
አለም ለሃይል ፍጆታ ከሚያውላቸውና ከማይተኩ የተፈጥሮ ሃብቶች ውስጥ የድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ በዋናነት ይጠቀሳሉ:: እነዚህን ሀብቶች ለሃይል ፍጆታ የማዋሉ አዝማሚያ ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መጥቷል:: የሰው ልጆችም እነዚህን ሀብቶች ብቸኛ የሃይል አማራጭ አድርገው መጠቀም ከጀመሩ ሰነባበተዋል::
የሰው ልጅ የማይተኩ የተፈጥሮ ሃብቶችን ለሃይል ምንጭነት ያለገደብ በመጠቀሙ የአየር ንብረት ለውጥ ተከስቶ ተፈጥሮ መልሳ እየቀጣቸው ትገኛለች :: በተለይ ደግሞ እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች ለሃይል ሲውሉ በየግዜው ወደ ከባቢ አይር በካይ ጋዝ ስለሚለቁ ለኦዞን ንጣፍ መሳሳት ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክተዋል:: ለተደጋጋሚ ድርቅና ጎርፍ መከሰትም የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል::
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሃገራትም በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ስምምነት ተፈራርመው ችግሩን ለመቀነስ በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ:: በተለይ ደግሞ አለም ከነዳጅ ሃይል ወደታዳሽ የሃይል አማራጭ ፊቱን እንዲያዞር ከፍተኛ ስራዎችን እየሰሩ ነው:: በርካታ ሀገራትም ፊታቸውን ወደ ታዳሽ ሃይል እያዞሩ ይገኛሉ::
ሲ ኤን ቢ ሲ ኒውስ ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ መሰረት ደግሞ አለም ለታዳሽ ሃይል ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱና በተለይ ባለፈው አስር አመት የፀሃይና የንፋስ ሃይል እያደገ መምጣቱን ተከትሎ እ.ኤ.አ በ 2030 ታዳሽ ያልሆኑ የሃይል ምንጮችን ከኤሌክትሪክ ሴክተር ገፍተው እንደሚያስወጡ ገልጿል:: በተለይ እድገታቸው በዚሁ ከቀጠለ የፀሃይና የንፋስ ሃይል በ2030 አጋማሽ የአለምን የኤሌክትሪክ ሃይል እንደሚያመነጩና እ.ኤ.አ በ2050 በአለም ዙሪያ ሙሉ የኤሌክትሪክ ሃይል እንደሚያቀርቡ ቲንክ ታንክ ካርበን ተራከር ያወጣውን ሪፖርት ዋቢ አድርጎ ዘገባው አስታውቋል::
የወቅቱ ቴክኖሎጂ አለም 6 ሺ 700 ፔታ ዋት ሀወር የኤሌክትሪክ ሃይል ከፀሃይና ከንፋስ እንዲይዝ ማስቻሉን የጠቆሙት የቲንክ ታንክ ካርበን ትራከር ተመራማሪዎች፤ ይህም እ.ኤ.አ በ2019 ከነበረው የአለም የኤሌክትሪክ ሃይል ፍጆታ በመቶ እጥፍ የሚበልጥ መሆኑን አስምረዋል:: ምንም እንኳን ከዚህ የሃይል አማራጭ ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ሃይል የመሰብሰብ አቅም ቢኖርም እ.ኤ.አ በ2019 ዜሮ ነጥብ 7 ፔታ ዋት ሀወር የፀሃይ ሃይልና 1 ነጥብ 4 ፔታ ዋት ሀወር የንፋስ ሃይል ብቻ መመንጨቱም በሪፖርቱ ተጠቅሷል::
በተለይ ደግሞ የፀሃይና የንፋስ ሃይል ዋጋ ከነዳጅ ሃይል ዋጋ ጋር ሲነፃፀር እየቀነሰ መምጣት ከእነዚሁ የሃይል አማራጮች የሚገኘው ሃይል ፍላጎት እንደሚጨምር በሪፖርቱ ተጠቁሟል:: 15 ከመቶ አመታዊ እድገት እያሳየ የመጣው የፀሃይና የንፋስ ሃይል እ.ኤ.አ በ2030 አጋማሽ አጠቃላይ የአለም ኤሌክትሪክ ሃይል እንደሚያመነጭና እ.ኤ.አ በ2050 ሁሉንም ሃይል ለአለም እንደሚያቀርብም ተነግሯል::
ሪፖርቱ እንዳሰመረው እ.ኤ.አ ከ 2010 ጀምሮ የፀሃይ ሃይል ፍጆታ ዋጋ በየአመቱ በአማካይ 18 ከመቶ መቀነሱንና በተመሳሳይ በዚሁ አመት የንፋስ ሃይል ዋጋም በየአመቱ በአማካይ በ 9 ከመቶ ዝቅ ብሏል:: ባለፈው አስር አመት ውስጥ የፀሃይ ሃይል በአማካይ 39 በመቶ አመታዊ እድገት ያሳያ መሆኑንና ይህም አቅሙ በየሁለት አመቱ በእጥፍ ማደጉን እንደሚያሳይ ሪፖርቱ አስታውቋል:: ይህ በእንዲህ እንዳለ የንፋስ ሃይል በአመት የ17 ከመቶ እድገት ማሳየቱም በሪፖርቱ ተመላክቷል::
በዚህ መነሻነትም አንዳንድ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በቅርብ ግዚያት ውስጥ ከነዳጅ ሃይል ወደ ታዳሽ ሃይል ሽግግር እንደሚኖር እየተናገሩ ሲሆን ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የአየር ንብረት የሳይንስ ሊህቃን በፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ በዋና ኢላማነት ከተቀመጡት ውስጥ በቅድመ ኢንዱስትሪ ደረጃ ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሽየስ በላይ እየጨመረ የመጣውን የምድሪቱን የሙቀት መጠን መገደብ እንደማይቻል ያስቀምጣሉ::
ለትርፍ ባለተቋቋመውና በአለም አቀፍ አካባቢ ህግ ማእከል ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ካሮል ሙፌት ለ ሲ ኤን ቢሲ እንደተናገሩት ከዚህ ወር ቀደም ብሎ አዳዲስ የሃይል መዋቅሮችና ኢንዱስትሪዎች እንዲቀንሱ የቀጠሉ ድጋፎች ወደታዳሽ ሃይል ምንጭ ለሚደረገው ሽግግር ትልቅ ለውጥ አምጥተው እንደነበር ገልፀዋል::
ብዙዎቹ አለም አቀፍ ትብብሮችም የአየር ንበረት ለውጥን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ ሲሆኑ በተቃራኒው ደግሞ ሌሎች ከነዳጅ የሚገኘውን ሃይል ለማሳደግ በእጥፍ ድጋፍ ሲመድቡ እንደሚታዩም ዋና ስራ አስፈፃሚው አብራርተዋል::
ሲ ኤን ቢ ሲ ኒውስ ‹‹ባንኪን ኦን ክላይሜት ካዮስ›› በሚል ርዕስ በ2021 ባወጣው ትንታኔ ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ ካሉ 60 ትላልቅ ባንኮች ውስጥ 33ቱ እ.ኤ.አ ከ2016 እስከ 2020 ባለው ግዜ ውስጥ ድጋፋቸውን ለነዳጅ ሃይል ሴክተር ከፍ አድርገው ታይተዋል ሲል ያስቀምጣል::
የቲንክ ታንክ ካርበን ትራከርስ ተመራማሪዎች በበኩላቸው የሀገር ውስጥ የሃይል ፍላጎታቸውን ከንፋስና ከፀሃይ ለማሟላት ባላቸው አቅም መሰረት ሀገራትን በአራት ቁልፍ ቡድን ለይተዋል:: በዚሁ መሰረትም አነስተኛ ገቢ ያላቸውና ዝቅተኛ ሀይል ተጠቃሚ የሆኑ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራትን ቢያንስ ከሀገራዊ ፍላጎታቸው 1 ሺ ግዜ የበለጠ ተጨማሪ ሃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው ሲል በአንደኝነት ገልፀዋቸዋል:: በተለይ ደግሞ የአፍሪካ አህጉር የታዳሽ ሃይል መሰረተ ልማቶችን ተግባራዊ ስታደርግ ትልቅ አቅም እንደሚኖራት በሪፖርታቸው ጠቁመዋል:: እንዳውም የአፍሪካ ቀጠና የታዳሽ ሃይል ዋነኛ ማማ ትሆናለች ሲሉም ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል::
በሌላ በኩል ደግሞ አውስትራሊያ፣ ቺሊና ሞሮኮን የመሳሰሉ ሀገራት የታዳሽ ሃይል መሰረተ ልማትና አስተዳደር የዘረጉ መሆናቸውን በሁለተኝነት ገልፀው ይህም ሃብታቸውን ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው አብራርተዋል:: ቻይና፣ ህንድና አሜሪካን ደግሞ ለራሳቸው የሃይል ፍጆታ ታዳሽ ሃይል የማምረት አቅም ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን በሶስተኝነት ተማራማሪዎቹ ተናግረዋል። ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና አብዛኛዎቹ የአውሮፓ ሀገራት ደግሞ ታዳሽ ሀብታቸውን በአግባቡ እየተጠቀሙ ያሉ ሀገራት ሲሉ በአራተኝነት አስቀምጠዋቸዋል::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20/2013