ወይዘሮዋ ለዓመታት በፍቅርና በመተሳሰብ ያፀኑት ትዳር በባላቸው ሞት ምክንያት ቤታቸው ቀዝቅዟል:: ባለቤታቸውን ካጡ ወዲህ በብዙ ይጨነቃሉ:: አሁን በአባወራው ትከሻ የነበሩ በርካታ ስራዎች የእሳቸው ድርሻ ሆነዋል:: ሁሌም እየተከዙ ለነገው ይወጥናሉ፣ ስለልጆች ያስባሉ፣ ስለራሳቸው ስለኑሮና ገቢያቸው ያወጣሉ፣ ያወርዳሉ:: ከሁሉም ግን አንድ ጉዳይ ያስጨንቃቸው ይዟል::
እስከዛሬ የቤተሰቡ መተዳደሪያ የእርሻ መሬት ነው:: በዚህ መሬት ሟች ባለቤታቸው እያረሱ ምርት ሲያፍሱበት ኖረዋል:: የቤተሰቡ ህልውና ነውና ከዓመት ዓመት በረከቱን መጠበቅ፣ ክምር ምርቱን መናፈቅ ልምድ ሆኖ ቆይቷል::
የእርሻ መሬቱ ከሟች አባወራው እናት የተላለፈ ሐብት ነው። እናት ልጃቸው በነበረ ጊዜ ለልጆች ማሣዳጊያ ለቤተሰቡ መተዳደሪያ ይሆን ዘንድ አበርክተዋል:: ልጅም በተራው መሬቱን እያረሰ መላ ቤተሰቡን ሲያኖርበት፤ እሱም ሲጠቀምበት ዘልቋል::
ወይዘሮ እናት በለጠ ከሰሞኑ ይህን እያሰቡ ትካዜ ገብቷቸዋል:: የቤተሰቡ ህልውና ሆኖ የቆየው የእርሻ መሬት እንደነበረው ላይቀጥል ፈተና እንደገጠመው አውቀዋል:: ባለቤታቸውና እናትዬው ከሞቱ በኋላ መሬቱ የሌላ ቤተሰብ ይዞታ ሆኗል:: ይህ ቢገባቸውም አሁንም ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጡም::
መሬቱን ወስደው መጠቀም የጀመሩት ወይዘሮ መብራት ድርጊታቸውን እንደመብት ይቆጥሩታል:: ለምን ለሚላቸው ደግሞ ከማንም በላይ እርሳቸው ቤተሰብ ስለመሆናቸው ዘርዝረው ይናገራሉ:: ለዚህ ማሳያም በቤተሰብ አባልነት የተመዘገቡት እርሳቸውና ልጆቻቸው እንደሆኑ እየጠቀሱ ማስረጃና እማኝ ይቆጥራሉ::
ወይዘሮ እናት የወይዘሮ መብራትን ድርጊትና ውሳኔ ካወቁ በኋላ ጉዳዩን በሠላም ለመፍታት በሽማግሌ አስጠየቁ:: ችግራቸውን እየነገሩ፣ ኑሯቸውን እያሳዩ በልመና ተማለዱ:: በዚህ መንገድ መፍትሄ አልመጣም፣ ችግር አልተፈታም:: ወይዘሮ መብራት መሬቱን እንደያዙ፣ ወይዘሮ እናት እንደለመኑ፣ እንዳስለመኑ ጊዚያት ተቆጠሩ::
የመጀመሪያው ክስ..
ቀናት ያለመፍትሄ መንጎዳቸውን ይዘዋል:: እስካሁን በሁለቱ ሴቶች መሀል የተፈጠረው አለመግባባት በወጉ አልተፈታም:: ወይዘሮ እናት ለሆነባቸው ችግር ብቸኛው የመፍቻ መንገድ ህግ መሆኑን ተረድተዋል:: ‹‹ተያዘብኝ›› ላሉት መሬታቸው መፍትሄ በመሻት ውሳኔ ይሰጠኝ ፣ ፍትህ ይፍረደኝ ሲሉም ወደ ፍርድ ቤት አምርተዋል::
የምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠሀናን ወረዳ ፍርድቤት በአመልካቿ የቀረበለትን አቤቱታ መመርመር ጀምሯል:: ወይዘሮዋ በክሳቸው እንዳመለከቱት ሟች ባለቤታቸውና እናትዬው በህይወት አለመኖራቸውን ተከትሎ ተጠሪ ወይዘሮ መብራት ቤዛ በህገወጥ መንገድ የእርሻ መሬታቸውን እንደወሰዱባቸው ጠቁመዋል:: ድርጊቱ ከህግ ውጭ ነው ያሉት አመልካች ይኸው ታውቆ የተያዘው መሬት ይለቀቅልኝ ሲሉ ጠይቀዋል::
ከሳሽና ተከሳሽ …
ፍርድ ቤቱ የከሳሽን ሀሳብ ተቀብሎና ተከሳሽን አቅርቦ ስለጉዳዩ ጠየቀ:: ከሳሽ ተጠሪዋ ‹‹ፈጸሙብኝ›› ያሉትን በደል አስቀድመው ችግሩን በዝርዝር አስረዱ:: ቦታው ቀደም ሲል የባለቤታቸው እናት የነበረና ለልጃቸው ወይም ለእርሳቸው ባለቤት አሳልፈው መስጠታቸውን ጭምር ማስረጃ እየጠቀሱ ገለጹ:: እስከዛሬም በዚህ የእርሻ መሬት ሲጠቀሙበት እንደቆዩና አሁንም የቤተሰቡ ህልውና የተመሰረተው በመሬቱ ላይ መሆኑን ተናገሩ::
ተጠሪዋ በፍርድ ቤቱ ቀርበው የተጠየቁትን አንድ በአንድ መለሱ:: በመሬት ይዞታው ላይ ‹‹ይገባቸዋል›› ያሉትን አራት ሰዎች በስም ጠርተውም አስመዘገቡ:: የወረዳው ፍርድ ቤት ተጠሪዋ ከሰጡት ምላሽ ተነስቶ የጃቢ ጠሀናን ወረዳ አካባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ስለጉዳዩ አጣርቶ ምላሽ እንዲሰጥበት አዘዘ::
ጽህፈት ቤቱም በበኩሉ በይዞታው ላይ በቁጥር አራት ሆነው የተመዘገቡ ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሶ የስም ዝርዝራቸው ግን በውል ተለይቶ ያለመቀመጡን አስታወቀ:: ይህም ጭብጥ በጽህፈት ቤቱ በኩል ምንም ማስረጃ እንዳልተያያዘበት ጭምር ጠቅሶ ገለጸ::
ፍርድ ቤቱ ከአስተዳደር ጽህፈት ቤቱ የተሰጠውን ምላሸ ይዞ ተጠሪዋን መልሶ ጠየቀ:: ተጠሪ የአራት ሰዎችን ማንነት በተመለከተ የስም ዝርዝራቸውን ለይተው ሊመሰክሩልኝ ይችላሉ ያሏቸውን እማኞች አቀረቡ::
እማኞቹ አራቱን ሰዎች በስም ዘርዝረው የተጠሪዋ ልጆች መሆናቸውን መሰከሩ:: ፍርድ ቤቱ የተጠሪዋን ቃል ከእማኞች ምስክርነት አዛምዶ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑት አራት ልጆችና ወላጅ እናታቸው የተጠቀሰውን ይዞታ ሊለቁ አይገባም በማለት ውሳኔ አስተላለፈ።
አቤቱታ…
አመልካች ወይዘሮ እናኑ በለጠ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንደሰሙ ለምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማመልከቻ አስገብተው ‹‹ይግባኝ›› አሉ :: ፍርድ ቤቱ የአመልካቿን አቤቱታ ተመልክቶ ምርመራውን ማጣራት ጀመረ:: በመጨረሻም ቀደም ሲል በስር ፍርድ ቤቱ የተላለፈውን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ፍርዱ ትክክል ነው ሲል አፀናው።
አመልካች አሁንም የምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያሳለፈባቸውን ውሳኔ በይሁንታ አልተቀበሉም:: በወረዳው የዐቃቤ ህግ ባለሙያ አስወክለው አቤቱታቸውን ቀጠሉ:: በማመልከቻቸውም ተጠሪዋ በሀሰት ምስክርነት ያቀረቡት የአራት ሰዎች ማንነትና የወረዳው ፍርድ ቤት ውሳኔ ተገቢ ባለመሆኑ ውሳኔው ይሻርልኝ ሲሉ ጠየቁ:: የጃቢ ጠሀናን ወረዳ የአካባቢ ጥበቃ መሬት አስተዳደር ጽህፈት ቤት የሰጠውን ማስረጃ በማጣቀስም ውሳኔው ያልተገባ ነው ሲሉ ተቃወሙ::
የወረዳው ፍርድ ቤት የሁለቱን ወገኖች ጉዳይ መልሶ በማየት ማከራከሩን ቀጠለ:: ማስረጃዎች ዳግመኛ ተፈተሹ:: የቀረቡ ሰነዶች አንድ በአንድ መታየት ጀመሩ:: ፍርድ ቤቱ ምርመራውን ሲያጠናቅቅ የቀድሞ ውሳኔውን ሽሮ የመሬት ይዞታው የሚገባው ለአመልካች ነው ሲል ብይኑን አሻሻለ::
አሁን የተጠሪዋ የቀድሞ ውሳኔ በአመልካቿ ዳግም ክስ ተፈትሾ ተቀልብሷል:: ተጠሪ በበኩላቸው ከፍርድ ቤቱ የተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም ለምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሲሉ አቀረቡ:: የምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማመልከቻውን ከቀረቡ ሰነዶች ጋር አገናዝቦ መመርመርና መፈተሸ ያዘ::
ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ባይዋ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህግ ቁጥር 5 መሰረት መስፈርቱን ስለማሟላታቸው ሳያስረዱ የቀድሞው ውሰኔ መሻሩ አግባብ አይደለም ሲል ለተጠሪዋ መልሶ የ‹‹ይገባቸዋል›› ውሳኔውን አሳለፈ:: የዚህ ውሳኔ ግልባጭም ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ሆኖ ውሳኔው በነበረው ሂደት እንዲፀና ተደረገ:: ይህ ውሳኔ በዚህ ብቻ አልተቋጨም:: ጉዳዩ ወደ ሰበር ችሎት ሊተላለፍ ግድ አለ::
ዳግም ችሎት…
የክርክር ሂደቱን በሰበር ስልጣናቸው የተመለከቱት የአማራ ክልል ሰበር ሰሚ ችሎትና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን መልሰው መፈተሸ ያዙ:: የሁለቱን ወገኖች የሕግ አካሄድ በጥልቀት ተመልክተውም በጉዳዩ ላይ መሰረታዊ የሚባል የህግ ስህተት አልተፈፀመም ሲሉ የጋራ ውሳኔ አሳለፉ::
አመልካች ከሰበር ሰሚ ችሎቱ የተላለፈውን ውሳኔ ተቀብለው ዝምታን አልመረጡም:: አሁንም ክሱን በማንቀሳቀስ የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም ለአጣሪ ጉባኤው አቤቱታ ጽፈው አስገቡ::
ወይዘሮዋ ባስገቡት አቤቱታ በ1989 ዓ.ም በተደረገው የመሬት ሽግሽግ በሟች ባለቤታቸው እናት አማካኝነት በቤተሰብ አባልነት መመዝገባቸውንና መሬቱን እስከ 2001 ዓ.ም ድረሰ ሲጠቀሙበት እንደቆዩ አስረዱ:: ይሁን እንጂ ባላቸውን በሞት ከተነጠቁ በኋላ የባለቤታቸው እህት ይዞታውን ያለአግባብ በመንጠቅ እንደወሰዱባቸው ጠቀሱ::
የይዞታቸውን መነጠቅ አስመልክቶ በፍርድ ቤት ክስ መመስረታቸውን የጠቆሙት አመልካች በተለያዩ ጊዜያት ጉዳዩ ሲያከራክር ቆይቶ ፍርድ ቤቶቹ ለተጠሪዋ ይገባቸዋል ሲሉ መወሰናቸውን በማመልከቻቸው ገልጸዋል:: ወይዘሮዋ አያይዘውም ውሳኔው የሕገመንግስቱን አንቀጽ 40/3/ እና 40/4/ላይ የተቀመጠውን ሕግ በመጣስ ከይዞታዬ ያፈናቀለኝ በመሆኑ የህገመንግስት ትርጉም ይሰጥልኝ ሲሉ ጠየቁ::
ምክር ቤቱ የጉዳዩን መነሻ ከስር መርምሮ ጉዳዩን ማጣራት ጀመረ:: የቤተሰብ አባላት ናቸው የተባሉ የአራት ልጆች ጉዳይና ከመሬት ይዞታው ጋር ተያይዞ ተፈጽሟል የተባለ የሀሰት ምስክርነት ሂደትን ለማጣራት ሞከረ:: ጉባኤው ጉዳዩን ሲመረምር የይዞታ መሬቱ ቀድሞ የማን እንደነበርና ማን ሲጠቀምበት እንደቆየ በማስረጃዎች አጣራ:: የአመልካችና የተጠሪ መተዳደሪያ ምን እንደሆነና ሁለቱ ግለሰቦች አርሶ አደር መሆን ያለመሆናቸውን፣ እንዲሁም የግል የመሬት ይዞታ እንዳላቸው፣ እንደሌላቸው ጭምር ለየ::
ምክር ቤቱ በሁለቱ ግለሰቦች ዙሪያ የሚፈልጋቸው ጉዳዮች እንዲጣራለት ባዘዘው መሰረት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን የጃቢ ጠሀናን ወረዳ የአካባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር ጽህፈት ቤት መረጃ እንዲሰጥ ተጠይቋል:: ጽህፈት ቤቱም በተጠየቀው መሰረት ለምክር ቤቱ ተገቢ ነው ያለውን ምላሽ ሰጥቷል::
ከጽህፈት ቤቱ በተገኘው መረጃ መሰረት የመሬት ይዞታው የአመልካች ባለቤት እናት ሲጠቀሙበት የነበረው ከነቤተሰባቸው ሲሆን፤ ተጠሪዋ ደግሞ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ በራሳቸው ስም የተሰጣቸው መሬት ስለመኖሩ ያስረዳል:: ከዚሁ ጋር ተያይዞም በወቅቱ አሁን ክርክር ባስነሳበት መሬት ላይ በቤተሰብነት የተመዘገቡት አመልካች ወይዘሮ እናት በለጠ ከሟች ባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋር ስለመሆኑ ተረጋግጧል::
አመልካች ቀደም ሲል በየፍርድ ቤቶቹ ባቀረቡት አቤቱታ ተጠሪዋ በተሳሳተ የሰነድ ማስረጃ በተሰጠ ውሳኔ‹‹ መብቴ ተነጠቀ፣ መሬቴ ተወሰደ›› በማለት አቤት ሲሉ ቆይተዋል:: ምክር ቤቱ ይህን አስመልክቶ ማጣራት እንዲደረግ ትዕዛዝ ሰጥቷል:: በትዕዛዙ መሰረትም የዞኑ የመልካም አስተዳደር ኮማንድ ፖስት አቤቱታቸውን በማየት የቀረበው ቅሬታ ወደ ቀበሌው ህዝብ ወርዶና ተጣርቶ እውነታው እንዲረጋገጥ አድርጓል፡፤
በዚህ የማረጋገጫ ሂደትም ትክክለኛው መረጃ በመገኘቱ ለወረዳው ፍትህ ጽህፈት ቤት ቀርቦ ክስ እንዲመሰረትና የአመልካች መሬት በህግ ውሳኔ የሚመለስበት ሂደት እንዲመቻች ተወስኗል:: ለዚህ ውሳኔ ተፈጻሚነት የፍኖተ ሰላም ከተማ አካባቢ ጥበቃ መሬት አስተዳደር የስራ ሂደት ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው አመራሮች ወደ ቀበሌው ወርደው መረጃውን በማጣራት እንዲያቀርቡ በማለት ትዕዛዝ ተላልፏል::
የምዕራብ ጎጃም ዞን የመልካም አስተዳደር ኮሚቴ ሰባት አባላት ባሉት ኮሚቴዎች ተደራጅቶ ጉዳዩን ማጣራት ጀመረ:: በቀበሌው የሚገኙ በርካታ ነዋሪዎችን አወያይቶም በመሬቱ ላይ አመልካቿ ቀደም ሲል በቤተሰብ አባልነት የተቆጠሩ መሆናቸውን አረጋገጠ፡፤
ግለሰቧ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን መሬቱን እንደተመሩ ያረጋገጠው ኮሚቴ ተጠሪዋ ግን በወቅቱ ራሳቸውን ችለው የሚኖሩና በራሳቸው ስም መሬት የተመሩ ስለመሆናቸው ጭምር ከነዋሪው ጋር በነበረው ውይይት ለማወቅ ቻለ::
ይህ ኮሚቴ ከቀበሌው ነዋሪ ጋር ተወያይቶ ያገኘውን ትክክለኛ መረጃ ለሚመለከተው የህግ አካል ቀርቦ ውሳኔ የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲመቻች በዞኑ አስተዳደር ግብርና ጽህፈት ቤት ደብዳቤ ተጽፎ መረጃው እንዲጣራ በማለት ልዩነት በሌለው ድምጽ የወሰነውን ሰነድ ለመላክ ቻለ::
በተጣራው ሂደት መሰረት ለክርክሩ መነሻ የሆነውን መሬት እያረሱ ሲጠቀሙበት የቆዩት ተጠሪዋ ሳይሆኑ አመልካቿ ወይዘሮ እናት በለጠ ስለመሆናቸው ተረጋግጧል:: ከዚሁ ጋር ተያይዞም ከገጠር ቀበሌ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ሁለቱም ሴቶች አርሶ አደር ስለመሆናቸው በማስረጃ ተያይዟል::
በመጨረሻም…
በህገመንግስቱ አንቀጽ40/3-4/ በተቀመጠው መሰረት የገጠርና የከተማ መሬት የመንግስትና የህዝብ ስለመሆኑ ተደንግጓል:: የክልሉ የገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ህጎችም የገጠር መሬት የሚተላለፍባቸውን ህጎች በግልጽ አስፍሯል:: በተያዘው የክርክር ጉዳይም አመልካች ከባለቤታቸውና ከአማታቸው ጋር ለመሬቱ በባለቤትነት የተቆጠሩ መሆናቸው በማስረጃዎች ተረጋግጧል::
ከዚሁ ጋር ተያይዞም ወይዘሮዋ በመሬቱ የሚተዳደሩና አርሶ አደር መሆናቸው እየታወቀ በፍርድ ቤቶቹ የሰው ማስረጃ ብቻ የተላለፈባቸው ውሳኔ የአመልካችን ከመሬት ያለመነቀል ሕገ መንግስታዊ መብት የሚቃረን እንደሆነ ምክር ቤቱ ግንዛቤ ወስዷል::
እስካሁን የነበሩ የፍርድ ቤቶች ውሳኔም የህገመንግስቱን አንቀጽ 40/4/ ላይ የተቀመጠውን ህግ የሚቃረን በመሆኑና ውሳኔው የአመልካችን ሕገ መንግስታዊ መብት የጣሰ በመሆኑ በአንቀጽ 9/1/ መሰረት ተፈጻሚነት እንደማይኖረው ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ አረጋግጦ ለወይዘሮ እናት መሬቱ እንደሚገባው የመጨረሻ ውሳኔውን አሳልፏል
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2013