የክርስትና እምነት ተከታዮች ትናንት የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በዓልን አክብረው ውለዋል። ትንሳኤ የመስዋዕትነትና የደስታ በዓል ነው። በዓሉ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ሳምንቱን ሙሉ ይከበራል። በዚህ ወቅት ዘመድ ከዘመድ ጎረቤት ከጎረቤት እየተጠራራ ገበታ ይጋራል፤ አቅም ለሌላቸውም ይመፀውታል።
ምዕመናን አብይ ጾማቸውንና ይህን እየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበትን የትንሳኤ በአል ያከበሩት በፈታኝ የኑሮ ውድነት፣ በየቦታው እየተፈጠሩ የዜጎችን ህይወት በቀጠፉ ክፉ ድርጊቶች አዝነውና በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ባለው የኮቪድ ወረርሽኝ ውስጥ ሆነው ነው። ለፈተናዎች ሳይበገሩ ይበልጥ ጠንካራ ሆነው እምነታቸው የሚፈቅደውን ሁሉ አድርገው በዓሉን አክብረዋል።
ፈተናዎቹ የሁሉም ኢትዮጵያዊና የሀገሪቱም ትልቅ ፈተናዎች ናቸው፤ ኢትዮጵያውያን በእምነታቸው ላይ ያሳዩትን ጥንካሬ አገራዊ ፈተናዎችን ለመሻገር ማዋላቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል።
በእርግጥ ለኢትዮጵያውንና ኢትዮጵያ ፈተና ከመሆን አያልፍም፤ ይዘጋጁበታል፤ ያልፉታል። በሀገር ውስጥ የሚፈጠረውንም ሆነ በውጭ ሀይሎች የሚዘጋጁትን ፈተናዎች የማለፍ ጥንካሬውም ብቃቱም እንዳላቸው ከአባቶቻቸው ታሪክ ይረዳሉ። የአድዋ ድል ያለፈተና አልተገኘም። ፋሽስት ጣሊያንም በጀግኖች አርበኞች የአምስት አመት የዱር መራር ትግል እንጂ በከንቱ አልተገኘም።
ኢትዮጵያ በዘመኗ ከውስጥም ከውጪም ጠላት አጥታ አታውቅም። አሁንም የውጭም የአገር ውስጥም ጠላቶች አሉባት። እነዚህ ጠላቶቿ ብቻቸውን አይደለም እየወጓት ያለው። ሀገራቸውን የካዱ፣ የእናት ጡት ነካሽ፣ ለዳረጎት ያደሩ ኢትዮጵያውያንንም በመጠቀም ጭምር ነው። ዛሬም በዚህ ቦይ የሚፈሱ ኢትዮጵያውያን አሉ።
ኢትዮጵያ ጠንካራ ከሆነች የአባይ ውሃን አጣለሁ ብላ በከንቱ የምትሰጋው ግብጽ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲስተጓጎል እስካሁን ያደረገችው ከንቱ ልፋት አልሳካ ሲላት በውክልና ጦርነት ኢትዮጵያውያንን እርስ በእርስ ለማጋጨት ያለዕረፍት ሰርታለች፤ አሁንም ይህንኑ አጠናክራ ቀጥላለች።
በተባበረ የኢትዮጵያውያን ጥረት የህዳሴ ግድብ ወደ ወሳኝ ምእራፍ መሸጋገር ግብጾችን ክፉኛ አስደንግጧቸዋል። ግድቡን በራሳችን አንጡራ ሀብት መገንባት ስንጀምር ይጨርሱታል ብለው አላሰቡም ነበር። ግን ቃላችንን ጠብቀን ልንጨርሰው ከጫፍ ደርሰናል።
በዚህም በስግብግብነት መንፈስ መክለፍለፍ ውስጥ ገብተዋል። በየአለም አቀፍ ተቋማቱና በየሃያላን ሀገሮቹ ደጅ አንጥፈው መለማመኑን አልሳካ ያላት ግብጽ ለእዚህ እኩይ ተልእኮ ሱዳንንም ከጎን አሰልፋለች።
የዚህ ሁሉ ክፋት መነሻ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እንዳይከናወን ለማድረግ ነበር። ግብጽ የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ብቻ አይደለም የምትሰራው። ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግስት እንዳይኖራት ለማድረግም ጭምር ነው። ሰሞኑን ደግሞ ከሀገሯ የወጡ ዘገባዎችም ይህንኑ አረጋግጠዋል። ኢትዮጵያ ይህን ፊቱንም አሳምራ ታውቀዋለች።
ለዚህ ደግሞ ጠንካራ መንግስት ለመመስረት ያስችላል ተብሎ በኢትዮጵያ መንግስትና በኢትዮጵያውያን ዘንድ ታምኖበት እየተሰራበት ያለውን ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ማምከን አንዱ ዓላማዋ አድርጋለች። ይህን ለማድረግ ግብጾች ፊት ለፊት አይመጡም፤ አለመደባቸውም። ጡት የጣሉበትን፣ ጥርስ የነቀሉበትን የውክልና ጦርነት አጠናክረው ቀጥለዋል እንጂ።
በሀገራችን እዚህም እዚያም እየተቀሰቀሰ የዜጎችን ህይወት በእጅጉ እየቀማ ያለው ጥቃትና ግጭት የውስጥ ጉዳይ ነው ብለን ብቻ የምንተወው አይደለም። የግብጽም እጅ ያለበት ነው። ይህን ደግሞ የግብጽ አክቲቪስት ነን ባዮች በአደባባይ ሲናገሩት አድምጠናል። ቀውሶቹን በፋይናንስና ሌላ ነገር እየደገፉ እንዳሉ ይህንን ስልት ከመሃመድ ሙርሲ የስልጣን ዘመን ጀምሮ በመገናኛ ብዙሃኖቿ እየሰማን ነው።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የውጪ ወራሪ አልመጣባትም ተብሎ አይታሰብም። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተነሳ መጥቶባታል፤ የግብጽ ዘመቻ ይህንን ያመለክታል። በዚህ አይነቱ የቁርጥ ቀን የሀገር ውስጥ ሀይሎች የቱንም ያህል ልዩነት ቢኖራቸው አብረው መቆም ግዴታቸው ነው፤ የውስጥ ጠላቶቻችን በዚህ ወቅት ስለሀገራቸው ሲሉ ከመንግስት ጎን መቆም በተገባቸው ነበር። የሆነው ግን የዚህ የተገላቢጦሽ ነው። ከመቼውም ጊዜ በላይ አገርን ለማዳከም እየሰሩ ናቸው።
ዋጋ እያስከፈለን ያለው የውስጡ ጠላት እስትንፋሱ ያለው በውጭ ወራሪው መዳፍ ውስጥ መሆኑ ነው። ስለሆነም ይህን የተቀናጀ የጥፋት ኃይል ማሳፈር ያለብን እንዳለፉት ዘመናት ሁሉ በኅብረት በመቆም ነው።
ለዚህ ደግሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛውን ምእራፍ የውሃ ሙሌት ለማሳካት እየተከናወነ ላለው ተግባር ድጋፋችንን በየትኛውም መልኩ ማጠናከር ይኖርብናል።
በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያን ባለ ጠንካራ መንግስት ሊያደርግ የሚችለውን ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በስኬት ማጠናቀቅ ይገባል። ይህን የቤት ስራ በሚጠበቀው መልኩ መከወን ማለት ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግስት እንዳይኖራት እሰራለሁ ለምትለው ግብጽ ታላቅ መርዶ ነው። በመሆኑም የሁሉም ነገር መፍትሄ ለሆኑት ለምርጫውና ለህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ስኬት በጋራ መስራት የውዴታ ሳይሆን የግዴታ ጉዳይ ነው!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 25/2013