዳለ ሌላ የገጠር አካባቢ ሄደው መኖር ይጀምራሉ::
ወይዘሮ መሬም ስለሁለተኛው ትዳራቸው እንዲህ ያስረዳሉ ‹‹ትሻልን ትቼ ትብስን አገባሁ፤ እንደሚባለው ለሁለተኛ ጊዜ ያገባሁት ባለቤቴም ከመጀመሪያው የባሰ ይሆንብኛል:: ነጋ ጠባ ይጨቃጨቃል፤ አንዳንዴም ለዱላ ይጋበዛል:: ዳግም ፈት ላለመባልና የማህበረሰቡን ትችት በመፍራት የሚያደርስብኝን በደል እየተቋቋምኩ ለመኖር ሞከርኩ:: እርሱ ግን ከዚህ በኋላ ከእኔ ጋር ከመኖር ውጭ ሌላ አማራጭ የላትም በሚል መሰለኝ ቁም ስቅሌን አሳየኝ:: ቤተሰቦቼን ላለማሳፈር ስል እየተበደልኩም ችዬ ለመኖር ብርቱ ጥረት አደረግኩኝ:: ማርም ሲበዛ ይመራል እንደሚባለው ከልክ በላይ ስንገፈገፍ አሁንም ከሁለተኛው ባለቤቴ ጋር ለመለያየት በቃሁ:: ከእርሱም ጋር እያለሁ አንድ ልጅ ወልጄ ነበር::
ከዚያ በኋላ ግን በዚያ አካባቢ ባል አግብቶ የመኖሩን ጉዳይ እርም ብዬ ሁለቱንም ልጆቼን ወላጆቼ ጋር በመተው ብን ብዬ ከአገር ጠፋሁ:: ከአገሬ ስወጣ ዋናው ዓላማዬ ሰርቼ ለመኖርና ልጆቼንም ለመርዳት በማሰብ ነበር:: በዚህ ሁኔታ ነበር ከሃያ ዓመት በፊት ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት::
አዲስ አበባ እንደመጣሁ ሰው ቤት ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩኝ:: የቤት ውስጥ ስራ እየሰራሁ ለዓመታታ ካሳለፍኩኝ በኋላ እራሴን ችዬ ለመኖር በማሰብ ቤት ተከራይቼ ያገኘሁትን ስራ እየሰራሁ መኖር ጀመርኩኝ:: ልብስ አጥባለሁ፣ ድግስ ባለበት ቤት እየተከፈለኝ እሰራለሁ፤ እንጀራ እየጋገርኩ እሸጣለሁ::
ህይወቴን በዚህ መልክ እየገፋሁ እያለ አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ አንድ ሰው የትዳር ጥያቄ አቀረበልኝ:: “እባብን ያየ በልጥ በረየ” እንዲሉ በትዳር ጉዳይ የደረሰብኝን የህይወት ፈተና ነግሬው የማግባት ፍላጎት እንደሌለኝ ገለጽኩለት:: ሰውየው ሰርቶ የሚያድርና የግንበኝነት ሙያ ያለው ነው:: አብረን ብንኖር ኑሮን መቋቋም እንደምንችልና ልጆችን ወልደን ማሳደግ እንደምንችል ይሰብከኝ ጀመር:: እኔም ለሶስተኛ ጊዜ ስህተት ውስጥ ላለመግባት አብሬው ከመኖሬ በፊት ስለባህሪው ማጥናት ጀመርኩ::
በእርግጥም መልካም ሰው ነው:: ጥሮ ግሮ ከመኖር ውጭ መጥፎ አመል የሌለበት ሰው መሆኑን ስረዳ አብረን መኖር ጀመርን:: ሁለታችንም እየሰራን ኑሯችንን ለማሸነፍ ተጋን:: አንድ ወንድ ልጅም ወለደን:: ፈጣሪ በትዳር የደረሰብኝን በደል ተመልክቶ የካሰኝ እስኪመስለኝ ድረስ ትዳሩን የሚያከብርና ልጁንም የሚወድ፣ የሚንከባከብ ሰው ስለሰጠኝ ደስ ብሎኝ እኖር ነበር ›› ይላሉ ወይዘሮ መሬም::
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ባልታሰበ ሁኔታ ሌላ የህይወት ፈተና ውስጥ እንደገቡ ወይዘሮ መሬም ይናገራሉ:: ባለቤታቸው ከዛሬ አስር ዓመት በፊት በግንበኝነት ሙያ የተሻለ ክፍያ አግኝተው ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ለመሄድ መዘጋጀታቸውን ይነግሯቸዋል:: ወትሮም ከልጃቸው መለየት የማይሆንላቸው አባት የቤተሰባቸውን ኑሮ ለማሻሻል ሲሉ ርቆ መስራቱ የውዴታ ግዴታ እንደሆባቸው በመግለጽ እቃቸውን ሸክፈው የሚያሰራቸውን ፎርማን ተከትለው ወደ ተባለው ቦታ ይሄዳሉ:: በዚህን ጊዜ ወይዘሮ መሬም ሁለተኛ ሴት ልጃቸውን ሊወልዱ የአምስት ወር ነፍሰ ጡር ነበሩ::
ለወይዘሮ መሬም የነገሯቸውም ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ የሚሄዱ መሆኑን እንጂ ልዩ ቦታው ምን አንደሚባል አልገለጹላቸውም:: እንደ ወይዘሮ መሬም አባባል ባለቤታቸው የሚሄዱበትን ቦታ ስም ያልነገሯቸው በውል የቦታውን ስም ስለማያውቁት ነው::
ባለቤታቸው እግራቸው ከቤት ከወጣ ጀምሮ ቀናት ተቆጠሩ፤ ወራት አለፉ፤ ዓመታትም ነጎዱ ድምጻቸው ግን የለም:: በህይወት ይኑሩ አይኑሩ የሚታወቅ ነገር የለም:: ወይዘሮ መሬም ዛሬም የልጆቻቸው አባት የውሃ ሽታ ሆኖ መቅረት ያስጨንቃቸዋል:: በተለይም በአካል የሚያውቃቸው ወንዱ ልጃቸው ሁሌም እንደሚናፍቃቸው እና ሴት ልጃቸውም አባቷን የማወቅ ጉጉት እንዳላት ይገልጻሉ:: ድምጻቸው ከጠፋ አስር ዓመት ቢያልፍም ቤተሰቡ ተስፋ ሳይቆርጥ አሁን ድረስ እየጠበቋቸው መሆኑን ይናገራሉ::
የሁለቱ ልጆቻቸው ጉዳይ በእርሳቸው ትከሻ ላይ ብቻ ከወደቀ አስር ዓመታት አለፉ:: ቀደም ሲል ልብስ እያጠቡና ሰው ቤት እንጀራ በመጋገር በሚያገኙት ገንዘብ ልጆቻቸውን ያኖሯቸው እንደነበር የሚናገሩት እናት አሁን ግን ጉልበታቸው እየደከመ ሲመጣ ቀጤማና ጎመን ከነጋዴዎች ላይ እየተረከቡ በመሸጥ በሚያገኗት ትርፍ እንደሚኖሩ ይገልጻሉ:: ወይዘሮ መሬም የሰባ ብር ቀጤማ ከነጋዴዎች ላይ በመውሰድ በችርቻሮ መቶ ብር እያጣሩ ሰባውን ካስረከቡ በኋላ ሰላሳውን ለራሳቸው እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ::
አልፎ አልፎም ጎመን በተመሳሳይ መልክ ከነጋዴዎች እየወሰዱ በሚያገኟት ጥቅም ይኖራሉ:: የቀጤማ ችርቻሮ ወቅታዊ እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ መሬም ከዓመት በዓል ውጭ ባሉ የአዘቦት ቀናት የተጠቀሰውን ያህል ጥቅም እንደማያገኙ ይናገራሉ:: ገበያ ሲጠፋ እንደውም ቀጤማው እየደረቀ እንደሚጣል ይገልጻሉ:: ጎን ለጎን ለማጠንት የሚሆን የወይራ እንጨት እና ጎመን በመሸጥ ገቢያቸውን ለማካካስ እንደሚጥሩ ያስረዳሉ::
ወይዘሮ መሬምን ያገኘኋቸው በረመዳን የጾም ወቅት ነው:: እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ ከሸጡ በኋላ ልክ የሶላት ሰዓት ሲደርስ እቤታቸው ሄደው ይሰግዳሉ:: ከሶላት በኋላ እስከ አስራ ሁለት ሰዓት እዚያው እስራ ቦታቸው ቆይተው ማታ ገብተው ያፈጥራሉ::
ሁል ጊዜ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ ባገኟት ሳንቲም ለልጆቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ገዝተው ይገባሉ:: በቀጤማ ችርቻሮ ጤፍ ገዝቶ እንጀራ የመጋገር አቅም ባይኖራቸውም እንጀራና ዳቦ እየገዙ ወጥ ሰርተው ያበሏቸዋል::
ሴት ልጃቸው የጁኔር ተማሪ ስለሆነችና እዚያው ትምህርት ቤት የምትመገብ መሆኗ እገዛ እንዳደረገላቸው ይናገራሉ:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማረው ወንዱ ልጃቸውም ቢሆን የዩኒፎርምና የደብተር ወጪው የሚሸፈነው በመንግስት መሆኑ እፎይታ እንደሰጣቸው ይገልጻሉ::
ወይዘሮ መሬማ በየወሩ ለቤት ኪራይ የሚከፍልላቸው ገጠር በግብርና ስራ የሚተዳደረው ወንድማቸው መሆኑን ይናገራሉ:: ወንድማቸው ከእኔ ችግር ያንቺ ይብሳል በሚል ድጋፍ ባያደርግላቸው ኖሮ ልጆቻቸውን ይዘው ጎዳና ለመውጣት እንደሚገደዱ ይገልጻሉ:: አሁን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አስራ ሁለት ትንሽ ቤት ተከራይተው ከኑሮ ጋር የጀመሩትን ግብ ግብ ቀጥለዋል::
ለበርካታ ጊዜ ቀበሌ በመመላለስ የመኖሪያ ቤት ችግራቸው እንዲፈታላቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም መልስ የሚሰጣቸው አካል አለመኖሩን ያስረዳሉ:: የወረዳው አስተዳደር ሰራተኞች ቀጤማ እየቸረቸርኩ እንደምኖር ብገልጽላቸውም ያለሁበትን የኑሮ ደረጃ ተገንዝበው ሊረዱኝ አልቻሉም ይላሉ:: አሁንም የመኖሪያ ቤት ችግሬን እንዲፈቱልኝ በዚህ አጋጣሚ ተማጽኖዬን አስተላልፉልኝ ብለዋል:: መልካሙን ሁሉ ተመኘንላቸው:: ቸር እንሰንብት
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2013