ህወሓት እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ የውሳኔ ሃሳብ ማስተላለፉ ይታወሳል።ይህን ተከትሎ ትናንት የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳቡን አጽድቆታል። እነዚህ ሁለቱ ሀይሎች በዜጎች ላይ ሽብርን የሚፈጽሙ፣ መሰረተ ልማትን የሚያወድሙና ህገ መንግስቱን የሚጥሱ መሆናቸው ይገለጻል።
ባለፈው ዓመት የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1176/2012ዓ.ም መሰረት የሽብር ድርጊት በሰው ልጆችና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ የሚገኝ ወንጀል ነው።ይህ ወንጀል ለአገራችንና ለዓለም ህዝብ ሰላምና ደህንነት ከፍተኛ ስጋት መሆኑን በመገንዘብ፤መንግስት የአገርና የህዝብን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑና ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባህሪውን ያማከለ ጠንካራ ቅድመ ጥንቃቄና ዝግጅት ማድረግ እንዲሁም አጥፊዎች ከድርጊታቸው ጋር ተመጣጣኝና አስተማሪ ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ የአዋጁ ዓላማ መሆኑ ይገለጻል።
በአዋጁ መሰረት የሽብር ድርጊት የሚባለው ማንኛውም ሰው የፖለቲካ፣የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ ህዝብን ወይም የተወሰነ የህብረተሰብን ክፍል ለማሸበር ወይም መንግስትን፣ የውጭ አገር መንግስትን ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅትን ለማስገደድ፤በሰው አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ፤ የሰውን ሕይወት ለአደጋ ያጋለጠ፤ ሰውን ያገተ ወይም የጠለፈ፤በንብረት፣በተፈጥሮ ሐብት ወይም አካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ፤ወይም የሕዝብ ወይም ማህበራዊ አገልግሎት እንዳይሰጥ በከፍተኛ ሁኔታ ያስተጓጎለ፤እንደሆነ ከአስር ዓመት እስከ አስራስምንት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል ይላል።
በአዋጁ የተፈጸመው ተግባር፣ ሰውን መግደል ወይም በታሪካዊ ወይም የባሕል ቅርስ ወይም የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ እንደሆነ ከአስራ አምስት ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል ሲል ያስቀምጣል።
በዚህ አዋጅ አንቀጽ 3 የተመለከተውን የሽብር ድርጊት ለመፈጸም የዛተ ሰው ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል።ዛቻ የሚያስቀጣው የዛተው ሰው አደርገዋለሁ ወይም አስደርገዋለሁ ያለውን ድርጊት ለመፈጸም ያለበት ሁኔታ ወይም ያለው ዕድል ወይም ያደረገው መዛት በህብረተሰቡ ወይም በህብረተሰቡ የተወሰነ ክፍል ላይ የፈጠረውን ወይም ሊፈጥር የሚችለውን ሽብር በማገናዘብ ይሆናል።
የሽብር ወንጀል ለመፈጸም ማቀድ እና መሰናዳት ረገድ ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀፅ 3 ላይ የተመለከተውን የሽብር ወንጀል ለመፈጸም የማቀድ ተግባር የፈፀመ እንደሆነ ከሶስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እሥራት ይቀጣል።ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 3 የተመለከተውን የሽብር ድርጊት ለመፈጸም የመሰናዳት ተግባር የፈፀመ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ አስራ ሁለት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል ሲሉ አዋጁ ይጠቅሳል።
የሽብር ወንጀል ለመፈጸም ማደም ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 3 የተመለከተውን የሽብር ወንጀል ለመፈጸም ወይም እንዲፈጸም ለማድረግ ያደመ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ አስራ ሁለት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል።
በሽብር ድርጊት በሐሰት ስለማስፈራራት በተመለከተም አዋጁ የሚያሰጡትን ጉዳዮች ዘርዝሯል። በተለይ ማንኛውም ሰው ሐሰተኛ መሆኑን እያወቀ የሽብር ድርጊት እንደተፈጸመ ወይም እየተፈጸመ እንደሆነ ወይም እንደሚፈጸም በማንኛውም መንገድ በመግለጽ ወይም የሀሰት ድርጊት በመፈጸም በህዝብ ወይም በህብረተሰብ ወይም በተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ድንጋጤን፣ ሽብርን፣ መረበሽን ወይም ስጋትን የፈጠረ እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም ነገሩ ጉዳት ያስከተለ እንደሆነ ከሶስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ነው ያስቀመጠው።
በሽብርተኛነት የተፈረጀ ድርጅት ድጋፍ ማድረግም የህግ ተጠያቂነት ያስከትላል።ማንኛውም ሰው የሽብር ወንጀል አፈጻጸምን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እያመቻቸ ወይም እየረዳ መሆኑን እያወቀ ወይም ሽብርተኛ ድርጅትን ለመርዳት በማሰብ፡- ሰነድ ወይም መረጃ ያዘጋጀ፣ ያቀረበ ሰጠ ወይም የክህሎት፣ የምክር ፣ የሙያ ድጋፍ የሰጠ ወይም ማንኛውንም ፈንጂ፣ ድማሚት፣ ተቀጣጣይ ንጥረ- ነገሮችን፣ የጦር መሳሪያ ወይም ሌላ ገዳይነት ያለው መሳሪያ ወይም መርዛማ ንጥረ-ነገሮች፣ ያዘጋጀ፣ ያቀረበ፣ የሰጠ፣ የሸጠ፤ ወይም ስልጠና የሰጠ ወይም አባላትን የመለመለ፤እንደሆነ ከሰባት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል።
ሌላው የተደረገው ድጋፍ የንብረት የሆነ እንደሆነ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 780/2005ዓ.ም መሰረት ይቀጣል።
የፈጸመ ሰው ዋናው የሽብር ወንጀል ባይፈጸምም ወይም ድጋፍ ማድረጉ ተለይቶ ለታወቀ አንድ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም ከሚደረግ ዝግጅት ጋር ወይም የሽብር ወንጀሉን ከሚፈጽመው ሰው ጋር ግንኙነት ባይኖረውም ለሽብር ወንጀል ድጋፍ ማድረግ ሆኖ ይቀጣል። ድርጊቱ የተፈጸመው በቸልተኝነት እንደሆነ ቅጣቱ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ይሆናል።
ለሽብር ተግባር ማነሳሳትም ህጋዊ ተጠያቂነት ያመጣል።ማንኛውም ሰው ሆን ብሎ ሌላውን ሰው በመጎትጎት፣ ተስፋ በመስጠት፣ በገንዘብ፣ በስጦታ፣ በማስፈራራት ወይም በማናቸውም ሌላ መሰል ዘዴ ወንጀል እንዲፈጽም ያነሳሳ ሆኖ ወንጀሉ የተፈጸመ ወይም የተሞከረ እንደሆነ ለወንጀል በተቀመጠው ቅጣት ይቀጣል።እንዲሁም ማንኛውም ሰው ወንጀል እንዲፈጸም ለማድረግ በንግግር፣ በጽሑፍ፣ በስዕል ወይም በሌላ ማንኛውም አድራጎት በግልጽ ሁኔታ ቅስቀሳ ያደረገ፣ ወይም እንደዚህ ዓይነት ይዘት ያለው ነገር መሆኑን እያወቀ ያተመ፣ ያሳተመ፣ ያስተላለፈ፣ ያሰራጨ፣ ያከማቸ፣ የሸጠ፣ ወይም በሌላ ማንኛውም መንገድ ለህዝብ ተደራሽ ያደረገ እና ወንጀሉ የተፈጸመ ወይም የተሞከረ እንደሆነ ከሶስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።
በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ተፈጽሞ፣ እንዲፈጸም የተፈለገው የሽብር ወንጀል ያልተሞከረ ወይም ያልተፈጸመ እንደሆነ በንኡስ አንቀጾቹ የተመለከቱትን ድርጊቶች የፈጸመ ሰው ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።ስለዚህ የሽብር ድርጊት የሚያስከትለውን ህጋዊ ተጠያቂነት በመገንዘብ ከህወሓትና ሸኔ ንክኪ ነጻ መሆን ያስፈልጋል።እነዚህ ሁለቱን ሽብርተኛ ድርጅቶችም በህዝብና በአገር ላይ የሚያደርሱትን ጥፋት በጋራ ሆኖ መታገል ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 29/2013