የክርስትና እምነት ተከታዮች ሰሞኑን የህማማት ሳምንትን አሳልፈዋል፡፡ ህማማት ደግሞ የሃዘን ሳምንት ነው፡፡ ህማማት እየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ሲል መከራ የተቀበለበት ወቅት ነው፡፡ የዛሬዋ ሌሊት ደግሞ የዚህ የመከራው ቀናት የመጨረሻ ቀን ናት፡፡ በእለተ ፋሲካ እየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ የሚነሳበትና ዳግም ለሰው ልጆች ትንሳኤን የሚያበስርበት እለት በመሆኑ ነገ የተሻለ ቀን እንደሚመጣ ትምህርት የሚሰጥ ትልቅ ተምሳሌት ነው፡፡ ይህ እውን ይሆን ዘንድ ግን ዛሬን በብልሃት ማለፍ የግድ ነው፡፡
እነሆ ካለፈው አመት ጀምሮ ምድራችን የኮቪድ 19ን ፈተና በመጋፈጥ ላይ ትገኛለች፡፡ ምንም እንኳን ይህ ፈተና ክርስቶስ ከተጋፈጠው ፈተና አንጻር ሲታይ ኢምንት ቢሆንም የሰው ልጅ አሁን በደረሰበት ስልጣኔም ሆነ ሊሸከመው ከሚችለው አቅም አንጻር ከባድ ፈተና ሆኖበታል፡፡ ይህ ፈተና እያስከተለ ያለው ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳትም የሰው ልጆችን እያስጨነቀ ይገኛል፡፡
ይህ ፈተና ታዲያ ለሃገራችንም “በቡሃ ላይ ቆሮቆር” እንደሚባለው ከወቅታዊው የሃገራችን የፖለቲካ ምስቅልቅል እና የኑሮ ውድነት ጋር ተ ዳምሮ የመንግስትና የህ ዝቡ ተጨማሪ ራስ ምታት በመሆን ለአንድ አመት ዘልቋል፡፡
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፤ የሚያስከትለው ሰብአዊ ቀውስም በዚያው ልክ እያየለ ሄዷል፡፡ ሰሞኑን በአንድ ቀን ብቻ ከ40 በላይ ዜጎችን በቫይረሱ የማጣታችንና ከሁለት ሺህ በላይ ዜጎቻችንም በአንድ ጀምበር በቫይረሱ መያዛቸው ለዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር ትናንት ያየናቸውና በቅርብ የምናውቃቸው ወዳጆቻችን ዛሬ ከጎናችን ሲለዩ እንደዘበት እያየን ችግሩን መላመዳችን ሌላ ማህበራዊ ቀውስ በመሆኑ ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡
እስካሁን ባለው ሁኔታም ከ255 ሺህ በላይ ዜጎቻችን በኮቪድ 19 የተያዙ ሲሆን፤ ከ3600 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በዚሁ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በሽታውን ይበልጥ አስፈሪ የሚያደርገው ደግሞ በተለይ የፅኑ ህሙማን ማቆያዎች ውስጥ የሚገቡ ታማሚዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ በቀጣይ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር የሚችልበት እድል እንዳለም ያመላክታል፡፡
በርግጥ ይህንን ፈተና አንድ ሆነንና በአንድ ልብ ተሳስበን መንቀሳቀስ ከቻልን በአጭሩ ልንገታውና የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ልናደርገው እንችላለን። ለዚህ ቻይናን በምሳሌነት መውሰዱ በቂ ነው። በቻይና ሁዋን ግዛት ቫይረሱ መከሰቱን ተከትሎ በተወሰደው ርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር ችለዋል።
እነሱ የሄዱበት መንገድ፤ የወሰዱት ርምጃ ዛሬ ከመንግሥትና ከጤና ባለሙያዎች ከሚሰጡን መመሪያዎች የተለዩ አልነበሩም፡፡ ውጤታማ የሆኑት የመከላከያ መልዕክቶችን በትክክል በመተግበርና የራሳቸውንም ኃላፊነቶች በተገቢው መንገድ መወጣት በመቻላቸው ነው። ዛሬ ተከርችመው የነበሩ ቤቶች ተከፍተዋል። የተቋረጡ እንቅስቃሴዎች ቀጥለዋል።
በመሆኑም እኛም በሽታውን መከላከል እንችል ዘንድ የሚሰጡንን ምክረ ሀሳቦች በትክክል ከተጠቀምንበት ከፊታችን የተደቀነውን የጽልመት አደጋ ብዙ ዋጋ ሳያስከፍለን ልንሻገር እንችላለን፤ ካልተጠቀምንበት ግን የምንመኛቸው መልካም ቀናት ይርቃሉ፤ የምናጣቸው ዜጎች የሚሰቃዩ ወገኖቻችንም እንዲሁ የበዙ ይሆናሉ።
በየቀኑ የምንሰማቸውን መጥፎ ዜናዎች ወደ መልካም ለመቀየር የጥንቃቄ ምክሮችን በቁርጠኝነት መተግበር፤ የነገ ተስፋዎቻችንን በእጃችን ለማስገባት በአንድ ልብ ሆነን ለመንቀሳቀስ ቃል መግባት ያለብን አሁን ነው።
በተለይ የፋሲካ በዓልን ስናከብር ራሳችንን ከእንዲህ አይነት አስከፊ ችግሮች ሊታደገን በሚችል መልኩ መሆን እንዳለበት ልንዘነጋ አይገባም፡፡ ለአንድ ቀን ደስታ ብለን ጥንቃቄ የጎደላቸው ተግባራትን ማከናወን ነገ ከማንወጣው አዘቅት ውስጥ የሚከተን በመሆኑ ጥንቃቄ አይለየን፡፡ በተለይ ቫይረሱ በቀላሉ በንክኪ ጭምር የሚተላለፍ በመሆኑ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በየመንደሩ ከሚደረጉ እርዶች ራሳችንን ማቀብ ይጠበቅብናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በገበያ ስፍራዎችም ቢሆን ማስክ በማድረግና አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ራሳችንን ከኮቪድ 19 እንጠብቅ፡፡
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ባጋጠመበትና መንግስት በዚህ ላይ ከፍተኛ መረባረብ እያደረገ ባለበት ሁኔታ የኮቪድ 19 መስፋፋት ተጨማሪ የኢኮኖሚ ቀውስ ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ስለዚህ በቀላሉ መከላከል የምንችለውን ኮቪድ 19 በራሳችን እንዝላልነት መከላከል ካቃተን በራሳችን ላይ ተጨማሪ አደጋ ማምጣት ነውና በጤና ባለሙያዎች ለሚሰጡ ምክሮች ጆሮ ልንሰጥ ይገባል፡፡
ሁላችንም ይህንን ወቅት በጥንቃቄ ማለፍ ከቻልንና ለራሳችን፣ ለቤተሰባችንና ለማህበረሰባችን ተገቢውን ዋጋ ከሰጠን ልክ እንደ ህማማቱ ሁሉ ይህ ቀን አልፎ እንደ ፋሲካው የደስታ ቀን ይመጣል፡፡ ያ ጊዜ ደግሞ ለሁሉም ነገር በቂ ነውና ይህንን አስቸጋሪ ወቅት ኮቪድ 19ን እየተከላከልን በብልሃት እንለፈው፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2013