የፋሲካ በዓል ከብዙ መከራ እና ውጣ ውረድ በኋላ የሚገኝ የደስታ ጊዜ በመሆኑ ልዩ ክብርና ሞገስ ይሰጠዋል። ከዚህ እለት በፊት የነበሩት የህማማቱ ቀናት በብዙ ፈተናና መከራ የዘለቁ በመሆናቸው ፋሲካ እነዚያን የኃዘን ቀናት ሁሉ ደምስሶ ደስታን የሚያጎናፅፍ ልዩ ቀን በመሆኑ በደስታ ይከበራል፡፡ ልክ እናት ከምጥ በኋላ ልጇን አቅፋ የደስታ ጸዳል እንደምትጎናፀፈው ሁሉ ክርስቲያኖችም በዚህ እለት በዓሉን በደስታ ያሳልፋሉ፡፡
አገራችንም አሁን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታም ከዚህ የፋሲካ ሰሞን ጋር ይመሳሰላል፡፡ ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል እንደሚባለው በአሁኑ ወቅት አገራችን ልክ እንደ ህማማቱ ቀናት እዚህም እዚያም በሚያስጨንቁ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች ነው ፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንድ በኩል ወደ ዴሞክራሲዊ ሥርዓት ለመሸጋገር የጀመረችውን የምርጫ ጉዞ ለማደናቀፍ የሚደረጉ ሩጫዎች፣ በሌላ በኩል ደግሞ ላለፉት አስር ዓመታት ሲገነባ የቆየውና ፍሬ ሊያፈራ ከጫፍ የደረሰውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ለማኮላሸት የሚሸረቡ ሴራዎች ለኢትዮጵያ የፈተና ጊዜ ሆነውባታል። ከዚህ በተጨማሪም ከዓለም ጋር በጋራ የምንጋራው ኮቪድ 19 ሌላው የዘመኑ ፈተና ነው፡፡
የቀደመውን ሥልጣኔ ማስቀጠል አቅቶን አገራችን ቁልቁል ስትምዘገዘግ ለምን ብለን ራሳችንን አለመጠየቃችን የውድቀታችን መነሻ ነው ፡፡ እነአክሱምን፣ እነላሊበላን፣ የገነቡ እጆች ከውጭ ድጋፍ እስከመጠበቅ የደረሱበትን ሂደት ተመልክተን ለምን አለማለታችን የቁልቁለት ጉዞአችንን አፋጥኖታል ፡፡ አድዋ ላይ በአንድ ጉድጓድ የተዋደቁ ዜጎች ዛሬ ምክንያት እየፈጠሩ ልዩነቶቻቸውን ሲያራግቡና ከዚህም አልፎ ጦር ሲማዘዙም ለምን አለማለታችን ሌላው የውድቀታችን ትልቅ ማሳያ ነው ፡፡ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የገዳ ሥርዓትን ያህል የዴሞክራሲ አባት ይዘን በዴሞክራሲ እጦት ስማችን በአደባባይ ሲብጠለጠልም ቆመን ማየታችን ሌላው የቁልቁለት ጉዞ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህንን የመጣንበትን መንገድ ለማስተካከል የተጀማመሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው ፡፡ እነዚህ ሁሉ የድህነታችንና የውድቀታችን መንገዶች ናቸው፡፡ ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ የተጀመሩት የለውጥ መንገዶች አካሄዳችንን የሚያስተካክሉ ናቸው ፡፡
ለምሳሌ ባለፉት ሶስት አመታት ወደ እድገት እና ብልፅግና የሚወስዱንን የልማት ስራዎች በራሳችን አቅም መስራትና ከጫፍ ማድረስ እንደምንችል በታላቁ ህዳሴ ግድብ አሳይተናል ፡፡ የሙስና እጆችን በማሳጠር ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት መሥራት እንደምንችልም በተግባር አስመስክረናል፡፡ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ቀዳሚ ብቻ ሳንሆን ሰላማዊ ምርጫ በማካሄድ የጠፋውን ዴሞክራሲ ለዓለም ለማሳየት ከጫፍ ደርሰናል ፡፡ እነዚህ ሁሉ ወደቀደመው ገናና ታሪካችን የሚመልሱን ሰላማዊ መንገዶች ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህ መንገዶች በጠላቶቻን ዘንድ የሚፈለጉ አካሄዶች አይደሉም ፡፡ የሃገራችንን ሰላምና እድገት የማይፈልጉ ኃይሎች ይህንን መንገድ ለማሳት የማይፈነቅሉት ድንጋይ፤ የማይምሱት ጉድጓድ የለም ፡፡ በተለይ በውስጥ ሆነው የጠላትን ሚና የሚጫወቱና ለሆዳቸው ብቻ ያደሩ አንዳንድ ኃይሎች ከአገራቸው እድገትና ብልጽግና ይልቅ የግል ጥቅማቸውን ብቻ በማሳደድ ከጠላት ጎን ለመሰለፍና አገራቸውን ለማዳከም ሲሞክሩ አንዳችም ሃፍረት እየተሰማቸው አይደለም፡፡
በዚህ የተነሳ በተለይ በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ትልቁን ፈተና እየተጋፈጠች ትገኛለች ፡፡ ገና 2013 ዓ.ም በገባ በሁለተኛው ወር የጀመረው የህወሓት ጁንታ የጥፋት መንገድ እነሆ ጦሱ ዛሬም ድረስ ሳይለቅ የፈተናውን ጊዜ እያራዘመው ይገኛል፡፡ ለ27 ኢትዮጵያ እየገዛ ዜጎቿ ነገም አብሮ እንዳይኖሩ ሴራ ሲሸርብ የኖረው የህወሓት ጁንታና ተላላኪው የኦነግ ሸኔ ሙሉ ለሙሉ ባለመወገዳቸው ሰላምን ሙሉ ለሙሉ ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
ከዚህም ባሻገር የነዚህ ኃይሎች ተላላኪዎችና ጋሻ ጃግሬዎች እዚህም እዚያም በሚፈጥሩት የጥፋት ሴራ እና አንድ እግራቸውን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ አድርገው ሌላኛውን እግራቸውን ደግሞ ከጥፋት ኃይሎች ጋር በማድረግ ሰላም የሚነሱ ኃይሎችም የተጀመረው የብልፅግና መንገድ እንዳይሳካ አቅማቸውን ሁሉ አሟጠው እየሰሩ ይገኛሉ ፡፡ በዚህም በተለያዩ መንገዶች መንግሥትን ፋታ የማሳጣትና ህብረተሰቡንም ተስፋ የማስቆረጥ ሥራዎች በስፋት ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
በተለይ ህብረተሰቡ የሰላም ስጋት እንዲኖርበት በማድረግ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ በሚሰራው ሥራ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በየጊዜው የሚሞቱ፣ የሚፈናቀሉ እና ንብረታቸው የሚወድም ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም። በዚህ የተነሳ ዜጎች በሰላም የመኖር ዋስትናቸው እንዲነጠቅ ተደርጓል፡፡ ይህ ደግሞ የፈተናው ጊዜ እንዲረዝም አድርጎታል።
ከዚህም በላይ እንደ አገርም የመደፈር አደጋው እየታየ ነው፡፡ ሱዳን ለብዙ ጊዜ ያልሞከረችውን የኢትዮጵያ ድንበር አልፋ የገባችውና መሬት የወረረችው ይህንን ውስጣዊ ክፍተት እንደ መልካም እድል በመጠቀም ነው፡፡
በአጠቃላይ እነዚህና መሰል ነባራዊ ሁኔታዎች እንዲህ ቢበዙም የኢትዮጵያ ትንሳኤ ግን ከፊት ለፊታችን ቁልጭ ብሎ ይታያል ፡፡ ይህንን ትንሳኤ እንድናይ ከእያንዳንዳችን የሚያስፈልገው በአንድ በኩል ነገ የሚመጣውን የኢትዮጵያ ተስፋ እያሰቡ የሚጋጥሙ ፈተናዎችን በቁርጠኝነት ማለፍ ሲሆን ለዚህም ሁሉም ዜጋ ለሰላም ዘብ በመቆም የጥፋት ቡድኖችን አምርሮ በመታገል ነው፡፡
አሁን ያለንበት የችግር፣ የብዥታና የጥርጣሬ ጊዜ ነው ። ጽናትና ጥንካሬያችን፣ መልካምነትና ተባባሪነታችን፣ አንድነትና ወንድማማችነታችን የሚፈተንበት ወቅት ነው። ስለዚህ ለሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ስህተት አንስራ፤ በፌስቡክና የአሉባልታ ወሬም ከእውነታው በልጦ አይውሰደን፤ ሌሎች ላይ ጣት ከመጠቆምና በፀያፍ ቃላት ከመጎሻሸም ተቆጥበን ከመከራው ቀንበር ለመሸከም ትከሻችንን እናደንድን፣ ከእንግልቱ ለማትረፍ ከመሞከርም የሕዝቡን መከራ ለመካፈል እንጣር፤ ይህ ሲሆን የነገውን ብሩህ ተስፋ እናያለን ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2013