ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ “ህወሓት” እና “ሸኔ” የተባሉ ፅንፈኛ ቡድኖች በኦሮሚያ ወለጋ አካባቢ፣ በቤኒሻንጉል መተከል ዞን እንዲሁም በአማራ ክልል አጣዬና ሸዋሮቢት ዙሪያ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለያየ ጊዜ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ በማካሄድ ንፁሃን ዜጎችን ሲያፈናቅሉ፣ ሲገድሉ፣ የህዝብን ንብረት በማውደም ለያዥም ለገራዥም አስቸጋሪ ሲሆኑ ተደጋግሞ ተስተውሏል።
ከሶስት ዓመታት በፊት ሃገሪቷን ሲመራ የነበረው የፖለቲካ ድርጅት “ህወሓት” የእሱ ተቃዋሚ የነበሩትን በሙሉ በጭፍን ጥላቻ ሽብርተኛ ብሎ ሲፈርጅ እንዳልነበረ ሁሉ በአሁኑ ወቅት የሰውን ደም እየጠጣ፣ ቤት ንብረት እያወደመ፣ ሃገርን ለማፍረስ ታች ላይ እየዳከረ ሲገኝ ሽብርተኛ ተብሎ አለመፈረጁ የዜጎችን ቅሬታ ፈጥሮ ቆይቷል።
ሸኔም ቢሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በወለጋና በመተከል አካባቢዎች ህፃናትን ጭምር አጋድሞ እስከማረድ የደረሰ የጭካኔ ሃይል መሆኑ ተደጋሞ ተስተውሏል። እነዚህ ሽብርተኞች በሚፈጥሩት ጭካኔ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ። አሁንም በየቦታው ሃገሪቱ ዜጎቿ ደማቸው ደመከልብ መሆኑ አልቆመም፣ ከተሞቿ እየነደዱ ወድመዋል፣ ማህበረሰቡ ተረጋግቶ ህይወቱን መምራት እየተሳነው ይገኛል። ለዚህም ዋናው ተጠያቂው በሽብር የተፈረጁት አካላት ቢሆኑም በሥርዓቱ ውስጥ ሆነው ለሽብርተኞቹ ቡድኖች መረጃ የሚያቀብሉ፣ የገንዘብ ምንጭ ፈሰስ የሚያደርጉ ከማህበረሰቡ ጉያ ውስጥ ያሉ ተላላኪዎች መኖራቸው የተደረሰበት ጉዳይ ሆኗል።
በዚህ ሴራቸው የመንግስትን ስልጣን በድርድር ለመካፈል በውጭ ሃይላት አማካኝነት ተፅዕኖ ለመፍጠር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ፍላጎታቸውን እያሳዩ እንደሆነም እየተስተዋለ ነው።
መንግስት ከእነዚህ ሽብርተኛ ሃይሎች ጋር ምንም አይነት ድርድር፣ ምንም አይነት የስልጣን ማጋራት እንደማያደርግ ሰሞኑን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሕወሓትን እና ሸኔን ሽብርተኛ ተብለው እንዲፈረጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱም ታውቋል። የእነዚህ ሃይሎች በሽብረተኝነት መፈረጅ ሕወሓትን ከመቃብር ለመጎተት፣ የተፈረካከሰውን ሸኔንም ለማቃናት የሚሞክሩ የውስጥና የውጭ ሃይላት እርማቸውን የሚያወጡበት እንደሆነ ግልፅ ነው።
እነዚህ ድርጅቶች መንግስትና ሕዝብን በማሸበር ዓላማቸውን ለማሳካት እንደሁኔታው ገባ ወጣ በማለት ሁኔታው ሲመች ሰላማዊ፣ ሳያመች ደግሞ የአመጽ ትግል ማካሄድ፣ ሁኔታው በጣም ሲከፋ ደግሞ ለአጭር ጊዜ ሽብርተኛ የሚሆኑ ሃይሎች ሆነው ተፈጥረዋል።
በዚህም ነው በሃገሪቱ የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ በተለያዩ ክልሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ሲፈጽሙ የቆዩት፤ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፉት፤ አካል ያጎደሉት፤ የህዝብንና የመንግስትን ንብረቶች ያወደሙት፤ እንዲሁም ለዘመናት በሰላምና በመቻቻል አብሮ የኖረውን ማህበረሰብ እርስ በርስ በማጋጨት በህዝብ ላይ እልቂት ሲፈጥሩ የነበሩት። በመሆኑም አሁን ሽብርተኛ ተብለው መፈረጃቸው የዘገየ እንጂ ተገቢ እንደሆነ ብዙዎችን አስማምቷል።
ሌላው መነሳት ያለበት ጉዳይ ሕወሓትና ሸኔ በአሁኑ ወቅት ነፍስ የሌላቸው የታጠቁ ሃይሎች ቢሆኑም ኢትዮጵያን የማፍረስ ፍላጎት ባላቸው የውጭ ኃይሎች ተረጅ መሆናቸው ነው። ይህም ሲባል እነዚህ አሸባሪ ሃይሎች በህዝብና በሃገር ላይ ጥቃት የሚያደርሱት የውጭ ሃይሎች እገዛ በመጠቀም መሆኑ ነው። የታቀደበት ለመሆኑ ማሳያው ደግሞ ሁለቱም ሽብርተኛ ሃይሎች አካል ቁመናቸው ተገርስሶ እንኳን አሁንም ከየቦታው የገንዘብ፣ የሃሳብ ድጋፍና የሚዲያ ሽፋን የሚያገኙበት ዘዴ እንዳላቸው መታየቱ ነው። ከግብጽ አካባቢም ለእነዚህ አካላት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑም ጥፋቱ የሚመራው ከየት እንደሆነ አመላክቷል።
መንግስት እነዚህን ድርጅቶች በሽብርተኝነት መፈረጁ ቀደም ሲል የዓለም አቀፉን የሽብርተኝነት ህግ ወደጎን በመተው በህጋዊ መንገድ ፋይናስ ሲያደርጓቸው የኖሩ አካላትን ድጋፍ ከማስቀረቱም በላይ የሚፈልጉትን የስልጣን ጥማት ለማሳካት ከመዳከር እንደሚገታቸውም ይታመንበታል። ድርጅቶቹ በሽብርተኝነት መፈረጃቸው ይበል የሚያሰኝ ሃገርን በሃላፊነት ከሚያስተዳድር መንግስት የሚጠበቅ ውሳኔ ነው።
ከሁሉም በበለጠ ሽብርተኞቹ የሀገረ መንግሥቱን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል አበክረው የሚሰሩ መሆናቸው ታሳቢ ተደርጎ ሃገሪቱ እንደሃገር እንድትቀጥል ይህ ውሳኔ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባል። ምክንያቱም ሽብርተኛን የሚደግፉ በርካታ የውጭ ሃይሎች መኖራቸው እሙን ነው። ይህንንም ከተለያዩ ሃገራት ተሞክሮ መውሰድ ይቻላል። በሊቢያ፣ በየመን እስካሁን ያልበረደው መመሰቃቀል ሽብርተኞችን የሚደግፉ ሃይሎች እገዛ ካለመቆሙ ጋር እንደሚያያዝ ብዙዎች የሚናገሩት ሀቅ ነው።
እነዚህ ሃገራት ግጭት ውስጥ ከገቡ በርካታ ዓመታትን አሳልፈዋል። ምክንያቱም ሽብርተኞቹ በገንዘብም ሆነ በመሳሪያ አቅማቸው ፈርጥሟል፣ መንግስት ሊይዘው ከሚችለው በላይ ታጥቀዋል፤ ደጋፊዎቻቸውም ፍላጎታቸው ይሄው ነው። ይህ አሰቃቂ ሁኔታ ወደ ሃገራችን ብቅ ቢልም ቶሎ እሳቱን ማጥፋት የሚቻለው በነዚህ ሽብርተኞች ላይ ያልዘገየ እርምጃ መውሰድ ተገንዝቦ መንግሰት የወሰደው እርምጃ በሁሉ መልኩ የሚደገፍ ነው! በአጠቃላይ ሕወሓትን እና ሸኔን ሽብርተኛ ተብለው ሲፈረጁ አካላዊና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ይደርቃል፤ የህዝብም በሰላም የመኖር መብት ይረጋገጣል፤ ብሎም የሃገር ህልውና ይቀጥላል!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26/2013