አንገታቸውን አስረዝመው ከተቀመጡበት በስተቀኝ አቅጣጫ የሚሰማውን ነጎድጓዳዊ ድምጽ ለማጣራት ሲማትሩ የሚታዩ በርካቶች ናቸው፡፡ ያ ነጎድጓዳዊ ድምጽ ቅርበቱ እየጨመረ ሲመጣ ደስታም ፍርሃትም ያከናንባል፡፡ አንዳች የሚንጥ ኃይልን የተጎናፀፉት ‹‹su-27 ኢንተርሴፕተር›› ተዋጊ ጄቶች የአየር ላይ ትርዒቶችን በማሳየት ከፊታችን ከመቅጽበት ተሰወሩ፡፡ ከትርዒት አቅራቢዎች አንዱ ተዋጊ ጄት ለሰው ልጆች በመሬት ላይ ሆኖ ለማሳየት አዳጋች የሆነውን የመገለባበጥ ትርኢት እንዲሁ እንደዋዛ በአየር ላይ እያሳየ የታዳሚውን ሁሉ ቀልብ ሰረቀ፡፡
ትርዒቱ አላለቀም የታዳሚው ነፍስ ጦር ሜዳ የገባ ያክል እንዲሰማው የሚያደርጉት ሌሎች እንደ ‹‹Mi-35›› ያሉ ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች፣ ‹‹Mi-17 ሄሊኮፕተር››፣ ‹‹Mig ቦምበር›› ሁሉ ተራቸውን እየጠበቁ ልብን የሚሰቅሉ የአየር ላይ ትርኢቶችን ያሳዩ ጀመር፡፡ ከመሬት ወለል በላይ ከ18 ሺህ ኪሎሜትር በላይ ርቀትን ተወንጭፈው የመሄድ አቅም ያላቸው እነዚህ ተዋጊ ጀቶች ታዲያ ብዙም ሳይቆዩ ወደላይ ሲፈተለኩ ከዕይታ ይሰወራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ‹‹አንቶኖቭ 12 የትራንስፖርት›› አውሮፕላን የጠላት አውሮፕላን የአየር ክልል ጥሶ ቢገባ እንዴት ተደርጎ በቁጥጥር ሥር ሊውል እንደሚችል የሚያሳይ ትርዒት አሳየ፡ ይህ ሁሉ የሆነው በአዳማ ከተማ በተካሄደው ሰባተኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን የመዝጊያ መርሃ ግብር ላይ ነው፡፡
በመሳሪያና በሄሊኮፕተር ታጅበው ከቀረቡት ትርዒቶች በተጨማሪ የአየር ኃይል፣ ምድር ኃይል፣ የኮማንዶና የልዩ ኃይል አባላት የሰልፍ፣ ጠላትን የመከላከልና የማጥቃት ብቃታቸውን አሳይተዋል፡፡ በመድረኩ ከተለያዩ አገራት ተጋባዥ ሆነው የተገኙ ኤታማዦር ሹሞች፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር አብይ አህመድ፣ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮችና የቀድሞ የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ሳሞራ የኑስ፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች፣ የቀድሞ የሠራዊቱ አባላት እንዲሁም የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ታድመዋል፡፡ በዚሁ ወቅት ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከአዳማ ከተማ አስተዳደር ለተቋሙ ሚኒስትርና ለጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሰዓረ መኮንን ሽልማት ተበርክቷል፡፡
‹‹ሕገመንግሥታዊ ታማኝነታችንንና ሕዝባዊ ባህሪያችንን ጠብቀን የተጀመረውን ለውጥ እናስቀጥላለን›› በሚል መሪ ሃሳብ በትላንትናው ዕለት በአዳማ ከተማ በተደረገው የሠራዊት ቀን መዝጊያ መርሃ ግብር ላይ የአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ይልማ መርዳሳ እንደተናገሩት፤ ሠራዊቱ ባለፉት ዓመታት አገርንና ሕዝብን ከመጠበቅ ባሻገር በልማቱም ላይ ሲያበረክት የነበረው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው፡፡ ቀኑ መከበሩም ከሕዝቡ ጋር ተገናኝቶ ህብረቱንና አንድነቱን እንዲያረጋግጥ ያግዘዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ህዝቡ ሲያነሳቸው የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ከፍተኛ ቅሬታዎችን መንግሥት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ለለውጥ እየሠራ ሲሆን፤ ተቋሙም ካለበት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚረዳውን የለውጥ ሥራ ጀምሯል፡፡
ብቃትንና ብሔራዊ ተዋፅዎን በጠበቀ ሁኔታ ከየትኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ ነፃ ሆኖ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ግዳጁን በብቃት የሚወጣበት፣ የተጣለበትን ኃላፊነትና አደራ ከዳር የሚያደርስበት አሰራር እየተዘረጋ ይገኛል፡ ፡ በዚህም የነፃነት ጮራ ይበልጥ እየደመቀ እንደሚጓዝ ጀኔራል ይልማ ጠቁመዋል፡፡ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሰዓረ መኮንን በመድረኩ እንደገለጹት፤ ዕለቱ ያለፉ ሰማዕታት የሚዘከርበት፣ ሠራዊቱ ቃሉን የሚያድስበትና ሕዝባዊ ወገንተኝነቱ የሚጠናከርበት ነው፡፡ ለዚህም ተቋሙ ማሻሻያ እያደረገ ሲሆን፤ ሕገ መንግሥቱንና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በማስጠበቅ ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቀድሞ ሲሠራው ከነበረው በላቀ ደረጃ ለማከናወን አቅዶ እንቅስቃሴን ጀምሯል፡፡
ጀኔራል ሰዓረ፤ ከምንም በላይ ጠንካራ ቁመና ያለው ሠራዊት ለመገንባት ብሎም ኑሮውን ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡ በሌላ በኩል በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጠሩ ግጭትና አለመረጋጋቶች ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን በጠበቀ ሁኔታ ሠላምን ለማስጠበቅ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም መንግሥት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማረጋገጥ፣ የሕዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማስፈን እንዲሁም የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለል በቁርጠኝነት እየሠራ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅትም በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ክቡር የሰው ልጆች ሕይወት ሲቀጠፍና ተቋማት ጉዳት ሲደርስባቸው ይታያል፡፡ በመሆኑም ችግሮቹን ለማቃለል ሕብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም የሠላም ማስከበሩን ጉዳይ በባለቤትነት ሊሠራ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር አብይ አህመድ፤ ሠራዊቱ በታማኝነት፣ በቁርጠኝነትና ከምንም በላይ ለአገርና ለሕዝብ ቅድሚያ በመስጠት ታላቅ መስዋዕትነት እየከፈለ ያለ ተቋም መሆኑን አወድሰው፤ ሠራዊቱ ከአገሪቱ አልፎ ለሰላም ማስከበር በተሰማራባቸው አገራት ሁሉ በውጤታማነትና በሕዝባዊ ወገንተኝነቱ ምስጉን ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ አሰራሩንም ሆነ ሕይወቱን ዘመኑ ከሚጠይቀው ነባራዊና ንድፈ ሃሳባዊ ደረጃ ጋር ከማስተሳሰር አንፃር በርካታ ውስንነቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡ ፡
ውስጣዊ አሰራሩ ግልጽነት የጎደለውና ለብልሹ አሰራሮች በር የሚከፍት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት እየተገነባ ያለው የመከላከያ ሠራዊት ዛሬ የሁሉንም ሉዓላዊነት የሚጠብቅ ነገ ደግሞ የሕዝብ ውክልና አግኝታችሁ ሥልጣን የምትይዙ ተረክባችሁ የምታስቀጥሉት ተቋም ነው›› ሲሉ ተቋሙን ሁሉም በባለቤትነት ስሜት ሊደግፈው እንደሚገባ ዶክተር አብይ ተናግረዋል፡፡
ዶክተር አብይ የነበሩትን ክፍተቶች በሚሞላ መልኩ ሪፎርም እያደረገ እንደሚገኝ፤ በዚህም የተቋሙን ቁመና ከማዘመንና ከማጠናከር ባሻገር ምሁራን የሆኑ እጩ መኮንኖችም ወደ ተቋሙ እንዲገቡ የሚስችል መሆኑን፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ፍላጎት ላላቸው ወጣቶችም መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ሪፎርሙም ተቋሙ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ፀድቶ ሙያዊ ሂደቱን ጠብቆ የሚያድግበትን ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ ለዛሬም ሆነ ለነገ የማይበጁ እኩይ ተግባራትም የሚጨምሩት በጎ ነገር ባለመኖሩ ሁሉም አሽቀንጥሮ ሊጥላቸው እንደሚገባ፤ አፍርሶ የመገንባት ሂደት አገሪቱን ከማሳደግ ይልቅ ጎታች በመሆኑ ያለው ላይ ማስተካከያ በማድረግ የጎደለውን እየሞሉና ክፍተቶችን በቅንነት እያረሙ መጓዝ አማራጭ መሆን እንዳለበት፤ ይህም የሚፈለገውን ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣት ያስችላልና ከዳር ሆኖ ተቋሙን ከመንቀፍና ከአፍራሽ የጅምላ ፍረጃ በመውጣት በባለቤትነት ስሜት ችግሩ እንዲቃለል በመወትወት ተማሪና አዳጊ ተቋም መፍጠር የሁሉም ድርሻ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2011
ፍዮሪ ተወልደ