አዲስ አበባ፦ በተለምዶ እሪ በከንቱ ተብሎ በሚጠራው የሸራተን ማስፋፊያ አካባቢ በህገወጥ መንገድ ላስቲክ ወጥረው ይኖሩ የነበሩና የደሀ ደሀ ተብለው የተለዩ 117 ዜጎች መጠለያ ማግኘታቸውን የአራዳ ክፍለ ከተማ አስታወቀ።
የክፍለ ከተማው ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ አበባ እሸቴ ትናንት በቢሯቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በክፍለ ከተማው ወረዳ 08 አካባቢ ላስቲክና ሸራ ወጥረው ይኖሩ የነበሩ መሆናቸውን አመልክተዋል። እንደሳቸው ማብራሪያ ባለፉት ዓመታት በአራዳ ክፍለ ከተማ ለማስፋፊያና ለልማት ተብሎ የፈረሱት ቤቶች በጣም በርካታ ናቸው።
ይህን ተከትሎም ከቦታው ለተነሱት በኪራይ ቤቶች አስተዳደር ይኖሩ ለነበሩ፣ ህጋዊ የመንግስት ተከራይ ለነበሩና የግል ቤት ለነበራቸው ዜጎች ህግና መመሪያው በሚፈቅደው መሰረት ተስተናግደው ሄደዋል። ይሁን እንጂ፤ በዚሁ አካባቢ የተለያዩ ዜጎች ተነሺዎቹን ተከትለው ልጆች ነን፤ ወላጆቻችን ይዘውን ሊሄዱ አልቻሉም፤ የትም መውደቂያ የለንምና መንግስት መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል በማለት ለረጅም ጊዜ ላስቲክ ወጥረው ቆይተዋል።
እነዚህንም ዜጎች ክፍለ ከተማው ሰብስቦ በማወያየት መግባባት ላይ ተደርሶ መኖሪያ ቤት እንዲያገኙ አድርጓል። ክፍለ ከተማው ለዚሁ ዓላማና በደሃ ደሃ ተመዝግበው ቤት ለማግኘት ለሚጠባበቁ ዜጎች የሚውሉ ቤቶችን መሬት ከከተማው አስተዳደር በመውሰድ በቦሌ ቡልቡላ ያስገነባቸውን ቤቶች በመጠቀም እጅግ በጣም የተቸገሩ ሕፃናትን ለያዙ እናቶች አስተላልፏል። ቤቶቹ የተላለፉት በቀጣይ በሚወሰን ኪራይ ሲሆን፤ ለግንባታውም ከ55 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉ ተገልጿል።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2011
ፍሬህይወት አወቀ