ትሁትና አመለ ሸጋ ነው። ይህ ባህሪው አሁን ለደረሰበት ደረጃ ትልቅ አስተዋፅኦው ስለማድረጉ አያጠራጥርም። በወጣትነቱ ስራ ሰርቶ ገንዘብ ማግኘት እንዳለበት አስቀድሞ በመረዳቱ ከወንድሙና ከሌሎች የሰፈሩ ልጆች ጋር በማህበር በመደራጀት የድንጋይ ጥበብ ስራን ‹‹ሀ›› ብሎ ጀመረ። በጊዜው ስራው አዲስና ብዙም ያልተለመደ በመሆኑ ነገሮች አልጋ በአልጋ አልነበሩም።
በድንጋይ ላይ ለመጠበብ በሃምሳ ሺ ብር ብድር የድንጋይ መቁረጫ ማሽን በማሰራት ከጓደኞቹ ጋር የመሰረተው ማህበር ፈተናዎችን እየተጋፈጠ መጀመሪያ አነስተኛ ስራዎችን አከናወነ። በመቀጠልም የድንጋይ ጥበብ አሻራን በትላልቅ ህንፃዎች፣ በመኖሪያ ቤቶችና አፓርትመንቶች ላይ አሳረፈ።
የስራው ስፋትና ተደራሽነት እየጨመረ በመምጣቱ በማህበሩ ጥላ ስር በመሆን አባላቱ የድንጋይ መቁረጫ ማሽኖችን በመከፋፈል ስራውን በየግላቸው መስራት ቀጠሉ። የድንጋይ መቁረጫ ማሽኑን ወደ መስራት ሂደትም ተሸጋገሩ። እንደ አንድ የማህበሩ አባል እርሱም የራሱን ማሽን በመያዝ በግሉ የድንጋይ ጥበብ ስራዎችን መከወኑን ተያያዘው።
በርካታ ህንፃዎችንና መኖሪያ ቤቶችንም በድንጋይ ጥበብ ማስዋብ ቻለ። በስሩ በርካታ ወጣቶችን በመቅጠር የስራ እድል ከመፍጠሩም ባለፈ የራሱንም ሀብት አፈራ የኤስ ዲ ኤፍ ስቶን አርት ማህበር አባልና ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ተስፋዬ።
አቶ ብሩክ ትውልድና እድገቱ እዚሁ አዲስ አበባ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምርቱን ከአንደኛ አስከ ስድስተኛ ክፍል በወጣቶች ገነት፣ ከሰባተኛ አስከ ዘጠነኛ ክፍል ሮያል በተሰኘ የግል ትምህርት ቤት ተከታትሏል። የአስረኛና አስራአንደኛ ክፍል ትምህርቱን ደግሞ በደጅአዝማች ወንድይራይድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል።
በትምህርቱ ለመግፋት ብዙም ፍላጎት ያለነበረው በመሆኑ ከአስራአንደኛ ወደ አስራሁለተኛ ክፍል ከተዘዋወረ በኋላ ትምህርቱን በራሱ ፍቃድ አቋረጠ። ያለስራም ለሁለት ዓመት ከቤተሰቡ ጋር ተቀመጠ። በሂደት ግን ትምህርቱን ማቋረጥ እንዳልበረበት ይቆጨው ጀመር። ያቋረጠውን ትምህርት ባይቀጥል እንኳን ቢያንስ በስራ ማካካስ እንዳለበት አመነ። ሙሉ ሃሳቡም ስለ ስራ ሆነ።
እውቀቱ ባይኖረውም የድንጋይ ጥበብ ስራ ሲሰሩ የነበሩ የሰፈሩ ልጆች ስለስራው ይነግሩት ጀመር። በተለይ ደግሞ ወንድሙ በዚህ ስራ ቀድሞ ገብቶ የነበረ በመሆኑ በርካታ የድንጋይ ጥበብ ውጤቶችን በፎቶ አስደግፎ ሲያሳየው ስራውን ወደደው። በዚህ ስራ ይበልጥ በመመሰጡም ከወንድሙና ከሌሎች የሰፈሩ ጓደኞቹ ጋር ስራውን ለመስራት ቆርጦ ተነሳ። ጓደኞቹም ከእርሱ ጋር አብረው ለመስራት ተስማሙ።
በቅድሚያ ድንጋዮችን በተለያዩ ቅርፆች ቆራርጦ የሚያወጣ ማሽን ከውጭ ሀገር ለማስመጣት እርሱና ጓደኞቹ አቅም ያልነበራቸው በመሆኑ እያንዳንዳቸው 15 ሺ ብር አዋጥተው የተሻሻለ ማሽን በሀገር ውስጥ አሰሩ። በጊዜው ማሽንኑ ማሰራታቸው ለእነርሱ ትልቅ ነገር ቢሆንም ማሽኑን የሚያንቀሳቅስ በቂ የኤሌክትሪክ ሃይልና የመስሪያ ቦታ ግን ማግኘት አልቻሉም።
መጀመሪያ ቦታ ተከራይተው አልያም ደግሞ በአንዱ ጓደኛቸው መኖሪያ ጊቢ ውስጥ ስራውን ለመጀመር ሃሳቡ የነበራቸው ቢሆንም በኋላ ላይ ግን በማህበር ተደራጅተው ቢሰሩ የኤሌክትሪክ ሃይልም ሆነ የመስሪያ ቦታ እንደሚያገኙ ይረዳሉ። በዚህ መነሻነትም ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት ስድስት ሆነው ኤስ ዲ ኤፍ ስቶን አርት በሚል ስያሜ ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት በማህበር ተደራጁ። የመስሪያ ቦታም ኮተቤ ወረዳ አስር አካባቢ ተረከቡ።
የድንጋይ ጥበብ ስራውን ሲጀምሩ ማሽንኑ አሻሽሎ ለማሰራት ካዋጡት አስራ አምስት ሺ ብርና ከአዲስ ቁጠባና ብድር ከወሰዱት የ 50 ሺ ብር ብድር ውጪ በቂ ካፒታል አልነበራቸውም። ድንጋይ ለማስገልበጫ የሚከፈል ገንዘብም አላገኙም። ይሁንና ተጨማሪ ብድሮችን በመውሰድ ለስራው ግብአት የሚሆን ድንጋይ ከለገጣፎና ለገዳዲ አካባቢ ማስመጣት ጀመሩ። ድንጋዩን በተለያዩ ቅርፆች በማሽን መቆራረጡ እምብዛም ባይቸግራቸው ስራውን ለማግኘት ግን ከባድ ፈተና ገጠማቸው።
ማሽኑ የሀገር ውስጥ ከመሆኑ አኳያ ድንጋዮችን በትክክል ስለማይቆርጥ ለትንሽ ጊዜም ቢሆን አስቸግሯቸው የነበረ ቢሆንም ሁሉም አባላት አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ ቀስ በቀስ ማሽንኑ በማስተካከል ስራውን እንዲሰራ አደረጉ። ለመጀመሪያ ጊዜም ኮተቤ አካባቢ ለአንድ ባለሀብት ስለስራው ሃሳብ በማቅረብ ስራ አገኙ። በዚህ ስራ መነሻነትም በአካባቢው ሌሎች ተጨማሪ ስራዎችን የመስራት አጋጣሚ ተፈጠረላቸው። ሌሎች ስራዎችም ከሌሎች አካባቢዎች ወደ እርሱ መምጣት ጀመሩ። ቀስ በቀስም ስራቸው እስከ መሀል ከተማ ድረስ በመዛመቱ ይበልጥ እየተዋወቀ ሄደ።
የበርካታ ሰዎችን ቀልብ የሳበው የወጣቶቹ የድንጋይ ጥበብ ስራ ከአዲስ አበባ አልፎ በክልል ከተሞች በተለይ ደግሞ በአክሱም፣ ደሴ፣ ባህርዳር፣ ጎንደርና አዳማ ላይ ነገሰ። ሌሎች ወጣቶችም በዚህ የድንጋይ ጥበብ ስራ ገብተው እንዲሰሩ በር ከፈተ። በወቅቱ ወረዳ ሄደው በማህበር ሲደራጁ ይህ የድንጋይ ጥበብ ስራ ዘርፍ ያለነበረ ቢሆንም እነርሱ ተደራጅተው መስራት ከጀመሩ ወዲህ ግን አንድ የመደራጃ የስራ ዘርፍ መሆን ቻለ። እስካሁን ባለው ሂደትም በዚህ የስራ ዘርፍ የተደራጁ ማህበራት አርባ ደርሰዋል።
በአሁኑ ጊዜ ደግሞ አቶ ብሩክ ያለበት ማህበር እንዳለ ሆኖ እርሱን ጨምሮ ቀሪ አምስቱ የማህበሩ አባላት ማሽን ተከፋፍለው ስራቸውን በተናጠል በመስራት የየራሳቸውን ገቢ ያገኛሉ። የማህበሩ አጠቃላይ ካፒታልም 1 ሚሊዮን ብር ተጠግቷል። የማህበሩ አባላትም የራሳቸው ሀብትና ገቢ አላቸው። በእያንዳንዱ አባላት ስር በሳይቶች ላይ የሚሰሩ ሰራተኞች እንዳሉ ሆነው በአቶ ብሩክ ስር ብቻ በወርክሾፖች ውስጥ ያሉትን ጨምሮ ለ16 ሰራተኞች የስራ እድል ፈጥሯል። አባላቱ በየራሳቸው ማሽኖች ድንጋይ ጥበብ ስራዎችን መስራታቸው እንዳለ ሆኖ በቅርቡ ደግሞ ማሽኖቹን ወደ መስራት እየተሸጋገሩ ይገኛሉ።
አቶ ብሩክም በግሉ ሙሉ ህንፃ ድንጋይ የመሸፈን /ክላዲንግ/፣ በድንጋይ ህንፃን የማስዋብ፣ የመስኮትና የበር ፍሬሞችን፣ ቅርፃቅርፆችን፣ የበረንዳ መደገፊያዎችን፣ የደረጃ መወጣጫ ድጋፎችንና ማንኛውንም የድንጋ ስራዎችን በተሰጠው ዲዛይን መሰረት ያከናውናል። አንድ ደምበኛ የድንጋይ ጥበብ ስራዎችን ለማሰራት ሲፈልግም ለስራው የሚጠየቀውን ዋጋ እንደስራው ቦታ ርቀትና አይነት ይወሰናል። በተለይ ስራው የሚሰራበት ቦታ ተጨማሪ ሌላ ስራ ሊያመጣ የሚያስችል ቦታ ከሆነ ዋጋው ዝቅ ብሎ ያለትርፍ ሊሰራ የሚችልበት ሁኔታ አለ። በአንዳንድ ሳይቶች ላይ ደግሞ አካባቢው ትልቅ ቦታ ሆኖ ስራው ብቸኛ ሲሆን ዋጋ ተቀንሶ ሊሰራ ይችላል። በአካባቢው ላይ ምንም አይነት ስራ ከሌለ ግን በተለመደው የዋጋ ተመን ስራው ይሰራል።
እስካሁን ባለው ሂደት አቶ ብሩክ በግሉ ከሰራቸው የድንጋ ስራዎች ውስጥ መስቀል ፍላወርና ሀያት አደባባይ አካባቢ የሰራው ሆቴል በዋናነት ይጠቀሳል። በርካታ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችን ፣ አፓርትመንቶችንና ልዩ ልዩ ህንፃዎችንም በድንጋይ አስውቧል። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ቢሮውን በኮተቤ አድርጎ በቦሌ፣ ላፍቶ፣ ሃይሌ ጋርመንት፣ አዲሱ ገበያ፣ ሃያት አደባባይና ጀሞ አካባቢዎች ላይ ሳይቶችን ተረክቦ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
አቶ ብሩክ ስራውን ለማከናወን በቅድሚያ ስራዎችን በፎቶ ለአሰሪዎች ያቀርባል። የተሰሩ ስራዎችንም በአካል ያሳያል። በአሰሪዎች ቤት ላይ የትኛው የድንጋይ ጥበብ ቢሰራ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ያማክራቸዋል። የእያንዳንዱን ሂሳብም ይነግራቸዋል። በመጨረሻ ከደምበኞች ጋር ውል አስሮ በተቀመጠው የመስሪያ ጊዜ መሰረት ስራዎችን ሰርቶ ካጠናቀቀ በኋላ ያስረክባል፤ ሂሳቡንም ይቀበላል።
በዚህ የድንጋይ ጥበብ ስራ ሰባት ዓመታትን መቆየቱን የሚናገረው አቶ ብሩክ በቀጣይ ወደ እምነበረድ፣ ግራናይትና ሌሎች ድንጋዮች መቁረጥ ስራ የመግባት ሰፊ እቅድ እንዳለው ይናገራል። ማርብልና ግራናይትን በሀገር ውስጥ ማሽኖች መቁረጥ ስለማይቻል ማሽኖቹን ከውጭ ሀገር ለማስገባትና በሊዝ ፋይናንሲንግ ለማግኘት ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ጋር ንግግር እያካሄደ መሆኑንም ይጠቁማል። በተለያዩ ቅርፆች በሚቆራረጡ ድንጋዮችም ሙሉ የቤት ስራዎችን የመስራት ሃሳብ እንዳለውም ያስረዳል።
አቶ ብሩክ በድንጋይ ጥበብ ህንፃን ማስዋብ አሁን አሁን እየተለመደና እየተፈለገ ያለ የስራ ዘርፍ ቢሆንም ስራውን በስፋት ለመስራት የጥሬ እቃ እንደለብ አለመገኘት ዋነኛ ፈተና ነው ይላል። ጥሬ እቃው በብዛት እንደሚገኝ ቢታወቅም ከአካባቢው ላይ አውጥቶ ለገበያ ለማቅረብ በርካታ ችግሮች እንዳሉም ይጠቅሳል። ስራው እያለና ገንዘብ ከፍሎ ጥሬ እቃውን ማግኘት እየተቻለ ጥሬ እቃው በሰአቱ እንደማይገኝም ያመለክታል። በሌላ በኩል ደግሞ የሃይል መቆራረጥ የዚህ ዘርፍ ሌላኛው ፈተና መሆኑን ጠቅሶ፤ በዚሁ የሃይል መቆራረጥ ምክንያት የመቁረጫ ማሽኖች ዲናሞ እንደሚቃጠሉም ይገልፃል።
የጥሬ እቃ አቅርቦቱ ቢስተካከልና በመንግስት በኩል በመስሪያ ቦታዎች ላይ የሃይል ማሳደግ ስራ ቢሰራ ይህን የስራ ዘርፍ ይበልጥ አሳድጎ መስራት የሚቻልበት እድል እንዳለ ይጠቁማል። አብዛኛዎቹ ስራዎች ከግለሰቦች የሚመጡ መሆናቸውንም ተናግሮ፤ በመንግስት በኩል እስካሁን ለማሰራት የመጣ አካል የሌለ በመሆኑ መንግስት ለዚህ ስራ በሩን ክፍት ማድረግ እንዳለበትም ያመለክታል።
ማህበሩ አቅም እንዳለው በመረዳትም መንግስት ቢያንስ ጨረታ ውስጥ ገብቶ እንዲወዳደር እድል መስጠት እንደሚገባውም ይጠቁማል። በርካታ የመንግስት ስራዎች በመኖራቸው እድሉ ቢኖር እርሱም ሆነ ሌሎች የማህበሩ አባላት ገብተው የመስራት ብቃት እንዳላቸውም ይመሰክራል።
‹‹በዚህ የድንጋይ ጥበብ ስራ ውጤታማ ነኝ›› የሚለው አቶ ብሩክ በስራው ከፍተኛ ልምድ ማግኘቱና ገንዘብ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል በዚህ ስራ ማወቁ የውጤቱ ማሳያ መሆኑን ይናገራል። መኪና ሌላም ሀብት ማፍራቱ የውጤቱ አንዱ ፍሬ መሆኑንም ይጠቁማል። በቀጣይ በርካታ ስራዎችን መስራት የሚችልበት አቅም ላይ መድረሱንም ይገልፃል።
ጠንክሮ መስራቱና ከአልባሌ ሱሶች ራሱን ማራቁ እዚህ ውጤት ላይ ለመድረሱ ዋነኛ ሚስጥር መሆኑንም ይጠቅሳል። በስራው አጋጣሚ ከበርካታ ሰዎች ጋር የሚገናኝ መሆኑም በርካታ ልምዶችንና ትምህርቶችን ለመቅሰም እንዳስቻለውም ያስረዳል። ከመልካም ስራው ብቻ ሳይሆን ከስህተቱም ጭምር ብዙ እውቀት ማግኘቱንም ይጠቅሳል።
በኮንስትራክሽን ስራዎች ላይ ብዙ ጊዜ በሰላም መለያየት እንደሌለም ገልፆ፤ እርሱ ግን በተቻለው አቅም ሁሉ ስራው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ደምበኞቹን ላለማስከፋትና ላለማጣት በትእግስት ሁሉንም ችሎ እንደሚያሳልፍ ይናገራል። ይህም ያሰሩት ደንበኞችን ጨምሮ ሌሎችም ስራውን ፈልገው ወደ እርሱ እንዲመጡ ማስቻሉን ይጠቁማል።
በተመሳሳይ ሌሎች ወጣቶችም በዚህ የሙያ ዘርፍ ገብተው ውጤታማ መሆን ከፈለጉ በቅድሚያ መቁረጫ ማሽኑን ማግኘት እንደሚኖርባቸው ይጠቁማል። ማሽኑን ካገኙ በኋላ ድንጋዮችን ቆራርጠው ቁጭ ከማለት ስራዎችን የሚያገኙበትን መንገድ መፈለግና ስራ ተቋራጮችን ማወቅ እንደሚገባቸውም ያመለክታል። ስራቸውን ጥራት ባለው ጥሬ እቃና በሰለጠነ ባለሙያ ማከናወን እንዳለባቸውና ይህም በአብዛኛው ሰው ዘንድ ተፈላጊነት እንዲኖራቸው ከማድረጉም ባሻገር በቀጣይ ትርፋማ ለመሆን እንደሚያስችላቸውም ይመክራል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2013