ዝብርቅርቅ የህይወት ገጽታ የሚታይባት የአዲስ አበባ ከተማ የማታሳየን የኑሮ አይነት የለም። ከፍ ስንል የቅንጦት ኑሮን የሚኖሩ ቱጃሮችን እናያለን፤ ዝቅ ስንል የጎዳና ላይ ህይወትን የሚመሩ ጎስቋሎችን እናገኛለን። ከሚሊየነርነት ወደ ቢሊየነርነት ሽግግር ለማድረግ ቀን ከሌት የሚጥሩና የእለት ጉርስና ማረፊያ ቦታ አጥተው የሚጨነቁ ሰዎችን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እናገኛለን። እስቲ የአዲስ አበባ ከተማን የጉስቁልና ህይወት ኢምንት ገጽታ እንመልከት።
ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ ነው። ካፊያ ቤጤ ይጥላል፤ ከአራት ኪሎ ወደ መገናኛ በሚወስደው መንገድ እያዘገምኩ ነው። ልክ ግንፍሌ ድልድይ አካባቢ ስደርስ ካፊያውን ለመጠለል ከአንዲት ሱቅ በር ላይ ቆም አልኩኝ። ግንፍሌ ድልድይ ስር መደዳውን የላስቲክ ቤቶች ከርቀት ይታያሉ። ካፊያው እንዳቆመ ወደ ቤቶቹ ተጠግቼ የነዋሪዎቹን ሁኔታ መቃኘት ጀመርኩ።
ቤቶቹ ዳርና ዳር ቆም ቆም ባሉ እንጨቶች ላይ ውድቅዳቂ ማዳበሪያና ላስቲክ ብጤ ጣል ጣል ተደርጎባቸው ቤት የሚል መጠሪያ የተሰጣቸው ናቸው። መግቢያ በራቸው አይታወቅም። አንዳንዶቹ ጭስ ይጨስባቸዋል። አንዳንዶቹ ዙሪያውን የለበሱት ሸራ ወደ ታች ከመሬቱ ጋር ተጣብቆ ድንጋይ ተኮልኩሎበታል።
አንዲት በሰላሳዎቹ የእድሜ ክልል የምትገኝ ሴትና ሁለት ህጻናት ከአንዱ የላስቲክ ቤት አጠገብ ቆመዋል። እናትና ልጆች ይመስላሉ። ከላይኛው አስፋልት የሚወርደው ፍሳሽ /ጎርፍ/ በእግራቸው ስር ይወርዳል። ከበድ ያለ ዝናብ ቢዘንብ ጎርፉ እቤታቸው ሊገባ እንደሚችል አሰብኩ።
ሴትየይቱ ችግር፣ ብርድ፣ ዝናብ፣ ጸሃይ እየተፈራረቁባት ልጆቿን የምታሳድግ ምስኪን እናት ነች፤ ልብስ እያጠበች ታስተምራቸዋለች፤ ከሰባት ዓመት በላይ ህይወትን በዚህ መልክ ያሳለፈች ጠንካራ ሴት ነች። ይቺ እናት የዚህ አምድ እንግዳ እንድትሆን በመፈለግ አነጋገርኳት። ፈቃደኝነቷን ገልጻልኝ የህይወቷን ውጣ ውረድ እንዲህ ታወጋኝ ጀመር።
ትዕግስት ንጉሴ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ነው። ወረዳውንና ቀበሌውን በውል አታውቀውም። ትዕግስት ገና የአራት ዓመት ልጅ እያለች ከገጠር ወደ አዲስ አበባ መጥታ ሰው ቤት ማደጓን ትናገራለች። አሳዳጊዎቿ ከወላጆቿ ጋር ምንም አይነት የስጋ ዝምድና እንደሌላቸው ትገልጻለች። ግን ልጅ ማሳደግ ስለፈለጉ ብቻ ትዕግስትን ከችግረኛ ቤተሰቦቿ ወስደው ያሳድጓታል።
የቤት ውስጥ ስራን እንድትሰራ ታስቦ በልጅነቷ ሰው ቤት ማደግ የጀመረችው ታዳጊ ከትምህርት ዓለም ተለያይታ እንዳደገች ትናገራለች። በልጅነት ጊዜዋ እንደልጆች ተጫውቶ እና ተሯሩጦ የማደግ ዕድል አልገጠማትም። እንደ ህልም ትዝ ትዝ የሚላትን የትውልድ መንደሯን ትታ አዲስ አበባ አቧሬ አካባቢ ከመጣች ጊዜ ጀምሮ በአንዲት ጠባብ ቤት ውስጥ ተወስና ለመኖር መገደዷን ትናገራለች።
የቤት ውስጥ ስራ እየሰራችና አንዳንዴም ወደ ሱቅ እየተላላከች ማደጓን ትገልጻለች። ከፍ ስትልም ቡና ማፍላት፣ ወጥ መስራት፣ ቤት ማጽዳትና ልብስ ማጠብን የመሳሰሉ ስራዎችን እየሰራች መኖር ትጀምራለች።
ትዕግስት ሁል ጊዜ ቤተሰቦቿን እየናፈቀች ስታለቅስ እንደነበርም ታስታውሳለች። አሳዳጊዎቿ የቤተሰቦቿን ሰላም መሆን እየነገሯትና አንድ ቀን መጥተው እንደሚያይዋት ካልሆነም ይዘዋት ሄደው እንደሚያገናኟት እየነገሯት ዓመታትን አስቆጠረች። ትዕግስት እስከ ስምንት ዓመት ድረስ ከቤተሰቦቿ ጋር ሳትገናኝ በዚህ መልክ ትቆያለች።
ነፍስ እያወቀችና እያደገች ስትመጣ የማንነት ጥያቄ በብርቱ ይፈታተናት ጀመር። አንድ ቀን እንደ እናት የምትመለከታቸውን አሳዲጊዋን ከቤተሰቦቿ ጋር እንዲያገናኟት ወጥራ ትይዛቸዋለች። አሳዳጊዋም እንደሚያገናኟት ቃል ገብተው ሁኔታዎችን በማመቻት ላይ እያሉ በድንገተኛ ህመም /በደም ግፊት/ ምክንያት ይሞታሉ።
በአሳዳጊዋ ድንገተኛ ሞት ምክንያት የትዕግስትና የወላጆቿ የግንኙነት መስመር ይቋረጣል። የናፈቀቻቸውንና የጓጓችላቸውን ቤተቦቿን የማግኘት ተስፋዋም ይሟጠጣል። ከዚያን ጊዜ በኋላ ትዕግስት በቀላሉ ሆድ እየባሳት፤ በትንሽ በትልቁ እየተከፋች ከቀሪዎቹ የቤተሰቡ አባላት ጋር መግባባት ያቅታታል። ቀን በቀን ጭቅጭቅ እየተፈጠረ የቤቱ ሰላም ሲደፈርስ ትዕግስት ሌላ ሰው ቤት ተቀጥራ ለመስራት ትወስናለች።
በዚሁ መሰረት ከዚያው ከምታውቀው ሰፈር ሳትርቅ አንድ ሰው ቤት ትገባለች። ይሁንና በገባችበት ቤትም የተሻለ ነገር እንዳልገጠማት ትገልጻለች። መማር ብትፈልግም የትምህርት እድል አላገኘችም፤ እንዲያውም ከበፊቱ የበለጠ የስራ ጫና ይበዛባት ጀመር። ነገር ግን ለምትሰራው ስራ ይከፈላታል። የሚከፈላትን ገንዘብ፤ ለልብስ፣ ለቅባት ወዘተ… ማዋል ስትጀምር ሰርቶ የመኖር ተስፋ እንዳላት መገንዘብ ትጀምራለች።
ትዕግስት የቤት ውስጥ ስራዎችን ሁሉ ልቅም አድርጋ መስራት ስትችል የሚከፈላት ገንዘብ በስራዋ ልክ እንዲያድግላት መጠየቅ ትጀምራለች። አሰሪዎቿ ግን በዚህ ሀሳቧ ሳይስማሙ ይቀሩና አሁንም ትዕግስት ከዚህኛው ቤት ለቃ ሌላ ቤት ትቀጠራለች።
እንዲህ እንዲህ እያለች ህይወቷን ትመራ የነበረችው ወጣት የቤት ሰራተኝነቱን ትታ በተለያዩ የጉልበት ስራዎች ላይ ለመሰማራት ታስባለች። በይበልጥም በግንበኝነት ዘርፍ ብትሰማራ ገቢ ከማግኘት ባሻገር ሙያም የመልመድ እድል እንደሚፈጥርላት በማሰብ ከቤት ሰራተኝነት ወደ ቀን ሰራተኛነት ትሸጋገራለች።
ትዕግስት ሰው ቤት ሰርታ ያጠራቀመቻትን ጥቂት ብር ይዛ መጀመሪያ ቤት ትከራያለች። ከዚያም የቀን ስራ በማፈላለግ በአንድ የህንጻ ግንባታ ስራ ውስጥ ተቀጥራ ባሬላ መሸከም ትጀምራለች። ከምታገኛት ገንዘብ በወር አምስት መቶ ብር ለቤት ኪራይ እየከፈለች ቀሪውን ለምግቧና ለተለያዩ ወጪዎች እያዋለች የግል ኑሮዋን አንድ ብላ መኖር ትጀምራለች።
እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ህይወቷን በዚህ መልክ ስትመራ ትቆያለች። ነገር ግን በየጊዜው እየጨመረ በሚሄደው የኑሮ ውድነት ምክንያት ህይወቷ ሊለወጥ እንዳልቻለ ትገልጻለች። ክፍያዋ እየጨመረ ሲሄድና ኑሮዋን ለማሻሻል ስትዘጋጅ፤ የቤት ኪራይና የምግብ ሸቀጦች ዋጋም በዚያው መጠን ይጨምራል። ከነገ ዛሬ ህይወቴ ይለወጣል የሚል ተስፋ ይዛ ከሶስት ዓመታት በላይ በግንበኝነት ስራ ህይወቷን እየመራች ትቆያለች። ህይወቷ ግን ሊለወጥ አልቻለም። ከምግብና ከቤት ኪራይ የሚተርፍ ገንዘብ ማግኘት አልቻለችም። አንዳንዴ እንዲያውም እርሱንም መሸፈን እንደሚያቅታት ትናገራለች።
‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ›› እንዲሉ ትዕግስት ከብቸኝነት ህይወት ይልቅ ተጋግዞ መኖር ይሻላል በሚል የትዳር ጥያቄ ላቀረበላት የስራ ባልደረቧዋ ፈቃደኝነቷን ገልጻ አብራ መኖር ትጀምራለች። እንዳሰቡትም ሁለቱም ሰርተው የሚያድሩ በመሆናቸው የሚያገኙትን ገንዘብ በጋራ መጠቀም ሲጀምሩ የኑሮ ጫና ይቀንስላቸዋል። ያም ብቻ ሳይሆን የቤት እቃዎችን አሟልቶ መኖር ያስችላቸዋል። ትዕግስትና ባለቤቷ ጎጇቸውን አሟሙቀው እንደአቅማቸው መኖር ይጀምራሉ። ጠዋት አብረው ወደ ስራ ሲሄዱ ምግባቸውን ቋጥረው ስለሚወጡ ለሌላ ወጪ አይዳረጉም። በዚህ መልክ ህይወታቸውን እየገፉ እያለ በመሃል ትዕግስት ታረግዛለች።
የከፋ ስቃይና መከራ የበዛበት ህይወቷ ከዚህ እንደሚጀምር ትገልጻለች። ትዕግስት አርግዛ መውለጃዋ እስኪቃረብ ድረስ ባሬላ መሸከሟን አላቆመችም።
ኋላ ግን የመውለጃ ጊዜዋ ሲቃረብ ስራዋን ለማቆም ትገደዳለች። ነፍሰ ጡሯ ሴት ስትወልድ የሚያስፈልጓት ነገሮች ብዙ ቢሆኑም እርሷ ግን ካለባት የኢኮኖሚ ችግር አንጻር ምንም ያዘጋጀችው ነገር አልነበረም።
በዚህም ላይ ባለቤቷ ፊት ይነሳት ጀመር። ይባስ ብሎ ትቷት ይጠፋል። ትዕግስት ግራ ትጋባላች። የሚላስ የሚቀመስ በሌለበት ቤት ውስጥ ጥቂት ቀናትን ተቀምጣ አማራጭ ስታጣ ወደ ጎዳና ትወጣለች። እዚያው ወልዳ እዚያው እየለመነች ለመኖር ትገደዳለች።
እንደ እመጫት የመታረስ እድል ሳታገኝና ወገቧ ሳይጠና ልጇን እያጠባች ወደ ስራ ለመመለስ ትሞክራለች። ግን እንደበፊቱ ባሬላ ለመሸከም አልመቻት ይላል። ሌሎች ቀላል ስራዎችን ለመስራት ትጣጣር ጀመር፤ በሰው ቤት ተመላላሽ ሰራተኛነትም ሆነ በልብስ አጣቢነት ለመስራት አስባ ሰዎችን ስታነጋገር ከልጅ ጋር አይመችሽም በሚል ብዙዎች እንዳልተቀበሏት ትናገራለች።
ትዕግስት አንድ ግንብ ስር የላስቲክ ቤት ሰርታ ቀን እየለመነች እዚያው ከልጇ ጋር መኖርን ተለማመደች። በጎዳና ህይወት ከሚደርስባት ጾታዊ ጥቃት ራሷን ለመጠበቅ ስትል የሚመስላትን ሌላ ሰው እንደጓደኝ ትቀርባለች። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አሁንም ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ ሌላ ልጅ ትወልዳለች።
አሁን ትዕግስት የሁለት ልጆች እናት ነች። ወንድ ልጇ ብሩክ ሰባት ዓመቱ ሲሆን ሴት ልጇ አርሴማ ደግሞ የአራት ዓመት ልጅ ነች። ሁለቱንም ልጆቿን ታስተምራቸዋለች።
ትዕግስት ተገዳ ከገባችበት ልመና በመውጣት ህይወቷን በፕላስቲክ ቤት ውስጥ አድርጋ ልብስ እያጠበች ልጆቿን ማኖር ከጀመረች ጥቂት ዓመታትን አሳልፋለች። እየተዟዟረች ልብስ የምታጥብላቸውን ደንበኞችን አፍርታለች። በሁለት እና በሶስት ቀን አንድ ቀን ልብስ እያጠበች በምታገኘው ገንዘብ ራሷንና ልጆቿን ታኖራለች። እንደልብሱ መጠን ባጠበች ቁጥር ከመቶ ሃምሳ እስከ ሁለት መቶ ብር ታገኛለች።
ባገኘቻት ገንዘብ እንጀራ ገዝታ ወጥ ሰርታ ልጆቿን ታኖራለች። ልጆቿን አስተምራ ለቁምነገር የማድረስ ህልም እንዳላት የምትናገረው ምስኪን ሴት አሁን በመንግስት ትምህርት ቤት እያስተማረቻቸው ትገኛለች። የዩኒፎርም ወጪያቸውን እና የትምህርት ቤት የምግብ ወጪያቸውን መንግስት እየሸፈነላት መሆኑ እረፍት እንደሰጣት ትገልጻለች። ከትምህርት ሰዓት ውጭ ለልጆቿ ማንኛውንም እንክብካቤ ታደርግላቸዋለች።
ትዕግስት የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ጽህፈት ቤት የመኖሪያ ቤት ችግሯን እንዲቀርፍላት በተደጋጋሚ ያደረገችው ተማጽዕኖ እንዳልተሳካ ትናገራለች። አንገት ማስገቢያ መኖሪያ ቤት ብታገኝ ከልብስ አጠባ በተጨማሪ እንጀራ በመጋገርና በሌሎችም ስራዎች ላይ በመሰማራት ህይወቷን በተሻለ ሁኔታ መምራት እንደምትችል ትናገራለች።
ቀደም ሲል የወረዳው ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ችግሯን ተገንዝቦ የአንድ ዓመት የልጇን የትምህርት ቤት ክፍያ እንደረዳት የምትናገረው እናት አሁን የሚያደርግላትን ድጋፍ እንዳቋረጠባት ገልጻለች። ወረዳው ከሁለት ልጆቿ ጋር እያሳለፈች ያለችውን ችግር ተገንዝቦ ካለችበት መጥፎ ህይወት እንዲያወጣት ትማጸናለች። በተለይም የመኖሪያ ቤት ጥያቄዋን እንዲመልስላት ትለምናለች።
ትዕግስት ዛሬም ድረስ ከወላጆቿ ጋር አልተገናኘችም። አባቷ አቶ ንጉሴ ደስታ እንደሚባሉ ታውቃለች። የእናቷን ሙሉ ስም ግን አታውቀውም። ልታገኛቸው ብዙ ጥራ ነበር። አሁን አሁን ግን ያለችበትን ህይወት ስታስብ ባታገኛቸው ትመርጣለች።
ለዚህ ሁሉ የጉስቁልና ህይወት የዳረጋት የወላጆቿ አለማወቅ መሆኑንም ትገልጻለች። ይህን ባሰበች ጊዜ እንደምትናደድባቸው ትናገራለች።
አሁንም በልጅነታቸው ከክፍለ ሀገር ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ልጆች ከእርሷ ህይወት እንዲማሩ ትፈልጋለች። አብዛኛዎቹ የጎዳና ተዳዳሪዎች በወላጆች ችግር ምክንያት ለከፋ ህይወት የተጋለጡ መሆናቸውን የምትናገረው ትእግስት፤ ህጻናት የሚደርስባቸውን በደል የሚመለከተው አካል መከላከል ይገባዋል ትላለች። ከትዕግስት ጋር በዚሁ ተሰነባበትን። ቸር እንሰንብት።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2013