ኢትዮጵያ ሀገራችን በዘመኗ በርካታ አስቸጋሪ ጋሬጣዎች ገጥመዋታል። እንደ ቅርጫ ስጋ ሊቀራመቷት የተነሱ የውጪ ወራሪ ሀይሎች ከቀኝ ከግራ ተነስተውባታል። በቀኝ ተገዥነት ሊያንበረክኳት በተደጋጋሚ ጊዜ ወረዋታል። ከውስጥም ከውጪ የጠላት ሀይል ተፈታትኗታል። ሆኖም በታሪኳ ለአንዱም አልተንበረከከችም። ታሪክ የሚመሰክረውም በተግባር ያረጋገጥነውም የወረሯትን ሀይሎች፤ የተነሱባትን ጠላቶች ሁሉ ድል አድርጋ ዛሬም ድረስ የድል ብስሯቷን እያስታወሰችና እያከበረች እንዳለች ነው።
ይሁን እንጂ ዛሬም በእኛ ዘመን ሀገሪቷን ለማፍረስ፣ ህዝቧንም ለመበትን እና ዳር ድንበሯን ለመድፈር ብዙዎች ቋምጠዋል። ከውስጥና ከውጭ ሆነው ታግለዋል፤ አሁንም ከባድ የትግል ወቅት ላይ እንገኛለን። ይሄ የሀገርን ሉአላዊነት የማስከበር ትግል ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል፤ የሰዎችን ህይወት ሊያስገብር ይችላል። የኢኮኖሚ ድቀትን ሊያመጣ ይችል ይሆናል። ነገር ግን ሀገራችን ለማንም በምንም ምክንያት ልትንበረከክ አትችልም። የጀግንነት ታሪኳን ሊያጎድፍ የሚችል ሀይልም አይኖርም። ይልቁንም ዛሬም እንደትላንቱ በጀግኖች ልጆቿ ታሪክን ትደግማለች። ጠላቶቿን ታንበረክካለች። ለማንም ቀኝ እንዳልተገዛች ሁሉ አሁንም ለማንም በምንም መልኩ ሸብረክ አትልም፤ አትገዛም።
ቀደም ባሉት ዘመናት በሀገር ውስጥ በመሳፍንቱና በመኳንንቱ በኩል ቅራኔዎች ነበሩ። ጣሊያንም ይሄንን ቅራኔ መጠቀሚያ አድርጎ ኢትዮጵያውያኑን በዘር ከፋፍሎ አንዳንዱንም ባንዳና ቅጥረኛ አድርጎ ሀገሪቱን በቀኝ ለመያዝ እንደ መልካም አጋጣሚ አድርጎ ሊጠቀምበት አስቦ ነበር። ሆኖም ግን የኢትዮጵያውያን የሀገር ስሜት እንዳሰበው ሳይሆን ለሀገሩ ክብር ግንባር ደረቱን ለጥይት የሚሰጥ ሆኖ አገኘው።
በየዘመኑ ከሀገር መሪዎች፣ አስተዳዳሪዎች ጋር የሀሳብ እና የአስተሳሰብ ልዩነቶች፣ የጥቅም ግጭቶች ነበሩ። አሁንም ይሄን መሰል ልዩነቶች ይኖሩ ይሆናል። ይሁንና ልዩነቱ፣ አለመስማማቱና በአንድ ሆኖ አለመታየቱ በሀገር ሉአላዊነት ላይ ሲሆን መልኩ ይቀየራል። ለውጪ ወራሪ ሲሆን መልኩ፣ ቅርጹና አይነቱ ይለወጣል። ልዩነቱ ሁሉ ውበት ሆኖ በአንድነትና በእናት ሀገር ስሜት በቆራጥነት ቀፎው እንደተነካበት ንብ አንድ ሆኖ በጋራ ይቆማል። የውስጥ ልዩነቶቻችን ወደ ጎን ይቆየንና ለአንድ ሀገራችን በጋራ እንቆማለን የሚለው ወደፊት ይመጣል። ይሄ ዛሬ የተጀመረ ብቻ ሳይሆን እስካሁንም ልዩነታችንን ለማጥቂያ ሊጠቀሙበት ለከጀሉት ሁሉ የተሰጠ ምላሽ ነው። ጠላትን በተደጋጋሚ ጊዜ አሳፍረን የሸኘነው በዚህ መንገድ ነው።
ኢትዮጵያውያን ለወዳጆቻችን ፍጹም ታማኝ ፣ ለፍትህና እኩልነት የተባበርን የነፃነት አርበኞችን ያሰለጠንን ህዝቦች ነን። የተገፉና የተሰደዱ ፤ አምነውን የተጠጉንን ህዝቦች አክብረንና አቅፈን የያዝን፤ ዛሬም ሀገር እያላቸው በሀገራቸው ሰላም አጥተው የተሰደዱ ስደተኞችን ተቀብለን የምናስተናግድ ህዝቦች መሆናችን ለአንድ ጊዜም ሊዘነጋ አይገባም። ይሄም ሆኖ በየዘመኑ ጠላት ዓይኑን በሀገራችን ልማትና ዕድገት ላይ ማነጣጠሩ አልቀረም። እርስ በእርስ ሊያባሉን የሚሞክሩ ብዙ ናቸው። ሆኖም የሞከሩን ወድቀዋል፤ ሊጥሉን ሲገፉን ይበልጥ አንድ ሆነን ጠንክረን ቆመናል። ይሄ ጀግንነታችን ጥንካሬያችን መቼም አይፈረከስም። አሁንም ዳር ሆነው ሊቀራመቱን ላሰቡት ውስጥ ሆነው ለተባበሩት መልሳችን አንድ ነው። አንድ ሆነን ልዩነታችንን ለነገ አሳድረን ለእናት ሀገራችን እንቆማለን። እናት ሀገራችንን ከገባችበት ማጥ አውጥተን ወዳሰብነው የብልጽግና ማማ በዳግም ድል እናሻግራለን።
የማያውቁንም ሆነ አውቀውም የዘነጉን ወዳጅ ጠላቶቻችን ሊያስታውሱና ሊያውቁ የሚገባቸው ጉዳይ ቢኖር ኢትዮጵያ በታሪኳ ሁሉ የማትንበረከክ ሀገር መሆኗን ነው። ኢትዮጵያውያን ቀኝ ግዛትን ዛሬም ትላንትም የታገልን፤ ታግለን ያሸነፍን መቼም ለባርነት እጅ የማንሰጥ ህዝቦች ነን። ለነፃነትና እኩልነታችን ለሀገራችን ዳር ድንበር የሀያላኑ ጫና ቢበረታ፣ አስፈራውና አማላዩ ቢበዛ ዛሬም ነገም አንበረከክም። እስካሁን በየዘመናቱ ሁሉ ጫና ሊፈጥሩ የሻቱትን ሁሉ በአንድነት አሽቀንጥረን ጥለናል። በየትኛውም አቅጣጫ የመጣብንን ሀይል የምንመልሰው በተመሳሳይ መንገድ ነው። የዛሬው የአርበኞችን የድል በዓል ስናከበር በዚሁ የጀግንነት ስሜት መሆን አለበት።
በፍቅር በወዳጅነት ለቀረቡን ደግሞ እንግዳ አስተናጋጆች፣ የተቸገረ ረጂዎች የተሰደደ ተቀባይ ህዝቦች መሆናችንን የታሪክ መዛግብት እማኝ ምስክሮች ናቸው። በሀገራችን ላይ በጠላትነት ለመጣብን ደግሞ አራስ ነብር ነን። ኢትዮጵያዊነት ማለት ይሄ ነው። ጠላቶቻችን ከውስጥም ከውጪም እንደሚያስቡትና እንደሚገምቱት የውስጥ ሰላም ሲደፈርስ ሀገራችንን ለጠላት አሳልፈን የምንሰጥ ህዝቦች አይደለንም። ልዩነታችንን በይደር አቆይተን የእናት ሀገራችንን ዳር ድንበር እናስከብራለን። በአጠቃላይ በየጀግኖች እናት ኢትዮጵያን በታሪኳ ሁሉ ማንበርከክ አልተቻለም፤ አሁንም አይቻልም !
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2013