ሁለቱ የህግ ባለሙያዎች ‹‹ሆነብን›› ባሉት በደል ቅሬታ አድሮባቸዋል። የህግ ባለሙያዎቹ እስከአሁን በነበረው የህይወት ጉዞ በርካታ ፈተናዎችን ተሻግረዋል። ሁለቱም ማየት የተሳነቸው ናቸውና በአካል ጉዳታቸው ሰበብ የሚገባቸውን መብት ሲነፈጉ ቆይተዋል። ማየት አለመቻላቸውን ያዩ አንዳንዶች አድልኦ ሲያደርሱባቸው እንደነበር ሁለቱም ጠንቅቀው ያውቃሉ።
እነሱን ጨምሮ ሌሎች ማየት የተሳናቸው መስራት እየቻሉ መገለል ይደርስባቸዋል። ማድረግ ሳያቅታቸው ‹‹አትችሉም›› ይባላሉ። እነዚህ ወገኖች በበረከቱ ፈተናዎች መሀል ማለፍ ልምዳቸው ሆኖ ኖሯል። ይህ መስመር ለእነሱ ቀላል የሚባል አይደለም። ጥቂት በማይባል መሰናክል የበረከተ ዋጋ ከፍለዋል።
እነዚህ ወገኖች ሁሌም በጉዟቸው ጋሬጣ አይታጣም። ከሚያልፉበት ጎዳና ጀምሮ ህይወታቸው በፈተና የተሞላ ነው። ማየት መሳን አለመቻል የሚመስላቸው ብዘዎች ዕድል ይነፍጓቸዋል። አካል ጉዳታቸውን የሚያሳብቡ በርካቶችም በግልጽ ያገሏቸዋል።
ብዙዎቹ ጠንካሮች ለእንዲህ አይነቱ ልማድ እጅ አይሰጡም። ችግሮችን አሸንፈው በጥንካሬ ድል ማድረግ መገለጫቸው ነው። ፡ ከእነዚህ መሀል ጥቂት የማይባሉት መቻላቸውን ችለው ያሳያሉ። ራሳቸውን በዕውቀት ይገራሉ፤ ከከፍታው ወጥተው ለሌሎች ተምሳሌት ይሆናሉ።
ሁለቱ የህግ ባለሙያዎችም እነሱን በመሰሉ ወገኖች ላይ የሚደርሰውን ፈተና እያለፉበት ቆይተዋል። ብዘዎቹ በማየት መሳን ሰበብ አድልዎና መገለል አድርሰውባቸዋል። በግንዛቤ እጦትና እያወቁ ጭምር የሚገባቸውን ሲነፍጓቸው ነበር።
ሁለቱ ሰዎች ይህ አይነቱን ፈተና ለመወጣት የወሰዱት አማራጭ በትምህርት ራስን ማሸነፍ ነው። በሚሰማሩበት የህግ ሙያ ካሰቡት ለመድረሰም ከፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ተቋም ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።
በትምህርት ጊዚያቸው ጥቂት ፈተናዎች አጋጥሟቸዋል። ለእነሱ ግን በህይወት ለውጥ የታጀበ እርምጃ ሆኗቸዋል። ከሌሎች ሳያንሱ፣ በስንፍና ሳይገለጡ፣ በአካል ጉዳት ሳያሳብቡ ቆይታውን በድል ተወጥተዋል።
ሁለቱ ዓይነስውራን፣ በተቋሙ የትምህርት ቆይታ ብዙ ዕቅዶች ሰንቀዋል። ከምርቃታቸው በኋላ በዳኝነት በመሰማራት የመጀመሪያ ህልማቸው ነው። በችሎት ተቀምጠው ፍትህ መስጠትን፣ ብይን ማሳለፍን ይሻሉ። በሙያቸው ሀገር ወገናቸውን ማገልገል ይፈልጋሉ።
በአዲስ ተስፋ-አዲስ ህይወት
አቶ ወሰን ዓለሙና አቶ ዳዊት ኦትቾ ከፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛ ተቋም የህግ ትምህርታቸውን ተምረው አጠናቀዋል። በሙያው ለመሰማራት የሚያስችለውን ግዴታም እንደተወጡ አረጋገጡ። አሁን እንዳሰቡት ሆኖ ነገን በችሎት ተሰይመው ለመዳኘት ጊዜው ደርሷል። ጥቁር ካባ ደርበው፣ የእንጨት መዶሻ አንስተው፣ ፍትህን ለተጠሙ ለማድረስ ዝግጁ ሆነዋል።
ከትምህርቱ ፍጻሜ በኋላ ባለሙያዎቹ ምደባቸውን ያውቃሉ። እስከዛሬ በማሰልጠኛ ተቋሙ በነበረ የአሰራር ልማድ መሰረት ሰልጣኝ ባለሙያዎች ዕጣ በማውጣት የስራ መደባቸውን ይለያሉ። ይህ ልየታም በዳኝነትና በዓቃቤ ህግ ሙያ ለማሰማራት ተወስኖ ዕጣ ይወጣበታል። ሁለቱ ሰዎች ይህ እንደሚሆን መረጃው አላቸው።
የዕጣ ማውጫው ቀን ደረሰ። በህግ ሙያ የተመረቁ ባለሙያዎች ዕጣቸውን እያነሱ ዕድላቸውን ወሰኑ። ዕጣው ለአንዳንዶች ዳኝነትን፣ ለአንዳንዶች ደግሞ ዓቃቤ ህግነትን ሰጠ። ሁሉም የእጆቹ ዕድል ያበረከተለትን ሙያ በአክብሮት ተቀበለ።
ሁለቱ ተመራቂዎች የስራ መደባቸውን በዕጣ ለመለየትና ዕድላቸውን ለመሞከር ጥያቄ አቀረቡ። የእነሱ ጉዳይ ከሌሎች እንደሚለይ ተነገራቸው። ሁለቱም ጉዳዩን ለማወቅ ተጨንቀው ምክንያቱን ጠየቁ። ለእነሱ የሚመጥናቸው ስራ ዳኝነት ሳይሆን ዓቃቤ ህግ መሆኑ በግልጽ ተነገራቸው። የተባሉት ሁሉ ባይገባቸው ደጋግመው ማብራሪያን ጠየቁ። ጉዳዩ በምክንያት ተብራርቶ ተገለጸላቸው። የተባሉትን በጥሞና አደመጡ። እውነታው በሁለቱም ላይ የሚስተዋለው ማየት የመሳን ችግር መሆኑን አወቁ።
አቶ ወሰንና አቶ ዓለሙ ውሳኔውን በይሁንታ ተቀብለው አልሄዱም። እነሱ በሚመርጡት የሙያ መስክ የመመደብ መብታቸው ሊከበር እንደሚገባ ሞገቱ፤ ሀሳቡን መሰረት አድርገውም እንደማንኛውም ባለሙያ በዕጣው ዕድል እንዲካተቱ ጠየቁ። ስለጥያቄያቸው የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግስት የፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ተቋም ተገቢ ነው ያለውን ምላሽ ሰጠ።
ሁለቱ ሰዎች ያነሱት ጥያቄ እስከዛሬ ያልተለመደ መሆኑን የጠቀሰው ተቋም ባለሙያዎችን ከማሰልጠን የዘለለ ማየት የተሳናቸው ባለሙያዎች ‹‹ዳኛ ይሆናሉ፣ አይሆኑም›› በሚለው ላይ ውሳኔ ማሳለፍ እንዳማይቻለው አሳወቀ። አቤት ባዮቹ ከተቋሙ ሀላፊዎች በቃል የሰሙት ምላሽ በጽሁፍ ሰፍሮ እንዲሰጣቸው ጠየቁ። ያሰቡት አልሆነም፣ የጠየቁት አልተፈጸመም።
እስካሁን በነበረው ተለምዷዊ አሰራር ማየት የተሳናቸው ወገኖች ዕጣ ውስጥ ተካተው አያውቁም። በዳኝነት እንዲሰሩ ዕድል ባለመኖሩም በዓቃቤ ህግ ሙያ ብቻ እንዲሰማሩ ይደረጋል። ይህ ተለምዷዊ መስመር ያልተመቻቸው ሁለቱ የህግ ሰዎችም ነባሩን አሰራር በመቃወም ለምን ሲሉ መሞገት ይዘዋል።
ሙግትና ምላሽ …
ክርክሩ ቀጥሏል። እነ አቶ ወሰን ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ወደሚሏቸው አካላት በመሄድ ጉዳያችን ይታይልን እያሉ ነው። አሁንም ማመልከቻቸውን ወደ ክልሉ የፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ተቋም ቦርድ አቅርበዋል። ቦርዱ ተሰብስቦ ባሳለፈው ውሳኔ ያለአንዳች መነሻ ማየት የተሳናቸውን ባለሙያዎች ዳኞች አድርጎ ለመሾም እንዳማይቻለው አሳውቋል።
ሁለቱ የህግ ባለሙያዎች አሁንም የቦርዱን ውሳኔ ተቀብለው ዝምታን አልመረጡም። ለምን ሲሉ ጥያቄ አቀረቡ። ቦርዱ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የበላይ ተቆጣጣሪነት የሚመራው የባህርዳር ዩኒቨርሰቲ በጉዳዩ ላይ ጥናት እንዲያደርግ በሚል መፍትሄ መቀመጡን አሳወቃቸው።
የህግ ባለሙያዎቹ ጉዞ አልተቋረጠም። በተሰጣቸው ምላሽ ላይ ቅሬታ እንዳደረባቸው በመግለጽ ለዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አቤት አሉ። ጉባኤው ማመልከቻውን ተመለከተ። ይዘቱ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ካልተመራለት በቀር ጉዳዩን ማየት እንደሚቸገር በመጥቀስ ምላሽ ሰጠ። ባለነጭ በትሮቹ አሁንም ዝምታን አልመረጡም። እስካሁን የተጓዙበትን አካሄድ ዋቢ አድርገው ቅሬታቸውን ለክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ ለምክር ቤቱ የህግ ቋሚ ኮሚቴ፣ ለክልሉ አስተዳደርና ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ለሚባሉ አካላት በሙሉ አቀረቡ። ቅሬታቸው እንዳሰቡት ሆኖ ተገቢውን ምላሽ አላገኘም።
ችሎት- በኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት
ሁለቱ የህግ ባለሙያዎች በተማርንበት የህግ ትምህርት የዳኝነት ሙያን ልናገኝ ይገባል ሲሉ ያቀረቡት ቅሬታ በተለያዩ ተቋማት መፍትሄ ሳያገኝ ጊዜያትን አስቆጥሯል። ባለሙያዎቹ በመጨረሻ ጉዳያቸውን የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ይመለከተው ዘንድ አቅርበው ውሳኔ መጠበቅ ይዘዋል።
ምክር ቤቱ የአመልካቾቹን ቅሬታና ጥያቄ በመመርመር ጉዳዩ የህገ መንግስት ትርጉም የሚያስፈልገው መሆኑን አረጋግጧል። የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጠው ዘንድም የተነሳውን ጥያቄና መፍትሄ ያልተገኘበትን ምክንያት ከየተቋማቱ ምላሽ ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን መመርመር ጀምሯል።
ምክር ቤቱ አስቀድሞ የአቤቱታውን መነሻ በጥልቀት አስተዋለ። ጉዳዩ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 41/2 እና አንቀጽ 25 የተደነገጉትን የኢኮኖሚና የእኩልነት መብቶችን የሚመለከት ነው።
አመልካቾች ሚያዝያ 8 ቀን 2007 ዓ.ም ጽፈው ባቀረቡት አቤቱታ ቀደም ሲል በነበረ ተለምዷዊ አሰራር ምክንያት ማየት የተሳናቸው የህግ ባለሙያዎች በዓቃቤ ህግነት ብቻ እንዲወሰኑ ሲደረግ ቆይቷል።
በክስ ማመልከቻው እንደተጠቆመው አንደኛ ተጠሪ ሆኖ የተጠቀሰው የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግስት የፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ተቋም ነው። ሁለተኛው ተጠሪም የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የዳኞች አስተዳዳር ጉባኤ ሆኗል።
አንደኛ ተጠሪ በደንብ ቁጥር 74/2003 መሰረት ሲቋቋም ከተሰጠው ስልጣን አንዱ በዩኒቨርስቲ የህግ ዲግሪ ያላቸውን ተመራቂዎች በቅድመ-ስራ ሰልጣኝነት መልምሎ ማስገባት ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ሰልጣኞቹን በዕውቀት፣ በክህሎት፣ በአመለካከትና በስነምግባር በማብቃት ህገመንግስታዊ ሰርአቱን የማክበርና የፍትህ ሰርአቱን ውጤታማ እንዲሆን የማስቻል ግዴታ ተጥሎበታል።
ምክር ቤቱ አንደኛ ተጠሪ የአ.ብ.ክ.መ የፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ተቋም ለአመልካቾቹ የሰጠውን ምላሽ አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቋል። በዚህም መሰረት ተቋሙ ተገቢ ያለውን መልስ ለምክር ቤቱ አድርሷል።
ሰልጥነው የሚመረቁ የህግ ባለሙያዎች የሚመደቡት በዳኝነት አሊያም በዓቃቤህግ ሙያ ነው። ተቋሙ በግልጽ እንዳሰፈረውም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የፍትህ ቢሮ በዕጣ ተለይቶ እንዲሰጣቸው በሚስማሙበት አግባብ ሂደቱ ተፈጻሚ ይሆናል። ይህ ሲከወንም የተቋሙ ቀጥተኛ ሀላፊነት ሆኖ አይደለም። ይሁን እንጂ ዕጣው በሚወጣበት ጊዜ ማየት የተሳናቸው ሰልጣኞች ከዳኝነት የስራ ባህርይ አንጻር ዳኛ እንዲሆኑ ባለመፈቀዱ በወቅቱ ዓቃቤ ህግ ሆነው እንዲመደቡ ተደርጓል በማለት ተቋሙ ማብራሪያ ሰጥቷል። አመልካቾች ለክልሉ ምክርቤት ‹‹አቤት›› ማለታቸውንና ዓቃቤ ህግ ሆነው እንዲመደቡ መወሰኑን በመጥቀስም በተቋሙ በኩል ምንም አይነት ክልከላ ያለመደረጉን ጭምር አስታውቋል።
ሁለተኛ ተጠሪ በመሆን የተጠቀሰው የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግስት የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ በበኩሉ ቅሬታውን ለጉባኤው ጽህፈት ቤት በማቅረብ ለአመልካቾች በወቅቱ በሰጠው ምላሽ ጉዳዩ በቀጥታ እንደማይመለከተው መጥቀሱን አስታውሷል።
ሁለተኛው ተጠሪ አያይዞ እንደጠቀሰው ሰልጣኞች ከፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ በዕጣ ወደ ፍርድ ቤትና ዓቃቤ ህግ ሙያ ተለይተው እንዲመደቡ የማድረግ ሀላፊነት አለበት። ይሁን እንጂ ዳኛና ዓቃቤ ህግ ይሁኑ ሲል የመወሰንና የመደልደል ስልጣኑ አልተሰጠውም።
የምክር ቤቱ የምርመራ ቆይታ
ምክር ቤቱ የአጣሪ ጉባኤውን የውሳኔ ሀሳብ መሰረት በማድረግ በጉዳዩ ላይ የምክር ቤቱ የህገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መርምሯል። በዚህም መሰረት፡- አመልካቾች አንደኛ ተጠሪ በሆነው የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግስት የፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ተቋም ገብተው የዳኝነትም ይሁን የዓቃቤ ህግ እንዲሁም የሌላ ተመሳሳይ ስራ ለመስራት የሚያስችለውን ትምህርት ተከታትለው አጠናቀዋል።
አመልካቾቹ በትምህርት ዘርፉ ለሙያው ብቁ የሚያደርጋቸውን ስልጠና ከተጠሪው ተቋም በመውሰድ በማጠናቀቅ መመረቃቸውም በማስረጃዎች ተረጋግጧል። ይህ እውነታ ባለበት አመልካቾች አብረዋቸው እንደተመረቁት የህግ ባለሙያዎች እኩል ጥበቃ በማድረግ በዳኝነት ወይም በዓቃቤ ህግ ሙያ ተመድበው እንዲሰሩ አለመደረጉን ምክር ቤቱ አላመነበትም።
ለአመልካቾች ዕጣ የማውጣት ሂደቱን ወደጎን በማለት ማየት የተሳናቸው ስለሆኑ ብቻ በህግ ያልተደነገገን ልማዳዊ አሰራርን በመተግበር ዳኝነትን መስራት አይችሉም መባሉ ተገቢነት የለውም።
ምክር ቤቱ በማጣራት ሂደቱ እንደተገነዘበው ሁለቱ ዓይነ ስውራን የህግ ባለሙያዎች በዳኝነት እንዳይሰማሩ የሚከለክል ህግ አልሰፈረም። ተጠሪዎች ያሳለፉት ውሳኔ በአካል ጉዳተኞች የስራ ስምሪት መብት አዋጅ ቁጥር 568 /2000 እና አገራችን ባጸደቀችው በአዋጅ ቁጥር 567/2002 ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብት ኮንቬንሽን ድንጋጌዎች መሰረት አካል ጉዳተኞች በጉዳታቸው ምክንያት መድልኦ እንዳይደረግባቸው የሚያሳስበውን ህግ የሚቃረን ነው።
የመጨረሻው ውሳኔ …
ተጠሪ ሆነው የቀረቡት ሁለቱ መንግስታዊ ተቋማት ተቀባይነት በሌለውና ልማዳዊ ሆኖ በሚሰራበት ህግ ላይ ተመስርተው የሰጡት ውሳኔ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ምክር ቤቱ በማጣራት ሂደቱ አረጋግጧል።
ውሳኔ
ውሳኔው በኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 41/2/ ላይ የሰፈረውንና ሁሉም ኢትዮጵያዊ መተዳደሪያውን፣ ስራውንና ሙያውን የመምረጥ መብት አለው በሚል የተደነገገውን ህገመንግስታዊ የእኩልነት መብት የሚጋፋ ነው፡፡ በመሆኑም የተጠሪዎቹ የልማድ አሰራርና ውሳኔ በህገመንግስቱ አንቀጽ 9/1 መሰረት ተፈጻሚነት ሊኖረው አይገባም ሲል የኤፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ የስራ ዘመን፣ 2ኛ አመት 1ኛ መደበኛ ስብሰባ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዝ ያ 23/2013