ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በሀገራችን እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ዕለት ተዕለት መልካቸውን እየቀየሩና አድማሳቸውን እያሰፉ ሀገርና ህዝብን ዋጋ እያስከፈሉ ይገኛሉ። ግጭቶቹ የለውጥ ማግስት ግጭቶች ከመሆናቸው አንጻር በአንድም ይሁን በሌላ ከለውጡ አስተሳሰቦችና አጠቃላይ መንፈስ ጋር በተቃርኖ የቆሙ ናቸው።
መላው ህዝባችን ለውጡን በማዋለድ ሂደት ውስጥ ከነበረው ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ፤ ከዛም በላይ መላው ህዝብ የለውጡ ኃይል ሆኖ ለለውጡ አቅምና መተማመኛ በመሆን ከሄደበት እና እየሄደ ካለበት ረጅም ርቀት አንፃር ግጭቶቹን ማየት ከተቻለ፣ ግጭቶች ሀገራዊ መሰረት እንደሌላቸው ለመረዳት ብዙም የሚከብድ አይደለም። ሀገራዊ የፖለቲካ ተቃርኖ ውጤቶች እንዳልሆኑም ለመገመት አይከብድም ።
በተለይም የለውጡ ሀይል ለውጡ ያለ ብዙ መንገጫገጭ ሰላማዊ ሽግግር እንዲኖረው ለማስቻል የሄደበት የይቅርታና የፍቅር መንገድ እንዲሁም የመደመር ፍልስፍና ግጭቶችን ለመቀነስ ፤ ያለብዙ ዋጋ ለውጡን በማስቀጠል የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ የሚያስችል አቅም መፍጠር የቻለ ነው።
የይቅርታና የፍቅር መንገዱ ቀደም ያሉ ቁርሾዎችን በማስወገድ፣ ቁስሎችን በማከም ብሄራዊ አንድነቱን ከማጠናከር ባለፈ ዘላቂ ሀገራዊ ሰላም በማስፈን ለተጀመረው ለውጥ ከፍያለ አቅም ሊፈጥርለት እንደሚችል የታመነ ነው። ይህ ሀገራዊ የፈውስ መንገድ ሀገራትን ከብዙ አደጋ መታደግ የቻለ መሆኑም የተለያዩ ሀገራት ታሪኮችን ዋቢ ማድረግ ይቻላል።
ከዚህ በላይ የመደመር መንገዱ ሁሉም ዜጋ ለለውጡ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለውና አስተዋጽኦውም በለውጡ ሂደት ውስጥ የማይተካና ትርጉም ያለው እንደሆነ በተጨባጭ ማሳየት ያስቻለ ነው። የለውጡ የአስተሳሰብ መሰረት ዜጎችን ሁሉ የለውጡ ሀይል አድርጎ የሚቀበል ነው።
ይህ ደግሞ ከመጣንበት እና ብዙ ዋጋ ካስከፈለን የተቃርኖ የለውጥ መንፈስ በፍጹም የተለየና አዲስ መንገድ ነው። ይህም በራሱ የለውጥ ወቅት ግጭቶችን ለማስወገድ ስትራቴጂክ አቅም እንደሚሆን ይታመናል። ከዛም በለፈ ዜጎች ለውጡን የራሴ ነው ብለው እንዲቀበሉና ባላቸው አቅም ለስኬቱ እንዲተጉ ያደረገ ነው።
እነዚህ አቅሞች እውን በሆኑበት ሀገራዊ የፖለቲካ መድረክ ውስጥ ግጭቶች የመከሰታቸውና ጎልተው የመውጣታቸው እውነታ ሀገራዊ መሰረት አለው ብሎ ለማመንና ለመናገር የሚያስችል አይደለም። የለውጡ ሀይል ለውጡ በራሱ የተቃርኖ ምንጭ እንዳይሆን የሄደበት የጥንቃቄ መንገድ ትናንቶችን እንዳንደግም እድል የሚሰጥ ነው።
እነዚህ ግጭቶች ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ፣ ሃገራዊ የፖለቲካ መድረኩን የግጭትና የሁከት በማድረግ ከዚህ
እንጠቀማለን የሚሉ ሀይሎች ሴራ ነው። በዚህ ሴራ ውስጥ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ጨምሮ ያልተገባ ጥቅማችንን አደጋ ውስጥ ይከተዋል የሚል ስጋት የነበራቸው የውስጥ ሀይሎች በስፋት የተሳተፉባቸውም ናቸው።
ለውጡን ገና ከጅምሩ ለማደናቀፍ ሀገራዊ የፖለቲካ መድረኩን የግጭትና የሁከት ለማድረግ የተንቀሳቀሰው የትህነግ ቡድን አንድም ባልተገባ መልኩ በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የነበረው የፈላጭ ቆራጭነት ግዝፈት ማክተሙ፤ ከዚህ ይመነጭ የነበረው ተጠቃሚነቱ ማብቃቱ የፈጠረበት ስጋት የሀገራዊ ሰላም አደጋ ሆኗል።
በሌላ በኩል ቡድኑ በስልጣን ላይ በነበረበት 27 አመታት የሰራችው ግፎች ፣ ዘረፋዎችና ሌብነቶች ሀገራዊ ጨለማው እየተገፈፈ ፣ ሲነጋና እየነጋም ሲሄድ ሊፈጥርበት የሚችለውን ተጠያቂነት ለማስቀረት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የታሪካዊ ጠላቶቻችን መሳሪያ በመሆን የሀገርን ሉአላዊነት አደጋ ውስጥ በሚከት የሴራና የአመጽ መንገድ ረጅም መንገድ ሔዷል።
የታሪካዊ ጠላቶቻችንን አጀንዳ በመቀበልም ሀገርን ሊበትን በሚችል የድፍረትና የእብሪት መንገድ ውስጥ ዳክሮ የጥፋት መንገዱ በራሱ በልቶ ውጦታል። ለዚህ እኩይ ተግባሩ በመላ ሀገሪቱ የዘራው የክፋት ዘር እስከ ዛሬ በሀገሪቱ የግጭትና ያለመረጋጋት ምንጭ ሆኖ እንደ ቀጠለ ነው።
ቡድኑ የከፈተውን የጥፋትና ሀገር የመበተን መንገድ የውጪ ሀይሎች እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የሀገርን ሰላም ለማደፍረስ በስፋት እየተጠቀሙበት ይገኛል። በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የለውጡ መንገድ ስጋት የሆነባቸውን ኃይሎች በማባበልና ገበያ ላይ እንዳለ ሸቀጥ በመግዛት በሀገር ላይ ክህደት እንዲፈጽሙ ፤በዚህም ህዝባችን ዋጋ እንዲከፍል እያደረጉት ይገኛሉ።
ትህነግ የሞተውን ፍጥረታዊ ሞት ሳይቀር ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ እነዚህ ኃይሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚጠቀሱ የመገናኛ ብዙሃን በኩል ለቡድኑ ትንሳኤ ለመፍጠር ቀን ከሌሊት ሲተጉ ይገኛል። ይህ ትጋታቸው ለቡድኑ ካላቸው ፍቅርም ሆነ ከበሬታ የመነጨ ሳይሆን ቡድኑ ለጥፋት ተልዕኳቸው የተሻለ ዕድል ፈጣሪ ስለሆነና ስለነበረ ብቻ ነው።
የቡድኑን ሞት ተከትሎ በቡድኑ ስፖንሰር ሲደረጉ የቆዩ ግጭቶች በአስገራሚ ሁኔታ የቀነሱበት እውነታ ቢኖርም ፤ ቡድኑ የጀመረውን የግጭት መንገድ በማስቀጠል ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴውንና ብሄራዊ አንድነቱን አደጋ ውስጥ የሚከቱ እኩይ ተግባራትን ቦታና ጊዜ መርጠው የሚፈጽሙ የቡድን የክፋት ልጆች ዛሬም ተኝተው ያደሩበት ወቅት አይደለም ።
ይህ ሀገራዊ መሰረት የሌለውና በውጪ ሀይሎች እና በሙታን ናፋቂዎች ሴራ የሚካሄዱ ግጭቶች የቱንም ያህል ዋጋ እያስከፈሉን ቢሆንም ሕዝባዊ መሰረት ስለሌላቸው መክሰማቸው የማይቀር ነው። ለውጡ ገና ከጅምሩ ለሰላማዊ ፖለቲካ ከፈጠረው መደላድል አንጻር ሁከትና ግጭቶችን አሸንፎ ለመውጣት እስትራቴጂክ አቅም የገነባ ነው። ጠላቶቻችን እንደሚያስቡት እና እንደሚመኙት የለውጥ ሀይሉ ራሱን የግጭት አካል አድርጎ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል የተቃርኖ መሰረት የለውም ።
የሀገራዊ ችግሮችና የችግሮቹ ምንጮች በግልጽ የሚታወቁ አንድ ሁለት ተብለው ሊዘረዘሩ የሚችሉ ናቸው። ከዚህም ባለፈ በውጪ ኃይሎች የሚዘወሩና የጀመርነውን የለውጥ ጉዞ በማደናቀፍ ሀገራዊ ህልማችንን የማክሰም ሴራ አካልም ነው። ይህንን በአግባቡ በመረዳት ብቻ ሴራውን ማክሸፍ ይቻላል። ለዚህ ሴራ ጦር መስበቅ በራስ ላይ አደጋ ከመጋበዝ የተለየ አይደለም!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20/2013