አስናቀ ፀጋዬ
ከአዲስ አበባ በደቡብ ምእራብ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከሚገኙ ዞኖች ውስጥ አንዱ ነው። በደቡብ የጋሞ ጎፋ ዞን፣ በምእራብ የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ በሰሜን የጎጀብ ወንዝ፣ በሰሜን ምስራቅ የሃድያና ከምባታ ጠምባሮ ዞን እንዲሁም በምስራቅ የወላይታ ዞን ያዋስኑታል። አራት ወረዳዎችንና ሁለት የከተማ አስተዳደሮችንም አቅፏል። የበርካታ ተፈጥሮ ሀብት ባለቤትና የከበሩ ማዕድናትን ጨምሮ ለኢንዱስትሪና ለኮንስትራክሽን ግብአትነት የሚውሉ መአድናት መገኛም ነው። ይሁንና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ያለውን የማዕድን ሃብት ሳይጠቀምበት ቀርቷል- የዳውሮ ዞን።
የዳውሮ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ሃላፊ አቶ ንጋቱ ቸርነት እንደሚገልፁት፤ በዞኑ በአብዛኛው ለኢንዱስትሪ ግብአትነት የሚውሉ በተለይ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ክምችቶች በስድስት ወረዳዎች ላይ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ለኮንስትራክሽን ግብአትነት የሚውሉ የአሸዋና ድንጋይ ማዕድናትም በዞኑ አስር ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ በስፋት ይገኛሉ። በተለይ የከሰል ድንጋይ በሁሉም ወረዳዎች ላይ ይገኛል። በዞኑ መቀመጫ ከተማ በሆነችው ተርቻም ብዛት ያላቸው የኮንስትራክሽን ማዕድናት ይገኛሉ።
በዞኑ የኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ በኩል ስራ አጥ ወጣቶች ተጣርተው በማህበር ተደራጅተው ከመጡ በኋላ ሂደቶችን ሲያጠናቅቁ የዞኑ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ማዕድናቱን እንዲያመርቱ የስድስት ወር ፍቃድ ይሰጣቸዋል። በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረትም የፍቃድ ግዜያቸው ሲጠናቀቅ ከአምራችነታቸው እንዲወጡ ተደርጎ ለሌሎች ወጣቶች ይሰጣል። ከማህበሩ የወጡ ወጣቶች ደግሞ ወደሌላ ዘርፍ ተሸጋግረው እንዲሰሩ ይደረጋል። በአሁኑ ግዜም ወደ ሃያ ሶስት የሚሆኑ ማህበራት በኮንስትራክሽን ማዕድን ማውጣት ስራ ተሰማርተው ይገኛሉ።
ከኢንዱስትሪ ማዕድን ጋር በተያያዘ በተለይ በድንጋይ ከሰል ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው እንዲያመርቱ የሚደረግ ቢሆንም ከማዕድን ሃብቱ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ወጣቶች በኩል የግንዛቤ እጥረትና ከአደረጃጀት በኩል ክፍተት በመኖሩና ይህንንም ተከትሎ አለመስማማቶች የነበሩ ቢሆንም በወረዳዎችና በዞን አቅጣጫ ተቀምጦ ችግሩ እንዲስተካከል ተደርጓል።
እስካሁን ድረስ የኢንዱስትሪ ማዕድናትን በከፍተኛ ደረጃ ለማምረት ወደ ዞኑ የመጡ ሌሎች ኩባንያዎች አለመኖራቸውን ሃላፊው ይናገራሉ። ኢስት አፍሪካ የተሰኘ አንድ ኩባንያ የድንጋይ ከሰል ለማምረት ወደ ዞኑ የገባ ቢሆንም ከአካባቢው ወጣቶች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ለቆ ወጥቷል። ሌሎች ኩባንያዎችም በክልሉ በኩል የድንጋይ ከሰል ለማምረት በየግዜው ጥያቄ ቢያቀርቡም ፍቃድ ከወሰዱ በኋላ የማዕድን ቦታውን ይዘው ወደማምረት ሳይሸጋገሩ ረጅም ግዜ ይቆያሉ። በዚህም የተነሳ ከክልሉ ጋር በመነጋገር መምሪያው ቦታውን ለቀው እንዲወጡ እያደረገ ይገኛል። በተመሳሳይ ብረትን ጨምሮ ሌሎች የኢንዱስትሪ ማዕድናትን ለማምረት ኩባንያዎች እየገቡ ቢሆንም ወደማምረት ግን አለመሸጋገራቸውን ነው የገለጹት።
በዞኑ ከፍተኛ ክምችት ያለው የድንጋይ ከሰል ማዕድን እስካሁን ድረስ ተመርቶ ጥቅም ላይ መዋል ያልቻለው ከዚህ ቀደም ማዕድኑን ለማምረት የገባውና ኢስት አፍሪካ የተሰኘው ኩባንያ ከወጣቶች ጋር ውል በመፈራረም ከራሱ ሼር ጋር ሆኖ እንዲሰራ ከክልሉ ጋር አቅጣጫ ተቀምጦ ነበር። ይሁንና ስራ እንደጀመረ በመካከል የኩባንያው ማሽን በአካባቢው ችግር ፈጣሪ አካላት በመቃጠሉ ቦታውን ለቆ ወጥቷል።
ሌሎች ኩባንያዎችም የከሰል ድንጋይ ለማምረት ወደዞኑ ቢመጡም የአቅም ችግር ያለባቸው በመሆኑ ደፍረው ወደስራው እንዳልገቡ አቶ ንጋቱ ይናገራሉ። የአካባቢ ተፅእኖ ግምገማና ሌሎች ሂደቶችንም በቶሎ አጠናቀው ወደማምረት አልተሸጋገሩም።በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ዞኑ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ሃብቱን በሚገባ ጥቅም ላይ አላዋለም።
ሃላፊው እንደሚሉት የድንጋይ ከሰል ብቻ ሳይሆን ካኦሊንን ጨምሮ ሌሎች ማዕድናትን በጥናት ለይቶ ጥቅም ላይ ከማዋል አንፃር ክፍተቶች ያሉ ሲሆን በርካቶች በክልልም ሆነ በፌደራል ደረጃ ፍቃድ አውጥተው በነዚህ የማዕድን ማውጣት ስራ ለመግባት ቢመጡም አብዛኞቹ ወደ ምርት ሲሸጋገሩ አይታዩም። ወደ ማዕድን ማውጫ ስፍራዎቹ ገብቶ ለመስራትም የመሰረተ ልማት ችግሮች በተለይ የመንገድ ችግሮችም አሉ። ማዕድን አውጪ ኩባንያዎችም ማዕድን ለመውጣት ወደ ቦታው ከመጡ በኋላ የመንገድ ችግር እንዳለ ይገልፃሉ። በመንገድ ችግር ምክንያት ያመረቱትን ማዕድን ጭነው ለመውጣት እንደሚቸገሩም ይናገራሉ።
‹‹የማዕድን ቦታውን ይዘው ወደምርት ያልተሸጋገሩ ኩባንያችም አሉ። ይሁንና የፍቃድ ግዜያቸው ሳያልቅ ከቦታው ማስለቀቅ የማይቻል በመሆኑ ሌሎች ኩባንያዎች ገብተው እንዳያመርቱ እንቅፋት ፈጥረዋል። በመሆኑም የፍቃድ ግዜያቸው እንደተጠናቀቀ ሌሎች ገብተው እንዲያመርቱ ይደረጋል።›› ሲሉ ይናገራሉ።
በዞኑ አጠቃላይ ያለውን የማዕድን ሃብት ለማወቅም የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ጥናት እስካሁን አልተካሄድም። ጥናቱ እንዲካሄድም የዞኑ መምሪያ ለክልሉ ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቧል። ከኢንዱስትሪና ኮንስትራክሽን ማዕድን ማምረት ጋር በተያያዘም በወጣቶች በኩል የሚታዩ አንዳንድ ችግሮች መኖራቸውን አቶ ንጋቱ አልሸሸጉም። የመሰረተ ልማት በተለይ የመንገድ ችግሮችም ኩባንያዎች ደፍረው ገብተው ወደማምረት እንዳይሸጋገሩ እንቅፋት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ሃላፊው እንደሚናገሩት ከነዚህ ችግሮች በመነሳት የዞኑ ውሃ፣ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ከዞኑ አስተዳደር ሜይን ስትሪም ኮሚቴ ጋር ውይይት አካሂዷል። በኮንስትራክሽን ማዕድናት አካባቢዎች ከዞን መንገድ ትራንስፖርትና ከገጠር መንገድ ጋር በመሆን አነስተኛ መንገዶችን ለመስራት ጥረት እየተደረገ ነው። ትላልቅ መንገዶችን ለመስራት ግን የአቅም ችግሮች በመኖራቸው ከክልልና ከፌደራል መንግስት በኩል ድጋፍ ያስፈልጋል።
ከወጣቶች በኩል ያለውን ችግር ከመቅረፍ አኳያም ከዞኑ አስተዳደር ጋር ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ይናገራሉ። ከማዕድን አጠቃቀም ጋር በተያያዘም ለወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችም በስፋት እየተሰሩ ነው። ማዕድን ለማውጣት ወደ ዞኑ የሚመጡ ባለሃብቶችንም በመቀበል ችግሩን ተረድተው በራሳቸው አቅም እንዲሰሩም ይደረጋል ሲሉ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 18/2013